በመንገድ ላይ የሚደርስን የትራፊክ አደጋ አምስት በመቶ መቀነስ የሚያስችል መመሪያ በተያዘው በጀት ዓመት የሚቀጥሉት ሦስት ወራት ውስጥ ይፋ እንደሚያደርግ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
መመሪያው የመንገድ ደኅንነት አሠራር የሚል ሥያሜ የተሠጠው ሲሆን፣ በመንገድ እና በመንገድ አካባቢ የሚገኙ የተለያዩ መሠረተ ልማቶች እና ግብዓቶች ደኅንነትና ሥጋት በሚኖርበት ወቅት ደኅንነትን ለማስጠበቅ የሚረዳ ነው ተብላል።
ከዚህ በፊት የዚህ ዓይነት ሥራዎች ይሠሩ የነበረው ጉዳዩ በሚመለከታቸው የመንግሥት ተቋማት በተናጠል የነበረ በመሆኑ፣ በሚጠበቀው ልክ ውጤት ማስመዝገብ እንዳልተቻለ ተጠቁማል።
በመዲናዋ በየዓመቱ በመንገድ ላይ በሚደርስ የትራፊክ አደጋ ሳቢያ በርካታ ሰዎች ለሞት፣ ለከባድ እና ለቀላል አካል ጉዳት እንደሚዳረጉ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህን አደጋ ለመቀነስ የሚያስችል መመሪያ ተዘጋጅቶ በቀጣዮች ሦስት ወራት ተፈፃሚ እንደሚሆን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አረጋዊ ማሩ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትራንስፖርት ቢሮ ከ‹ብሉምበርግ ኢኒሼቲቭ ፎር ግሎባል ሮድ ሴፍቲ› እና የአዲስ አበባ ከተማ አጋር ከሆነው ‹ወርልድ ሪሶርስ ኢንስቲትዩት› ጋር በመተባበር የአሠራር መመሪያው እንደወጣ ያነሱት ዳይሬክተሩ፣ ይህ መመሪያ፣ አደጋን ቀድሞ ለመከላከል የመንገድ ደኅንነትን ማረጋግጥ እንደሚገባ፣ እንዲሁም በመንገድ ላይና አካባቢው የሚደረጉ ግንባታዎች ከዕቅድ እና ዲዛይን ጀምሮ፣ በግንባታ ወይም በጥገና ወቅት ጥብቅ ቁጥጥር የሚያደርግ ነው ተብሏል።
ዳይሬክተሩ አክለውም፣ ተግባራዊ የሚሆነው መመሪያ በትራፊክ አደጋ እና ግጭት ምክንያት በመንገድ ኃብት ላይ የሚደርሰውን ኪሳራ ለመቀነስ አስተዋጽዖ አለው ብለዋል።
ይህን መመሪያ ተግባራዊ ለማድረግ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር ማለትም ከኢትዮ ቴሌኮም፣ ከአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን፣ ከአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን እና ከሌሎች አጋር ተቋማት ጋር እንደተወያየበት እና በቀጣይም በጥምረት እንደሚሠሩ ዳይሬክተሩ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።
የመሠረተ ልማት ተቋማት በተለይ መንገዶች ላይ የሚገነቡና የሚጠገኑ ሥራዎችን በተመለከተ፣ ተናበው መሥራት እንዳለባቸው እና አሽከርካሪዎችም ግንባታ በሚከናወንባቸው አካባቢዎች በሰዓት 30 ኪሎ ሜትር ባነሰ ፍጥነት ማሽከርከር እንዳለባቸው ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
አያይዘውም፣ መንገድ ላይ የሚከናወኑ ጥንቃቄ የጎደላቸው ግንባታዎች በተጠቃሚዎች ዘንድ ጉዳት እየደረሱ እንደሚገኝ እና ግንባታዎች ተገቢውን ደኅንነት መስፈርት አሟልተው ባለመከናወናቸው ለመንገድ ትራፊክ አደጋ ምክንያት እየሆኑ መምጣታቸውን አስረድተዋል።
በመንገድ ግንባታዎች ላይ በቂ ማመላከቻዎች ባለመኖራቸው፣ መንገዶች በመቆራረጣቸው፣ እንዲሁም በአካባቢው የተለያዩ ቁሳቁሶች ጥቅም ላይ በመዋላቸው አደጋዎች እየደረሱ ነው ተብሏል።
የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ በመዲናዋ የሚስተዋለውን የትራንስፖርት ዕጥረት እንዴት መቅረፍ ይቻላል በሚለው ጉዳይ ላይ እና የተሽከርካሪዎች የጊዜ ምልልስን ለማሻሻል መሠራት ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ከሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ጋር በጋራ እየሠራ ነው ተብሏል።
በቀጣይ ሦስት ወራት የብዙኀን ትራንስፖርትንም ሆነ የታክሲ የምልልስ ጊዜን ለማሻሻል፣ ከታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ እና የሚጭኑ አሽከርካሪዎችም ላይ ጠንካራ ክትትል የማድረግ ሥራ ይሠራል ተብሏል።
ከዚሁ ጎን ለጎን የትራፊክ ፍሰቱን ለማሻሻል ከትራፊክ ፖሊስ፣ ከትራፊክ ቁጥጥር ባለሙያዎች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ እየተሠራ መሆኑን ዳይሬክተሩ ጠቁመዋል።
ቅጽ 4 ቁጥር 179 ሚያዝያ 1 2014



