ዕረቡ ሚያዝያ 5 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው በቅርቡ የተሾሙት መስፍን ጣሰው አዲስ የማኔጅመንት ቡድን አዋቅረዋል፡፡
በአዲሱ የማኔጅመንት ቡድን፤ ቀደም ሲል በተጠባባቂነት የሃላፊነት ቦታዎች ይዘው ሲያገለግሉ የነበሩ ሀላፊዎች ቦታው የጸደቀላቸው ሲሆን አንዳንድ ሀላፊዎች ከቦታቸው ተነስተው በሌሎች ባልደረቦቻቸው ተተክተዋል፡፡
በዚህም መሰረት በተጠባባቂነት በቺፍ ኦፕሬቲንግ ኦፊሰርነት ሲያገለግሉ የነበሩት ረታ መላኩ ሹመቱ ፀድቆላቸዋል።
የበረራ ኦፕሬሽን ም/ል ፕሬዝደንት የነበሩት ካፒቴን ዮሀንስ ሃ/ማርያም በካፒቴን ዮሴፍ ሀይሉ ተተክተዋል፡፡ አየር መንገዱን ለ38 ዓመታት ያገለገሉት ካፒቴን ዮሀንስ ወደ በረራ ስልጠና ክፍል እንደሚገቡም ተሰምቷል፡፡
ቺፍ ኮሜርሺያል ኦፊሰር የነበሩት ኢሳያስ ወ/ማርያም የዓለም አቀፍ አገልግሎት ሀላፊ በነበሩት ለማ ያደቻ የተተኩ ሲሆን፤ መስፍን ብሩ የዓለም አቀፍ አገልግሎት ሀላፊ ሆነው ተሹመዋል። የአየርመንገዱን ማርኬቲንግ ክፍል በሃላፊነት ለረጅም ዓመታት የመሩት እና ለአጭር ጊዜ ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ያገለገሉት ኢሳያስ ወ/ማርያም እስካይ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው ይሾማሉ የሚል ግምት ተሰምቷል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የስትራቴጂክ ፕላኒንግ ም/ል ፕሬዝደንት ሆነው ሲያገለግሉ የቆዩት ቡሴራ አወል የፍሊት ፕላኒንግ ም/ል ፕሬዝደንት በነበሩት ዳንኤል አበበ ተተክተዋል፡፡ የሰው ሀይል አስተዳደር ተጠባባቂ ም/ል ፕሬዝደንት የነበሩት ዋሲሁን አስረስ በዘነበወርቅ ገ/ፃዲቅ ተተክተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ተጠባባቂ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩት እስክንድር አለሙ እና የጥገና ክፍል ተጠባባቂ ማኔጂንግ ዳይሬክተር የነበሩት ቅዱስ መልካሙ ቦታቸው ጸድቆላቸዋል፡፡
ሀይለመለኮት ማሞ የኢትዮጵያ ሆሊዴይ እና ዲጂታል ሴልስ ም/ል ፕሬዝደንት ሆነው የተሸሙ ሲሆን፤ ጌትነት ታደሰ የአየርመንገዱ ዋና ኢንፎርሜሽን ኦፊሰር፣ ታደለ ባረጋ የግራውንድ ሰርቪስ ማኔጂንግ ዳይሬክተር፣ መንግስቱ በዜ ኢንተርናል ኦዲት ኮምፕሊያንስ እና ቢዝነስ ሰስቴኔብሊቲ ም/ል ፕሬዝደንት ሆነው መሾማቸውን ኢትዮ የንግድና ኢንቨስትመንት መድረክ ዘግቧል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n




