ዕረቡ ሚያዝያ 5 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) ዓለም ባንክ በኢትዮጵያ በግጭት ምክንያት የተጎዱ ዜጎችን ለመደገፍ በዓለም ዐቀፍ ልማት ማህበር በኩል የ300 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ድጋፍ የሚያደርግ ፕሮጀክት አጸደቀ፡፡
ፕሮጀክቱ የህብረተሰቡን መሰረታዊ ፍላጎቶችን ለመቅረፍ፣ በግጭት የወደሙ መሠረተ ልማቶችን መልሶ ለማቋቋም እና የግጭት ተፅዕኖዎችን በዘላቂነት ለመፍታት የተዘጋጀ ነው ተብሏል፡፡
መሰረታዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ እንዲሁም ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር መሠረተ ልማትን መልሶ ለመገንባት ጥረት የሚያደረግ መሆኑም ተነግሯል፡፡
በግጭት የተጎዱ ማህበረሰቦችን በተለይ በትምህርት፣ ጤና፣ ውሃ እና በንፅህና ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በፍጥነት ለመቅረፍ በፕሮጀክቱ በትኩረት እንደሚሰራ ተጠቁሟል፡፡
በግጭቱ ምክንያት የሥነ ልቦና ችግር የገጠማቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የተሻለ አገልግሎት እና እንክብካቤ እንዲያገኙ ይደረጋልም ተብሏል፡፡.
ፕሮጀክቱ በግጭት በተጎዱ አካባቢዎች የድጋፍና የአገልግሎት ውስንነትን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚያግዝ የኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሱዳን የዓለም ባንክ ዳይሬክተር ኦስማን ዳዮኔ ተናግረዋል።
ፕሮጀክቱ በአፋር፣ አማራ፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ ኦሮሚያ እና ትግራይ ክልሎች የሚተገበር እንደሆነም ከዓለም ባንክ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



