የማዳበሪያ ዋጋ መናር እና መዘዙ

0
1840

ዓለም አንድ መንደር የመሆን ያህል እየጠበበች መሆኗ አንድም ጉዳት ያለው መሆኑን ማሳያ የሚሆኑ የተለያዩ ክስተቶች በተለያየ አጋጣሚ ተስተውለዋል። ከዚህ መካከል አንደኛው በሩስያና በዩክሬን መካከል የሚደረገው ጦርነት፣ አገራቱ ከነመኖራቸው እንኳ በግልጽ የማያውቀውን የአርሶ አደር ገበሬን ቤት አንኳቶ ኑሮውንና ነገውን እየፈተነ ይገኛል። ይህም በይበልጥ በአፈር ማዳበሪያ ላይ ጎልቶ ታይቷል።

የምጣኔ ሀብት ደረጃዋን ከፍ ለማድረግና ለሕዝቧ የተሻለ ኑሮን ለመስጠት የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን የሚጠበቅባት ኢትዮጵያ፣ ለዚህም የተለያዩ መንገዶችን ስትጠቀም ነበር። ዘመናዊ የግብርና ዘዴዎችንም ቤተኛ አድርጋ የቆየች ሲሆን፣ የአፈር ማዳበሪያ የሆኑ ኬሚካሎችና የተለያዩ ግብዓቶችን ከውጭ አገራት በማስመጣት ስትጠቀም ቆይታለች። ይህ ግን አሁን ላይ የፈተናዋ ምክንያት ሆኗል። ነገን መገመት ባይቻልም፣ ከዛሬው በበሳ የኑሮ ውድነቱ ላይና የአርሶ አደሩ ሕይወት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ሊመጣ እንደሚችል የዘርፉ ምሁራን ከወዲሁ እያሳሰቡ ይገኛሉ።

የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ይህን ጉዳይ በማንሳት፣ የቀደሙ የተለያዩ ሰነዶችን በማገላበጥና ዓለማቀፍ ሁኔታዎችን በማጣቀስ እንዲሁም ባለሞያዎችን በማናገር ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሠረቱን ግብርና ላይ ያደረገ ሲሆን፣ አብዛኛው የማኅበረሰብ ክፍል ኑሮውን በግብርና የሚመራ ነው። ግብርና ከኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ትልቁን ድርሻ የሚይዝ ቢሆንም ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያላትን ሀብት በአግባቡ ባለመጠቀሟ በምግብ ራሷን ላለመቻሏ እንደ ምክንያት ይነሳል።

ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሠረት ሲሆን፣ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ግብርናን እንደ ዋና መተዳደሪያው አደርጎ ይኖራል። የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው ከሆነ፣ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (GDP – Growth Domestic Product) ግብርና በ2012 በጀት ዓመት  32.7 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን፣ ድርሻው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ እንደመጣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መረጃ ያመላክታል። ከጠቅላላው የአገር ውስጥ ምርት ትልቁን ድርሻ ከመያዙ በተጨማሪ ኢትዮጵያ ለምታገኘው የውጭ ምንዛሬ ገቢ ከፍተኛውን ድርሻ ይይዛል።

ምንም እንኳን ግብርና የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዋልታ ቢሆንም፣ እንደ አገር ኢትዮጵያ በግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ ላይ ተጨባጭ ለውጥ እንዳላመጣች የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ለዚህም እንደ ማሳያ የሚነሳው የተሻሻሉ ዘሮችን አለመጠቀም፣ የማዳበሪያ እና ፀረ ተባይ መድኃኒቶች አጠቃቀም ውስንነት፣ የገበያ ትስስር ድክመትና ዘመናዊ ግብርናን በስፋት አለመጠቀም የሚሉት ተጠቃሽ ናቸው። የኢትዮጵያ ግብርና መር ኢኮኖሚ ዕድገት አለማሳየቱ የኢትዮጵያን ስር የሰደደ ድህነት ለመቅረፍና የምግብ ዋስትናን ለማረጋጋጥ ዘላቂ መፍትሄ እንዳያገኙ መሰናክል መሆኑን በተደጋጋሚ ሲገለጽ ይሰማል።

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ያዘጋጀው ዐስር ዓመት የልማት ዕቅድ (2013-2022) እንደሚሳየው፣ ከ2003 እስከ 2013 የነበረው 10 ዓመት፣ የኢኮኖሚ መዋቅራዊ ለውጥ ዝቅተኛ ምርታማነት ካላቸው የኢኮኖሚ ዘርፎችና ንዑስ ዘርፎች፣ ከፍተኛ ምርታማነት ወዳላቸው ዘርፎችና ንዑስ ዘርፎች እየተሸጋገረ እንደሆነ ነው። ባለፉት 10 ዓመታት የግብርናው ዘርፍ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት ያለው ድርሻ እየቀነሰ ቢመጣም፣ በግብርናው ዘርፍ ውስጥ ዝቅተኛ ምርታማነት ካላቸው የግብርና ንዑስ ዘርፎች ከፍተኛ ምርታማነት ወዳላቸው ንዑስ ዘርፎች የተደረገው ሽግግር እጅግ አዝጋሚ በመሆኑ በግብርና ዘርፍ ውስጥ የተመዘገበው መዋቅራዊ ሽግግር አጥጋቢ እንዳልነበረ በዕቅዱ ግምገማ ላይ ተመላክቷል።

የኢትዮጵያን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ለማረጋገጥ የግብርናውን ዘርፍ በእጅጉ ማዘመን እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ምክረ ሐሳብ ሲያቀርቡ ይደመጣሉ። በመንግሥት በኩል ደግሞ ግብርናን ለማዘመንና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ትኩረት ሰጥቼ እሠራለሁ ቢልም፣ በዘርፉ ተጨባጭ ሥራ አለመሠራቱን የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

በኢሕአዴግ የመሪነት ዘመን ባሕላዊና ኋላቀር የሆነውን የአመራረት ዘይቤ በመለወጥ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ ልማት ለማምጣት መንግሥት ለግብርናው ዘርፍ ቅድሚያ እንደሚሠራ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ነበር። ከኢሕአዴግ ሥልጣን የተቀበለው የአሁኑ መንግሥትም ግብርናን በማዘመን የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ እንዲያድግ ግብርናን ማዘመን እንደሚያስፈልግና ግብርና ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት ለግብርና ቅድሚያ ሰጥቶ እንደሚሠራ በተደጋጋሚ ሲገልጽ ይደመጣል።

ይሁን እንጂ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሠረት ግብርና ቢሆንም፣ ግብርናን በማዘመንና ኢትዮጵያ በግብርናው ዘርፍ ያላትን ሀብት በአግባቡ መጠቀም እንዳልተቻለና ከወሬ ያለፈ ተጨባጭ ለውጥ መታየት አልቻለም። አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መሠረት የሆነው ግብርናው ፈተና እንደገጠመው የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። ግብርናው በአሁኑ ወቅት ከገጠሙት ፈተናዎች መካከል በተለያዩ አካባቢዎች ለዓመታት የዘለቁ የጸጥታ ችግሮችና የሰሜኑ ጦርነት እንዲሁም የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ መናር ተጠቃሽ ናቸው።

ማዳበሪያና የኢትዮጵያ ግብርና

የኢትዮጵያ ግብርና ከጊዜ ወደ ጊዜ በአፈር ማዳበሪያ ላይ ጥገኛ እየሆነ መምጣቱን የዘርፉ ባለሙያዎችና የአፈር ማዳበሪያ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ይገልጻሉ። አርሶ አደሩ በሰብል ልማት ላይ ማዳበሪያ መጠቀሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣቱን ተከትሎ የአርሶ አደሩ ማዳበሪያ መልመዱ ይገለጻል። በዚህም የአርሶ አደሩ የግብርና ሥራ በአፈር ማዳበሪያ ላይ ጥገኛ እየሆነ መምጣቱ ይነገራል።

የአርሶ አደሩ ምርቱን ለማሳደግ ማዳበሪያ ተጠቃሚነቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህርና የግብርና ኢኮኖሚ ባለሙያው ዓለሙ መብራቱ (ዶ/ር) ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ የአርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም ሳይንሳዊ ምጣኔን የተከተለ አይደለም ይላሉ። የኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም፣ ከዓለም ዐቀፍ የማዳበሪያ አጠቃቀም ምጣኔ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ልዩነት እንዳለው የሚገልጹት የግብርና ኢኮኖሚ ባለሙያው፣ የዓለም ዐቀፍ የአፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም በአንድ ሄክታር 110 ኪሎ ግራም ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ አጠቃቀም ምጣኔ ለአንድ ሄክታር 12 ኪሎ ግራም መሆኑን ይጠቁማሉ።

የሰሜን ሽዋ ዞን የጅሩ ወረዳ አርሶ አደር የሆኑት ከተማ ከበደ ለሰብል ልማት ማዳበሪያ መጠቀም ከጀመሩ ዓመታት እንዳስቆጠሩ ይናገራሉ። አርሶ አደሩ የአፈር ማዳበሪያ መጠቀም የጀመሩት ለስንዴ ሲሆን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሬቱ ማዳበሪያ እየለመደ መሄዱን ተከትሎ ለሌሎች ሰብሎችም ማዳበሪያ እንዲጠቁሙ እንዳስገደዳቸው ይገልጻሉ። አርሶ አደሩ እንደሚሉት፣ ማዳበሪያ የለመደው መሬታቸው መጀመሪያ አካባቢ አነስተኛ ማዳበሪያ ካገኘ ሰብሉን የሚያዳብረው ቢሆንም፣ ማዳበሪያው ካልበዛ የሰብሉ መዳበር የመቀነስ ሁኔታ እንደሚጋጥማቸው ይናገራሉ።

በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል ከጊዜ ወደ ጊዜ አርሶ አደሩ ማዳበሪያ ተጠቃሚ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ የምታስገባው የአፈር ማዳበሪያ መጠን ከዓመት ዓመት እየጨመረ መምጣቱን መረጃዎች ያሳያሉ። የኢትዮጵያ አፈር ማዳበሪያ አጠቃቀም በ1960ዎቹ ውስጥ 35 ሺሕ ኩንታል የነበረ ሲሆን፣ በአሁኑ ጊዜ ከ17 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ደርሷል።

ከአምስት ዓመት በፊት በ2008/2009 የምርት ዘመን  የኢትዮጵያ አፈር ማዳበሪያ ዓመታዊ ፍጆታ አምስት ሚሊዮን 800 ሺሕ ኩንታል ሲሆን፣ ከአምስት ዓመት በኋላ በ2013/14 የምርት ዘመን 17 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ እንደተጠቀመች የግብርና ሚኒስቴር መረጃዎች ያመላክታሉ። ባለፉት አምስት የምርት ዓመታት ኢትዮጵያ የተጠቀመችው ማዳበሪያ በየዓመቱ እያደገ መጥቶ በአምስት ዓመት ውስጥ ከ11 ሚሊዮን ኩንታል በላይ እድገት አሳይቷል።

የዋጋ ነገር!

የኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ ፍጆታ ከዓመት ዓመት እያደገ ከመምጣቱ በተጨማሪ የማዳበሪያ ዋጋም ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ እንደመጣ መረጃዎች ያሳያሉ። በዘንድሮው ማለትም በ2014/15 የምርት ዓመት የታየው የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ጭማሬ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ እጅግ የተጋነነ ሆኗል። የአፈር ማዳበሪያ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ ከባለፈው ዓመት ከኹለት እጥፍ በላይ ጨምሯል።

ለዓለም ገበያ ከፍተኛውን የአፈር ማዳበሪያ የምታቀርበው ሩሲያ ከዩክሬን ጋር ጦርነት ውስጥ መግባቷን ተከትሎ የዓለም የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ሪከርድ መስበሩን ፋይናንሻል ታይምስ ያወጣው መረጃ ያሳያል። እንደ ፋይናንሻል ታይምስ መረጃ ከሆነ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ውስጥ ከገቡ በኋላ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሬ አሳይቷል።

የኹለቱ አገራት ጦርነት የዓለም የአፈር ማዳበሪያ መሸጫ ዋጋ እንዲያሻቅብ ከማድረጉ በተጨማሪ፣ የአቅርቦት ችግር እንዲከሰት ምክንያት እንደሆነ እየተነገረ ነው። ታዲያ በየዓመቱ የአፈር ማዳበሪያ ፍጆታዋ እየጨመረ ለመጣችው ኢትዮጵያም የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ መናር ውስብስብ ችግር ፈጥሯል። የዋጋውን መናር ተከትሎ፣ ኢትዮጵያ ወደ አገር ውስጥ ገዝታ ያስገባችው ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ የሚሸጥበት ዋጋ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱ በአርሶ አደሩ ዘንድ ቅሬታ ፈጥሯል።

በኢትዮጵያ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የዘንድሮው ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ የጀርባ አጥንት ለሆነው ለሰፊው አርሶ አደር ትልቅ ችግር ሆኗል። በ2013/2014 የምርት ዓመት 1700 ብር ይሸጥ የነበረው አንድ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ዘንድሮ ዋጋው ከእጥፍ በላይ ጨምሮ 4200 ብር መድረሱ ተሰምቷል።

አፈር ማዳበሪያን አዘውትሮ መጠቀም የለመደው የኢትዮጵያ አርሶ አደር በተከሰተው የዋጋ ንረት ምክንያት የመንግሥትን በር ከማንኳኳት አደባባይ እስከ መውጣት ደርሷል። አርሶ አደሩ ከዚህ በፊት የለመደው የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ በድንገት ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ የመግዛት አቅሙን እንደሚገዳደረው እየገለጸ ይገኛል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው በስንዴ ምርት የሚታወቀው የጅሩ ወረዳ አርሶ አደር የሆኑት ከተማ፣ የዘንድሮው የማዳበሪያ ዋጋ ጭማሪ ከእቅዳቸውና ከአቅማቸው በላይ እንደሆነባቸው ይናገራሉ። አርሶ አደሩ አክለውም፣ ከዚህ በፊት የሚገዛበትን ዋጋ ታሳቢ አድርገው የማዳበሪያ መግዣ ገንዘብ አዘጋጅተው እየጠበቁ ድንገት የተከሰተው የዋጋ ጭማሪ ከፍተኛ ስጋትና ድንጋጤ እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ።

‹‹በየዓመቱ ማዳበሪያ መብላት የለመደ ማሳ ስላለኝ የምገዛበትን ሳንቲም አዘጋጅቼ ስጠባበቅ የመጣው ዋጋ ከአቅሜ በላይ ሆነብኝ።›› የሚሉት ከተማ፣ መንግሥት የዋጋ ማስተካከያ ካላደረገ መሬታቸው ላይ ያለ ማዳበሪያ ለመዝራት እንደሚገደዱ ጠቁመዋል።

በዘንድሮ ዓመት የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ የጨመረበት ምክንያት ከአቅርቦት ችግር ጋር ተያይዞ በዓለም ገበያ የማዳበሪያ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ በማሻቀቡ መሆኑን የኢትዮጵያ ግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን የኮርፖሬት ኮምዩኒኬሽን ኃላፊ ጋሻው አይችሉህም ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ግብርና ሚኒስቴር ለ2014/15 ምርት ዓመት ባቀረበው የአፈር ማዳበሪያ አገራዊ ፍላጎት መሠረት የኢትዮጵያ የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን 12 ሚሊዮን 876 ሺሕ 623 ኩንታል ማዳበሪያ ግዥ ፈጽሟል ተብሏል።

ኮርፖሬሽኑ ለ2014/15 የምርት ዓመት 20 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት በዚሁ ዓመት ጨረታ ማውጣቱ የሚታወስ ሲሆን፣ ይሁን እንጂ የተፈጸመው ግዥ መጀመሪያ ከታቀደው ግዥ የ7.1 ሚሊዮን ኩንታል ቅናሽ አሳይቷል። የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትን የሚወስነው ግብርና ሚኒስቴር መሆኑን የሚገልጹት ጋሻው፣ ሚኒስቴሩ ጥናት አድርጎ መጀመሪያ ከታቀደው 20 ሚሊዮን ኩንታል ወደ 12 ሚሊዮን ዝቅ እንዲል ማድረጉን ጠቁመዋል።

ግብርና ሚኒስቴር የምርት ዓመቱን የአፈር ማዳበሪያ ቅናሽ ያደረገው በውጭ ምንዛሬ እጥረት ምክንያት መሆኑ የተጠቆመ ሲሆን፣ የውጭ ምንዛሬ እጥረት ለተደረገው የግዥ ቅናሽ አስገዳጅ ምክንያት እንደሆነ ተመላክቷል። ጋሻው እንደሚሉት፣ ምንም ግብርና ሚኒስቴር ለኮርፖሬሽኑ ያቀረበው የተስተካከለው የግዥ ምጣኔ በውጭ ምንዛሬ ምክንያት ቢሆንም፣ ካለፈው የምርት ዓመት የተረፈ የአፈር ማዳበሪያ ግብዓት መኖሩ ታሳቢ ያደረገ ነው።

ኢትዮጵያ በ2013/14 የምርት ዓመት ያስገባችው ማዳበሪያ በ2014/15 ካስገባችው የአምስት ሚሊዮን ቅናሽ ቢኖረውም፣ በአቅርቦት ላይ የሚፈጥረው እጥረት አለመኖሩ በጥናት ተረጋግጧል ተብሏል።

የግብርና ኢኮኖሚ ባለሙያው ዓለሙ መብራቱ በበኩላቸው፣ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ መናር በአርሶ አደሩ ላይ ቅሬታ መፍጠሩን አውስተው አርሶ አደሩ ያቀረበው ጥያቄ ተገቢ ነው ይላሉ። የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ንረቱ ከዓለም ዐቀፍ ሁኔታ ጋር የሚገናኝ መሆኑን የሚገልጹት ባለሙያው፣ የዋጋ ጭማሪው ለኢትዮጵያ አርሶ አደር የሚቻል አይደለም ይላሉ። የኢትዮጵያ አርሶ አደር አቅም አሁን የታየውን የዋጋ ጭማሪ የሚችል አለመሆኑን የሚገልፁት ባለሙያው፣ በአርሶ አደሩ ምርት ላይ ችግር እንዳይፈጠር ከወዲሁ ለችግሩ እልባት መስጠት እንደሚገባ ይጠቁማሉ።

አርሶ አደሩ እያነሳ ያለው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት እንዳለበት የሚጠቁሙት ዓለሙ፣ የተከሰተውን የዋጋ ንረት መንግሥትና አርሶ አደሩ መጋራት እንዳለባቸው ይመክራሉ። መንግሥት የአርሶ አደሩን አቅም ያገናዘበ ድጎማ ማድረግ ወይም ብድር ማመቻቸት እንዳለበት የገለጹት ዓለሙ፣ በአርሶ አደሩ በኩል ኢትዮጵያ ያለችበት ወቅታዊ ሁኔታና ዓለም ዐቀፍ ሁኔታውን መረዳት እንዲሁም በመንግሥት በኩል የአርሶ አደሩን ጥያቄ ተቀብሎ ከ10 እስከ 20 በመቶ ድጎማ ማድረግ ወይም ብድር ማቅረብ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የማዳበሪያ ዋጋ መናር መዘዙ

በአፈር ማዳበሪያ ዋጋ መናር ምክንያት አርሶ አደሩ የአፈር መዳበሪያ ሳይጠቀም ሰብል ካለማ፣ ያለ ማዳበሪያ አልዘራም ብሎ ማሳውን ጾም ካሳደረ ወይም የማዳበሪያ መጠኑን ለማዳረስ ብሎ በዝቅተኛ ምጣኔ ከተጠቀመ በሚቀጥለው የምርት ዓመት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እንደሚፈጥር ብዙዎች ከወዲሁ እየገለጹ ነው።

ሙያዊ ሐሳባቸው ለአዲስ ማለዳ ያካፈሉት የግብርና ኢኮኖሚ ባለሙያው ዓለሙ፣ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ መናር በአርሶ አደሩ ምርታማነት ላይ ተጽዕኖ ሊፈጥር እንደሚችል ይገልጻሉ። አርሶ አደሩ ማዳበሪያ ተጠቅሞ የሚያለማቸው ሰብሎች ከምርት በኋላ ለገበያ ሲቀርቡ ከአፈር ማዳበሪያ ዋጋው ጭማሪ ጋር ተከታትሎ ማደጉ እንደማይቀር ጠቁመዋል። አርሶ አደሩ አሁን የአፈር ማዳበሪያ የሚገዛበት ዋጋ ከጨመረበት ከምርት በኋላ ምርቱን ለገበያ ሲያቀርብ በዚያው ልክ የዋጋ ጭማሪ ሲያደርግ በሸማቹ ማኅበረሰብ ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚፈጥር አብራርተዋል።

የግብርናው ዘርፍ በውስጣዊና በውጫዊ በወቅታዊ ሁኔታዎች የተነሳ ችግር ውስጥ መከበቡን የሚገልጹት ዓለሙ፣ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት የሆነው ግብርና ችግር ውስጥ ከገባ የሚቀጥለው ዓመት አስከፊ እንዳይሆን ስጋት አላቸው።

አሁን ላይ ያጋጠመው የተጋነነ የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ ጭማሪ የኢትዮጵያን ግብርና ውጫዊ ፈተና መሆኑን የገለጹ ሲሆን፣ አርሶ አደሩ አፈር ማዳበሪያን በአግባቡ ካልተጠቀመ የምርት መቀነስ ሊገጥም ይችላል ይላሉ። እንዲሁም የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ መናር በሚቀጥለው ዓመት ለገበያ በሚቀርቡ የሰብል ምርቶች ላይ የሚያጋጥመው የዋጋ ንረት እየተባባሰ ለመጣው የኑሮ ውድነት አባባሽ ምክንያት እንዳይሆን ከወዲሁ መጠንቀቅ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

አርሶ አደሩ ያጋጠመው የአፈር ማዳበሪያ ዋጋ መናር በመንግሥት ድጎማ ወይም ብድር ካልተስተካከለለት የማዳበሪያ ወጪውን አስቦ ምርቱን ለገበያ በሚያቀርብበት ወቅት የዋጋ ማስተካከያ ማድረግ እንዳለበትም ዓለሙ ጠቅሰዋል። አርሶ አደሩ ወጪና ገቢውን እየመዘገበ ለገበያ በሚያቀርብበት ወቅት የዋጋ ማስተካከያ አደርጎ መጠቀም አለበትም ብለዋል።

ከውስጣዊ ችግሮች አንጻር በሰሜኑ ጦርነትና በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱት የጸጥታ ችግሮች መጋቢ የሆኑ የእርሻ አካባቢዎች ሳይታረሱ ጾም የሚያድሩበት ሁኔታ ከቀጠለ የምርት መቀነስ ማጋጠሙ እንደማይቀር ባለሙያው አያይዘው አሳስበዋል። በጦርነትና በጸጥታ ችግር ምክንያት በተለያዩ አካባቢዎች ላለፉት ሦስት ዓመታት የተስተጓጎለው ግብርና አሁንም የሚቀጥል ከሆነ ችግሩ እስከ አሁን ከነበረው የከፋ እንደሚሆን የሚጠቁመት ባለሙያው፣ መጋቢ የነበረ አርሶ አደር በጸጥታ ችግር ማረስ ሲያቆም፣ ከመጋቢነት ወደ ተመጋቢነት መቀየሩ ስለማይቀር ችግሩን ድርብርብ እንደሚየደርገው አመላክተዋል።

እንደ አጠቃላይ በግብርና ዘርፍ ላይ የሚፈጠሩ ችግሮች ወደፊት በሚፈጥሩት የዋጋ ንረትና የምርት አቅርቦት እጥረትን ተከትሎ፣ በተለይ በሸማቹ የማኅበረሰብ ክፍል ላይ የሚከሰተውን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም መንግሥት፣ የመንግሥት ሠራተኛውን ወይም የሸማቹን ማኅበረሰብ ኑሮ ማሻሻልና ገቢውን ከጊዜው ጋር ማሳደግ እንዳለበት ባለሙያው መክረዋል።


ቅጽ 4 ቁጥር 180 ሚያዝያ 8 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here