“ጫፍ የያዙ ጡዘቶችን አቀዝቅዘን ካላየን አስቸጋሪ ነው”

0
972

ዩሐንስ በንቲ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበርን ለረጅም ጊዜ በፕሬዝዳንትነት የመሩና አሁንም እየመሩ ያሉ ሰው ናቸው። በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር በ1984 የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኬሚስትሪ ተቀብለዋል። ከዛም ለተወሰኑ ዓመታት በምዕራብ ወለጋ በሚገኝ ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በኬሚስትሪ መምህርነት አገልግለዋል። እንደ መምህርነት ሙያ ሁሉ ለትምህርትም ልዩ ፍቅር አለኝ የሚሉት ዮሐንስ፣ በእቅድና ሥራ አመራር ኹለተኛ ዲግሪ ተቀብለዋል፣ በሕግ ትምህርት በርቀት የተከታተሉ ሲሆን፣ ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ከአዲሰ አበባ ዩኒቨርሲቲ በትምህርት ፖሊሲና ሥራ አመራር አግኝተዋል።

ስድስት መቶ ሺሕ በላይ የሚሆኑ አባላት ወዳሉት መምህራን ማኅበር መሪነት ከመምጣታቸው አስቀድሞ በወረዳ፣ በዞን እንዲሁም በክልል ደረጃ ማኅበሩን ማገልገላቸውን ያስታውሳሉ። አሁንም ከሐምሌ 2001 ጀምሮ ለ13 ዓመታት ማኀበሩን በፕሬዝዳንትነት በማገልገል ላይ ይገኛሉ። የመምህራን ማኅበሩ በተለያየ ጊዜ ባሳየው አቋም የተነሳም በአፍሪካ ደረጃ የተሻለ አኳኋን ላይ የሚገኝ ነው ተብሎ፣ እርሳቸውም አፍሪካን በመወከል የትምህርት ዓለማቀፍ ማኅበር ፎረም አባል መሆናቸውን ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ የትምህርት ጥራት መቀነስ፣ የመምህራንና የመምህርነት ሙያ ክብር የተነሳ እንደሆነ ብዙ ቅሬታዎችና ‹ነበር› የሚሉ ታሪኮች ሳይጠቀሱ አይቀሩም። በእንቅርት ላይ እንዲሉ፣ በዚህ ላይ በተለያዩ ያለመረጋጋትና ሰላም ማጣት ውስጥ በምትገኘው ኢትዮጵያ፣ የችግሩ ሰለባ ከሆኑት መካከል መምህራንና ተማሪዎች ተጠቃሽ ናቸው። ወቅታዊውን የመምህራን ሁኔታ፣ የመምህራን ማኅበርን እንቅስቃሴና የግል ልምዳቸውን በሚመለከት የአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ የተለያዩ ጥያቄዎችን በማንሳት ከኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርጋለች።

ከማስተማር ከራቁ በርካታ ዓመታት አልፈዋል። እንዴት ነው መምህርነት አይናፍቅም፣ አልናፈቅዎትም?
በጣም! እዚህ ዓለም ላይ አሉ ከሚባሉ ሙያዎች ሁሉ የምወደው ሙያ ነው። በእርግጥ በንድፈ ሐሳብም ደረጃ መምህርነት ወሳኝ ሙያ መሆኑን እረዳለሁ፣ ሠርቼም ዐይቼዋለሁ። እንደ መምህርነት ሙያ የሰዎችን አእምሮ ለመቅረጽ እድል የሚሰጥ፣ ከራስ በላይ ለሌሎች የማሰብን፣ ውስጣዊ ፍላጎትና መሰጠትን የሚገኝበት ሙያ ለእኔ እሱ ነው።

ደግሞም በራስሽ የምትወስኚው ነው እንጂ እንዲህ አድርገሽ አስተምሪ ወይም ከፍ አድርገህ አስተምር፣ ዝቅ አድርገህ አስተምር የሚል የለም። ‹ሌሰን ፕላን› ራሴ ነው የማዘጋጀው፣ ለልጆቹ በሚገባቸው መልክ በየደረጃቸው ቀርቦ ማስረዳት የሚችለው መምህር ነው። እንዲህ አድርገህ አስተምር የሚልም የለም። መምህሩ/መምህርቷ ባመኑበት ልክ እና ለልጆች በሚመጥን ልክ አገልግሎት መስጠት የሚቻልበት የሙያ ዘርፍ ቢኖር መምህርነት ነው። እናም አዎን ይናፍቀኛል።

ለመምህርነት የነበረውን ክብርና አሁን ያለውን ሁኔታ እንዴት ያዩታል?
የተደበላለቀ ነው። የመምህርነት ሙያን የሚተካ አሁንም የለም። ሙያው ክብር የለውም ቢባል፣ እኔ ከንግግር አያልፍም ባይ ነኝ። ምክንያቱም አሁንም ወሳኝ ነው። ለመምህርነት ቦታ የማይሰጥና የማያከብር ሕዝብ የትም ሊደርስ አይችልም። ያደጉ አገራት ልዩነት የፈጠሩት በሳይንስና በምርምር ነው። ይህ ደግሞ በትምህርት የሚመጣ ነው። ስለዚህ ሙያው ወሳኝ ነው። እና መምህርነትን ምንም ነገር ሊተካው አይችልም።

ከሀይማኖትም ጋር የሚያያዝ ነው። ስለበጎ ነገር ያስተምሩ የነበሩ መምህር እየተባሉ ነበር የሚጠሩት። እሱ በየእምነቱ አልቀረም። ስለዚህ አሁንም ቢሆን እኔ መምህርነት ወሳኝ ሆኖ ይቀጥላል ብዬ ነው የማስበው።

አንዳንዴ ከጥቅምና ወቅታዊ ክፍያ ጋር እኩል ተደርጎ ታይቶ በዚህ ምክንያት ወድቋል የሚባለው ትክክል አይደለም። ቁሳዊው ነገር ይምጣ ብሎ መታገል ይቻላል። የአቅም ጉዳይ ካልሆነ በቀር ለዚህ የሚሰስት ኢኮኖሚ መኖር የለበትም። እኛ የምንገፋውም እሱ እንዲመጣ ነው። ስለዚህ፣ በተቻለ መጠን ሙያው ሳቢና ጥሩ ተከፋይ እንዲሆን፣ ቢያንስ የአገር ኢኮኖሚ ነገር ሆኖ በሚገባ ኪሱን [የመምህሩን] መሙላት ባይቻል እንኳ ሌሎች በርካታ የማበረታቻ ስልቶች አሉ። እና እነዚያ በጥናት ተለይተው እየተተገበሩ ሙያው ተመራጭና ተፈላጊ እንዲሆን ማድረግ የእኛ ሙያ ማኅበር፣ የመንግሥትና የማኅበረሰቡም አጠቃላይ ኃላፊነት ነው።

ከዛ ወጪ መምህርነትን ዝቅ ማድረግ አይቻልም፣ ሊሆንም አይችልም። ያኔ የውድቀትን መንገድ መርጠናል፣ ወደ መጥፋት እየሄድን ነው ማለት ነው። ለችግሮች መፍትሄ መገኘት ያለበት ከትምህርት ቤቶች ነው። አሁን ያለው ወቅታዊ የፖለቲካ ይሁን ማኅበራዊ ወይ ኢኮኖሚ ችግር መፍትሄው ትምህርት ነው ሊሆን የሚችለው። ሕዝባችን ውስጥ ላለው ችግር መፍትሄ የምንፈልገው ከትምህርት ቤት ነው። የሌሎች አገራት ልምድና ተሞክሮ እሱን ነው የሚያሳየው።

በደንብ ትምህርትን ብናሰርጽ፤ በሚገባ እውቀት፣ ክህሎትና አመለካከትን ብንገነባ ኖሮ፤ መደማመጥን፣ መቻቻልን፣ አብሮ መኖርን፣ ሠርቶ መለወጥን፣ የሥራ ባህልንና እነዛን ሁሉ ብናስተምር፣ ይህች አገር የት በደረሰች። እና ችግር ካለ የችግሩ ምንጭ ትምህርት ነው መሆን ያለበት። እሱን ወደ መፍትሄ ማምጣት አለብን።

ሰዎች ለምን እንደዛ እንደሚሉ እረዳለሁ። ሰዎች ይገቡና ይወጣሉ [በመምህርነት ሙያ]፣ የተወሰነ ጊዜ ይቆዩና የተሻለ ብለው የሚያስቡት ጋር ይሄዳሉ። የተሻለ የሚባለው ክፍያ ነው። የፈለገውን ያህል ቢከፈል ግን ክፍያ ብቻውን አያረካም።

በእርግጥ! ሰው በልቶ መኖር አለበት። ለመምህርም ቢሆን ዝቅተኛ ኑሮውን መምራት የሚችልበት ክፍያ ያስፈልገዋል። ነገር ግን፣ ገንዘብ ብቻ የሚያረካ ቢሆን ሀብታሞች ቁጭ ባሉ ነበር። ዓለም ላይ ቢሊየነሮች አሉ፣ እኛም አገር እንደዛው። ግን አልበቃቸውም፣ እነሱም መሥራት ይፈልጋሉ።

ቢያንስ ለኑሮ የሚበቃ (ዝቅተኛ) ክፍያ ያስፈልጋል። ለዛ እየሠራን ነው፤ እንታገላለን። ነገር ግን፣ በእሱ ብቻ መለካት የለበትም። ውስጣዊ መሠረትን ጭምር ዐይተው፣ ሰውን የመለወጥ፣ አእምሮን የመቅረጽ ፍላጎት ያላቸው ሰዎች አሁንም ወደዚህ ሙያ መምጣት አለባቸው ብዬ አምናለሁ።

በትምህርት ቤት ‹ውጤታችሁ ጥሩ ካልሆነ እንደእኔ መምህር ትሆናላችሁ!› የሚሉ መምህራን እንዳሉ፣ እኔም ከግል ገጠመኜ በመነሳት መጥቀስ እችላለሁ። መምህራን የሙያውን ክቡርነት ምን ያህል ተረድተዉታል ማለት ይቻላል?
አንዱ ችግር እሱ ነው። ‹ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለውም› ይባላል። እኔ ሳስተምርም፣ በደንብ ካልሠራችሁ አስተማሪ ትሆናላችሁ ብዬ አላውቅም። እንደውም በደንብ ከሠራ ጎበዝ ተማሪ ነው አስተማሪ መሆን ያለበት። ምክንያቱም በትምህርት ሌሎችን መለወጥ ይቻላል።

ጎበዝና ተሸላሚ መምህራን አሉ። ሰሞኑን የሰማነው አንድ በሙያው ያገለገለና አሁን ጡረታ የወጣ መምህር፣ ተማሪዎቹ ትልቅ ቦታ ደርሰው ከተለያየ አገር ሆነው፣ አዋጥተው መኪና ገዝተው የሸለሙት አለ። እዚህም እንደዛው ጥሩ ሥራ የሚሠሩ፣ ዝቅተኛ ክፍያ እየተከፈላቸውም፣ ተማሪዎቻቸው የነበሩ ‹ለሕይወታችን መለወጥ ምክንያት የሆኑ› ብለው የሚሸልሟቸው አሉ።

ስለዚህ መምህር እንደዛ ማለት የለበትም። በነገራችን ላይ እንዲህ ዓይነት ሙያ ውስጣዊ ፍላጎት ይፈልጋል። ይህ ፍላጎት በትምህርት ነው የሚቀሰቀሰው። ምሳሌና አርአያ ዐይተን ነው የምንቀየረው። አንዳንድ ሰው ደግሞ ክፍያውን አይቶ ነው [ሥራውን] የሚመርጠው። ሰው ሥራ ስላጣ አይደለም ወደ መምህርነት የሚመጣው፣ ሥራ ያጣ ወደ መምህርነት አይምጣ። ሌላ ሥራ ይፈልግ። መምህርነት የሙያ ፍላጎትን፣ ለሌሎች ምሳሌ መሆንን፣ እውቀትን፣ ለሌሎች ለማካፈል ተነሳሽትን ይዞ ነው መምጣት ያለበት። እኔ ሰውን ባስተምር ሰው ይለወጣል።

አዎን! በቂ ክፍያ ይገባዋል። አገር በምትችለው አቅም ያንን ማድረግ እንዳለባት እንታገላለን፣ እየሠራን ነው። እየመጣ ያለ ለውጥ አለ። መቼም ክፍያም ሲጨምር ኑሮ ውድነት እየጨመረ ሲሄድ፣ ወቅታዊ በርካታ ሁኔታዎች ሲመጡ፣ እንደ አሁኑ ጊዜ ምንም ያህል ክፍያ ቢኖር መልሰሽ የምታወጪ ከሆነ በእጅሽ የሚቀር የለም። ያም ችግር ነው። መምህርም የግል ሕይወት ስላለው፣ ዝቅተኛ ቢያንስ ለኑሮ የሚበቃ ማግኘት አለበት። ለዛ የሚሆን ክፍያን አገሪቱ ልታቀርብ ይገባል። ከዛ ውጪ ግን ዝቅተኛ ነጥብ ካመጣህ አስተማሪ ትሆናለህ? አይቻልም። ዝቅተኛ ነጥብ የሚያመጣ ሰው መምህርነት ሙያ ጋር መምጣት የለበትም።

ሙያችን ክብር ያለው እንዲሆን እንዴት እንሥራ የሚለውን በራሳችን እናወራ ይሆናል፤ ተማሪ ፊት አይደለም። ክፍተቶችም አሉ። ግን በእኛም በኩል ግንዛቤ መፍጠር ያስፈልጋል። ሙያው ምንድን ነው፣ አሰፈላጊነቱስ የሚለውን ማኅበረሰቡም ትኩረት አድርጎ፣ መምህርና አስፈላጊውን ክብር እንዲያገኙ፣ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ማድረግ ያስፈልጋል። ክብር የሚሰጥበት ብዙ መንገድ አለ። ቀበሌ ሄዶ ሲሰለፍ ‹አስተማሪ እዚህ ካለ ቅድሚያ ለመምህር፣ ልጆቻችንን ሊያስተምር ነውና የሚሄደው ጊዜ የለውም።› ብሎ ወረፋችን ነው ሳይሉ ለመምህራን ቅድሚያ እየተሰጠ ነው ክብር የሚመጣው። በአዋጅና በክፍያ ብቻ ይመጣል ብዬ አላስብም። ክፍያ ግን ይገባዋል፣ ለዛ እየታገልን ነው።

ስርዓቱስ በዚህ ላይ ምን ያህል ያግዛችኋል? ምክንያቱም ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ሲገቡ መምህርነት ላይ የሚመደቡበት አካሄድ ከፍላጎት ይልቅ ውጤት ላይ መሠረት ያደረገ ነው። በዚህ ላይስ ድምጽ የምታሰሙበት እድል አለ?
አንደኛ ነገር ተማሪዎቻችን የየራሳቸው ምርጫ አላቸው። እኔ ሕክምና እመርጣለሁ ያለን ሰው መምህርነት ምረጥ ብሎ በማስገደድ የተማሪዎች የመምረጥ መብት ላይ ጫና ማሳደር አንፈልግም፣ ሌላውም ጫና እንዲፈጥር አንፈልግም። ነገር ግን የምንሠራቸው ሥራዎች አሉ።

ለምሳሌ ‹የነገው ሰው መምህር› የሚባል ክበብ በትምህርት ቤቶች አለ፣ ጠንካራ ላይሆን ይችላል። ፍላጎት ያላቸው፣ ሌሎችን የማስተባበር አቅም ያላቸው ይገባሉ። መምህርነት መምራትም ነው፣ ክፍል ውስጥ ሲያስተምር እየመራ፣ ዲሲፕሊን እያስጠበቀ፣ የቤት ሥራ ሥሩ እያለ ነው። ይህ አመራርም አለበት። ያን ዓይነት ክህሎትና ፍላጎት፣ ሰውን አስረድቶ የማሳመን ወይም እንዲረዳና እንዲቀበል እውቀትን እንዲቀስም የማድረግ ዝንባሌ ያላቸው ተማሪዎች በዚህ ክበብ ከታች ጀምሮ እንዲመጡ የማድረግ ጥረት አለ። ያ በተጠናከረ ሁኔታ እየተሠራ ነው ወይ ከተባለ፣ አይመስለኝም።

ግን ይሄ ይጠቅማል ተብሎ ነው የሚታሰበው። ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ለሚገቡ ደግሞ የወጪ መጋራት ስርዓት አለ። ማንኛውም ዘርፍ የሚገባ ተማሪ የወጪ መጋራት ይከፍላል። ቢያንስ ተምሮ ሲወጣና ወደ ሥራ ሲሰማራ የሚከፍልበት ስርዓት አለ። ለመምህርነት የታሰበው ግን በደንብ አልተሠራበትም፣ ግንዛቤ አልተጨበጠበት እንደሆነ እንጂ፤ ሙያውን የሚመርጡ ተማሪዎች ከዚህ ወጪ መጋራት ስርዓት ነጻ ይሆናሉ። በአገልግሎት ነው የሚከፍሉት፣ የተወሰነ ዓመት ሙያው ውስጥ ካገለገሉ ያ የወጪ መጋራቱን እንደከፈሉ ይወሰድላቸዋል። እንደዛ ከሆነ ተማሪው በኋላ ወጥቼ ከምከፍል ወደዚህ ልግባ በሚል የተሻለ ሰው ይመጣል ነው ሐሳቡ። ግን በሚድያው ማስተዋወቅን ይፈልጋል።

ሌላው ከመንግሥት ጋር ተወያይተን፣ ተደራድረን 2008 ላይ መፍትሄ ያገኘው የመኖሪያ ቤት አቅርቦት አለ። መኖሪያ ቤት ለመምህራን የመኖሪያ ብቻ ሳይሆን የሥራ ቦታም ነው የምንለው። በዚህ መሪ ቃል ነው ስንወያይና ስንከራከር የነበረው። መንግሥት ይህን አምኖበት ፈቀደ። ፓኬጁ ከማዕከላዊ መንግሥት ጽድቆ ወደ ክልል ሲሄድ፣ ክልሎች እንደተጨባጭ ሁኔታቸው ደግሞ እያዩ እንዲያስተናግዱ ሥራ እየተሠራ ነው። እሱ ባለፈው ዓመት ድረስ ባለን ሪፖርት ከ110 ሺሕ በላይ መምህራን፤ ኮንዶሚንየም ቤት አግኘተዋል፣ ወይም ቤት መሥሪያ ቦታ አግኝተዋል። ይህ የማበረታቻ ስልት ነው።

ቀርቦ ለማስረዳት እድል አላችሁ ወይ የሚለውን፣ በምናገኘው አጋጣሚ እናስተዋውቃለን። በሚድያ፣ በቃለመጠይቆችም እንናገራለን። በደንብ ግን የተሠራበት አይደለም። በሙያ ማኅበር ብቻ ሳይሆን በመንግሥትም ደረጃ እንዲህ ተደርጎ በደንብ ቢሠራ የተሻሉ ሰዎችን ወደ ሙያው ማምጣት ይቻላል።

ማኅበሩ ረጅም ጊዜን አሳልፏል፣ በተለያዩ የፖለቲካ ስርዓቶችም አልፏል። ማኅበሩ በጣም ተፈተነበት የሚባለው ጊዜ የትኛው ይሆን?
በየጊዜው የየራሱ ፈተና ነበረበት። ለምሳሌ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖ የ70 ዓመት ታሪኩ እየተጻፈ ነው። ማኅበሩ የተቋቋመው በ1940 ነው፣ መተዳደሪያ ደንብ አጽድቆ ተመሠረተ የምንለው ደግሞ በ1941 ነው። በ1953 የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ በነበረ ጊዜ፣ ማኅበሩ ተጠርጥሮ ነበር። ለውጥ ፈላጊነት ተብሎ ወደጎን የተገፋበት ጊዜ ነበር። ከዛ በኋላም በ1957 አገር ዐቀፍ ሥያሜውን አገኘ። የዛን ጊዜ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ የበላይ ጠባቂ ነበሩ፤ የሚያሰጋ ተቋም ሆኖ ስለነበር ነው።
በ1959 ከደሞዝ ጭማሪና በተያያዥ ነገሮች የተነሳ ከመንግሥት ጋር ግጭት ተፈጠረ። አገር ዐቀፍ እውቅና ያገኘው በ17 ዓመቱ ነው። ግንቦት 1960 ደግሞ ሕጋዊ እውቅና ጠይቆ፣ በዓመቱ አካባቢ ፍቃድ አገኘ።

ከዛ በኋላ ከትምህርት ዘርፍ ክለሳ ጋር ተያይዞ፣ በአፄ ኃይለሥላሴ የተሞከረ ነገር ነበር። እሱን ማኅበሩ ስላልተሳተፈበት አልቀበልም አለ። ጉዳዩ አስቀድሞም ምስጢር ነበር፣ ከወቅቱ ፓርላማ ጭምር ምስጢር ተደርጎ ተይዞ ነበር። እና ሕዝብ ያልተወያየበትና ማኅበሩ የማያውቀውን እንቃወማለን አለ ማኅበሩ። እናም እንዳይተገበር እንዲዘገይ ተደረገ። ያም አስተዋጽኦ አድርጎ ለጊዜው መንግሥት ስርዓት ውድቀት ምክንያት ሆነ።

እነዘህ ፈተናዎች ነበሩ። ነገር ግን የዛን ጊዜ ወደ ሥልጣን የመጣው የደርግ መንግሥት የማኅበሩን ፍላጎት ያውቅ ስለነበር አብሮ መሥራት ጀመረ። ግን ደግሞ በመሃል ግጭት ተፈጠረ፣ ከ1969 እስከ 1971 ድረስ ማኅበሩ ከደርግ ጋር ተጣልቶ ግጭት ወስጥ ገባ። ያኔ የታሰሩም የሞቱም አባላት እንዳሉ የማኅበራችን ታሪክ ያስረዳናል። በ1983 ሥልጣን ላይ የመጣው መንግሥት ወርዶ አዲሱ ሲተካም በማኅበሩ ውሰጥ የተፈጠረ አለመግባባት ነበር።

በየዘመኑ የራሱ ፈተናዎች እያለፈ የመጣ ማኅበር ነው። አሁንም የወቅቱ የማኅበራት እንቅስቃሴ የመግሥታት የዴሞክራሲ ነጸብራቅ ነው የሚሆነው። እና ወቅቱን እየዋጁ ከዘመኑ ጋር መራመድን ነው የሚጠይቀው። ግን ለመብት የሚከራከር ተቋም ከተለያዩ አካላት ጋር መጋጨቱ አይቀርም። ታሪክ ደግሞ ሌላውን የቀረወን ያወጣዋል።

አሁንስ ምን ያህል ኃይል አለው?
እንዳልኩት ትግሎች አሉ በየወቅቱ። አሁንም ቢሆን ለማኀበሩ የማይስማማውን ነገር አይሆንም ማለት አይቸግረውም። የሚመጡት ሁሉ እየሆኑ አይደለም። ለምሳሌ የመኖሪያ ቤት አሰጣጥ በነጻ የመጣ አይደለም። ዓመታትን የወሰደ ነው፣ ግን ጊዜ ይፍጅ እንጂ ማኅበሩ የያዘውን ዓላማ ሳያሳካ አይቀርም። በ1997ም እንደዛው፣ ሰዉ አልተገነዘበው ይሆናል እንጂ ማኅበሩ አገራዊ ሰላማዊ ሰልፍ አድርጎ ነበር። በ1994 ውጤት ተኮር የሥራ አፈጻጸም ግምገማ ስርዓት መሆን አለበት የሚል ነገር ነበር። መምህራን በዛ ውጤት ተኮር ስርዓት ካልተገመገሙ እድገት አይሰጣቸውም ተብሎ ነበር።

ማኅበሩ ይህን ተቃወመ፣ አልተስማማም። ድርድር ተደርጎ መንግሥት ካልተቀበለ ሰላማዊ ሰልፍ እናደርጋለን ብሎ ጉባኤው ወሰነ። ሥራ አስፈጻሚው ኃላፊነቱን ወስዶ እንደተባለው ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ሁሉ ተወያይቶ አልተስማማም፤ መንግሥት አልተቀበለም። ስለዚህ በጉባኤው ውሳኔ መሠረት 1997 ጥቅምት 10 ሰልፍ ይደረግ ተብሎ፣ የሰልፍ አወጣጥ ስርዓትና አዋጅ አለ፣ እሱን አያይዘን መፈክር ጭምር ለይተን በየክልሎች ላክን። ሰልፉ ተካሄደ።

ጊዜው ምርጫ የሚደረግበት ነበረ። አንዳንዴ ፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው ታግለው አሸነፉ የሚባለው። በእርግጠኝት የምናገረው የማኅበራችንም ሚና ነበር። ገዢው ፓርቲ ድምጽ እንዲያጣ የተደረገው በዚህም ነው። ምክንያቱም ማኅበሩ ባገኘው ድጋፍ [በምርጫው ላይ] በመታዘብም በማስተማርም ገብቶበት ነበር። ከዛ በኋላ ነው ከወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ሥራ አስፈጻሚው ቁጭ ብሎ ተወያይቶ፣ ይህን እናስተካክለላለን ተባለ። አንድ ዓመት ቆይቶ ወደኋላ የሦስትና አራት ዓመት ወደኋላ ክፍያ ተገኘ። እነዚህ ነገሮች ብዙም አልተሰሙም ይሆናል።

እናም ማኀበሩ ጠንካራ ነው፣ ጠንካራ ዓለማቀፍ ግንኙነት አለው። ተጽእኖ የመፍጠር አቅሙ ጠንካራ ነው። አንዱ ጥንካሬው በዘላቂነት ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ እየታገለ ለትምህርት ስርዓቱም፣ አቅሙ የሚችለውን ለማኀበሩና ለመምህራን አባላት ጥቅም እየሠራ የመጣ ነው። እንደተቋም የራሱ ድክመት ቢኖርበትም ግን ጠንካራ ጎንም እንዳለው መናገር ፈልጌ ነው።

አሁን ላይ የመምህራንን ምደባ በሚመለከት ማንነትን መሠረት ያደረጉ ምደባዎችና ወደ አዲስ አበባ የሚደረጉ ዝውውሮች እየተካሄዱ ነው የሚሉ ቅሬታውች ከመምህራን ይሰማሉ። እዚህ ላይ ማኅበሩ ምን ይላል?
በምክር ቤት ደረጃ በማኅበራችን ጥያቄው ቀርቦ ምንድን ነው ይህ ጉዳይ ብለን ተወያይተንበታል። በነገራችን ላይ አዲስ አበባ ብቻ ሳይሆን የክልል ክልል ዝውውር አለ። መምህራን እንደ አንድ መብትና ጥሩ ነገር የሚወስዱት የዝውውር ፈቃድ አላቸው። ይህን የሚመራ የመምህራን ማኅበርና ትምህርት ሚኒስቴር በጋራ ያዘጋጁት መመሪያ አለ። ያን መነሻ አድርጎ ለክልሎች ተልኮ ክልሎች እንደራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ያዘጋጁት የዝውውር ስርዓት የሚባል አለ።

በአገልግሎት፣ በማኅበራዊ ችግሮች፣ በጋብቻ ወይ በሌላ ምክንያት ዝውውር ይደረጋል። ክልል ውስጥ ያሉ ዞኖች ችግር የለውም፣ በክልል ውስጥም ብዙ አያስቸግርም። ከክልል ክልል ዝውውር አለ፣ ግን ቀላል አየደለም። ያ ክልል ያንን መምህር እቀበላለሁ ሲል፣ የተቀበለውን ያህል ሰው ወደላከው ክልል መላክ አለበት። አዲስ አበባም በዛ መልክ ነው የሚስተናገደው።

አዲሰ አበባ ለተወሰነ ጊዜ ተቋርጦ ነበር። ድርድር ተደርጎ ነው የተፈታው፣ ለሌሎችም እድል እንዲሰጥ። ቅርብ ጊዜም ከበጀት ጋር የሚያያዙ ነገሮች አሉ። ከክልል ክልል ወይም በአንድ ክልል እንደሚደረግ ዝውውር ወደ አዲስ አበባ የሚደረግ ዝውውር ፍሰቱ ቀላል አይደለም። የተለያየ ነገር ነው የሚነሳው። በአዲስ አበባ የመምህራን ቁጥሩ ብዙ ነው፣ ትናንሽ ሎድ ነው የያዙት የሚሉ አሉ። በሌላ በኩል ከተጨማሪ ቋንቋ ጋር የተያያዙ ትምህርት ቤቶች ሲከፈቱ እነዛ ደግሞ ክፍተት አላቸው። አፍ መፍቻ ቋንቋ፣ የሕጻናት መብት ኮንቬንሽን አለ፤ በዛ መሠረት ተማሪዎች እንዲማሩ ትምህርት ፖሊሰው ይደግፋል።

ከሕዝብ ጥያቄ ጋር ተያይዞ መንግሥት ጉዳዩን ለመፍታት ትምህርት ቤት ይከፍታል። ያን ሲከፍት ደግሞ ያንን ቋንቋ የሚያስተምሩ መምህራን ቋንቋውን ከሚያስተምሩ ክልሎች የሚገቡባቸው አግባቦች አሉ።

እሱም ቢሆን ግን በፍትሃዊ መንገድ ተወዳድረው ነው የመጡት ወይስ እንዴት ነው የሚለው ውስጡ በጣም ፍተሻ ይፈልጋል። እዚህ አካባቢ የሚነሱ ቅሬታዎች አሉ። እሱን ተከታትሎ ስርዓት ያለው ማድረግን ይጠይቃል። በዚህ በኩል የምንሠራው ሥራ አለ። ከዛ ውጪ እንዲህ ያሉ ዝውውሮች አሉ።

አሁን ይህን ብንከለክል ደግሞ እነዛ ተማሪዎች የመማር እድል ያጣሉ። አንዳንድ ጊዜ እዚህ አገር የሚነሱትን ጫፍ የያዙ ጡዘቶችን አቀዝቅዘን ካላየን አስቸጋሪ ነው። አንድም ችግር እየሆነ ያለው እሱ ነው። ከሕዝብ አብሮ መኖርና አብሮነት አንጻር የሚነሱትን ጥያቄዎች በእርጋታ ካላየናቸው ችግር ይፈጥራሉ። እሱን መከልከል አግባብ አይሆንም። [በዝውውር] ሲመጡ ግን ፍትሃዊ መሆን አለበት። እነማን ናቸው የመጡት? በዛ ቋንቋ የሚያስተምሩም ቢሆን አመጣጣቸው እንዴት ነው የሚለው ፍተሻ የሚፈልግ ነው።

በነገራችን ላይ አንዳንድ ክልሎች ላይም ይኸው ጉዳይ ችግር የሆነባቸው አሉ። ስለዚህ ሰፋ ያለ ነገር ነው፣ በሚፈልጉት ልክ ዝውውር ላያገኙ ይችላሉ። መምህራን የሚጠይቁት ዝውውሩ ፍትሃዊ ይሁን ነው። ለምሳሌ መመሪያው ላይ ለዝውውር አንዱ መስፈርት አገልግሎት ነው። እንዲሁም የትምህርት ደረጃና የትምህርት ዓይነት፣ በተለይ መምህሩ/መምህርቷ ምን ያህል ነው ሥራው ላይ የቆዩት የሚሉ ነገሮች ይታያሉ። እና በዛ መሠረት መሄድ ቢቻል የመምህራንን ቅሬታ ቢያንስ ይቀንሳል። የጠየቀ ሁሉ ዝውወር ላያገኝ ይችላል፣ ግን የሚገባው ሰው አግኝቷል ወይ የሚለውን በየደረጃው በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሠሩ ሰዎች በትኩረት እንዲያዩት፣ ከማኅበሩም ጭምር ይጠበቅብናል።

በማኅበሩ የሴት መምህራት እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
ማኅበራችን የሴት መምህራን ዘርፍ አለው። አሁንም ሴቶችን ማብቃት (ኢምፓወር ማድረግ) አለብን በሚል እምነት ምክትል ዋና ፀሐፊ የሚል ዘርፍ ከፍተናል። የሴት መምህራን ኮከስም አለ። ሴት መምህራት የሚወያዩት፣ ሐሳባቸው ለማኅበሩ ምክር ቤት የሚያቀርቡበት ስርዓትም ዘርግተናል። በምክር ቤታችንም ለምሳሌ ቢያንስ በጉባኤም፣ በምክር ቤትም 30 በመቶ ሴቶች መሆን አለባቸው ብለን አስቀምጠናል። ይህም ከ10 ዓመት አካባቢ በፊት ደንቡ ሲዘጋጅ ሴት መምህራን አባላት በዛ መጠን ስለነበሩ ነው። ቁጥራቸው በጨመረ ቁጥር ደንቡ እየተሻሻለ ይሄዳል ነው ሐሳቡ።

ሴት መምህራን የራሳቸው ፍላጎት አላቸው፣ በአመራር ውስጥ ባዋጡት ልክና በአባልነታቸው ልክ አመራርነት መለማመድ አለባቸው የሚል መሪ ሐሳብ ነው የምንከተለው። ለምሳሌ በጥናት እንደተረጋገጠው በአንደኛ ደረጃና በቅድመ መደበኛ ትምህርት ላይ ሴት መምህራት ቢበዙ፣ የእናትነት ፍቅር ስለሚያሳዩ ልጆችን በእንክብካቤ ያሳድጋሉ ተብሎ ስለሚታሰብ እንዲበዙ ይፈለጋል። በኹለተኛ ደረጃም እንዲበዙ ይፈለጋል፤ እንደሚፈለገው እየሆነ ባይሆንም።

ስለዚህ ቁጥሮች እየበዙ በሄዱ ቁጥር በአመራር ውስጥም ሴቶች እየበዙ ይሄዳሉ። በኃላፊነት ደረጃ ግን የክልል ማኅራት ፕሬዝዳንት ውስጥ ሴት አለች። ምክትል ፕሬዝዳንቶችና ዋና ፀሐፊዎችም አሉ። እዚህ ዋና ማዕከልም እንደዛው አሉ። የኦዲት ኮሚቴ ሊቀመንበርም ሴት ናት። ስለዚህ የመምህራን ማኅበር ስርዓተ ጾታ አገናዛቢ (ጀንደር ሴንሴቲቭ) ነው። እንዲሳተፉ ይፈለጋል፤ ያበረታታል ይደግፋል።

ማኅበሩ አሁን በጣም የሚያሳስበው ጉዳይ ምንድን ነው?
እንደ ማኅበር ከሆነ የፋይናንስ አቅሙ ነው። ያው አገር ስትኖር ነው ማኅበሩ ሊኖርና ኃላፊነቱን ሊወጣ የሚችለውና፣ የአገሪቱም ሁኔታ ያሳስበዋል።

ስለትምህርት ከፍ ያሉ እይታዎች ነበሩ። ብሂሎቻችንም ያንን ነበር የሚነግሩን። አሁን ግን ቸል እየተባለ ይመስላል። ትምህርትን ወደከፍታው ለመመለስና ለአገር እንዲጠቅም የትኛውን መንገድ መከተል ያስፈልጋል?
ትምህርት አስፈላጊነቱ መቀጠል አለበት። ምክንያቱም ትምህርት ከሌለ ወደ ጨለማው መመለስ ነው። ድምጻዊ ዓለማየሁ እሸቴ በሙዚቃው ‹ስማኝ ልጄ ሌት ፀሐይ ነው፤ ላልተማረ ሰው ግን ቀኑ ጨለማ ነው› እንደሚለው ነው። በተፈጥሮ ብርሃን ዐይናችን እያየ ቢሄድ፣ ትምህርት ግን ከሌለ ሰው ማመዛዘን አይችልም። በጣም ወሳኝ ነው። የተማረ ሰውና ያልተማረ ሰው ልዩነቱ እሱ ነው።

አሁን በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደዛኛው ጊዜ መኖር አይቻልም። ምክንያቱም በቴክኖሎጂ ነው ሁሉ ነገር እየሄደ ያለው። ያንን ለማድረግ መማር ግድ ነው፣ ቴክኖሎጂን ለመከተለም እንደዛው። አማራጨ የለም። አንድ ሰው ወረቀት ያዘ፣ በደንብ በሚገባው ወረቀቱ ላይ የተገለጸውን ያህል አገልግሎት አልሰጠ ይሆናል ወይም አልተጠቀመበትም ይሆናል። እሱ ችግሩ ምንድን ነው ብሎ መፈተሽ ነው የሚሻለው።

በእርግጥ የተያዘው ወረቀት ላይ የተጻፈውን የሚመጥን ነው ወይ እውቀቱ ነው አንዱ፣ እንዴት መጣ ወረቀቱ? በትክክል ወይስ ልክ ባልሆነ መንገድ ነው የመጣው። ልክ ባልሆነ መንገድ የመጣ ከሆነ እሱን ማየት ነው። ያ ሰው ለዚህ ሙያ ብቁ ነው የሚያስብል ዓይነት ምዘና ውስጥ በትክክል አልፏል ወይ? በዛ ምዘና ካላለፈና በዛ ልክ አገልግሎት ካልሰጠ እውነትም ዋጋ ላይኖረው ይችላል። በሚገባው ልክ አልፎበት፣ ውጣ ውረዱን ችሎ ተቋቁሞ፣ በሚገባ ተመዝኖ በዛው ልክ የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ማድረግ የሚችል ሲሆን ነው የተማረ ሰው የሚባለው ወይም ተምሯል የሚባለው።

በዛ ሁኔታ መሠረት አሁን ላይ የምናያቸው ችግሮች አሉ። አንዳንድ ሰዎች እንደምንሰማው የራሳቸው ያልሆነ ሰርተፍኬት የሚይዙበት፣ ፎርጅድ የሚያሠሩበትን ሁኔታ በትክክል ስርዓት ተዘርቶ የሚመለከተው ክፍል ተከታትሎ ስርዓት ማስያዝ አለበት። ለዛ ማኅበራችን እንዲህ ካለ ተቋም ጋር ተሰልፎ ለመሥራት ፍላጎት አለው። የተማረ ሰው ሰርተፍኬቱ ላይ ያለውን የሚመጥን ደረጃና እውቀት ያለው መሆን አለበት። ለዛ ደግሞ የተለያዩ የምዘና ዘዴዎች አሉ።

አሁን ለምሳሌ ከምርቃት በኋላ የመውጫ ፈተና የሚባል ነገር አለ። ሰው ወደ ሥራ ሲቀጠር ፈተና ተፈትኖ ነው ማለፍ ያለበት። ሰዉ ሰርተፍኬት ሲይዝ ይህን ማወቅ አለበት። ሰርተፍኬት የያዘ ሁሉ ላይሠራበት ይችላል።

በጠቅላላው አሁንም ትምህርት ወሳኝ ነው። እንደውም በዚህ 21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የበለጠ አስፈላጊ እየሆነ ይመጣል። እንደውም የተለማመድነው ዓይነት ሳይሆን ላቅ ያለ የተወሳሰበ ከወቅቱ ጋር ሊሄድ የሚችል ዓይነት ትምህርር ሰው ፈልጎ ማግኘት አለበት። ለዛም መንግሥትም፣ ትምህርት ሚኒስቴርም እኛም እንደ ሙያ ማኀበር መሥራት አለብን።

የመምህራን ማኅበር ከፖለቲካው ጋር ምን አገናኘው? ሰዉ በዛ መልክ አስተያየት እንዲሰጥ ያደረገው ምን ይመስላችኋል?
አሁንኮ ፖለቲካ ያልሆነ ነገር ያለ አይመስለኝም። ሁሉም ነገር ፖለቲካ ስለተደረገ፣ ከመንግሥር ጋር የሚደራደር ሰው ወይም አካል ከፖለቲካ ጋር ተያይዞ ቢነሳ የሚገርም አይደለም። እንደዛ ሆኖ ምን አደረገ ነው ነገሩ። እንደዛ ሆኖ የመምህራንን ጥቅም አስከበረ ወይስ አሳልፎ ሰጠ? እንደዛ በመሆኑ ተሸጋግሮ ምን ጥቅም አገኘ? የመምህራን ማኅበር ሊቀመንበር ወይም ሌላው የተለየ የሚያገኙት ጥቅም የለም። መሸጋገሪያ ምናምን ቢሆን ስንት ቦታ ደርሰናል ይሄኔ።

እንደሰዉ ግንዛቤ ነው። በቅርቡ ከሚያየው ተነስቶ ነው። ደግሞ መላምትም ሊሆን ይችላል። ሁሉም ሰው እንደ እኔ ወይም እንደ አንቺ ያስብ ማለት አይቻልም። ስለዚህ ሙያ ማኅበሩ የፖለቲካ ተጋላጭነቱ የጎላ ነው። ቅድም እንዳነሳሁት፣ ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ የተጋለጠ ነው፣ የተደራጀ ኃይል ስለሆነ። ሰዉን ማስተባበር የሚችል፣ ማኅበረሰብ የያዘ ስለሆነ ነው። በስሩ መምህራን፣ ተማሪዎችና ወላጆች አሉ። ስለዚሀ እዚም እዛም ምን ይሆን ብሎ የሚጠይቅ ይኖራል። አንድና ኹለት አካል አይደለም ይህን ማኅበር የሚከታተለው፣ ሁሉም ነው።

ነገር ግን ማኅበሩ ከደንቡ ውሰጥ በግልጽ የተቀመጠ፤ ከፖለቲካ፣ ከጎሳ፣ ከሃይማሞት፣ ከጾታና ከተለያዩ ልዩነቶች ነጻ ሆኖ የማኅበሩን ዓላማ ብቻ ለመስፈጸም የተቋቋመ መሆኑ እንዲታወቅልን ብሏል። መንግሥትም ይህን አውቄአለሁ፣ እሺ አለ። ይህ ትርጉም አለው፣ በዚህ ግቡ በዚህ ውጡ አትበሉን ነው ለመንግሥት። ፖለቲከኞችም የተደራጀ፣ አንጋፋና ተጽእኖ ፈጣሪ የሆነ ማኅበር ስለሆነ እንዲጠቀሙበት ይፈልጋሉ። ማኅበሩ ግን እኔ አያገባኝም የእናንተ ጉዳይ ነው። የራሳችሁ የፖለቲካ ጉዳይ ራሳችሁ ሥሩ። እኔ የምሠራው ደንቡም የሚለው ይህንን ነው ብሎ ቀደም ብሎ አውቆ ተገንዝበው እዛው እንዲቆዩ ነው።

ከዛ ውጪ 600 ሺሕ የሚሆን የማኅበሩ አባል አለ ስንል፣ ሁሉም እዚህ አገር ባለው የፖለቲካ ፓርቲ ያህል አመለካከት ያለው አስተማሪ አለ ማለት ነው። ያ የፖለቲካ መብቱን እዛው የፖለቲካ ፓርቲው ጋር ሄዶ ይተግብር። እዚህ መምህራን ማኅበር የሚመጣው ግን በሙያው ነው። ማንም የፈለገው የፖለቲካ አመለካከት ቢኖረው በዛ ውስጥ እዛ ሄዶ እንጂ እዚህ ማኅበሩ ጋር ሲመጣ ግን መምህሩ ሊያገኝ የሚገባውን ጥቅም እንዲያገኝ ማኅበሩ ይታገልለታል።

የደረጃ እድገት፣ ዝውውር፣ የትምህርት እድል፣ የመኖሪያ ቤት አቅርቦት አለ። አንተ የዚህ ፖለቲከ ፓርቲ አባል ስለሆንክ ይህን ጥቅም አታገኝም ብሎ የሚል ካለና ማኅበሩ ይህን ከሰማ ይከራከራል።

ከዛ ውጪ እንዳልኩት ለፖለቲካ ተጋላጭ ነው። በደርግ ጊዜና በኃይለሥላሴ የነበረውን እናውቃለን። ከዛ የሰሙትን የታሪክ መረጃ ተከትለው አሁንም እንደዛው ነው የሚሆነው ብለው ቢጠረጥሩ አይፈረድባቸውም። ግን በተጨባጭ አሠራሩን አያዩ መገምገም ነው።
ሁሉ ነገር ፖለቲካ ሊሆን አይችልም። መምህራን ማኅበሩ ከየትኛውም የፓርቲ ፖለቲካ ነጻ ሆኖ የሙያ ማኅበሩን ዓላማ የሚያራምድ መሆኑን ቢገነዘቡ ጥሩ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 180 ሚያዝያ 8 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here