መፍትሔ ያላገኘው የአንበጣ መንጋ

0
1192

የአንበጣ መንጋ በታሪክ ውስጥ የሰውን ልጅ ለረሀብ እና ለስደት ከሚዳርጉ የተፈጥሮ ክስተቶች መካከል አንዱ ነው። ከ2011 ጀምሮም ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ የአፍሪካ ቀጠና የበርሀ አንበጣ መንጋ አረንጓዴ ሰብሎችን ሁሉ በስፋት እያወደመ ይገኛል።

በዚህም ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰውና እንስሳትን ለረሃብ መዳረጉን እና አንበጣው የቀይ ባህር አዋሳኝ አገራትን አካሎ የነፋስ አቅጣጫ እየተከተለም ከአገር አገር በፍጥነት እየተዛመተ ነው። ከየመን እስከ ደቡብ ሱዳን፣ ከኬንያ እስከ ኤርትራ ከሶማሊያ እስከ ኢትዮጵያ የአንበጣ መንጋ ወረራ መከሰቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቁሟል።

ከ15 ዓመት በፊት በምዕራብ አፍሪካ ተከስቶ የነበረው የአንበጣ መንጋ 2.5 ቢሊዮን ዶላር የሚደርስ የሰብል ውድመትን ማስከተሉን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ገልፆ ነበር። ከ60 ዓመታት በፊትም ከባድ የሚባሉ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኞች አጋጥመው እንደነበር ድርጅቱ ይጠቁማል።

በምልሰት ወደኋላ ስናቀና በመርስዔ ኀዘን ወልደ ቂርቆስ የተጻፈውን ‹የኻያኛው ክፍለ ዘመን መባቻ› የተሰኘ መጽሐፍ እናገኛለን፣ ይህም ወደ 1922 ይመልሰናል። በዛን ዓመት የአንበጣ መቅሰፍት በአገር ላይ ወርዶ የቆላውንም የደጋውንም ሰብል ያጠፋ እንደነበር ተጠቅሶ ይገኛል። ‹‹በጊዜውም ግርማዊ ንጉሥ ተፈሪ የአደጋውን ከባድነት ስለተመለከቱ ሕዝቡ ምህላ ይዞ በጸሎት እግዚአብሔር እንዲለምን አደረጉ። ጉዳት ለደረሰበት ሁሉ የምህረት አዋጅ አስነገሩለት።›› ሲሉ መርስዔ ኀዘን አስፍረውታል። የአዋጁ የተወሰነ ክፍል እንዲህ ይላል፤
‹‹…በየአደባባይ ለነገር የተቀመጥህ ሰው በየቤት ገብተህ እስከ ታኅሳስ ልደታ አዝመራህን ሰብስብ። …የዘንድሮውንም የ1922 ድሃው መኸሩን እንዲሰበስብና በአንበጣ የተጎዳውም አገር በጭራሽ እንዳይጠፋ፣ ለአንድ ዓመት የዳኝነትና የውርርድ ዕዳ ግማሹን እንዲከፍል አድርገናል።

…ቆላ አገር ግን በድርቅና በውርጭ በአንበጣም በችግር ምክንያት ሰብል ስቶብህ ከ1919 ከሦስት ዓመት ወዲህ ቤትህን ዘግተህ በጭራሽ ተሰደህ ቦታህን ለቀህ የሄድክ ሰው ከተሰደድህበት አገር ተመልሰህ ገብተህ እረስ። ያለፈውን የግብር ዕዳ ምረንሃል። ወደፊትም የጠፋብህን እርሻና ቤትህን የምታቀናበት ኹለት ዓመት ቀን ሰጥተንሃል። መስከረም 11 ቀን 1922።››

ይህ እንግዲህ የኢትዮጵያ ታሪክ አካል ነው። በዓለማችንም ከፍተኛውና ብዙ ወጪና ኪሳራ ያስከተለ የበረሃ አንበጣ ወረርሽኝ ከ1986 እስከ 1989 ሲከሰት ኢትዮጵያና ሶማሊያን አጥቅቷል። ይህን ችግር ያስከተለው የአንበጣ መንጋ የተነሳው ከኤርትራ እና ሱዳን ቀይ ባህር ድንበር ሲሆን፣ ይህም የበረሃ አንበጣ የሚራባበት ስፍራ እንደሆነ ብዙዎች በእርግጠኝነት ይናገራሉ።

በጊዜው በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ይካሄድ የነበረውና ሠላሳ ዓመታትን የዘለቀው ጦርነት ትኩረት በመውሰዱ፣ የአንበጣ መንጋው በጊዜ እንዳይደረስበት ሆኗል። ከዛም በላይ በአራት ዓመታት ውስጥ አንበጣው ወደ 23 የአፍሪካ አገራት እንዲሁም ወደ እስያ አገራት ጭምር እንዲሰራጭ ጊዜ ሰጥቶታል።

የቅርብ ዓመቱን ክስተት ስንመለከት፣ ከኹለት ዓመት በፊት ባጋጠመ የአንበጣ መንጋ በዐስር ዓመታት ውስጥ ካጋጠመው የከፋ አደጋ የተባለለት ነው። ይህም ጅቡቲን፣ ኢትዮጵያንና ሶማሊያን ጨምሮ የአፍሪካ ቀንድን በማዳረስ ሰብሎችንና የእንስሳ ግጦሽን ማውደሙን የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) ጠቅሷል።

ክስተቱ የአካባቢውን አገራት የምግብ ደኅንነት አደጋ ላይ ጥሏል። የአንበጣ መንጋው በዚያው ዓመት በጥርና በየካቲት ወር በፍጥነት ተዛምቶ ኢትዮጵያን፣ ሶማሊያንና ኬንያን በማዳረስ በምሥራቅ አፍረካ በፍጥነት መዛመቱ አይዘነጋም። ወረርሽኙ ለኢትዮጵያና ለሶማሊያ በ25 ዓመት እንዲሁም ለኬንያ ደግሞ በ70 ዓመት ውስጥ ካጋጠሟቸው የከፋው ነው ተብሏል።

ታድያ ፋኦ ስጋቱን ገልጾ፣ ከመጋቢት ወር በኋላ ያለው እርጥብ የአየር ሁኔታ ኹለተኛ ዙር የአንበጣ ወረርሽኝ በማስከተል በአካባቢው ሕዝብ ሕይወት ላይ ‹ታይቶ የማያውቅ ስጋትን› ይደቅናል ሲል አስገንዝቦ ነበር። የአንበጣ መንጋውን የመቆጣጠሩ ሥራ በፍጥነት ካልተከናወነ መንጋው በ20 እጅ ሊጨምር እንደሚችልም ማስጠንቀቁ ይታወሳል። ይህም በግጭቶች፣ በድርቅና በጎርፍ ምክንያት ከፍተኛ የምግብ እጥረት ባለበት በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ ከባድ ጉዳትን እንደሚያስከትል እና በተጨማሪም የአንበጣ መንጋው እየተራባ ባለባቸው በኢራንና በየመን ጉዳቱ የባሰ ይሆናል ብሏል። በዚህም በምሥራቅ አፍሪካ አገራት ውስጥ የሚገኙ በአስር ሺህ ሔክታሮች የሚገመት ግጦሽ መሬት በአንበጣ መንጋው መውደሙ አይዘነጋም።

ባለፈው ዓመት 2013 በመጨረሻዎቹ ኹለትና ሦስት ወራት ከሱማሌ ላንድ የገባው የአንበጣ መንጋ በሱማሌ ክልል ከዐስር በላይ ወረዳዎች እና በባሌ በአንዳንድ ቦታዎች መንጋው ተከስቶ ነበር። ሆኖም ወደ ሌሎች አከባቢዎች ሳይራባ መንጋውን መቆጣጠር እንደተቻለ የግብርና ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።

ዛሬስ?
ባለፈው ዓመት የነበረውን የበረሃ አንበጣ ሁኔታ መቆጣጠር መቻሉን ተከትሎ ‹በአሁኑ ወቅት በእርግጠኝነት አይደገምም› ተብሏል። ለዚህም ብዙ ምክንያቶች ተጠቅሰዋል። ከእነዚህም መካከል የአየር ሁኔታው አንደኛው ነው ሲል ግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል። በኢትዮጵያ በአንዳንድ ቦታዎች የተከሰተው የድርቅ ጊዜ ረዘም ማለቱን ተከትሎ ‹‹አንበጣው እንቁላል ለመጣል እርጥበት ያስፈልገዋል። በድርቁ ምክንያት እርጥበት ማግኘት ስላልቻለ የመራባቱን መጠን በእጅጉ ቀንሶታል›› ብሏል።
ስለዚህም አንበጣው የእድገት ጊዜውን ለመጨረስ እና እንቁላል መጣል የሚጀመርበት ደረጃ ላይ አይደለም።

በጎረቤት አገራት ያለውን ሁኔታ በተመለከትም፣ በአብዛኛው የአየር ሁኔታው ከአገር ውስጥ ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ የአንበጣ መንጋው ከውጭ ገብቶ ጉዳት ያደርሳል የሚል ስጋት እንደሌለም ተገልጿል።

ነገር ግን በፑንትላንድ እና ቀይ ባህር አካባቢ መጠነኛ መራባቶች አሉ። ሚኒስቴሩ ካለው ዝግጁነትና ኃይል ጋር ሲነጻጸር ግን መቆጣጠር የሚያስችል ሙሉ አቅም እንዳለው ነው የተገለፀው። አገር ውስጥም ቢሆን ዝናብ ሲጥል የአንበጣ መንጋው የመራባት አቅም ቢኖረውም፣ አገሪቱ ካላት አቅም አንጻር ‹በቂ ዝግጅት ስለተደረገ መቆጣጠር ይቻላል› ሲል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።

የግብርና ሚኒስቴር አንበጣ መቆጣጠሪያ አውሮፕላኖችን በመጠቀም፣ አንበጣ ባይኖርም እንኳ ቅኝት በማድረግ ለቁጥጥር የሚያስችል ዝግጅት እያደረገ መሆኑም ተገልጿል።

ሆኖም ግን በአሁን ወቅት ታዲያ በኢትዮጵያ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ተልታሌ ወረዳ በሚገኙ 5 ቀበሌዎች የአንበጣ መንጋ መከሰቱን የዞኑ ኮምዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ለአል ዐይን አማርኛ ጠቁሟል። የአንበጣ መንጋው በወረዳው በሚገኙ መካሳ፣ ጋዲል፣ ኤል ኩኔ እና ዋንዶ ዲግሬ በተባሉ 5 ቀበሌዎች መከሰቱን በተልታሌ ወረዳ የግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ቢሮ የቁጥጥር እና ክትትል የሥራ ሂደት ባለቤት እንግዳ ዮሃንስ ናቸው የተናገሩት።

በአሁኑ ወቅትም የአንበጣ መንጋው በ400 ሄክታር መሬት ላይ በማረፍ ጉዳት ማስከተሉን እና ከዚህም ውስጥ 30 ሄክታር መሬት ላይ የኬሚካል ርጭት መደረጉን የወረዳው የግብርናና የተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ ብርሃኔ አማረ መግለጻቸው ተዘግቧል። የኬሚካል ርጭቱን ሥራ በመኪና በማከናወን ላይ እንደሆኑ ያስታወቁት ብርሃኔ፤ ይህም ሥራውን በሚፈለገው ፍጥነት ለማከናወን አዳጋች አድርጎታል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም ሲደረግ የነበረው የአውሮፕላን ርጭት አሁን ላይ አለመኖሩን ያስታወቁ ሲሆን፤ አንበጣው እየደረሱ ባሉ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የአውሮፕላን የኬሚካል ርጭት ድጋፍ እንዲደረግም ጠይቀዋል።
የግብርና ሚኒስቴር፤ በኢትዮጵያ አንበጣ መንጋ እንዳይከሰት የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እየተሰራ እንደሚገኝ ማስታወቁ ይታወሳል።

የአግሮ ኢኮኖሚክስ ባለሙያው ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) ግብርና ሚኒስቴር በኢትዮጵያ በየዓመቱ የሚፈጠረውን የአንበጣ መንጋ ለመቆጣጠር እየሠራ ቢሆንም፣ ምን ያህል ርቀት ተጉዟል የሚለውን እንዲህ ነው ብሎ ለመግለጽ እቸገራለሁ ብለዋል።
ነገር ግን በቀጣይ የግብርና ሚኒስቴር አገራዊ አቅምን በማጎልበት ከምሥራቅ አፍሪካ አንበጣ መከላከል ተቋም ጋር በመሆን በአሁን ወቅት አንበጣ መንጋው በተከሰተበት አካባቢ ከመቆጣጠር ባሻገር በቀጣይ የበረሀ አንበጣ መንጋው ከቀይ ባህር፣ ከየመን፣ ከሱማሌ እና ከሌሎች አገራት ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ በትኩረት መሥራት እንደሚያስፈልገው አሳስበዋል።

በግብርና ሚኒስቴር የእፅዋት ጥበቃ ዳይሬክተር በላይነህ ንጉሤ በበኩላቸው ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት፣ በእነዚህ አካባቢዎች የተከሰተው አንበጣ መንጋ እስከ አሁን ባለው ምንም አይነት ጉዳት እንዳላደረሱ እና ከሚኒስቴሩ አቅም በላይ እንደማይሆን ነው ያመለከቱት።
ዳይሬክተሩ አክለውም፣ የግብርና ሚኒስቴር የአንበጣ መንጋው በተከሰተበት አካባቢ ኹለት አውሮፕላኖችን ተከራይቶ የኬሚካል ርጭት እና የመከላከል ሥራ እየሠራ ነው ብለዋል።

ኬኒያ እና ሶማሌ የበረሀ አንበጣ መንጋውን ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ መቆጣጠር ባለመቻላቸው እና የቁጥጥሩ ሂደቱም አናሳ መሆኑን ተከትሎ፣ በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት ለሚፈጠረው መንጋ ምክንያት እንደሚሆን እና መሉ በሚባል ደረጃ ለመቆጣጠር አዳጋች እንዳደረገው ተናግረዋል።

የግብርና ሚኒስቴር በቀጣይ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በአሁን ወቅት የበረሀ አንበጣ መንጋው ከተከሰተባቸው ቦታዎች ባሻገር ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዳይራባ እና ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሠራ ነው የጠቆሙት።


ቅጽ 4 ቁጥር 180 ሚያዝያ 8 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here