ድብርት ወይም ድባቴ (Depression) የአዕምሮ በሽታ ሲሆን፣ በስሜት መረበሽና ለነገሮች ፍላጎት በማጣት የሚፈጠር ድብርት መሆኑን የሥነ ልቦና ባለሙያዎች ይገልጻሉ። የመንፈስ ጭንቀት የተለመደ እና ከባድ ሕክምና የሚያስፈልገው ሕመም ሲሆን፣ ሰዎች በሚሰማቸው ስሜት፣ በአስተሳሰብ እና በድርጊታቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳድር የአሜሪካ ሳይካትሪክ አሶሴሽን ስለ ድባቴ በድህረገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ ይገልጻል።
ድባቴ ወይም ድብርት መታከም የሚችል ህመም መሆኑን የሚገልጸው የማሕበሩ መረጃ፣ ድብርት የሀዘን ስሜትን ወይም በአንድ ወቅት በወደዷቸው እንቅስቃሴዎች ላይ ፍላጎት ማጣት ያስከትላል ይላል። ድብርት ለተለያዩ ስሜታዊ እና አካላዊ ችግሮች ሊዳርግ ይችላል የሚለው ተቋሙ፣ ህመሙ ያለባቸው ሰዎች በሥራ ቦታ እና በቤት ውስጥ የመሥራት ችሎታቸውን እንደሚቀንስ ያብራራል።
እንደ የዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ በአለም ላይ በግምት 280 ሚሊዮን ሰዎች የድብርት ህመም አለባቸው። ከወንዶች ይልቅ ሴቶች የበሽታው ተጠቂ ሲሆኑ፣ ሰዎች ሳይጠነቀቁ ቀርተው የሚይዝ በሽታም እንዳልሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይገልጻሉ። የድብርት ታማሚዎች በተለይ በአፍሪካ አገራት ብዙውን ጊዜ ህመማቸውን የመደበቅ ሁኔታ እንደሚታይባቸው ጥናቶች ያመላክታሉ። የመንፈስ ጭንቀት በአለም ላይ የተለመደ በሽታ ሲሆን፣ ከጠቅላላው ህዝብ 3.8 በመቶ ይገመታል። በዓለም ዙሪያ በድብርት በሽታ ከሚጠቁት ሰዎች መካከል 5 በመቶ በአዋቂዎች እና 5.7 በመቶ ከ 60 ዓመት በላይ ዕድሜ ባላቸው ሰዎች ላይ ይከሰታል።
የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳው፣ በዓለም ዙሪያ ከአራት ሰዎች አንዱ ሰው የአእምሮ ጤና መታወክ ይሠቃያል። ነገር ግን፣ 60 በመቶው ተጠቂዎች ህመማቸውን በመደበቃቸው ምክንያት የህክምና አርዳታ አያገኙም።
ድብርት በሽታ ከተለመደው የስሜት መለዋወጥ እና በአጭር ጊዜ ለሚቆዩ ስሜታዊ ምላሾች እንዲሁም በዕለት ተዕለት ሕይወት ውስጥ ለሚፈጠሩ ተግዳሮቶች ምክንያት መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ይገልፃል። በተለይም፣ በተደጋጋሚ በሚከሰትበት ጊዜ እና መካከለኛ ወይም ከባድ ከሆነ፣ ድብርት ከባድ የጤና ችግር ሊሆን ይችላል። የተጎዳው ሰው በከፍተኛ ሁኔታ እንዲሰቃይ እና በስራ ቦታ፣ በትምህርት ቤት እና በቤተሰብ ውስጥ በደንብ እንዳይሰራ ሊያደርግ ይችላል። በጣም በከፋ ሁኔታ ላይ ከደረሰ ደግሞ፣ የመንፈስ ጭንቀት ራስን ማጥፋት ሊያስከትል ይችላል። የአለም ጤና ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየው በየዓመቱ ከ700 ሺሕ በላይ ሰዎች ራሳቸውን የሚያጠፉ ሲሆን፣ ራስን ማጥፋት ከ15-29 ዓመት ባለው የእድሜ ክልል ውስጥ አራተኛው የሞት መንስኤ መሆኑን የድርጀቱ መረጃ ያመላክታል።
ለአእምሮ ሕመሞች ውጤታማ የሆኑ ሕክምናዎች ቢኖሩም፣ ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ውስጥ ከ75% በላይ ሰዎች ምንም ዓይነት ሕክምና አያገኙም። ለውጤታማ እንክብካቤ እንቅፋት የሚሆኑት የሀብት እጥረት፣ የሰለጠኑ የጤና አጠባበቅ ባለሙየዎች እጥረት እና ከአእምሮ መታወክ ጋር የተያያዘ ማህበራዊ መገለል ናቸው።
በሁሉም የገቢ ደረጃዎች ውስጥ የሚገኙ የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው ሰዎች ብዙውን ጊዜ በትክክል አይመረመሩም። የተለያዩ የስሜት መረበሽ ዓይነቶች እንዳሉ የአለም ጤና ድርጅት መረጃዎች ያመላክታሉ። ኮቪድ 19 ከተከሰተ በኋላ የድብርት በሽታ በዓለም ላይ በ25 በመቶ እንደጨመረ ጥናቶች ያመላክታሉ።
ደብርት የሚከሰተው በማህበራዊ፣ ስነ-ልቦናዊ እና በባይሎጂካል ሁኔታዎች ውስብስብ መስተጋብር መሆኑን የአለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል። በአሉታዊ የሕይወት ሁኔታዎች ውስጥ ያለፉ ሰዎች (ሥራ አጥነት፣ ሐዘን፣ አሰቃቂ ሁኔታዎች) ለድብርት የመጋለጥ እድላቸው ከፍተኛ ነው። የመንፈስ ጭንቀት፣ በተራው ወደ ተጨማሪ ጭንቀት እና ወደ ስራ መቋረጥ ሊያመራ እና የተጎዳውን ሰው የህይወት ሁኔታ እና የመንፈስ ጭንቀት እራሱን ሊያባብስ ይችላል። በመንፈስ ጭንቀት እና በአካላዊ ጤንነት መካከል ግንኙነቶች እንዳለ የሚገልጸው የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ፣ ለምሳሌ የካርዲዮ ቫስኩላር በሽታ ወደ ድብርት ሊያመራ እንደሚችል ይጠቁማል።
እንደ አሜሪካ ሳይካተሪክ አሶሼሽን መረጃ፣ የድብርት ምልክቶች ከቀላል እስከ ከባድ ሊለያዩ እንደሚችሉ ይጠቁማል። ከድብርት በሽታ ምልክቶች መካከል የጭንቀት ስሜት፣ በአንድ ወቅት በተደሰቱ እንቅስቃሴዎች ላይ ፍላጎት ወይም ደስታ ማጣት፣ የምግብ ፍላጎት ለውጦች፣ ክብደት መቀነስ ወይም መጨመር (ከአመጋገብ ጋር ያልተዛመደ)፣ እንቅልፍ የማጣት ችግር ወይም ከመጠን በላይ መተኛት፣ ጉልበት ማጣት ወይም ድካም፣ ዓላማ የለሽ አካላዊ እንቅስቃሴ መጨመር (ለምሳሌ፣ ዝም ብሎ መቀመጥ አለመቻል፣ መጨናነቅ) ወይም የዘገየ እንቅስቃሴ ወይም ንግግር፣ ዋጋ ቢስነት ወይም የጥፋተኝነት ስሜት መፈጠር፣ የማሰብ፣ የማተኮር ወይም ውሳኔ የማድረግ ችግር፣ የሞት ወይም ራስን የማጥፋት ሀሳቦች መጨመር ይገኙበታል።
የድብርት ህመምን ለመከላከል ለልጆች እና ለወጣቶች ትምህርት ቤትን መሰረት ያደረጉ አዎንታዊ ፕሮግራሞች ጠቃሚ እንደሆኑ የአለም ጤና ድርጅት ይመክራል። ለአረጋውያን የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ የመንፈስ ጭንቀትን ለመከላከል ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ድርጅቱ ይመክራል።
ድብርትን ለመከላከል ባለፈ ጥፋት ወይም ውድቀት ላይ በማተኮር ጸጸት ውስጥ አለመግባት፣ ከባለፈው ስህተት በመማርና ዛሬ ላይ ማተኮር፣ ማህበራዊ ተሳትፎዎችን ማዳበር፣ ከተለያዩ እፆችና አልኮል ሱሰኝነት መቆጠብ፣ ግጭቶችን፣ ቅራኔዎችንና አለመግባባቶችን በአግባቡ መፍታት፣ ውጥረትንና ጭንቀትን የሚፈጥሩብዎትን ነገሮችና ሁኔታዎችን መለየትና ከእነሱ መራቅ፣ በጎ ማድረግና ምላሹን ከሰዎች አለመጠበቅ፣ ጭንቀትና ድብርት ሲሰማዎ ለቅርብ ወዳጅ፣ ጓደኛ ወይም ቤተሰብ ማጋራት፣ ድንገተኛ ችግር ሲያጋጥምዎ፤ ራስን ማረጋጋት፣ ሌሎች ሰዎች ስለእርስዎ በሚሰጡት ትችት እና አስተያየት አለመረበሽ፣ የህይወትን ጥሩ ገፅታ ማየት፣ በአላማና በእቅድ መኖር፣ ጊዜን በስራ ማሳለፍ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ማድረግ፣ ንፅህናን መጠበቅ እና ጤናማ የአመጋገብ ስርአትን መከተል፣ ለራስ ጊዜን መስጠትና እረፍት ማድረግ፣ በፈጣሪ መተማመን በባለሙያዎች የሚመከሩ ናቸው።
ድብርት ውጤታማ ህክምና እንዳለው የሚገልጸው የአለም ጤና ድርጅት፣ በጊዜ ሂደት የድብርት ምልክቶች ክብደት ላይ በመመስረት፣ የጤና ባለሙያዎች እንደ የባህሪ ማነቃቂያ፣ የግንዛቤ ባህሪ ቴራፒ እና የግለሰባዊ ሳይኮቴራፒ ወይም ፀረ-ጭንቀት መድሀኒቶች ያሉ የስነ-ልቦና ህክምናዎችን ሊሰጡ ይችላሉ።
ለተለያየ ደረጃ ላይ የሚገኙ የድብርት ህመሞች የተለያዩ መድሃኒቶች ጥቅም ላይ እንደሚውሉ የአለም ጤና ደደርጅት መረጃ ይጠቁማል። የጤና ባለሙያዎች ከፀረ-ጭንቀት መድሀኒት ጋር ተያይዘው ሊከሰቱ የሚችሉትን አሉታዊ ተፅእኖዎች፣ የትኛውንም ጣልቃ ገብነት የማድረስ ችሎታን (በሙያው፣ ወይም የህክምና መገኘት) እና የግለሰብ ምርጫዎችን ማስታወስ እንዳለባቸውም ያስገነዝባል። ከግምት ውስጥ የሚገቡ የተለያዩ የስነ-ልቦና ህክምና ዜዴዎች በግለሰብ ወይም በቡድን ፊት ለፊት የሚደረጉ የስነ-ልቦና ህክምናዎችን በባለሙያዎች እና ክትትል የሚደረግባቸው ቴራፒስቶች መከታተል በድርጅቱ ተመካሪ የህክምና መፍትሔዎች ናቸው።
ጸረ ድብርት ወይም ጭንቀት መድኃኒቶች በልጆች ላይ ደብርትን ለማከም ጥቅም ላይ መዋል እንደሌለባቸው የአለም ጤና ድርጅት ይመክራል። እንዲሁም ፣ጸረ ድብርት መድሃኒቶች በጉርምስና ዕድሜ ላይ የሚገኙ ወጣቶች ተመራጭ የሕክምና መስመር አለመሆናቸውን የሚገልጸው ድርጅቱ፣ የጸረ ድብርት መደኃኒት አጠቃቀም ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባ ይጠቁማል።
ቅጽ 4 ቁጥር 180 ሚያዝያ 8 2014



