የብሔራዊ ሎተሪ የአጭር የጽሑፍ መልዕክት ዕጣ እክል ገጠመው

0
1339

. ተቋሙ ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብቷል

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በጋራ በመሆን የአጭር የጽሑፍ መልዕክትን በመጠቀም ሊጀምር የነበረው የሎተሪ ጨዋታ ችግር እንዳጋጠመው ለአዲስ ማለዳ ገለፀ።

አስተዳደሩ እንደገለፀው ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በድርሻ ክፍፍል ምክንያት ሒደቱን ማስቀጠል እንደተሳነው መረዳት የተቻለ ሲሆን ይህም ከሚገኘው ገቢ 40 በመቶ የሚሆነውን ኢትዮ ቴሌኮም የይገባኛል ጥያቄ በማንሳቱ እንደሆነ ታውቋል። ከዚህም ጋር በተያያዘ ብሔራዊ ሎተሪ ከጠቅላላ ገቢው ከ35 እስከ 40 በመቶ የሚሆነውን ለባለ ዕድለኞች የሚሸልምበት አግባብ እንዳለ የተጠቀሰ ሲሆን የትርፍ ክፍፍሉ ይህን ታሳቢ የሚያደርግ ባለመሆኑ ሒደቱን ማስቀጠል እንዳልተቻለ ከአስተዳደሩ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በሌላ በኩል ደግሞ የተጠቀሰውን የትረፍ ክፍፍል አስተዳደሩ ተቀብሎ ወደ ሥራ ቢገባ እንኳን የሎተሪ ጨዋታው በተጀመረ ጊዜ ወደ ተጠቃሚዎች የተንቀሳቃሽ ስልኮች መልዕክቶች ሲላኩ ኢትዮ ቴሌኮም 10 በመቶ ጭማሪ ገቢ ያገኛል። ይህ ሁሉ ተደማምሮ የአስተዳደሩን ገቢ ወደ 16 በመቶ ዝቅ ያደርገዋል።
የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ቴዎድሮስ ንዋይ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት ዕጣ ለመጀመር ኅብረተሰቡ በመጀመሪያ ደረጃ መረጃው ሊኖረው ስለሚገባ በአጭር የጽሑፍ መልዕክትና በቴሌቪዥን ወይም በሬዲዮ ማስተዋወቅ እንደሚገባና ይህም ወጪው በአስተዳደሩ አንደሚሸፍን አስታውቀዋል።

ይህም ይላሉ ቴዎድሮስ በአንደኛ ደረጃ በብሮድካስት ባለሥልጣን አዋጅ መሰረት ባለሥልጣኑ ሳይፈቅድ በተንቀሳቃሽ ስልክ ላይ የንግድ ይዘት ያላቸውን መልዕክቶች መላክ ክልክል ነው። ይሁን እንጂ አሁን ላይ የባለሥልጣኑን ሙሉ ፍቃድ እንደተገኘ ቴዎድሮስ ያስረዳሉ። በኹለተኛ ደረጃ ደግሞ በተለያዩ የብሮድካስት መገናኛ ዘዴዎች ማስተዋወቅ ደግሞ በዋጋ ደረጃ ከፍተኛ ወጪ እንደሚጠይቅ ቴዎድሮስ ያስረዳሉ።

በዚህም የተነሳ አስተዳደሩ ከሚገኘው ጠቅላላ ገቢ 60 በመቶ ወስዶ ለማስታወቂያና ለባለ ዕድለኞች ከፍሎ ምንም ትርፍ ስለማይኖረው ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በጋራ የመሥራት ሐሳቡን አሁን ባለው ደረጃ ለማቆም እንደተገደደ ለመረዳት የተቻለ ሲሆን፤ በኢትዮ ቴሌኮም በኩልም አጭር የጽሑፍ መልዕክቶችን ወደ ተጠቃሚዎች ለመላክ ፈቃደኛ አለመሆን ትልቁ እንቅፋት እንደሆነ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ቴዎድሮስ በመጨረሻም ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ የታቀደው የሎተሪ ጭዋታ ተግባራዊ ቢሆን፤ ለኹለቱም ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ገቢ ከማስገኘቱም በላይ ወደ መንግሥት ካዝና ፈሰስ የሚደረገው ገቢም ይጨምራል ሲሉ ሐሳባቸውን ይደመድማሉ።

ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በዚህ ግማሽ ዓመት በታሪኩ ከፍተኛ ትርፍ 114 ሚለዮን ብር ማስመዝገቡ የሚታወስ ሲሆን፤ ከወረቀት ሎተሪ ሽያጭ እና ከሌሎች በአስተዳደሩ ቀጥተኛ ተሳትፎ ከሚሰበሰቡት ገቢዎች በተጨማሪ ወደ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ተደራሽ ለመሆን በተንቀሳቃሽ ስልክ በመጠቀም ሎተሪ በማጫወት በቀጣይ አስተዳደሩ ከዘርፉ የሚያገኘውን ገቢ የማሳደግ ዓላማ እንደነበረው ታውቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here