300 ቢሊዮን ብር ዕዳ ያለበት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከፋይናንስ ትችት ነፃ ነኝ አለ

0
675

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ከገንዘብ ነክ ትችቶችና ክፍተቶች ነፃ መሆኑን አስታወቀ።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከትችቶች ነፃ ከመሆኑም ባሻገር ጤናማ የገንዘብ አያያዝ ስርዓትን እየተከተለ እንደሆነም ጨምሮ ገልጿል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሞገስ መኮንን ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የኦዲት ችግሮች ቢኖሩበትም አሳሳቢ እንዳልሆነ አስረድተዋል። ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይጠቀም የነበረው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎትን ስርዓት በመሆኑ በኦዲት ግኝቱ ላይ ክፍተት እንዲኖር ምክንያት መሆኑንም ሞገስ አክለዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በየዓመቱ ከሚነሱበት ከገንዘብ ጋር የተያያዙ ትችቶች ነፃ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለመላው ሠራተኞቹ በፋይናንስ ሕግ መሰረት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ጥሪውን አስተላልፏል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ይህን ይበል እንጂ በኮርፖሬት ቦንድ መልኩ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የተበደረውን 216 ቢሊዮን ብር የመክፈል አቋም ላይ አለመሆኑን አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም ዕትሟ ላይ ምንጮችን ጠቅሳ ማስነበቧ ይታወሳል።

ምንጮች እንደሚያመላክቱት የኢትዮጵያ ኤልክትሪክ ኃይል ከውጭ አበዳሪዎች የወሰደው ብድር ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ብድር ጋር ተደምሮ 300 ቢሊዮን ብር እንደሚደርስና ይህም የአገሪቱን 80 በመቶ አመታዊ በጀት ጋር የሚስተካከል ነው። ከዚህም ጋር ተያይዞ 2.7 ቢሊዮን ብር ባለፈው በጀት አመት መሰብሰቡን ያሳወቀው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በዛው መጠን 58ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር በአመት ለዕዳ ክፍያ እንደሚያወጣ የታወቀ ሲሆን፤ ይህም የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በየአመቱ 56 ቢሊዮን ብር ኪሳራ እያስመዘገበ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል።

ከገቢው ጋር እጅግ የተራራቀ ዕዳ ውስጥ የተዘፈቀው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በዛው መጠን 16 ቢሊዮን የዕዳ ወለድ እንዳለበት የባለፈው አመት ሪፖርት ያመላክታል። ምንጮች እንደሚገልፁት ድርጅቱ ከሚያስገባው ገቢ 90 በመቶ የሚሆነው አስተዳደራዊ ወጪዎችን ለመሸፈን እንደሚውልና ከዚህ የዘለለ ጠቀሜታ ላይ ስለማይውል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋነኛ የገቢ ምንጭ ከብድር የሚገኙ ገንዘቦች መሆናቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አሁን ላይ ደርሻለሁ ከሚለው ነፃ የኦዲት ግኝት ጋር የማይታረቅ ሀሳብ ነው። ከውጭ አበዳሪ የገንዘብ ተቋማትም ኮርፖሬሽኑ ከአራት እስከ ዘጠኝ በመቶ በሚደርስ የወለድ መጠን 45.3 ቢሊዮን ብር መበደሩን አዲስ ማለዳ ለማወቅ ችላለች ።

በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የልማት ድርጅቶች ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማውጣት ትላልቅ አገራዊ ግንባታዎችን የሚያካሒደው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል፤ በተለያየ ጊዜ የሚጀመሩት ግንባታዎች በተያዘላቸው ጊዜ ተጠናቀው ወደ ሥራ ባለመግባታቸው እና በዛው መጠን የብድር ወለዱ ስለሚጨምር መሥሪያ ቤቱ ብድሩን ላለመክፈሉ ዋነኛ ማነቆ መሆናቸው ለመረዳት ተችሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here