ባልደራስ በደቡብ ክልል ህዝባዊ ስብሰባዎችን እንዳያደርግ መከልከሉን አስታወቀ

0
619

ፓርቲው በአርባ ምንጭ ከተማ የአገር አቀፍ ፊርማ ንቅናቄ ማስጀመሩን ገልጿል

ዕረቡ ሚያዚያ 12 (አዲስ ማለዳ) ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) ፕሬዚደንቱ እስክንድር ነጋ እና የአደረጃጀት ጉዳዮች ኃላፊው ስንታየሁ ቸኮል የአገር አቀፍ ፊርማ ንቅናቄን ለማስጀመር ዛሬ ረቡዕ ሚያዚያ 12 ቀን 2014 ደቡብ ኢትዮጵያ፤ አርባ ምንጭ ከተማ መግባታቸውን አስታወቀ።

አመራሮቹ ወደ ቦታው ያቀኑት ባልደራስ አገራዊ ፓርቲ መሆኑን አስመልክቶ በአካባቢው የሚደረገውን የድጋፍ ፊርማ የማሰባሰብ ንቅናቄ ለማስጀመር መሆኑን ፓርቲው ገልጿል።

ፓርቲው የፊርማ አሰባሰቡን ንቅናቄ ለማስጀመር በአርባ ምንጨ እና በወላይታ ሶዶ ህዝባዊ ስብሰባዎች ለማድረግ ጠይቆ ከተፈቀደ በኃላ፣ “ከበላይ የመጣ ትዕዛዝ ነው” በሚል ስብሰባዎቹ እንዳይደረጉ መከልከሉን አስታውቋል።

ጉዳዩን አስመልክተው የተናገሩት የፓርቲው ፕሬዚዳንት፣ “ስብሰባ ሊከለክሉን ይችላሉ፧ አርባ ምንጭ እንዳንመጣ ግን ሊከለክሉን አይችሉም፤ እንዳንመጣ ቢፈልጉም እኛ ግን የማንንም ፍቃድ ሳንጠይቅ መጥተናል”ብለዋል።

የአደረጃጀት ጉዳዮች ኃላፊው በበኩላቸው፣ “አዳራሽ ብንከለከልም፣ የአርባ ምንጭ ህዝብ ግን ተቀብሎ የፊርማ አሰባሰቡን ንቅናቄ አስጀምሯል” ማለታቸውን ከፓርቲው ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ባልደራስ) የካቲት 22 ቀን 2014 ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በፃፈው ደብዳቤ ከክልላዊ ፓርቲ ወደ አገር አቀፍ ፓርቲነት ለማደግ ትብብር የጠየቀ ሲሆን፤ ቦርዱም ፓርቲው የመስራች አባላት ፊርማ ለማሰባሰብ በሚዘዋወርባቸው ክልሎች እና የከተማ አስተዳደሮች ትብብር እንዲደረግለት መግለፁ ይታወሳል።

______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here