በጣይቱ አገር ሰማይ ሥር

0
616

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

የዓድዋ ድል የሰውነት ልክ መስፈሪያ ነው። በዓድዋ የሰውን ሰውነት ዝቅ በማድረግ የናቁ፤ ከፍ በማድረግም የታበዩ ሁሉ አፍረዋል። በዓድዋ ድል የዝማሬ ድምጽ፤ ከሰው እንበልጣለን ያሉ አላዋቂዎች እንዲሁም ከሰው እናንሳለን ብለው አንገታቸውን የደፉ ሁሉ ባንነዋል፤ ነቅተዋል። የዓድዋ ነገር «የሰውነት ማህተም» የተባለው ለዛ ነው፤ የሰው ልጅ ሁሉ እኩልነት ፍንትው ብሎ የታየበት በመሆኑ።

ይህ ኹነት የተፈጠረው፤ ይህ ተዓምር በሰው ልጅ የተሠራው በእኛዋ በኢትዮጵያ ምድር ነው። አገራቸውን በደማቸው አቆይተው ለዓለምም የሰውን ልጅ ክቡርነት በመስዋዕትነት ያሳዩት አባቶች የእኛው እናቶች፤ የእኛው አባቶች ናቸው። እንግዲህ የሰውነት ልክ በዛ መጠን የገባው ሕዝብ፤ ዛሬ ላይ በልጆቹ እንደ አዲስ የሴቶች እኩልነት እየተባለ «ግንዛቤ» እየተሰጠው ነው ሲባል ምንኛ ያሳዝን!

እቴጌ ጣይቱ የሴት ቁና፤ መስፈሪያ ልኩ ነበሩ። በአገራችን እንደ ጣይቱ ሁሉ ሥማቸው ደምቆ የሚነሳ ከአፄ ዘርዐ ያዕቆብ ቤተ መንግሥት ንግሥት ኢሌኒ እንዲሁም ሻገር ስንል እቴጌ ምንትዋብ አሉ። በእነዚህ ብርቱ ሴቶች አገር ሰማይ ሥር፤ ዛሬ ላይ የሴቶች ወደ ሥልጣን የመምጣት ነገር ወንድሞችን በማንጸሪያነት የሚያስቀምጥ መሆኑስ አይደንቅም? «እሳት አመድ ወለደ» እንዲሉት ሆኖብን ነው’ንጂ!

እነ ጣይቱ የሰውነት ከፍታን ከጾታም ከማንነትም በላይ አኑረው አሳይተዋል። «ፌሚኒዝም» የሚባለውን እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ ቀለም በትህትና እና በእውነት፤ ባሕልንና እምነትን በራስ ወዳድነት በመሻር ሳይሆን በብልሃት አሳይተዋል።

እቴጌ ጣይቱ ጣሊያዊውን ዲፕሎማት አንቶኔሊ እንዲህ ብለውት ነበር፤ «…እኔ ራሴ ሴት ነኝ። ጦርነት አልፈልግም። ነገር ግን ይህን ውል ብሎ ከመቀበል ጦርነትን እመርጣለሁ» በዚህ ዓረፍተ ነገር ሴትነታቸውን ጠቅሰዋል፤ ስሜታቸውን ገልጸዋል፤ ላመኑበት ግን የት ጥግ ድረስ እንደሚሔዱ ቁልጭ አድርገው ተናግረዋል፤ በተግባርም አሳይተዋል።

በጣይቱ አገር ሰማይ ሥር፤ የሰው ልጅ ሁሉ እኩል ነው። እንኳንና በተፈጥሮ በሚታደለው ጾታ ይቅርና የሰው ልጅ ደክሞ ባገኘው ሀብት እንኳ ከፍና ዝቅ ሊል አይገባም። «ብርሃን ዘኢትዮጵያ» በተሰኙት በጣይቱ አገር ሰማይ ሥር፤ ሴት ቤቷን አይደለም አገር ትመራለች። የራሷን ክብር አይደለም የዓለምን ሕዝብ ክብር የሚያስጠብቅ ምሳሌን ታሳያለች።

በነጣይቱ አገር ሰማይ ሥር፤ እነ እምዬ ምኒልክ በንግሥናቸው ታብየው ቀኝ እጃቸውን የሚገፉ አልነበሩም። እነርሱ የሰው ልጅ ክቡርነት የታያቸው ናቸው፤ ሰውን ከማንነቱ ሳይሆን ከአመለካከቱ መዝነዋል። እናሳ!? በጣይቱ አገር ሰማይ ሥር፤ እንኳን እኛ ዓለም ሊጠለል አይገባም ነበር? ይህን የመገንዘቡ ጊዜ ሩቅ እንዳይሆን ተስፋ እናደርጋለን።

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here