የአየር ብክለትን ታሳቢ ያደረጉ የነዳጅ ውጤቶች ወደ አገር ውስጥ ሊገቡ ነው

0
449

መንግሥት ለከባቢ አየር ንብረት ብክለት ትልቅ ትኩረት በመስጠት ለመጀመሪያ ጊዜ ከዚህ ቀደም ከነበረው አሰራር በተለየ ወደ አገር ውስጥ የሚያስገባቸውን ነዳጅና የነዳጅ ውጤቶችን አገራዊ ደረጃ ሊያወጣላቸው እንደሆነ ከወደ ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ተሰምቷል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እንዳስታወቀው ከዚህ ቀደም ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት ነዳጅና የነዳጅ ውጤቶች ምንም ዓይነት አገራዊ ደረጃ የሌላቸው እና ከአየር ንብረት ጋርም ያላቸውን መስተጋብር የተጠና እንዳልነበር ለመረዳት ተችሏል። በዚህም ምክንያት ባለፉት ዓመታት በርካታ አሉታዊ ተፅእኖዎች በአየር ንብረት ላይ ያሳድሩ እንደነበር የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ለአዲስ ማለዳ ተናግሯል።

ከአለፉት ዓመታት ትምህርት በመውሰድ በነዳጅና በነዳጅ ውጤቶች ምክንያት የሚደርሰውን የከባቢ አየር ብክለትና በውጤቶች ላይ ሚደርሰውን ብክነት ለመከላከል ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከነዳጅ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ምርቶች ዓለም ዐቀፋዊ ሁኔታ በመመዘን ኢትዮጵያዊ ደረጃ ለማውጣት ከጥራትና ደረጃ መዳቢ ባለሥልጣን፤ እንዲሁም ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ጋር በቅንጅት እንደሚሠራ መረጃዎች ያመላክታሉ። የሚውጣውም አገራዊ የጥራት ደረጃ ለአገሪቱ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል።

በማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር የነዳጅ ዘርፍ አሠራርና ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ኃይሉ ተክለአብ ለአዲስ ማለዳ ሲናገሩ፤ ኢትዮጵያ በዓመት 3 ቢሊዮን ዶላር ነዳጅና የነዳጅ ውጤቶችን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ወጪ እንደምታደርግ አውስተው፤ የሚገቡት ምርቶች ግን በአቅም ማነስ ምክንያት ጥራታቸው ወጥ እንዳልሆነና ይህም ለከባቢ አየር ብክለትና ለተጠቃሚዎች በደረሰ ጊዜ ደግሞ በተሽከርካሪዎች የሞተር ጤንነት ላይ እክል እንደሚሆን ያስረዳሉ። አያይዘውም በተለይ እስከ ዛሬ ወደ አገር ውስጥ ይገባ የነበረው የናፍጣ ዓይነት ለከባቢ አየር ብክለት ዋነኛ ተጠቃሽ የሚባለውን የሰልፌት ንጥረ ነገር በብዛት ያካተተ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

በዚህ አያበቁም ኃይሉ፤ በናፍጣው ውስጥ እንደታየው የሰልፌት መጠን አይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለው የቤንዚን ዓይነት ቀላል የማይባል የካርቦን መጠን እንዳለው አክለው ከዚህ ቀደም ‹‹ሱፐር ቤነዚን›› የሚባል የጥራት ደረጃው ከፍ ያለ የቤንዚን አይነት ገበያ ላይ ይከፋፈል እንደነበር እና በኋላም በአቅም እጥረት ምክንያት እንደቀረ አንስተዋል።

እንደ ኃይሉ ገለፃ ከዚህ በኋላ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት ቤንዚን፣ ናፍጣ፣ ኬሮሲን እና የአውሮፕላን ነዳጅ ኢትዮጵያዊ የጥራት ደረጃ እንደሚወጣላቸውና በከባቢ አየርም ላይ የሚኖራቸውን አሉታዊ ተፅእኖ ለመቀነስ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጠንክሮ እንደሚሠራ ታውቋል።

ወደ አገር ውስጥ የሚገቡትን ነዳጅና የነዳጅ ውጠየቶችን ከብክለትና ከብክነት ጠብቆ ለኅብረተሰቡ ፍትሐዊነትን በተከተለ መንገድ እንዲሠራጭ ማድረግ የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ዋነኛ ኃላፊነት እንደሆነ የሚታወቅ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here