የፋሲካ ገበያ ከዓመት እስከ ዓመት

0
1675

‹እንኳንስ ዘንቦብሽ…› እንዲሉ፣ ብዙዎችን እያማረረና እያሰጋ ያለው የኑሮ ውድነት የበዓል ሰሞን ደግሞ ይብስበታል። ለወትሮም በዓልን ጠብቀው የሚደረጉ የዋጋ ለውጦችን ጭማሬዎች እንደሚኖሩ ቢጠበቅም፣ በ2014 የፋሲካ በዓል ግን የዋጋ ጭማሬዎቹ የተጋነኑና የብዙዎችን የበዓል አከባበር ልምድ ሊቀይሩ እንደሚችሉ የሚጠበቁ ናቸው።

በ365 ቀናት ልዩነት የበግ፣ የዶሮ፣ የቂቤ፣ የእንቁላል እንዲሁም የዘይትና ከበዓል ከበራ ጋር በተያያዘ ሸማች ሊሸምት የሚሻቸው ምርቶች ዋጋቸው አልቀመስ ብሏል። አምና ይህን ጊዜም የነበረው ገበያ ዋጋ እና የዘንድሮው ሲነጻጸርም የአንድ ዓመት ሳይሆን አምስት ወይም ዐስር ዓመት በፊት የነበረ ያህል ይመስላል። የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ ይህን ጉዳይ በማንሳት፣ በአዲስ አበባ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ገበያዎችን በመቃኘትና ሸማቾችንም በማነጋገር የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

ፋሲካ በኢትዮጵያ ከሚከበሩ በዓላት በተለይ በክርስትና ዕምነት ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ኃይማኖታዊ በዓል ነው። በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የፋሲካ በዓል የሃይማኖቱ ተከታዮች ከወትሮው በተለየ በዓሉን ለማድመቅ በየዓመቱ የሚታትሩበት ወቅት ነው። በዓሉን ለማክበር ከወትሮው የተለየ የበዓል ዝግጅቶች ለማድረግ ከማኅበረሰብ እስከ ግለሰብ ድረስ ሽር ጉዱ ይደምቃል።

በበዓላት ወቅት ለበዓሉ ተፈላጊ የሚባሉ ምርቶች ላይ የተወሰነ የዋጋ ጭማሪ መታየቱ የሚታወቅ ቢሆንም፣ የዘንድሮ ግን ከወትሮው በተለየ ሁኔታ ቀድሞ ከተፈጠረው የኑሮ ውድነት ጋር ተደራርቦ የዋጋ ንረቱን የበለጠ የተጋነነ እንዲሆን አድርጎታል።

የዋጋ ንረቱ በተለይ ዝቀተኛ ገቢ ያለውን የኅብረተሰብ ክፍል በእጅጉ እየፈተነ ባለበት ወቀት፣ የፋሲካ በዓል ገበያ ከወትሮው የተለየ መሆኑ ደግሞ ሌላ ተደራቢ ችግር ሆኗል። መንግሥት ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችን እያደረገ መሆኑን ቢናገርም የሸቀጦችን ዋጋ ከመናር ያስቆመው ነገር የለም።

በየጊዜው እያሻቀበ የመጣው የዋጋ ንረት ጋር ገቢውን ማሳደግ ያልቻለው የማኅበረሰብ ክፍል፤ ወትሮውንም በኑሮ ውድነት እየተፈተነ ቢሆንም፣ በበዓላት ወቅት ደግሞ በዓልን በወጉ ለማክበር አዳጋች እንዳደረገበት አዲስ ማለዳ በበዓላት ገበያ ላይ አግኝታ ያነጋገረቻቸው ሸማቾች ይገልጻሉ።

ታዲያ በዕምነቱ ተከታዮች ዘንድ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የፋሲካ በዓልን ለማድመቅ ከወትሮው የተለዩ የበዓል ማድመቂያ ዝግጅቶች ያዘጋጃሉ። በዓሉን ለማድመቅ ከሚዘጋጁት መካከል ከምግብና ከመጠጥ እስከ ቤት ማስዋብና አዲስ አልባሳትን እስከመግዛት ይደርሳል። የዘንድሮው የፋሲካ በዓል ገበያ የበዓል ማድመቂያ ግብዓቶችን ለመግዛትና እንደከዚህ ቀደሙ በዓልን በድምቀት ለማክበር የማይችሉ የማኅበረሰብ ክፍሎች እንዲኖሩ የሚያደርግ እንደሆነ ለበዓል ገበያ የወጡ ሸማቾች ይናገራሉ።

የበዓል ገበያ ከመድረሱ ከ15 ቀናት በፊት የነበረው ገበያ የበዓል ዋዜማ ሲደርስ በተለይ መሠረታዊ የበዓል ዝግጅት ግብዓቶች ዋጋ መናር ማጋጠሙን ነው ሸማቾች የሚጠቅሱት። የዘንድሮውን የፋሲካ በዓል ገበያ በአዲስ አበባና ገበያ በሚደራባቸው የክልል ከተሞች ከዚህ ቀደሙ የተጋነነ ሆኖ መዋሉን አዲስ ማለዳ ባሰባሰበችው መረጃ አረጋግጣለች።

ገበያው እንዴት ዋለ!
የፋሲካ ገበያ ከሌሎች ክብረ በዓላት በላይ የሚደራ ገበያ ሲሆን፣ ከእንሰሳት እስከ እንስሳት ተዋጽዖ፣ ከፍራፍሬ እስከ ቅመማ ቅመም ከሸቀጣ ሸቀጥ እስከ ሰብል ምርቶች በየአካባቢው ገበያው ይደራል። አሁን አሁን ገበያ መድራቱ ቀርቶ ገበያ አልቀመስ አለ ወደሚለው ያመራ ይመስላል። ለዚህም እንደ ዋና ምክንያት የሚነሳው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ የመጣው የዋጋ ንረት ቢሆንም፣ ከፋሲካ ቀደም ብሎ በነበሩት ሳምንታት የነበረው የገበያ ሁኔታ በፋሲካ ዋዜማ ለውጥ አሳይቷል።

አዲስ ማለዳ የዘንድሮው የፋሲካ በዓል ገበያ ከደራባቸው የክልል ከተሞችና ከአዲስ አበባ መረጃዎች አሰባስባ የበዓል ገበያ ከዓመት እስከ ዓመት ያለውን ልዩነት በዝርዝር ተመልክታለች። የዘንድሮው የፋሲካ በዓል ገበያ በ2013 ከነበረው የፋሲካ በዓል ገበያ ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ጭማሪ አሳይቷል። ዘንደሮው የበዓል ገበያ ጭማሪ እንዲታይበት ካደረጉ ምክንያቶች መካከል በየጊዜው እያደገ የመጣው የዋጋ ንረት መሆኑ ይነገራል።

የበሬ ገበያ ከሚደራባቸው ዓመታዊ ክብረ በዓላት መካከል የፋሲካ በዓል አንዱ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የእርድ በሬ በማድለብ በሚታወቁት የጅሩ አርሶ አደሮች መንደር የበሬ መሸጫ ዋጋ ከዓመት ዓመት ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ መጥቷል። ይሁን እንጂ በዚህ ዓመት አንድ በሬ የተሸጠበት ዋጋ ከዚህ በፊት ተሰምቶ አይታወቅም። ለዚህም ይመስላል ከሰሞኑ ነገሩ ብዙዎችን አጀብ ያስባለው።

በአማራ ክልል ሰሜን ሽዋ ዞን የምትገኘው የሞረትና ጅሩ ወረዳ አርሶ አደሮች ከስንዴና ጤፍ አምራችነታቸው በተጨማሪ በተለይ ለገና እና ለፋሲካ በዓላት የእርድ በሬ አደልበው ለገበያ በማቅረብ ይታወቃሉ። በዘንድሮው የፋሲካ በዓል የጅሩ አርሶ አደሮች ለገበያ ካቀረቧቸው የድልብ በሬዎች መካከል አንድ በሬ ከ200 ሺሕ ብር መሸጡ ብዙዎችን ከማስገረም አልፎ ‹ወዴት እያመራን ነው!› የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ የጋበዘ ሆኗል።

አዲስ ማለዳ ከሞረትና ጅሩ ወረዳ መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ያገኘችው መረጃ እንደሚያመላከተው፤ በዘንድሮው የፋሲካ ገበያ አንድ አርሶ አደር ለገበያ ያቀረበው ድልብ በሬ በነጋዴዎች 220 ሺሕ ብር ቢቆጠርለት አልሸጥም ማለቱ ተሰምቷል። የጅሩ አርሶ አደሮች በየዓመቱ በድልብ በሬ የታወቁ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ወትሮውንም የበሬ መሸጫ ዋጋቸው ከሌሎች አካባቢዎች ጭማሪ የሚታይበት ነበር። ይሁን እንጂ የዘንድሮው ከምንጊዜውም በላይ ከፍተኛ ጭማሪ የታየበት መሆኑ አነጋግሯል።

የሥጋ በሬ በማድለብ የሚታወቁት የጅሩ አርሶ አደር ሰለሞን ድንቁ በ2013 የፋሲካ ገበያ አንድ በሬ 150 ሺሕ የሸጡ ቢሆንም፣ እኚህ አርሶ አደር በ2014 ለፋሲካ ገበያ ያቀረቡትን ድልብ በሬ ነጋዴዎች 220 ሺሕ ብር ቢሰጧቸውም አልሸጥም ብለዋል። አርሶ አደሩ በአንድ ዓመት ልዩነት ከአንድ በሬ 70 ሺሕ ልዩነት ያለው ዋጋ ተሰጥቷቸው አልሸጥም ማለታቸው ብዙዎችን ከማስገረሙ ባሻገር፣ ምን ያክል ሊሸጡ ነው የሚለው ጉዳይ ሌላ ጥያቄ ሆኗል።

በየዓመቱ የሥጋ በሬ በማቅረብ የሚታወቁት የጅሩ አርሶ አደሮች፣ ለገበያ ያቀረቡት በሬ ተመሳሳዩ በ2013 የፋሲካ ገበያ 160 ሺሕ ብር ተሸጦ የነበረ ሲሆን፣ በ2014 የፋሲካ በዓል ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ 200 ሺሕ ብር ተሸጧል። በአንድ ዓመት ልዩነት የአንድ በሬ ዋጋ የ40 ሺሕ ብር ልዩነት አሳይቷል። የጅሩ አርሶ አደሮች መካከለኛ የደለበ በሬ 130 ሽሕ ብር የተሸጠ ሲሆን፣ ዋጋው አዲስ አበባ ካለው ገበያ በላይ ሆኗል።

በአዲስ አበባ በ2013 የፋሲካ ገበያ የበሬ ዋጋ ዝቅተኛው 40 ሺሕ፣ መካከለኛ 60 ሺሕ እና ትልቁ ደግሞ እስከ 90 ሺሕ ነበር። በዘንድሮው ገበያ ደግሞ ምንም እንኳን እንደ በሬው አቅም ዋጋው የተለያየ ቢሆንም፣ አምና ከፍተኛ የነበረውን መሸጫ ዋጋ ወደ መካከለኛ መደብ ያወረደ ሆኗል። በአዲስ አበባ እስከ ማክሰኞ ባለው ገበያ አንድ በሬ እስከ 160 ሺሕ ብር የተሸጠ ሲሆን፣ በከፍተኛ ዋጋ ተገዝተው ከጅሩ ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ በሬዎች ለገበያ ሲቀርቡ ዋጋው በዚያው ልክ ማደጉ አይቀርም። በአንዳንድ የክልል ከተሞች አዲስ አበባ ካለው ገበያ በላይ ሆኖ ውሏል።

በግ ለፋሲካ በዓል በብዛት ለእርድ ከሚቀርቡ የቤት እንስሳት መካከል አንዱ ሲሆን፣ የዘንድሮው የበግ መሸጫ ዋጋ ከቦታ ቦታ የተለያየ ነው። ሆኖም እንደሌሎች ገበያዎች ጭማሪ የታየበት ገበያ ነው። በአዲስ አበባ የበግ ገበያ ከአንዳንድ ክልል ከተሞች ጋር ሲነጻጸር መጠነኛ ቅናሽ አለው። በክልል ከተሞች አንድ በግ 28 ሺሕ ብር የተሸጠ ሲሆን፣ አዲስ አበባ አዲስ ማለዳ ይህን ዘገባ እስካዘጋጀችበት ቀን ድረስ አንድ በግ 21 ሺሕ ብር ተሸጧል።

በ2013 የፋሲካ በዓል ገበያ ዝቅተኛው የበግ ዋጋ 2500 ብር ሲሆን፣ መካከለኛ 4500 እንዲሁም ከፍተኛ የሚበላው የሚባለው እስከ 11 ሺሕ 500 ብር መሸጡ የሚታወስ ነው። በአዲስ አበባ ያለውን የመሸጫ ዋጋ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ10 ሺሕ ብር ልዩነት ሲኖረው በክልል ከተማ ከተሸጠው ጋር ሲነጻጸር የ17 ሺሕ ብር ልዩነት አለው።

የፋሲካ በዓል ማድመቂያ ከሆኑት የበዓል ምግቦች መካከል ዶሮ አንዱ ሲሆን፣ አዲስ ማለዳ ቅኝት ባደረገችበት በአዲስ አበባ ሾላ ገበያ እስከ ማክሰኞ ባለው ገበያ ከ650 እስከ 800 ብር መሸጡን ተመልክታለች። ይሁን እንጂ በዚሁ በአዲስ አበባ በሌሎች አካባቢዎች እስከ አንድ ሺሕ ብር እንደሚጠራም ታዝባለች። በአንዳንድ የክልል ከተሞች አንድ ዶሮ 1100 የተሸጠበት ገበያ መኖሩንም አዲስ ማለዳ ሠምታለች።

በ2013 የፋሲካ በዓል ገበያ አዲስ ማለዳ በሾላ ገበያ ቅኝት ባደረገችበት ወቅት ትልቅ የሚባል ዶሮ በ550 ብር ተሸጦ የነበረ ሲሆን፣ በአብዛኛው አነስተኛ ዶሮ ከ250 እስከ 300 ብር መሸጡ የሚታወስ ነው። በዶሮ ገበያ የዘንድሮው የበዓል ገበያ ባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ከፍተኛ ዋጋ ጋር ሲነጻጸር ከ450 ብር በላይ ልዩነት አሳይቷል።

ቅቤ በተለይ በፋሲካ በዓል በበዓሉ አክባሪዎች ዘንድ ተፈላጊነት ያለው የምግብ ማጣፈጫ ሲሆን፣ በዘንድሮው የፋሲካ በዓል አዲስ ማለዳ ቅኝት ባደረገችበት ሾላ ገበያ አንድ ኪሎ ቅቤ ከ600 እስከ 800 ብር ሲሸጥ ነበር። የቅቤ ዋጋ እንደሚመጣበት አካባቢ የሚወሰን ሲሆን፣ ከፍተኛ ተፈላጊነት ያለው ቅቤ ከ700 እስከ 800 ብር እየተሸጠ ነው።

አዲስ ማለዳ በ2013 የፋሲካ በዓል ገበያ በተመሳሳይ በሾላ ገበያ ባደረገችው ቅኝት አንድ ኪሎ ለጋ ቅቤ እስከ 580 ብር፣ መካከለኛ ከ450-500 ብር መሸጡን ዘግባ ነበር። የቅቤ መሸጫ ዋጋ ከዓመት እስከ ዓመት በአንድ ኪሎ የ120 ብር ጭማሪ አሳይቷል።

እንቁላል ሌላኛው የፋሲካ በዓል ማድመቂያ ምግብ ሲሆን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጭማሪ እያሳዩ ከመጡ የእንስሳት ተዋጽዖዎች መካከል አንዱ እየሆነ መጥቷል። በዘንድሮው የፋሲካ በዓል ገበያ የሐበሻ እንቁላል ከ7 ብር እስከ 8 ብር እየተሸጠ ሲሆን፣ የፈረንጅ እንቁላል ደግሞ ከ6 ብር እስከ 7 ብር እየተሸጠ ነው። የእንቁላል መሸጫ ዋጋ ከሌሎች አንጻር ከዓመት እስከ ዓመት ያሳየው ጭማሪ መጠነኛ ሊባል የሚችል ቢሆንም፣ ያሳየው ጭማሪ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር እስከ ኹለት ብር የሚደርስ ጭማሪ አሳይቷል።

ሽንኩርት ወትሮውንም ከማኅበረሰቡ የእለት ከዕለት ኑሮ ጋር ከፍ ዝቅ ሲል የሚኖር ቢሆንም፣ በበዓል ወቅት ዋጋ ጭማሪ ከሚታይባቸው ፍጆታዎች አንዱ ሆኗል። ለበዓል ከሚያስፈልጉት ግብአቶች አንዱ እና ዋነኛው ሽንኩርት ሲሆን፣ በዘንድሮው የበዓል ገበያ በአዲስ አበባ አንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት እስከ 45 ብር ተሸጧል። የሽንኩርት መሸጫ ዋጋ ከቦታ ቦታ የተለያየ ቢሆንም ከባለፈው ተመሳሳይ ዓመት ጋር ሲነጻጸር ጭማሪ አሳይቷል።

በአዲስ አበባ በ2013 የፋሲካ በዓል የነበረው የቀይ ሽንኩርት ዋጋ ከ30 እስክ 35 ብር የነበረ ሲሆን፣ በዘንድሮው የፋሲካ በዓል ገበያ እስከ 45 ብር ተሸጧል። በአንድ ዓመት ውስጥ በአንድ ኪሎ የ10 ብር ልዩነት ያሳየ ሲሆን፣ የዋጋ ጭማሪው 40 ብር የገባው በበዓል ዋዜማ ነው።

ከጊዜ ወደ ጊዜ አንገብጋቢ እየሆነ የመጣው የምግብ ዘይት ዋጋ በተለይ በዘንድሮው ዓመት ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱ ይታወቃል። ምንም እንኳን የምግብ ዘይት ከፋሲካ በዓል አስቀድሞ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ተከትሎ ከበዓሉ ጋር በተገናኛ የተጋነነ ጭማሪ ባይታይበትም፣ አምስት ሊትር ፈሳሽ የምግብ ዘይት ከ900 ብር በላይ እየተሸጠ መሆኑን አዲስ ማለዳ ተመልክታለች። በአንዳንድ የክልል ከተሞች አምስት ሊትር ዘይት ከአንድ ሺሕ ብር በላይ እየተሸጠ ነው።

አዲስ ማለዳ በ2013 የፋሲካ በዓል ገበያ በተለያዩ ቦታዎች ቅኝት አድርጋ ባጠናቀረችው ዘገባ፣ አምስት ሊትር የምግብ ዘይት በተለያዩ አካባቢዎች ከ490 ብር እስከ 550 ብር መሸጡን ተመልክታ ነበር። በአንድ ዓመት ልዩነት የአምስት ሊትር የምግብ ዘይት ዋጋ ከ550 ብር ወደ 1000 ብር ከፍ በማለት የዋጋ ጭማሪው የ450 ብር ልዩነት አሳይቷል።

የበዓል ገበያ የዋጋ ጭማሪ ለማሳየቱ እንደ ምክንያት የሚጠቀሰው መቆሚያ ያልተገኘለት የዋጋ ግሽበት አሁንም ማሻቀቡን እንደቀጠለ ነው። የኢትዮጵያ ስታቲስቲክስ አገልግሎት በየወሩ የሚያወጣው የዋጋ ግሽበት መረጃ እንደሚያሳየው የመጋቢት ወር 2014 አጠቃላይ የዋጋ ግሽበት ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ34.7 ከመቶ ጭማሪ አሳይቷል።

የምግብ ዋጋ ግሽበት የመጋቢት ወር 2014 ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ43.4 በመቶ ጭማሪ ያሳየ ሲሆን፣ ከየካቲት ወር 2014 ጋር ሲነጻጸር በ1.5 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል። በያዝነውም ወር በአብዛኛው በእህሎች የዋጋ ጭማሪ የታየ ሲሆን፣ የአትክልት ዋጋም ላይ መጠነኛ ጭማሪ ተስተውሏል። የምግብ ዘይትና ቅቤ ዋጋ በፍጥነት የጨመረ ሲሆን፣ ቡናና ለስለሳ መጠጦች ተከታታይ የዋጋ ጭማሪ አሳይተዋል።

ሸማቹ ምን ይላል?
የዘንደሮው የፋሲካ በዓል ገበያ ከቦታ ቦታ የተለያየ ቢሆንም፣ በ2013 ዓመት ከነበረው የበዓል ገበያ ጋር ሲነጻጻር ቀላል የማይባል ዋጋ ንረት ታይቶበታል። ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ካለችበት ወቅታዊና ዓለም ዐቀፍ ሁኔታ ጋር በተያያዘ የዋጋ ንረት ከአምናው ጭማሪ ቢታይበትም የፋሲካ ገበያ ከወትሮው ለየት ያለ ሆኗል።

አዲስ ማለዳ የገበያ ሁኔታውን በማስመልከት ሸማቾችን ያነጋገረች ሲሆን፣ ከዚህ በፊትም በበዓል ወቅት የገበያ ሁኔታዎች ለውጥ የሚታይባቸው ቢሆንም ከወቅቱ የዋጋ ንረት ጋር ተዳምሮ የዘንድሮው የበዓል ገበያ የሸማችን አቅም የፈተነ ነበር ይላሉ። አዲስ ማለዳ ሾላ ገበያ ሸማች ሆነው ያነጋገረቻቸው የአዲስ አበባ ነዋሪ አቢዮት ሽንባቸው ከዚህ በፊት በየዓመቱ ለፋሲካ በዓል በግ አርደው ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሲያከብሩ እንደነበር ይገልጻሉ። ይሁን እንጂ በዘንድሮው የፋሲካ በዓል የኑሮ ውድነቱ በመባባሱና የመግዛት አቅማቸውን በመፈታተኑ ዶሮ ገዝተው በዓሉን ለማክበር መወሰናቸውን ይናገራሉ።

ሌላኛው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ሰለሞን ክፍሌ ከዚህ በፊት ለገና እና ፋሲካ በዓል በየዓመቱ ከጎረቤት ጋር ተሰባስበው ብር በማውጣት በሬ በመግዛት ቅርጫ የሚከፋፈሉ ሲሆን፣ በዘንድሮ ዓመት መግዛት አለመቻላቸውን ይገልጻሉ። ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያነሱት የሸማቹ ገቢ ባለበት ቆሞ የዋጋ ግሽበቱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱን ተከትሎ የመግዛት አቅማችን ስላልቻለ ነው ይላሉ። ሰለሞን እንደሚሉት ሸማቹ የማኅበረሰብ ክፍል የመግዛት አቅሙ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተዳከመ መምጣቱን ተከትሎ በበዓል ወቅት ከወትሮው የተለየ የበዓል ፍጆታ መግዛት ተስኖታል።

የዘንድሮው የፋሲካ በዓል ገበያ በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ላለው የማኅበረሰብ ክፍል የሚቀመስ አለመሆኑን የሚገልጹት አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሸማቾች፣ የዋጋ ንረቱ በዚህ ከቀጠለ የዕለት ከዕለት ፍጆታን ለመሸመትም አዳጋች እንደሚሆን ይናገራሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 181 ሚያዝያ 15 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here