በእንተ ትምህርት!

ሁሉንም እንዳወቀ የሚያስብ ተጨማሪ ለማወቅ ስለማይጥር የሚተላለፍለትንም ዕውቀት ስለማይቀበል እንደሞተ ይቆጠራል ይባላል። ትምህርት ማለቂያ የሌለው የሥልጣኔም ሆነ የፅድቅ መንገድ እንደሆነ ተደጋግሞ ቢነገርም፣ ትውልድን ለማብቃት የሚደረገው ተግባር ግን ከሚጠበቀው በጣም የወረደ እንደሆነ ይነገራል። ከቀደሙት ኢትዮጵያውያን ምሁራን መካከል ስለትምህርት አስፈላጊነት ያመኑበትንና ያወቁትን ለማካፈል ከጣሩት ሊቃውንት መካከል “የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ” መጸሐፍ ደራሲ እጓለ ገብረዮሐንስ ከቀዳሚዎቹ ይመደባሉ። ስለመጽሐፋቸውና አተያያቸው ለዘመናችን ይመጥናል ያሉትን በማንሳት በድሉ አበበ ተከታዩን አስፍረዋል።

አንዳንድ ዘመን፤ ዘመን ተሻገሪ ሰዎችን ይፈጥራል ይባላል። ሰዎቹም ዘመንን ከመመጠን አልፈው ዘመናትን በዕይታ አድማስ ይሻገራሉ። በተመሳሳይ መልኩም አንዳንድ ሰዎች ከተቋም ይገዝፋሉ ይባላል። ከጊዜም ይገዝፋሉ፤ ዋርካ ሆነው ከዘመናቸው ተሻግረው፤ ከትውልዳቸው አበርክቶ አልፈው ለመጪው ትውልድ ፋና ወጊ ይሆናሉ። የዘመን መንፈስን ቅኝት (zeitgeist) ቃኝተው ያስቃኛሉ፤ በእውነትና በእውቀት ብርሃን ፈክተው ያፈካሉ። ለምሳሌ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ፤ ደራሲ ከበደ ሚካኤል፤ ፊታውራሪ ተ/ሐዋሪያት ተ/ማሪያም፤ በጅሮንድ ይልማ ዴሬሳ፤ ተ/ጻድቅ መኩሪያ፤ እጓለ ገ/ዮሐንስንና ሌሎችን የዛን ዘመን ዘመነኞች መጥቀስ እንችላለን።

መቼም ደጋግሜ ባነበብኩት ቁጥር የሚገርመኝ የዘመኑን ፍልስፍና ‹ከፈረሱ አፍ› ጭምር የተማሩት፤ ከምንጩ ሄደው የቀዱት፤ አውሮፓን የዋኙት፤ ሥነ ምግባርን የኖሩትና የሰበኩት ትሁቱ ሊቅ እጓለ ገ/ዮሐንስ በ‹የከፍተኛ፡ ትምህርት፡ ዘይቤ› መጽሐፋቸው ውስጥ ያሳዩት ትህትና ያስደምማል። ለብዙ ደራሲያንም አርዓያ የሚሆን ነው።

ማስረጃ ልጥቀስ (ሀ) አንባቢን በአንቱታ መጥራት (ለ) መጽሐፉ ውሰጥ የተጠቀሱትን ሐሳቦች ‹የኔ የምላቸው ጥቂቶች ናቸው› ማለት (ሐ) ‹ቤተ መንግሥቱን ቤተ ትምህርት› ያደረጉትን አጼ ኃይለሥላሴን፤ መምህራኖቻቸውንና ምንጮቻቸውን ማመስገን (መ) ‹በመወዳደርና በመፎካከር› እንዳልጻፉ ማብራራት (ሠ) አስተያየት ያለው ‹በጋዜጣ ወይም በጽሑፍ› መልስ ይስጥ ብለው መጋበዝ (ረ) ስህተት ሊኖርብኝ ይችላል ብለው ማመን። ስህተቱም እንደውም ለመጀመሪያ ጊዜ በ‹አማርኛ› በመቅረባቸው ኹለትም ‹የሐሳብ ገለጻ› ስህተት (ሰ) በ‹አቅም ማነስ ምክንያት ብዙም አላልሁ ይሆናል›፤ ‹በደንብ አጥንተን ስላልተገኘን› ሲሉ ያክላሉ (ሸ) በመጨረሻም ‹ነቀፌታ እንሰማለን› ይላሉ። ነቀፌታውንም ‹ዋጋ የማንሰጠው አለ›፤ ‹አመለካከት እንቀበላለን›ና ‹መልስ እንሰጣለን› ብለው በሦስት ይከፍሉታል።

እጓለ ገ/ዮሐንስ ስለ ትምህርት የጻፉ የማይዘነጉ ጉምቱ ቀዳሚ ኢትዮጵያዊ ደራሲ ናቸው። በተለይ ስለ ትምህርትና የትምህርት ፍልስፍና ጥልቅ የንባብ ልምዳቸውንና ዕይታቸውን ባጋሩባት መጀመሪያ በቃል፤ በራዲዮ ጣቢያ በኋላ በመጽሐፍ ቀንብበው ያቀረቡልን ‹የከፍተኛ፡ ትምህርት፡ ዘይቤ› ከእጓለ ገ/ዮሐንስ በጥልቀትም በርቀትም በይዘትም በጉዳዩ በአማርኛ ከተጻፉቱ ቀዳሚና ዐይን ገላጭ መሆኑ አያጠያይቅም። ይሄ ወቅት ትምህርትና የትምህርት ሚኒስቴር ተወዛግበው ያወዛገቡበት ወቅት ስለሆነ አንዳንድ ነገሮችን ከመጽሐፉ እያጣቀስን ስለ ትምህርት አናውጋ፡-

ለመሆኑ ትምህርት ምንድን ነው?
እንደ እጓለ ገለጻ ትምህርት ማለት ‹የሰውነት ደረጃ› ነው። ይህ ማለት የ‹ተማረ› የምንለው ሰው በሂደት ከሰውነት ትልቁ ደረጃ ይደርሳል ማለት ነው። ሰው ሦሰት ምርጫዎች አሉት። ሰው እንደ እጽዋትና እንስሳት መሆን ይችላል፤ በምርጫው። ክብሩና ጸጋው ቁልቁል ሲወርድ ማለት ነው። ሰው ‹ሰው› መሆንም ይችላል። ልክ ሰው የመሆኑ ጥልቅ እሴት ሲገባው ማለት ነው። ይህ እውነተኛ ሰዋዊ ተፈጥሮው ነው። ሰው ከብሩን ሲጨምር፤ መንፈሳዊ ኃይሉን ሲያበረታ ደግሞ ‹ምድራዊ መልዓክ› ሊሆን ይችላል። የመጀመሪያው እንስሳዊ፤ መካከሉ ሰው መሆን፣ ሦስተኛው ከፍታ ደግሞ ‹መልዓካዊ› ነው ማለት ነው።

ራሱን ‹ሰዋዊ እንስሳ› ማድረግ የሚችለውን ያህል ለምድራዊ መልዓክነትም ራሱን ሊያጭ ይችላል። ስለዚህ የተማረ ሰው ማለት ሰው የሚባል ሰው፤ የሰውነትን ልክ የሚያሟላ ፍጥረት ይሆናል ማለት ነው። መማርም ይሄንን ጸጋ ያጎናጽፋል እንደ ማለት።

ስለዚህ እጓለ እንደሚሉት ‹ሰው የሚባል ሰው እንኳ ለመሆን› መማር ያስፈልጋል። መማር የሰውነትን ደረጃ፤ ሰው መሆንን ይሰጣልና። የሰው ልጅ አካል፤ ልቦናም መንፈስም ነፍስም ነው። ሙሉ በሙሉ ሥጋ ብቻ አይደለም። ሙሉ በሙሉ ልቦናዊ ወይም መንፈሳዊ ብቻም አይደለም። ሙሉ በሙሉ ነፍስ ብቻም አይደለም። የሦሰቱ ተዋህዶ ነው እንጂ። ስለዚህ በገዛ ፍቃዱ ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ በሥጋ ባህርይ ከተዘፈቀ ‹እጽዋት›ን ወይም ‹እንስሳ›ን ይሆናል። ይህም ከ‹ተማረ› ሰውነት ያጎድለዋል ማለት ነው።

በአንጻሩ ደግሞ ሙሉ በሙሉ ለነፍሱ ካደላ ‹ነፍሳዊ› ከ‹ተማረ› ሰውነት በላይ ይበራል ማለት ነው። እነሆ መማር ማለት መኻሉን፤ ጥቅሙ የሚበልጠውን፤ አሳታፊውን፤ ‹ሁሉን መርምሮ መልካሙን መያዝ› ማለት ነው። የበለጠው በበለጠ ይመከራል። ይሄንን ሲያብራሩ እጓለ ‹ትክክለኛ ትምህርት ፈጣሪን መምሰል ነው› ብለዋል። በአንጻሩም የሰው ልጅ ትምህርት ካላገኘ ፕላቶ ያለውን ተውሰው ‹ሰው ትምህርት ካላገኘ በምድር ላይ ካሉ አራዊት ሁሉ የባሰ ነው› ብለዋል። በመቀጠልም፣ ‹ትምህርት ከሰው ልጅ ዋነኞቹ ክፍሎች አንዱ ነው፤…ከታሪካዊ ዕድሉ[ም] ለመድረስ መሣሪያው አንድም ትምህርት ኹለትም ትምህርት ሦስትም ትምህርት ነው› ብለዋል።

ትምህርትን የበለጠ ሲያብራሩ ደግሞ፡- ‹ትምህርት ሦስት ጥያቄዎችን የያዘ፣ ለሦስቱም ጥያቄዎችም መልስ የሚሰጥ ነው› ብለዉታል። እነዚህም ምን ለምንና እንዴት መሆናቸውን አብራርተዋል። ሁሌም እነዚህን ጥያቄዎች እንድንጠይቅም ይጋብዛሉ። ትምህርት በይነ ዲሲፕሊናዊ መሆኑንም ያብራራሉ። ትምህርት በመከራ እንደሚገኝም አስፍረዋል። ስለዚህ ትምህርት የ‹ሕሊና ሥነ ሥርዓት›፤ ‹ያማረና የሰመረ ሕሊና [Cosmos]› ባለቤትነት፤ ‹የተመሳቀለና የተዘባረቀ ያልሆነ ሕሊና› ባለቤት መሆን ማለት መሆኑን ያሰምሩበታል።

ትምህርት የሁሉም ነገር መፍትሄ ነው
እጓለ ገ/ዮሐንስ ‹ስለ ትምህርት ያለን አመለካከት ትክክለኛ ከሆነ ማናቸውም የሕይወት ችግር ሊፈታ ይችላል› ብለዋል። ትምህርት በሂደት የምንደርስበት ጉዳይ መሆኑን ያስተማሩንን ያህል ትምህርት ለዕውቀት ዋነኛው ግብዓት መሆኑን ጽፈዋል። የሰው ልጅ ትምህርት ኹለት ‹ብዕሲት› እንዳለው ደግሞ የኦክፎርድ ምሁሩን ጳጳስ ዋቢ አድርገው ትምህርት በኹለት ነገር ይጸናል ይሉናል። እነዚህንም አስራኤል ዘሥጋ ከግብጽ ወደ እስራኤል ሲጓዙ ቀን በዓምደ ደመና ሌሊት በዓምደ ብርሃን የመመራታቸው ምሳሌ ነው ይላሉ። ስለዚህ ትምህርት ያለውም ‹የተማረ› ሰው በኹለቱ የበር መግቢያ ደጃፎች ባሉት ሰው ይመስሏቸዋል። እነሱም ሰናይት [Virtues] እና ዕውቀት [Knowledge] ናቸው።

ትምህርት መጥፎ ያለመሆኑን ያህል፤ ጥሩ፤ በጣም ጥሩም፤ ግሩምም ሳይሆን እጅግ በጣም ጥሩ [Par excellence] ወይም ሰናይት [virtues] መሆኑን ይነግሩናል። በእርግጥ ጥሩ [Par excellence] ከሰናይት [virtues] ያንሳል። ስለዚህ መማር ማለት በሙያችን ጥልቅ የሆነ ዕውቀት፤ በአንዳንድ ጉዳዮች ደግሞ ጠቅላላ ዕውቀት ሲኖረን ነው ማለት ነው።

በተጨማሪም፣ የተማረ ማለት እጅግ ጥልቅ ሥነ ምግባር፤ ትህትና እሴት እንዲሁም ሰናይት በአንድ ላይ ሲኖሩት ማለት ነው። ለምሳሌ፣ እኔ ዐስር የሚያህሉ ኢትዮጵያ ፕሮፌሰሮች በከፍተኛ ሁኔታ አስተምረውኛል። አሠልጥነውኛልም። አሁንም የሚያማክሩኝ አሉ። አብሬ ሠርቻለሁ። አሁን አብረን እየሠራን ነው። ከአዲስ አበባ፤ ከጎንደር፤ ከጅማ፤ ከባህር ዳር፤ ከሐረማያና ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲዎች ናቸው። ከዕውቀታቸው ጥልቀት ባሻገር እጅግ የሚገርመው ሁላቸውም የበዛ ትሁት መሆናቸው ነው።

ለአንድ ወዳጄ እንዲያውም ‹ኢትዮጵያ ፕሮፌሰርሺፕ ተጠንቅቃ ነው የምትሰጠው› ብዬዋለሁ። ያው በመጽሐፋቸው የሽፋን ገጽ እጓለ ‹..ሠናያት ሠላማዊት እንተ ናፈቅር በጽድቅ› እንዳሉት ማለት ነው። በውስጥም ‹… የተማረ ሰው ግን ከለዘበው ከለሰለሰው መንፈሱ መልካሞች ጽጌያትና ፍሬያት ያስገኛል፤… ሕሊናንም ከድንቁርና ባርነት ነጻ ያወጣል› ሲሉ እንደገለጹት ማለት ነው። (ገጽ 30)
የተማረ ሰው የራሱንም፣ የማኅበረሰቡንም፣ የአገሩንም ችግር ይፈታል። በማኅበራዊ ኑሮ ረገድ ‹የእያንዳንዱ ሰው መብት ተጠብቆ ሰው በንጹህ ምኞቱ መሠረት በሰላም ለመኖር ይችል ዘንድ ትክክለኛ ፍርድን በሕግ ይወስናል።› (ገጽ 30) ይህም ነጮቹ ፍትህ [Justice] የሚሉት መሆኑ ነው። የተማረ ሰው ፍርድ አያዛባም። ለድሃና ለተበደለ ይጮሃል። ለማኅበራዊ ፍትህ ይተጋል ማለት ነው። ይህንን ስናነብ እኛ የቱ ጋር እንዳለን ውሉ ይጠፋናል።

የተማረ ሰው የራሱንም፤ የማኅበረሰቡንም፣ የአገሩንም ችግር ይፈታል። በምጣኔ ሀብት (ኢኮኖሚክስ) ረገድ ረሀብና ሌሎችንም አካላዊ ችግሮች አስወግዶ እንደ ልቡ ተዝናንቶ ለመኖር ይችል ዘንድ ጠቅላላውን ሥራ ለየራሱ ተካፍሎ የአምስት የዐስር ዓመት ፕላን አውጥቶ ይሠራል።› ይህም ቺቸሮ እንዳለው ‹ትምህርት አዕምሮን የማለዘብ፤ የማለስለስ የመንፈስ እርሻ [Cultura Animi] ብሎ የሰየመው ማለት ነው። በጥበብ ረገድ ‹ጣዕመ ዝማሬን፤ ሥነ ጽሑፍ፤ ሥነ ሥዕልን፤ ሥነ ሕንጻንና ሌሎቹንም ረቂቃን ፍጥረት ያስገኛል።

ትምህርት የሰው ልጅ ከባርነት ነጻ የወጣበት መሣሪያ ነው። የሚገርመው ሥልጣኔ የሚለው ቃል civilization ና cultura animi ከተሰኙት የኢንግሊዘኛ ቃላት በበለጠ የሚገልጸውና ምናልባትም ለአውሮፓውያን ማዋስ የምንችለው ቃል ነው ሲሉ ይቆጫሉ። ትምህርት የሥልጣኔ ምንጭ ነው። ሥልጣኔ ደግሞ በኹለት ይከፈላል። እነሱም አካላዊና መንፈሳዊ ሥልጣኔዎች ናቸው። ትልቁም ሥልጣኔ የነፍስ ሥልጣኔ መሆኑን አስምረውበታል።

- ይከተሉን -Social Media

ትምህርት በአጠቃላይ ሦስት ትልቅ ፋይዳዎች አሉት ማለት ነው። የተማረ ሰውም በእነዚህ ሦስት መመዘኛዎች ይለካል ማለት ነው። እነሱም ዕውቀትን ማስፋት [Expansion of Knowledge]፤ ማኅበረሰብን ማገልገልና ችግሩን መፍታት [Rendering Community Service and solving community Problems] እና ማኅበራዊ ፍትህን (Social justice) ማንገሥ ናቸው። ታዲያ እኛ ተማርን የምንል ሰዎች በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ በሦስቱ ሚዛን ብንመዘን የት እንገኝ ይሆን? ሠላም!
በድሉ አበበ በኢሜይል አድራሻቸው bediluab@gmail.com ላይ ይገኛሉ።


ቅጽ 4 ቁጥር 181 ሚያዝያ 15 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች