“ጊዜው ማስተዋልን፣ መረዳዳትን ይጠይቃል”

0
1074

ራሔል አባይነህ ይባላሉ። የሦስት ልጆች እናት ናቸው። ኹለተኛ ልጃቸው ኦቲዝም ያለው መሆኑን ተከትሎ የነህምያ ኦቲዝም ማዕከልን ከከፈቱ 11 ዓመታት እየተጠጉ ነው። ኦቲዝም ያለው/ያላት ልጅ የወለዱ ቤተሰቦች በሁኔታዎች የሚጨነቁና የሚጎዱ ቢሆንም፣ እርሳቸው ነገሮችን ቀለል አድርገው ማየትን የታደሉ በመሆኑ እንዳልተጎዱ ይናገራሉ።

መሳቅ መጫወት ይወዳሉ። ‹ደስተኛ፣ ምርጥ ምርጥ ልጆች ያሏት እናት ነኝ› የሚሉት ራሔል፣ አምላካቸውን ጠርተው አመስግነው አይጠግቡም። አገራቸውን የሚወድዱ ለሰው የሚያስብና የሚራራ ልብ እንዳላቸው ይናገራሉ። ለነህምያ የኦቲዝም ማዕከል እዚህ ደረጃ መድረስም የማዕከሉን ሠራተኞችና አብረዋቸውን ያሉ ሁሉ አመስግነዋል። የፋሲካ በዓልን ምክንያት በማድረግ ከአዲስ ማለዳዋ ሊድያ ተስፋዬ ጋር ተከታዩን ቆይታ አድርገዋል።

በቅድሚያ እንኳን አደረሰዎ/አደረሳችሁ። ለራሔል ከሁሉም በዓላት በተለየ ተወዳጅ የሆነ በዓል የትኛው ነው?
እንኳን አብሮ አደረሰን!

በጣም የምወደው የገና በዓልን ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር አንድያ ልጁን የሰጠን፣ የመጀመሪያው የቃልኪዳን ትስስር የተጀመረው ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ምድር በመምጣቱ ነው። ዓመተ ምህረት የሆነልን፣ ምህረት የተደረገልን። ስለዚህ ለገና በዓል ትልቅ ቦታ አለኝ።

በዓላትን በምን መልክ ነው የሚያሳልፉት?
በዓልን በመብላትና በመጠጣት ብቻ ማለፍ የለበትም ብዬ አምናለሁ። የተደረገልንን ነገር ማወቅ መቻል አለብን። ሁልጊዜ ለስካርና ለብዙ ነገር የሚዳረጉ ሰዎችን ዐያለሁ። ለልጆቼ ምን ላብላ ብሎ ራሱን ያጠፋ ሰው በልጅነቴ አውቃለሁ። እና ብዙ ከመብላትና ከመጠጣት ጋር ብቻ የተያያዘ እንዳይሆን ሁልጊዜ እፈራለሁ። እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ሰጥቶን፣ ድጋሚ እድል የተሰጠንን፤ እሱን በማሰብ ነው ማክበር የምፈልገው።

እና ሰዎች ከዛ መውጣት አለባቸው። ግርግሩ በጣም ደስ ይላል፤ ሁሉ ነገር ጥሩ ነው። ሆኖም ያንን ያላሟሉ ቤቶች ጋር የሚፈጥረውን ተጽእኖ ዞር ብሎ ማሰብ መቻል አለብን። አብዛኛው ሰው ደግሞ አይተሽ እንደሆነ ተበድሮም ቢሆን ያንን በዓል በጣም አላስፈላጊ ወጩ የሚያወጣበት ነው። እና መለስ ብለን በማስተዋል ያንን ቀን ማክበር ነው። እኔ ቤቴ በአቅሜ ነው የሚከበረው። ስለዚህ በጣም በጥንቃቄ ነው የማከብረው። እንደሌላ ሰው የተጋነነ ነገር አላደርግም። ባለን፣ በኑሯችን ልክ በመጠናችን ከልጆቻችን ጋር መልካም ጊዜ ማሳለፍ ነው ያለብን ብዬ አስባለሁ።

በእርግጥ አሁን ኑሮውም ውድ እየሆነ መምጣቱ ወደዛ ሳያስጋን አይቀርም፤

አዎን! ድሮ የነበሩት ነገሮች ቆም ብለን ስናይ ዛሬ ላይ የሉም። አሁንም ማስተዋል ይጠይቃል። ዘንድሮ ደግሞ በጣም እየባሰ ነው። ዛሬ ሽንኩርት 44 ብር ገባ ሲባል ሰማሁ፤ አንዱ ኪሎ። እና በጣም ከባድ ነው። ጊዜው ማስተዋልን፣ መረዳዳትን ይጠይቃል። እኔ ቤት ቅርጫ የሚኖር ከሆነ፣ ሌላውንም ማሰብና ማካፈል ያስፈልጋል ብዬ አስባለሁ።

በዓልን ጠብቀው የሚደረጉ ድጋፎች አሉ። ያንን የሚደግፉ ሰዎች እንዳሉ ሁሉ አንዳንዶች ደግሞ በዓልን ጠብቆ ድጋፍ ማድረግ አይገባም ሲሉ ይቃወማሉ። በየትኛው ይስማማሉ?
ቢሆን ጥሩ ነበር፣ በዓልን ብቻ ባንጠብቅ። ግን አብዛኞቻችን ምን ያህል የተሰጠን ነን (ኮሚትድ) ያንን ለማድረግ። እና ይህንንም አናሳጣቸው እላለሁ። ምን ያህል ምክንያት ፈላጊ እንደሆንን አውቃለሁ። ምክንያት እንፈልጋለን፣ ለመርዳትም ለማገዝም። ይህ ክርስትያኑ ላይ ብቻ ሳይሆን ሙስሊሙ ኅብረተሰብም ላይ ጾም ሲሆን ድጋፍ ይጨምራል። እና ተዛማጅ ነገር የምንፈልጋቸው አሉ። ባይሆን ጥሩ ነበር። ከሆነም ግን ምክንያትም ተፈጥሮም ቢሆን ሌሎችን መርዳትና ማገዝ አለብን።

ሁሌም ግን ካለን ላይ ማካፈል የሚባለውን ብናውቅ፤ አንደኛ በማካፈል ማንም ሰው ከስሮ አያውቅም። ምክንያቱም ብድራትን የሚመልስ እግዚአብሔር ነው፤ ለሁላችንም። እግዚአብሔር ዘንድ ደግሞ የሚታጣ ነገር የለም። በማካፈል ውስጥ ያለውን በረከት፣ ጤና እና ሰላም ሁሉም ሰው ቢያውቀው ብዬ አስባለሁ። ሰጥቶ የሚከስር ሰው የለም። ሁልጊዜም ካለን ላይ ማካፈል አለብን። በበዓል በቻ ባይሆን በጣም ጥሩ ነበር። ግን ያለን አስተዳደጋችን ይሁን ከየት እንደመጣ አላውቅም፤ በዓላትንና ጾምን እየተንተራስን ነው ሰውን የምንረዳው።

ወደ ማዕከሉ እንምጣ። ለነህምያ የኦቲዝም ማዕከል ሥያሜ እንዴት መረጡ?
ነህምያ ያልኩበት ምክንያት፣ የእኔ ልጅ (ኹለተኛው ልጄ) ኦቲዝም አለው። በሰዓቱ አንድ የኦቲዝም ማዕከል ነበር፣ እሱም ጆይ ሴንተር ነው። እዛ ስሄድ ቦታ የለም ተባለ፣ ብዙ ወላጅ ያለቅሳል። እና ወይዘሮ ዘሚም በልጇ የተነሳ ነበር የከፈተችው። የነእዚህ ልጆች ጉዳይ ሕመሙ የሚሰማን ለእኛ ለወላጆች ብቻ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ነህምያ የእስራኤል ቅጥር በፈረሰ ጊዜ መብላትም መጠጣትም አልቻለም ይላል። ትልቅ ሸክም ነበረው። ስለዚህ እኔም ለእነዚህ ልጆች ልክ እንደ እስራኤል ቅጥር ቅጥራቸውን፣ ክፉ ነገር እንዳያገኛቸው፤ ዛሬ እኛ በሕይወት አለን፣ ነገ ምን ይሆናሉ የሚለውን ዛሬ በቁሜ ነው ቅጥሩን መሥራት ያለብኝ ብዬ በማሰብ ነው ነህምያ ያልኩት።

ልጅዎ ኦቲዝም ያለው መሆኑን ሲያውቁ የተሰማዎ ስሜት ምን ነበር? (አንድ ጊዜ ይህን ተመሳሳይ ጥያቄ ለዘሚ የኑስ (ነፍስ ኄር) አቅርቤላቸው፣ ከማኅበረሰቡ አስተያየት አንጻር ለአፍታ ፍርሀት ሽው ብሏቸው እንደነበር ነግረውኛል።) መፍራት ወይም መጨነቅ ዓይነት ስሜት ነበረው ወይስ አስቀድመው ስለ ኦቲዝም ያውቁ ነበር?
እኔ እንደዛ ዓይነት ስሜት አልተሰማኝም። ለምን እንዲህ ዓይነት ልጅ ተሰጠኝ ብዬ ግን አስቤያለሁ። ምን አጥፍቼ ነው ከእግዚአብሔር ዘንድ፣ የቱ ጋር የሆነ ነገር ተገኝቶብኝ ነው ብዬ ነበር ራሴን መለስ ብዬ ያየሁት። ግን እየቆየሁ ስሄድ ኦቲዝም ‹ጀስት ዲስኦርደር› ነው። አንድ ሰው ከቁመቱ መጨመር እንደማይችል፣ ምንም ልታስተካክይ የማትችያቸው ነገሮች አሉ። ስለዚህ የልጄም አፈጣጠር ምንም ልናስተካክለው አንችልም፣ እንደዚሁ ሆኖ ነው የመጣው።

መጀመሪያ ላይ ከባድ ነው። ዘላቂ የሆነ ዲስኦርደር ልጅሽ ላይ ማየት ቀላል ነገር አይደለም። ግን እየቆየ ሲሄድ ትንሽ ትዋሃጂዋለሽ። ምንአልባት በእነ ዘሚ ጊዜ የነበረው ደግሞ ምንም ግንዛቤ አልነበረም፣ ከባድ ሰዓት ነበር። እና ኦቲዝም ሲባል አውቃለሁ፣ ቃሉን። ቲቪ ላይ ዐይቼ ነበር። ግን ለምን እግዚአብሔር እንዲህ ዓይነት ልጅ ሰጠኝ ነበር የእኔ ጥያቄ።

ዛሬ ላይ ግን ለምን የምለውን ትቻለሁ፣ ምክንያቱም ብዙዎችን ለመድረስ ሌሎችን ለማገዝ ነው። አንዳንዴ ካልተነካሽ የማይገባሽ ብዙ ነገር አለ። እና ነካ ተደርጌ ነው የገባኝ። ኦቲዝም ውስጥ ምን ዓይነት ሕመምና ችግር እንዳለው የገባኝ ስለተነካሁ ነው። ለዛ ነው ብዬ አስባለሁ።

አንዳንድ ቤተሰብ ውስጥ ለየት ያለ ክብካቤ የሚፈልጉ ልጆች ሲኖሩ የተቀሩት እህት ወንድሞች ትኩረት ላይሰጣቸው ይችላል። ሆነ ተብሎም ባይሆን በሁኔታዎች አስገዳጅነት። እና ሌሎቹ ኹለት ልጆችዎ እንዴት ናቸው?
ትክክል ነው። አንዳንድ ሰው ኦቲዝም ላላቸው ልጆች ሲያዳላ አያለሁ። አንዳንዶቸ ጋር ደግሞ ለነዛኛዎቹ። ያልተመጣጠነ ነገር አለ። ግን ተጠንቅቀን ኹለቱንም አስተካክለን መሄድ አለብን ብዬ አምናለሁ።

እኔ መጀመሪያ ላይ በጣም ወደሱ [ኦቲዝም ወዳለው ልጄ] ሆኜ ነበር። ሁሉ ነገሬ የሚታየኝ እርሱን ማብላትና የመሳሰለው ነው። አንድ ቀን ግን የመጀመሪያ ልጄ ትንሽ እያለ (አሁን 18 ዓመት ሆኖታል)፣ እኛን’ኮ አትወጂንም አለኝ። እና በጣም ነበር የደነገጥኩት። ከዛ አስተዋልኩኝ። አንድ ነገር ሲያደርግ መትቼው ነው መሰለኝ፣ ለዛ ነው እኛንማ አትወጂንም እሱን ብቻ ነው የምትወጂው ያለኝ።

ከዛ በኋላ ነው ማሰብና መጠንቀቅ የጀመርኩት። አሁን ላይ እነሱም ያግዙታል። ምክንያቱም በእኛ ፍቅር፣ ጊዜና እርዳታ የሚፈልግ ልጅ ነው። ይህን እየደጋገምሽ ስትነግሪያቸው ይገባቸዋል። ደግሞም አሁን እያደጉ ስለመጡ፤ እኔ ባልልም አሁን እርዳታ የሚያስፈልገው ወንድም እንዳላቸው ያውቁታል። ስለዚህ የተወሰነ ሰዓት ላይ እንደተባለው ትንሽ ከባድ ነበር። ከዛ በኋላ ግን ተመልሼ አሁን ሁሉንም እያመጣጠንኩኝ እየሄድን ነው።

ነህምያ ሲመሠረት የነበረዎ ራዕይና ምስልን አሁን ከደረሱት ጋር ሲያነጻጽሩት ምን ይመስላል?
ጥሩ ነው፤ ምንም አይልም። ካለው የአገራችን ነባራዊ ሁኔታ ጋር ስታስተያይው እግዚአብሔር ይመስገን አለመዘጋቱም ትያለሽ። ምክንያቱም አገር በቀል መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው።
ስንነሳ የእኔ እቅድ በየሦስት ዓመቱ ቅርንጫፍ እንከፍታለን የሚል ነበር። አሁን በተጠባባቂ እኛ ጋር ከ800 በላይ ተማሪዎች አሉ። ስለዚህ እቅዳችን በጣም ብዙ ነበር። ሚድያ ላይ ወጥቼ ልጄ ኦቲዝም አለው ብዬ ከተናገርኩ በኋላ ብዙ ሰው ከቤት ይወጣ ነበር። ስለዚህ ያሰብኩት መንግሥትም ይደግፈናል፣ ግለሰብና የሆነ ድጋፍ ሰጪ እናገኛለን ብለን ነበር።

ግን ኢቲዝም ያልተነካ ጉዳይ ነው ማለት ይቻላል። መንግሥትም ትኩረት አያደርግም። ተቋማት ጋር ስንሄድ አብዛኛው የሚገድል በሽታ ነው ወይ ይሉናል። መሞት አለብሽ ጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠው! ግን ይህ ደግሞ እናትን በቁም ነው የሚገድለው፣ ነገ ተስፋሽን ነው የሚያሳጣሽ። ነገን ትፈሪያለሽ፣ የልጅሽን እድገት ትፈሪያለሽ።

ለምሳሌ ጥርሷ ተነቃነቀ ብላ ያለቀሰች ወላጅ አለች፣ ጉዴ ፈላ ልጄ እያደገች ነው ብላ። እና ነገን እንድትፈሪ፣ እንዳታምኚው ያደርግሻል። በሄድንበት ቦታ ‹ይገድላል ወይ?› እየተባልን ነው። እና መንግሥትም ትኩረት ያልተሰጠው አካባቢ ነው።

እኛ ሰብረን ስንወጣ እነርሱ ይረዱናል፤ ነገሮች ይስተካከላሉ ብዬ ተስፋ አድርጌ ነበር። ያ ግን እንዳሰብኩት አልሄድም። በዛ ላይ ኮቪድ መጣ። ድርጀቶችና ግለሰቦች ድጋፍ የሚያደርጉት ሲያተርፉ ነው፤ ካላተረፉ በምን ድጋፍ ይሰጡናል? እና በዛ የተነሳ ያለንበትን ሁኔታና የደረስንበትን ሳስበው እግዚአብሔር ይመስገን ጥሩ ላይ ነን እንላለን። ቅርንጫፍ መክፈቱም ቀርቶ እንዲሁም ስላለን እግዚአብሔርን አመሠግናለሁ። ምክንያቱም አብዛኛው ድርጅት ዘግቷል፤ ይረዱንና ያግዙን የነበሩም ይቅርታ እያሉ ወጥተዋል። ስለዚህ ደኅና ነን፣ ምንም አንልም። እግዚአብሔርን ስታመሰግኚ ያው ይጨመራል።

ተጠባባቂ የተባሉ እየጠበቁ ያሉ ተማሪዎች እንዳሉ ጠቅሰዋል። ከአዲስ አበባ ነው በብዛት ወይስ ከክፍለ አገራትም አለ?
አዎን! በየአገሩ አለ። በጣም ብዙ አሉ። አዲስ አበባ ይበዛል ማለት አልችልም። ምክንያቱም በየሚድያው በዩትዩቡ ላይ ሁሉ ነገር ላይ ኦቲዝም በጣም ይነሳል። ምንአልባት የክፍለ አገሩ ግንዛቤው በቂ አይደለም። እዛ ሄደን ፕሮግራም ቢዘጋጅ ምንአልባት ወላጆች ከቤታቸው ልጆቻቸውን ማውጣት ይችላሉ። ሶሻል ሚድያ የማይጠቀም ብዙ ሰው አለ። እና የተደራሽነት ጉዳይ ይመስለኛል።

እኛ ጋር ከ800 በላይ ተመዝግበው ያሉት፣ የአዲስ አበባ ሰዎች ናቸው። የክፍለ አገሮቹን እስከምንችለው ድረስ በስልክ እናግዛለን። ለምሳሌ የመጀመሪያውን ደረጃ፣ ‹ኦቲዝም ያለው ልጅ ተረጋግቶ አይቀመጥም። እርሱ እንዲቀመጥ አድርጊው። ከዛ ፖፖ ማስለመድ። አንድ ልጅ ካልተቀመጠ ፖፖ አይለምድም። መቀመጥን ማስተማር አለብሽ። የዐይን ግንኙነት የላቸውም› ወዘተ እያልን በስልክ የምንረዳቸውና የምናስተምራቸው ብዙ ወላጆች አሉ። እና የግንዛቤው እንጂ በየአገሩ ያለ ጉዳይ ነው።

በጉዳዩ ላይ በቂ ጥናቶች እንዳልተካሄዱ ነው የምንሰማው። ከአካዳሚ አንጻር ጤና ላይ የሚሠሩ ተቋማትም በኩል የተሠራ ለእናንተ ተደራሽ የሆነ ጥናት አለ ይሆን?
ምንም መረጃ የለንም። ጩኸታችንም ይኸው ነው፣ እስከ አሁን ድረስ ትኩረት አልተሰጠውም። እኔ አሁን ልጄ 15 ወደ 16 እየሄደ ነው። ያኔ ከመቶ ሀምሳ ልጅ አንድ ልጅ ላይ ነበር ኦቲዝም የነበረው። አሁን ላይ ከ30 አንድ ልጅ ላይ ደርሷል። ስንት ልጅ ላይ ሲደርስ እንደሆነ ርብርብ የምናደርገው አላውቅም። እና በጣም ቁጥሩ እየጨመረ ነው። መረጃ እንኳ እጃችን ላይ የለም፣ ከውጪ ባለው መረጃ ነው ይህንንም ቁጥር ማውራት እንኳ የቻልነው።

በቅርቡ የኦቲዝም ወርን ምክንያት በማድረግ በናዝሬት ትምህርት ቤት የግንዛቤ መስጫ ዝግጅት እንደነበራችሁ ዐይቻለሁ። ብዙ ጊዜ ግንዛቤ መስጠት ሲነሳ ለሴቶች ነው ትኩረት የሚሰጠው፣ ለወንዶች ያለው ሥራ እምብዛም ነው። ወንዶቹስ በቂ ግንዛቤ ሊኖራቸው አይገባም?
በአጋጣሚ እድሉን ስላገኘን ናዝሬት ስኩል ሄደን እንጂ ለወንዶችም ያስፈልጋል። እንደውም እናት እናት ናት። አባቶች ናቸው ብዙ ጊዜ ትተው የሚሄዱት። መሠራትም ያለበት አባቶች ላይ ነው ብዬ አስባለሁ። እኛ በየወረዳው፣ በየቤተክርስትያኑም ባገኘነው ቦታ ሁሉ ኅብረተሰቡን እናስተምራለን። ምክንያቱም አሁን እኛ ጋር ያሉት ከ75 በመቶ በላይ ልጃቸውን ለብቻ የሚያሳድጉ እናቶች (ሲንግል ማሞች) ናቸው።

ብዙ ባል ትቶ ነው የሚሄደው። ዘርሽ፣ ሃይማኖትሽ፣ አካባቢሽ፣ የመጣሽበት አገር እያሉ ይጠቀሳል። ምክንያት ነው የሚፈለገው። ይህንን የሚያደርገው ደግሞ ባል ብቻ ሳይሆን የባል ቤተሰብ፣ እናቶች፣ እህቶች ናቸው። አንቺን አግብቶ ነው የሚሉ አሉ። ይህን መስበር አለብን። ማንም ፈልጎ እንዲህ ያለ ልጅ አይወልድም። በዛ ላይ ልጅ ደግሞ የአባትም የእናትም ውጤት ነው። እናት ብቻ አይደለችም።

ሌላው ደግሞ እግዚአብሔር ነው ልጅ የሚሰጠው፣ ምንም ይሁን ስጦታ የሚሰጥ እግዚአብሔር ስለሆነ የተሰጠንን ተቀብለን ምንድን ነው መሥራት ያለብን፣ ይህ ልጅ ለምን ተሰጠኝ፣ ምንድን ነው የታየብኝ ብቃት ብለን መጠየቅ አለብን። መቼም ውስጣችን ያለውን ነገር ሳያይ እንዲህ ያለ ልጅ አይሰጠንም ብዬ አምናለሁ። ስለዚህ ለምን ተሰጠኝ የሚለውን ሳይሆን ወደፊት ምን ላድርግለት፣ ሌሎችን ልጆች እንዴት ነው የምረዳው የሚለውን ነው ማሰብ ያለብን።

እድሉን ስላገኘነው ነው ናዝሬት ስኩል የሄድነው። እኔ በበኩሌ መኪና መንዳት እንዴት ነው ተብዬ ስጠየቅ ራሱ ስለኦቲዝም አወራለሁ፤ ግንዛቤ እንዲፈጠር። ባገኘሁት አጋጣሚ በሙሉ ስለ ኦቲዝም ሳላወራ አልሄድም፤ የቱንም ዓይነት አጋጣሚ ሳገኝ። ዶክተሮች ጋር፣ ሰው ልጠይቅ ስሄድም ስለኦቲዝም ታውቃላችሁ ወይ ብዬ ሳልናገር አልቀርም። ሁሉም ጋር ያስፈልጋል፤ መማርና ማወቅ አለባቸው።

ብዙ ጊዜ ከልጆች ጤናና መሰል ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሴቶችን እንጂ ወንዶችን ብዙ ስለማናይ፤ በእናንተ በኩል የምታደርጉት የተለየ ሥራ ካለ ለማመላከት ነው ጥያቄውን ያነሳሁት፤
እኛ ጋር 60 ወላጆች አለን። ስብሰባ ሲጠራ እንጃ 2 ወይም 3 ወንድ ካየሽ በቂ ነው። አባቶች አይመጡም፤ ያስቸግራሉ። ብዙ ጊዜ እንዲህ ያለ ቦታ ላይ እናቶችን ነው የሚልኩት። ቢመጡኮ ሐሳብ ይሰጣሉ፣ ብዙ ነገር ትመካከሪያለሽ። ግን እንደዛ አይደሉም። ምናልባት ቤት ቁጭ ብለው ልጆችም እየጠበቁ ሊሆን ይችላል። ግን እንደዛም ሆኖ አይመጡም።

ቀጣይ 10 ዓመት በነህምያ የኢቲዝም ማዕከል እንዲሁም የኦቲዝም ግንዛቤ ዙሪያ ምን ለውጥ ይታይዎታል?
እግዚአብሔር በሰላም በጤና ያድርሰን፣ አገራችን ሰላም ትሁንልንና፤ አዳሪ ትምህርት ቤት መክፈት እንፈልጋለን። አሁን እየገጠመን ያለው እናትም አባትም በሕይወት አይኖሩም፤ ደግሞ የሚገርመው አብዛኛው ደብቆ ነው ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት እና እህቶቻቸው ወንድሞቻቸው (የልጆቹ አክስቶችና አጎቶች) ባህሪያቸውን እንኳ አያውቁም። እና ልጆቹን ይዘውልን ይመጣሉ። እናት አባት ሞተ፣ ይህን ልጅ ምን እናድርገው ይላሉ። ባህሪውን ምንም አያውቁትም።

ምክንያቱም ወላጆች በራሳቸው ራሳቸውን አግልለዋል። ምንአልባት በንግግርም ጎድተዋቸው ሊሆን ይችላል። ስለዚህ አዳሪ ትምህርት ቤት ለልጆቹ ያስፈልጋል። በደንብ እንክብካቤ የሚያገኙበት። ነገ እነዚህ ልጆች ምን ይሆናሉ የሚለው ፍርሃት የሁሉም ወላጆች ነው፣ የልጆቹ እድገትም ጭምር ያስደነግጣቸዋል፤ ማደጋቸው ያስፈራቸዋል።

ይህን መስበር የሚቻለው አንድ አዳሪ ትምህርት ቤት ቢከፈት ነው። ነህምያ ውስጥ ለ60 ልጅ 30 አስተማሪ አለን። ልክ እንደዛው ይህም በደንበኛ ደረጃውን የጠበቀ አዳሪ ትምህርት ቤት መክፈት ነው የሚታየኝ። ኖርንም አልኖርንም፤ ቢያንስ እዛ ውስጥ እስከገቡ ድረስ፤ ስርዓት ከዘረጋሽ በዛ ስርዓት ነገሮች እንዲቀጥሉ ማድረግ ይቻላል።

እንደገና ቢያንስ በየክፍለ አገሩ አንድ አንድ ማዕከል መክፈት አለብን ብዬ አስባለሁ። አዳማ፣ ሐዋሳ፣ ነቀምቴ ላይ ተጀምሯል። ጥሩ ተስፋ አለው። ዐስርም ኻያም ልጅ አድርጎ ሁሉም ቦታ ሁሉም ሰው የሚነቃነቅ ከሆነ፣ ጥሩ ነገር ይታየኛል። ስለዚህ ዐስር ዓመት ላይ በየክፍለ አገር ላይ አንድ አንድ ማዕከልና አንድ የማደሪያ ትምህርት ቤት መክፈት አለብን።

በዘርፉ የምትንቀሳቀሱ ማኅበራት ብዙ አይደላችሁም። እና በጋራ የምትሠሩበትና የምትነጋገሩበት አውድ አላችሁ?
ከዚህ በፊት ጥሩ ኔትወርክ አልነበረንም። አብሮ የመሥራት ነገራችን ጥሩ አልነበረም። የተወሰንነው እንገናኛለን፣ ሥልጠናም ምንም ሲኖር እንደዋወላለን። ግን ሁሉም አልነበረም። አሁን ላይ ግን አንድ ኔትወርክ እየፈጠርን ነው። እና ወደ 13 የሚሆን ድርጅት ተሰብስበን የመንግሥት ትምህርት ቤቶችን ጨምረን ኔትወርክ እየፈጠርን ነው።

አንድነት ሁልጊዜ ኃይል አለው፤ የተሻለ ነገር ለማምጣት ያስችላል። ሁሉም የያዘውን ይዞ ከሚሮጥ፣ ተረዳድተን ይሻላል ብለን አሁን ይመስለኛል አንድ ሦስት ወር አካባቢ ሆኖናል፤ ይህ ሐሳብ መጥቶ ቁጭ ብሎ መነጋገር መመካከር ጀምረናል። አብረን እየሠራን ነው ያለነው። በፍቅር ኢትዮጵያ አማካኝነት ነው ይህ ነገር ሊፈጠር የቻለው። ሁልጊዜ እነሱን እያመሰገንን ነው። ኦቲዝምም፣ ዳውን ሲንድረምም፣ የአካል ጉዳትም ያላቸው ልጆችን በሙሉ፣ ሁሉንም ሰብስበን አንድ ኔትወርክ ፈጥረናል።

በዓል በነህምያ እንዴት ነው የሚከበረው?
አጋጣሚውን ተጠቅመን እንግዳ እንጠራለን። ፋሲካ ያው ከአርብ ጀምሮ ስለሚከበር ብዙ ጊዜ አክብረነው አናውቅም። ዘንድሮ ግን ሼፍ ዘሪሁን የበዓል ፕሮግራም ስለነበረው፣ እሱ ለጾመኞች አገልግል አሠርቶ ድምቅ ባለ ሁኔታ ነው ያሳለፍነው። እና ደስ ይላል፤ ከልጆቹ ጋር የምናሳልፈው ነገር። ዓመት በዓል ላይ ግን ብዙ ጊዜ የሚገጥመን ችግር ለልጆቻችን ኬክ አይመከርም፣ ለስላሳ አይመከርም።

እና አንዳንድ ጊዜ እኛ ጋር ልደት ሊያከብሩ ሲመጡ፤ ፍራፍሬ ይቅረብ ስንል ግራ ይገባቸዋል፤ የተለመደ ነገር አይደለም። በልተው ‹ሃይፐር› ሆነው እነሱን ማረጋጋት ለእኛ ሌላ ሥራ ነው የሚሆንብን። ስለዚህ አመጋገባቸው ከጤናቸው ጋር የተያያዘ ስለሆነ ትንሽ ከበድ ይለናል። የፈለገ የጾምም ኬክ ቢሆን፣ ስኳር ስላለውና ስንዴ ስለሆነ ይጎዳቸዋል። ስለዚህ እኛ ጊቢ ትንሽ ከበድ ይላል። ዓመት በዓልን በተቻለ መጠን ፍራፍሬዎችንና የመሳሰለውን ለመጠቀም እንሞክራለን።

መልዕክት ካለዎት በዚህ አጋጣሚ ያስተላልፉ?
አሁን የምንጠይቀው፤ ያለነው በቤት ኪራይም ስለሆነ፣ የመንግሥት አካላት ጉዳዩን ትኩረት እንዲሰጡት ነው። እኔ እንደወረርሽኝ እንዳይወጣ [ኦቲዝም] እፈራለሁ። አሁን ወደዛው ቀርቧል። በፊት ከአንድ ቤተሰብ አንድ ኦቲዝም ያለው ልጅ ነበር የሚወጣው። ከሦስት ዓመት በፊት ደግሞ ኹለት ልጆች መምጣት ጀመሩ። አሁን ላይ ከአንድ ቤት ሦስት ኦቲዝም ያላቸው ልጆች እየወጡ ነው። ነገ የሚያስፈራ ነገር አለ። መንግሥት ከአሁኑ ትኩረት ሰጥጦ ለእነዚህ ልጆች እንደ ዜግነታቸው መደረግ ያለበት ነገር እንዲደረግ።

ሥልጣኔ ሲባል ሁሉንም ያማከለ መሆን አለበት። ለምሳሌ አዲስ አበባ ላይ ብዙ ትምህርት ቤቶች አሉ። አካትቶ ትምህርት ተብሏል፤ መንግሥት በትልቅ ደረጃ የተፈራረመበትና ቃል የገባበት ጉዳይ ነው። ግን እየተሠራበት ነው ወይ ስትይ አይደለም። ምናልባት የአእምሮ እድገት ውስንነት ያለባቸውን ሊቀበሉ ይችላሉ። እሱም በጣም ጥቂት። ኦቲዝም ከሆነ ግን ይህን የሚችለው የለም አንቀበልም ብለው ይመልሱታል። ስለዚህ ይህ ልጅ አልተካተተም ማለት ነው።

ስለዚህ ትኩረት መደረግ አለበት። ዛሬ መንግሥት መሥራት ካልቻለ ቢያንስ ከሚሠሩ ሰዎች አጠገብ መቆም መቻል አለበት። እኔ ለልጄ ትምህርት ቤት መክፈት አልነበረብኝም። ሲሆን ሌላው እንደሚያማርጠው እኛም ለልጆቻችን ትምህርት ቤት ማማረጥ ነበረብን። ግን እሱ ይቅር ቢያንስ ለልጆቻችን ትምህርት ቤት እንክፈት ስንል መንግሥት ግድ አጠገባችን መቆም አለበት ብዬ አስባለሁ።

ኅብረተሰቡ፣ ሁሉም ሰው በሚችለው ማገዝ አለበት። የግድ ሀብታም መሆን የለብንም። ካለችን ነገር ማካፈል እንችላለን። ጊዜአችንን፣ ፍቅራችንን መስጠት እንችላለን። ይህ መረዳዳት ክህሎት እንዲጨምር እፈልጋለሁ። ሥልጣኔ ሰውን መውደድ፣ ማክበር ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 181 ሚያዝያ 15 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here