የአየር ጥቃቱ በሲቪል ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ማድረሱም ተነግሯል
ዕረቡ ሚያዚያ 19 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የፌደራሉ መንግሥት በስፋት በኦሮሚያ ክልል በሚንቀሳቀሰው የኦነግ ሸኔ ታጣቂ ኃይል ላይ በሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) የታገዘ ጥቃት እየፈጸመ እንደሚገኝ የአካባቢው ባለሥልጣን እና የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ ተናገሩ።
እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራው እና የፌደራሉ መንግሥት አሸባሪ ሲል የፈረጀውን ‘ሸኔ’ ቡድን ለማጥፋት ለአንድ ወር የሚዘልቅ የተጠናከረ ወታደራዊ ዘመቻ መጀመሩን መንግስት ከጥቂት ሳምንታት ማስታወቁ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ ባለፉት ሳምንታት በተለይ በምዕራብ ሸዋ ዞን በኹለቱ አካላት መካከል ጥንካራ ውጊያ ሲካሄድ መቆየቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በምዕራብ ሸዋ ዞን አቡና ግንደበረት ወረዳ ነዋሪ በአካባቢው በታጣቂ ቡድኑ እና በመንግሥት ኃይሎች መካከል ከፍተኛ ውጊያ ሲካሄድ መቆየቱን ገልፀዋል።
ነዋሪዎች፣ ባለፈው አርብ ሚያዚያ 14 ቀን 2014 ብአቡና ግንደበረት ወረዳ ብደጎማ ኮቢ ቀበሌ መንግሥት በፈጸመው የአየር ጥቃት በሲቪል ነዋሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ተናግረዋል።
“ባለፈው ዓርብ ደጎማ ኮቢ ቀበሌን ምሽት 12 ሰዓት ላይ በአየር ከደበደቡ በኋላ 25 ሰዎች ተገድለዋል። በዛ አካባቢ ወደ 400 ሰዎች ይኖራሉ አሁን ጥቃቱን በመሸሽ አንድም ሰው መንደር ውስጥ የሉም። ሸሽተው ጫካ ገብተዋል።” ሲሉ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
የምዕራብ ሸዋ ዞን ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ተስፋዬ ሚሬሳ በበኩላቸው፤ በአካባቢው መንግሥት በድሮን የታዘገ ጥቃት መሰንዘሩን ገልጸው በአየር ጥቃቱ ንጹሃን ሰዎች ስለመጎዳታቸው መረጃው የለኝም ብለዋል።
“መንግሥት ሙሉ አቅም ተጠቅሞ እርምጃ እየወሰደ ነው። ሲቪል ሳይጎዳ ድሮን ጥቅም ላይ ውሏል። በዚህ አካባቢ ያለን መረጃ ጉዳት እየደረሰበት ያለው ኦነግ ሸኔ እንደሆነ ነው እንጂ ሲቪል ሰዎች ላይ አይደለም። ከአባቢው የወጡ ሲቪሎች እንዳሉ ግን መረጃው አለን” ብለዋል።
የኦሮሞ ነጻነት ጦር ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ በተመሳሳይ መንግሥት በሠራዊታቸው ላይ የድሮን ጥቃት መሰንዘሩን ገልጸው፤ “በአየር ድብደባው ወታደራዊ ስኬት አላገኙም። ይልቁንም ሲቪሎች ናቸው እየተጎዱ ያሉት። ደጎማ የሚባል ቦታ ሦስት ቤቶች አቃጥሏል። እኛ ላይ የደረሰ ጉዳት የለም። የሚያሳስበን በሲቪሉ ሕዝብ ላይ የሚደርሰው ጉዳት ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ክልል ከቀናት በፊት “ሸኔን የማጽዳት” ዘመቻው ተጠናክሮ መቀጠሉን እና ይህ ወታደራዊ ዘመቻ የተፈለገለትን ዒላማ እያሳካ እንደሆነ በመግለጫ አውጥቶ ነበር።
ይሁን እንጂ የታጣቂ ቡድኑ ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ፤ “ወታደሮቻችን እየተዋጉ ነው። ድል እንጂ ሽንፈት አልገጠመንም። ከ400 በላይ ወታደር ማርከናል። የተለያዩ ጦር መሣሪያዎችን ማርከናል” ብለዋል።
ነዋሪዎች በምዕራብ ሸዋ ዞን አቡነ ግንደበረት ወረዳ የመንግሥት ጥቃትን ተከትሎ የታጣቂ ቡድኑ አባላት አካባቢውን ጥለው ወጥተዋል ቢሉም ኦዳ ተርቢ ግን፤ “ለወታደራዊ ስትራቴጂ ቦታ ይቀያይራሉ እንጂ አልወጡም” ይላሉ።
“ድል እያደረግን ነው። መንግሥት ወታደር ልኮ የያዘው ቦታ የለም” በማለት ቃል አቀባዩ ይናገራሉ።
የምዕራብ ሸዋ ዞን ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ተስፋዬ ሚሬሳ ባለፉት ቀናት በዞኑ በሚገኙ በርካታ ወረዳዎች ‘ኦነግ ሸኔን’ የሚያወግዙ ሰልፎች ሕዝቡ አከናውኗል ይላሉ።
“ሸኔ በሕዝቡ ላይ የሚያደርሰው ስቃይ እጅግ እየተባባሰ በመምጣቱ በዞኑ ባሉ በርካታ ወረዳዎች የተቃውሞ ሰልፎች እየተካሄዱ ነው። ታጣቂዎቹን የሚቃወመው ሰልፍ እየተካሄደ ያለው ታጣቂዎቹ በሚንቀሳቀሱባቸው ወረዳዎች ውስጥ ነው” ብለዋል።
የኦሮሚያ ክልል ከአንድ ሳምንት በፊት ሚያዚያ 12 ቀን 2014 ባወጣው መግለጫ “አሸባሪውን ሸኔ የማጽዳት ዘመቻ ተጠናክሮ ይቀጥላል” ያለ ሲሆን፤ “በቡድኑ ላይ እየተመዘገቡ ያሉ ድሎች የኦሮሞ ሕዝብ በቅርቡ ከቡድኑ እረፍት እንደሚያገኝ ማሳያዎች ናቸው” ማለቱም የሚታወስ ነው።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n



