”በከተማችን የተፈጠረው ችግር በምንም ሁኔታ የሙስሊሙንና የክርስትና ዕምነት ተከታይ ማህበረሰቡን የማይወክል ነው።” ፦ የጎንደር ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት

0
898

ዕረቡ ሚያዚያ 19 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በትናትናው ዕለት በጎንደር ከተማ የተፈጠረው ችግር በምንም ሁኔታ የሙስሊሙንና የክርስትና ዕምነት ተከታይ ማህበረሰቡን የማይወክል መሆኑን የጎንደር ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ምክር ቤት አስታወቀ።

በከተማ አስተዳደሩ በአራዳ ክፍለ ከተማ ላይ የተፈጠረው ግጭት በምንም ሁኔታ የኹለቱን ዕምነት ተከታይ ማህበረሰብን የማይወክል ጥፋት ተፈጽሟል! ያለው የከተማው የፀጥታ ምክር ቤት፤ ጥፋቱ የተፈፀመው በጥቂት ጽንፈኛና አክራሪ ግለሰቦች የተከበሩትን የኹለቱን ዕምነት ተከታዮች ወደ ለየለት ግጭት ለማስገባት ሆን ተብሎ ለግጭት የማያበቃ ምክንያትን በመምዘዝ ጥፋት እንዲፈጠር የተቀነባበረና የተመራ ሴራ ነው ብሏል።

የጎንደር ከተማ ፀጥታ ምክር ቤት ጉዳዮን አስመልክቶ ዛሬ ባወጣው መግለጫ በዚህ እኩይ ተግባር ከኹለቱም የዕምነት ተከታዮች የህይዎትና አካል መጉደል እንዲሁም የንብረት መቃጠልና ዘረፋ ማጋጠሙን ገልፆ፤ በተፈጠረው ግጭት በንጹሃን ሕይወት፣ አካል እና ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት የከተማ አስተዳደሩ ጥልቅ ሀዘን የተሰማው መሆኑን በመግለፅ ለተጎጂ ቤተሰቦችም መጽናናትን ተመኝቷል።

”ይህ ቡድን የፈለገው ጎንደርን ማቃጠል፣ መዝረፍና ማዋረድ ሲሆን፤ ይህ ክፉ ተልዕኳቸው በፀጥታ መዋቅሩ፣ በኹለቱም የዕምነት አባቶችና ወጣቶች እንዲሁም በአገር ሺማግሌዎች ጥረት የፈለጉት ጥፋት ሳይደርስ መቆጣጠር ተችሏል” ሲልም ገልጿል።

በተፈጠረው ችግር ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጠልለው የተገኙ ሙስሊሞች እንደ ነበሩና የእምነቱ አባቶችም ጉዳት ሳይደርስባቸው ለፀጥታ አካላት ያስረከቡ መሆኑን፣ በተመሳሳይም በመስጊድ ውስጥ የተጠለሉ የክርስትና አማኞች እንደነበሩና ከጥቃት የዳኑ መሆኑ መረጋገጡን ፀጥታ ምክር ቤቱ አስታውቋል።

ይህ ልምድ ደግሞ የዛሬ ሳይሆን ትናንትም የእምነት ተቋማትና አባቶች የችግር ጊዜ ታማኝ መሸሸጊያ /መጠለያ/ ዋስትና መተማመኛ መሆኑ ታውቆ ያደረ በመሆኑ አንደኛው በሌላኛው በእጅጉ የሚያምን አንድና ያው የሚባል የህብረተሰብ ክፍል በመሆናቸው ነው ሲልም ገልጿል።

የጎንደር ህዝብ ታሪክ መረዳዳት መከባበር መቻቻል መፋቀር በፋሲካ ሙስሊሞች የሚያስተባብሩበት በኢድም ክርስቲያን ወንድሞች የሚያግዙበት እንጂ፤ ዛሬ በጥቂት የጥፋት ቡድኖች የተመራው ጥፋት በፍፁም የጎንደርን ልክ የሚመጥንና የሚወክል ባለመሆኑ መላው ህዝብ በአገኘው አጋጣሚ እያወገዘው ይገኛል! በቀጣይም ሊያወግዘው ይገባል ያለ ሲሆን፤ የተፈጠረውን ቃጠሎም ህዝቡ በነቂስ በመውጣት በከፍተኛ ርብርብ መቆጣጠር መቻሉንም በመግለጫው አስታውቋል።

አሁን አካባቢው ሙሉ በሙሉ ከፀጥታ መዋቅርና ከአካባቢው ነዋሪ ጋር ትብብር በማድረግ የተረጋጋ ሰላም ለመፍጠር በሁሉም አካባቢ ስምሪትና ቁጥጥር እየተደረገ ይገኛል ያለው የከተማው ፀጥታ ምክር ቤት፤ ኹሉም የጎንደር ህዝብ ለከተማችን መረጋጋት ከፀጥታ አካሉ ጎን በመሰለፍ ቀንደኛና የጥፋት ሃይል የሆኑ በህይዎትና በአካል ጉዳት እንዲሁም በዘረፋ የተሰማሩት እየተለቀሙና እየተያዙ በመሆኑ ለዚህም ህዝቡ የተለመደውን ንቁ ተሳትፎ በማድረጉ ምስጋናውን አቅርቧል።

የከተማዋ ነዋሪም፤ በቀጣይም ቀሪ የጥፋት ሃይሎችንም አጋልጦ ለፀጥታ መዋቅሩ በማስረከብ የተለመደውን ትብብር እንዲቀጥል፣ በብሎክ አደረጃጀትም አካባውንና ሰፈሩን፣ የንግድ ተቋማትን እንዲሁም የዕምነት ተቋሞችን በመጠበቅ ከተማዋን ከጥፋት እንዲያድን የጎንደር ከተማ ፀጥታ ምክር ቤት ጥሪ አቅርቧል።

ከዚህ እኩይ ተግባራቸው የማይታረሙ አጥፊዎችን ህግ ለማስከበር በጭራሽ የማይታገስ መሆኑን የገለፀው ምክር ቤቱ፤ በኹከቱ የደረሰውን ጥፋት የምርመራ ቡድኑ እያጣራ ስለሆነ መረጃው እንደተጠናቀቀ ለህዝቡ ይፋ የሚደረግ መሆኑን አስታውቋል።
_____________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here