የአንበጣ መንጋ፣ ኮቪድ-19 እና የምግብ አቅርቦት

Views: 404

ኮቪድ 19 የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ በቀጠለበት በዚህ ሳምንት፣ አፍሪካ ከሌሎች ክፍላተ ዓለም አነስተኛ ነው ቢባልም እድገቱ ያልቀነሰ የቫይረሱን ወረርሽኝ አስተናግዳ ቀጥላለች። ይህም ስርጭት ከአሁን በባሰ ወደፊት ይመጣል የሚል ስጋት እየተሰማ ሲሆን፣ አፍሪካ የሚሆነውን በመጠበቅ ውስጥ የነበሩ ችግሮቿንም ለማዳመጥ እየሞከረች ነው።
ሽመልስ አረአያ ይህን ነጥብ በማንሳት ይልቁንም ከምግብ አቅርቦትና ዋስትና እንዲሁም ከግብርና አለመዘመን ጋር ተያይዞ፣ የምግብ ችግር አስጊ ሊሆን እንደሚችል ያነሳሉ። ይህም እንኳን እንዲህ በጨነቀው ጊዜ በደኅናውም ጊዜ የሚስተዋል መሆኑን በመጥቀስ፣ በዚህ ላይ ከቫይረሱ መሰራጨት አስቀድሞ አስቸግሮ የነበረው የአንበጣ መንጋም ያለውን እህል እንዳያወድም በአፍሪካ ያለውን ስጋት አካፍለዋል። ወረርሽኙ አሳሳቢ ቢሆንም እነዚህ ጉዳዮችን ኢትዮጵያ ቸል ማለት አይገባትም ሲሉም ያሳስባሉ።

ቀጣይ የኮቪድ-19 ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ዋና ማእከል አፍሪካ ትሆናለች የሚል ጉዳይ እየተስተጋባ ነው። በኢኮኖሚ አቅምና በጤና ስርዓት ደካማነት የተነሳም ብርቱ ክንዱን በማሳረፍ የከበደ ቀውስ ያስከትላል ተብሎ ተፈርቷል። ይህን ጽሑፍ በማዘጋጅበት ወቅት በዓለም ከኹለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በምርመራ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ሲለዩ፣ የሟቾች አሃዝ ከመቶ ሰማንያ አምስት ሺሕ በላይ አሻቅቧል። በቫይረሱ ከተከሰተ ሞት ውስጥ ከአራቱ አንዱ በአሜሪካ እንደሆነ መረጃው ይጠቁማል።

ከኹለት ወራት በፊት ለመጀመሪያ ጊዜ ቫይረሱ በአፍሪካ ስለመግኝቱ በግብፅ ይፋ ከተደረገ ወዲህ ከኹለት አገራት ውጭ ሁሉንም አዳርሷል። እስከ አሁንም ቫይረሱ በግዛታቸው ስለመገኘቱ በይፋ ያልገለፁት ኮሞሮስና ሌሶቶ ናቸው። እነኚህ በዓለማቀፍ ደረጃ የአገርነት እውቅና አላቸው ካላልን በቀር፣ በቆዳ ስፋታቸው ይሁን በሕዝብ ብዛት በኢትዮጵያ ደቡብ ክልል ከሚገኘው ከወላይታ ዞን ጋር የሚተካከሉ ናቸው። በመሆኑም ቫይረሱ አፍሪካን በሞላ አላዳረሰም ማለት አይቻልም።

ወቅታዊ መረጃ እንደሚጠቁመው በአፍሪካ የቫይረሱ ተጠቂዎች ከ25 ሺሕ በላይ ሲሆኑ፣ የሟቾች አሃዝ ከአንድ ሺሕ ኹለት መቶ አልፏል። በዚህም እስካሁን በአኅጉሪቱ በቫይረሱ ውድ ሕይወታቸውን የተነጠቁ ሰዎች በዓለም ከተመዘገበው ድርሻቸው በጣም ትንሽ ነው። ይህ ግን አሳሳች መሆን የለበትም። የአዲስ ተጠቂ ቁጥር በየዕለቱ እየጨመረ ባለበት በሙሉ ኃይሉ ወደ ማጥቃት ከተሻገረ፣ በወር ውስጥ የማይገመት ውድመት እንደሚያደርስ ከአሜሪካ ታይቷል። በአሜሪካ በፈረንጆቹ መጋቢት 19 የሟቾች ቁጥር ከኹለት መቶ አልዘለለም ነበር። ነገር ግን በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ በዚያች የዓለም ልዕለ ኃያል አገር የሆነውን ለማመን ይከብዳል።
በአገራችንም በይፋ የተገለፀው የተጠቂዎችና ሟቾች አሃዝ ከሌሎች ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ ነው። በአብዛኛው እየተጠቁ በምርመራ እየተለዩ የሚገኙት ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የገቡና በማቆያ ማእከላት የነበሩ እንደሆነም ይጠቀሳል። ከሌሎች አገራት አንፃር ሲታይ አነስተኛ ምርመራ በመደረጉ እንጂ ሳይታወቅበት የቫይረሱ ስርጭት ኢትዮጵያን ሳያዳርሳት እንዳልቀረ በስጋት የሚገልጹ አሉ። የዚህ ወቀሳ እውነትነት ያለው ስለመሆኑ ከሌሎች ጎረቤት አገራት አንፃር ማየት እንችላለን። ለአብነትም የኬንያና የጅቡቲን ጉዳይ ለማነፃፀሪያነት እንጠቀማለን።

ሚጢጢዋ ጅቡቲ እስካሁን ይፋ ያደረገችው የተጠቂዎች ቁጥር ከኢትዮጵያ በዘጠኝ እጥፍ የሚልቅ ሲሆን ከአስር ሺሕ በላይ ሰዎችን መርምራለች። በዚህም ከእያንዳንዱ ሚሊዮኖች ውስጥ ለዐስር ሺሕ ሦስት መቶ ሰዎች ምርመራ አድርጋለች እንደማለት ነው። በሌላ በኩል ኬንያ ከአስራ አምስት ሺሕ ሰው በላይ የመረመረች ሲሆን፣ ከእያንዳንዱ ሚሊዮኖች ኹለት መቶ ሰባ አምስት ሰዎች መርምራለች። ከእነዚህ ጋር ሲነፃፀር የኢትዮጵያ በጣም ዝቅተኛ ነው።

ይኸውም ይህን ጽሑፍ እስከተጻፈበት ድረስ ዐስር ሺሕ ሰው እንኳን አልተመረመረም። በዚህም ከሚሊዮኖች ሰማንያ አምስት ሰዎችን ብቻ እንደመመርመር ማለት ነው። በመሆኑም ወቀሳው እውነትነት የሚያላብሰው ነገር እንዳለው ያሳያል። በዚህ አነስተኛ የምርመራ አፈፃፀም የተነሳ ቢያንስ አንድ ታማሚ ሳይለይ ወደ ኅብረተሰቡ ቢቀላቀል በቫይረሱ የስርጭት ባህርይ አገሪቱን በሞላ የሚያጥለቅለቅ መሆኑ የተዘነጋም ይመስላል።

በአፍሪካ ኢኮኖሚ ላይም በፍላጎትና አቅርቦቶች ላይ መዛባት ያስከትላል። በአቅርቦት በኩል የሰው ኃይል እንደተለመደው ወደ ሥራ በመሄድ በሥራው መሰማራት አይችልም። የእንቅስቃሴ ገደቦች በዚህ ላይ የሚያሳድረው ተፅዕኖ ከበድ ይላል። ከተወሰኑ ቁሳቁሶች በስተቀር በሌላው የምርትና አገልግሎት ላይ የሚኖር የፍላጎት መቀዛቀዝ ከፍተኛ ነው።

በዚህም ኢኮኖሚውን ለከፋ ዝቅጠት ይዳርጋል። ብዙ ተቋማት ገበያ በማጣት ለመዘጋት ይገደዳሉ። የአብዛኛው ፍላጎት በተቀዛቀዘበት ኹለት ነገሮች ግን እጅግ ተፈላጊ ሆነዋል፡- ምግብና የጤና አገልግሎት። የጤና ጉዳይ ወሳኝ ነው። በመሆኑም የጤናውን ዘርፍ ለማጠናከር የሚደረገው ድጋፍ የበለጠ መጠናከር አለበት። ምግብም እጅግ ተፈላጊው ሸቀጥ ሆኗል። በዚህ ወቅት የምግብ አቅርቦት ሰንሰለት በምንም ሁኔታ እስትንፋሱ ሳይቋረጥ በሕይወት እንዲኖር ማድረግ ያስፈልጋል። ይህን ባለማድረጋችን ተያይዞ ለሚመጣ የምግብ እጥረትና አለመረጋጋት የሚያስከትለው ዳፋ ብዙ እንደሆነ ከዚህ በፊት በሚገባ አንስቻለሁ።

ፈዋሽ፣ አራሽ፣ ቀዳሽ እና ተኳሽ
ምንጩን ባላስታውሰውም አገር ለመምራት የሦስት ሰዎች መኖር በቂ ነው የሚል ማንበቤን አልረሳም። በአስፈላጊነታቸው የተጠቀሱት ሦስቱ አርሶ የሚያበላ ገበሬ (አራሽ)፣ ከፈጣሪ ጋር በጸሎት የሚያገናኝ የሃይማኖት አባት (ቀዳሽ) እንዲሁም ሕግና ስርዓት እንዲያስከበሩ መንግሥት የሚያዛቸው የፀጥታ አካላት (ተኳሽ) እንደሆኑ ይጠቅሳል።

ቀዳሾች የሁሉም ሃይማኖት አገልጋዮች መሆኑን ለማመላከት የተሰጠ የጋራ መጠሪያ ነው። ከእነዚህ ውስጥ ያልነበረ አሁን የተጨመረው የጤና ባለሙያ (ፈዋሽ) ነው። እነኚህ አራቱም በዚህ ቫይረስ የተነሳ ዛሬ የሰው ልጅ ለገባበት ምስቅልቅል እጅግ አስፈላጊ ናቸው ቢባል ማጋነን አይሆንም። አሁንም አገራት ሁሉ አማትረው እየተመለከቱ ያሉት ወደ ፈዋሾች፣ አራሾች፣ ቀዳሾች እና ተኳሾች ነው። ስለጤናው ዘርፍ አቅም ግንባታ ማጠናከር ከዚህ በፊት በጻፍኳቸው ብዙ ብያለሁ። አወዳሽ መፈለጉንም ለባለቤቱ እተወዋለሁ። የእንቅስቃሴ እገዳውን ለማስፈፀም ተኳሹን ማሰናዳት መንግሥት ለራሱ ሲል ይጨነቅበት። በመሆኑም የዛሬው ትኩረት ስለምግብ ይሆናል።

ከሕክምና ቁሳቁስ ባልተናነሰ አገራት በምግብ ሸመታም ተጠምደዋል። በመሆኑም የምግብ ሸቀጦች በገበያ ተፈላጊ ሆነዋል። ወቅቱ የምግብ ሻጭ መሆንን ያስመኛል። በደኅናው ጊዜም ቢሆን የምግብ ነገር እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ አልነበረም። በምግብ ራስን መቻል አንድምታው ብዙ ነው። ምግብ የአገር ደኅንነት ጉዳይ ነው። የበለፀጉት አገራት ገበሬዎቻቸው የተትረፈረፈ እንዲያመርቱ ድጎማ በገፍ ያቀርቡላቸዋል። የእኛ ገበሬዎች ደግሞ ድጎማው ቢቀር ለግብዓት መግዣ የሚሆን ብድር በወጉ አያገኙም።

ታዲያስ እንዴት ራሳችንን መመገብ እንችላለን? ወደውጭ የምንልካቸው የግብርና ምርቶች እንኳን ተጠቃሚዎች ለድሎት የሚገዟዋቸው እንጂ እንደምግብ ለሕይወት እጅግ አስፈላጊ አይደሉም። በዚህም ለውጭ የምናቀርባቸው ምርቶች ከጥጋብ በኋላ የሚሸጡት በዋናነት ቡና እና አበባ ናቸው። በቀጣይ የተትረፈረፈ የምግብ ምርት እድገት ትሩፋቶች እራስ ከመመገብ አልፎ እንዴት ወደምንፈልገው የኢንዱስትሪ ሽግግር ለማድረግ እንደሚያግዘን እራሱን በቻለ አርዕስት ለማየት በቀጠሮ ለይደር እናቆየው። ለአሁኑ በወረርሽኙ የተነሳ ስለናረው ምግብ እንነጋገራለን።

ከሰባት ዓመት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በዓለም ገበያ የሩዝ ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ እንደታየ እየተነገረ ነው። በስንዴም እንዲሁ በፈረንጆቹ ከመጋቢት ወር ጋር ሲነፃፀር የአስራ አምስት በመቶ የዋጋ ጭማሪ እንዳለው ተነግሯል። የአፍሪካ አገራት በደኅናው ጊዜ ሳይቀር መጠኑ ከፍተኛ የሆነ የምግብ ሸመታ እንደሚያደርጉ ይታወቃል። በየዓመቱ ኢትዮጵያ ከውጭ የምታስገባውን ስንዴ ብቻ ማሰቡ ለዚህ በቂ ነው።

በወቅቱ ፈተና የተነሳ እራሳቸውን መመገብ የማይችሉ ዜጎች ኑሮአቸው እጅጉኑ ይመሳቀላል። በመሆኑም መንግሥት ተጋላጭ ለሆኑ ለእነኚህ የኅብረተሰብ ክፍሎች ከለጋሾች ጋር በመተባበር የምግብ እደላ ለማድረግ መዘጋጀት እንዳለበት የሚያመላክቱ ጽሑፎች በባለፉት ጊዜያት በማውጣት ጥቆማ አድርጌያለሁ። በአንዳንድ የክልል መስተዳደሮች በከፋ ሁኔታ ለምግብ እጦት አደጋ ተጋላጭ ለሆኑ የከተማ ነዋሪዎች የምግብ እደላ ለማድረግ ጥረቶች የተጀመሩ ሲሆን፣ ይህንንም የበለጠ እንዲጠናከር ማድረግና ሌሎች ክልሎችም ተሞክሮ በመውሰድ ለአካባቢውና አገር ሰላም ሲባል የምግብ ድጎማ ማድረግ ተገቢ ነው። ለምን የተባለ እንደሆን ሰላም የሚያሰፍነው በምንሠራው ሥራ ውጤት በመሆኑ ነው።

ምግብና ኮሮና
ይህ ቀውስ ከመነሳቱ በፊት፣ በዓለም የምግብ ገበያ ላይ ምንም ጥድፊያ ያልነበረበት፣ በአጠቃላይ የምግብ ዋጋም ዝቅተኛ የነበረበት፣ የምግብ ሸቀጦችም ከተትረፈረፉበት ተነስተው ወደሚፈለግበት ቦታ እንደተለመደው ይጓጓዙ ነበር። የቫይረሱን ስርጭት ለማስቆም በሁሉም አገራት ከሞላ ጎደል እየተደረገ ባለው የእንቅስቃሴ እገዳ የተነሳ ግን ይህን የተለመደው የምግብ አቅርቦት ተግባር እጅግ ፈታኝ አድርጎታል። ይህን በወለደው ስጋት የተነሳም በጥድፊያ የሚደረገው ግዢ በምግብ ገበያ የዋጋ ንረት እንዲፈጠር ምክንያት እንደሆነ የዓለም ምግብ ፕሮግራም (WFP) ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል።

በዚህ የጥድፊያ ግዢ የምግብ ዋጋ ለሸማቾች እጅጉኑ አስደንጋጭ እየሆነ መምጣቱን በተመሳሳይ ሮይተርስ በመጋቢት 20 በተባበሩት መንግሥታት የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት (FAO) ውስጥ የሚሠሩ ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ አብዶልረዛ አባስያን ጠቅሶ ዘግቦ ነበር።

ባለሙያው እንዳሉትም ‹‹በሁሉም ዘንድ [አስመጪዎችና መንግሥታት] እየታየ ያለው በጥድፊያ በሚፈፅሙት ግዢ በምግብ ገበያ ላይ ያልተለመደ ነገር መከሰቱን ነው። ይህ የአቅርቦት እጥረት ጉዳይ አይደለም፣ ነገር ግን ምግብን በሚመለከት የግዢ ባህሪ ለውጥ ነው። ብዙዎች በግንቦት ወይም ሰኔ የስንዴ ወይም የሩዝ አቅርቦት ማግኘት አንችልም ብለው ሲያስቡ ምንድነው የሚከሰተው? በዓለም ደረጃ የምግብ አቅርቦት ቀውስ ያመጣው ይህ ነው።›› ሲሉ ተናግረዋል።

ቀውሱ ከተጠቃሚዎች ባልተናነሰ በአምራቾች ላይ የሚያሳድረው ኪሳራ እንዲሁ ቀላል አይደለም። በኢትዮጵያ ስለወረርሽኙ እንዲህ ከመስተጋባቱ በፊት የዋና ዋና ሰብል ምርቶች ተሰብስበው ለገበያ የቀረቡ ሲሆን፣ በመስኖ የሚለሙ የአትክልት፣ የፍራፍሬ እንዲሁም የወተትና የመሳሰሉት አምራቾች ግን የበለጠ ለኪሳራ ተጋልጠዋል። ይህም የተከሰተው የመስተንግዶ ዘርፍ (ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶች፣ ካፍቴሪያዎች…ወዘተ) ላይ ባለው ገበያ መቀዛቀዝ የተነሳ አብዛኞቹ ሥራውን ከሞላ ጎደል ለተወሰነ ጊዜ ለመዝጋት በመወሰናቸው ተያይዞ የመጣ የገበያ እጦት ነው።

ነገር ግን ቀውሱ በአምራቾችና በተጠቃሚዎች መካከል ላሉት አስተላላፊዎች ያልታሰበ ሲሳይ ያስገኘላቸው ይመስላል። አምራቾቹ በቀጣይ ገበያ እናጣለን ብለው በወረደ ዋጋ በሩጫ የሚሸጡ ሲሆን በከተማ የሚገኙ ቸርቻሪዎችና ተጠቃሚዎች ደግሞ በቀጣይ አቅርቦት ሊቋረጥ ይችላል በሚል ፍራቻ በተጋነነ ዋጋ በሽሚያ ይገዛሉ። ለቀናት አልያም ሰዓታት ብቻ ባደረጉት አስተዋፅኦ አስተላላፊዎች የተጋነነ ጥቅም ያገኛሉ ማለት ነው።

አምራቾች በፍራቻ ዓመቱን ሙሉ የለፉለትን የመጣል ያክል እንዲሸጡት ይገደዳሉ። ይህ እንዳይከሰት የምግብ ገበያና አቅርቦት መቼም ቢሆን እስትንፋሱ እንደማይቋረጥ በአካባቢው መስተዳድሮች በኩል መረጃው ለአምራቾች እንዲደርስ ማድረግ ያስፈልጋል። አምራቾቹ በተጋነነ ዋጋ ለቀጣይ ምርት የሚሆን ግብዓት ለመሸመት እንደሚገደዱም በዓለም ምግብ ፖሊሲ ምርምር ተቋም በኩል በተሠራው የዳሰሳ ጥናት ተመላክቷል።

በመሆኑም አርሶ አደሮች በኹለት በኩል ተጎጂ እየሆኑ እንደሚገኙ ነው። በዚህም መንግሥት ለግብርናው ክፍለ ኢኮኖሚ መሰረት የሆኑት ግብዓቶች በድጎማ እንኳን ባይሆን አምራቾች የተጋነነ ዋጋ እንዳይከፍሉ የቁጥጥር ሥራውን ከማጠናከር አልፎ የብድር አቅርቦት እንዲያገኙ ከተቋማት ጋር በማስተሳሰር የግብርና ሥራው ወቅቱን ጠብቆ እንዲሠራ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ማድረግ አለበት።

ከቀናት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎች ማለትም ምርጥ ዘር፣ ማዳበሪያና፣ ተባይ ማጥፊያዎችን በወቅቱ ለአርሶ አደሩ እንደምናቀርብ አረጋግጣለሁ ሲሉ በትዊተር ገፃቸው አስፍረዋል። ነገር ግን በኢትዮጵያ በዋናነት የዘር ግብይት ኋላቀርነትና ስር በሰደዱ ተቋማዊ ማነቆዎች የተነሳ አርሶ አደሩ የምርት ማሳደጊያ ቴክኖሎጂዎችን ተጠቃሚ እንዳይሆን እንቅፋት ሆኗል።

ሌላው ለአርሶ አደሩ የሚቀርበው እውነትም የተሻሻለ ምርጥ ዘር ቢሆን ኖሮ ለተባይ ማጥፊያ የሚወጣ ወጪም አይኖርብንም ነበር። አለበለዚያ ምኑ የተሻሻለ ዝርያ ሆነ? በተያያዘም ምን ያህሉ ገበሬ የምርጥ ዘር ተጠቃሚ እንደሆነ የሚያሳየው መረጃ አስደንጋጭ ነው። ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከአጠቃላዩ በሰብል ከሚሸፈነው ማሳ በምርጥ ዘር የሚሸፈነው ድርሻ ከአምስት በመቶ ያነሰ ነው።

በተመሳሳይ የፕላንና ልማት ኮሚሽን ኮሚሽነር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሰሞኑ ቀርበው ‹ምርጥ ዘርና ሌሎች ግብዓቶች ለአርሶ አደሩ በሚገባ ተሰራጭቷል› በማለት ተናግረዋል። እውነት ለመናገር ለየትኛው ሰብል እንደዚሁም ስንት ኩንታል እንደተሰራጨ ቢጠየቁ ማስረጃውን ስለማቅረባቸው በጣም እጠራጠራለሁ። ይህን የምልበት ዋናው ምክንያትም ከዘር አቅርቦት ጋር በተገናኘ የመስክ መረጃ በመሰብሰብ እንደተረዳሁት አርሶ አደሩ የአዳዲስ የሰብል ዝርያዎችን የመጠቀም ፍላጎቱ ከፍተኛ ቢሆንም በደኅናው ጊዜ እንኳን ጥራቱን የጠበቀ ምርጥ ዘር በወቅቱ ማቅረብ አንዱ ደንቃራ ችግር ነው። በዚህም ገበሬዎቹ ወቅቱ ከማለፉ በፊት መሬታቸው ጦም እንዳያድር ከባለፉት ዓመታት የተቆጠበ በአካባቢያቸው በተገኘ ዘር የሚሸፍኑት መሆኑን ስለማውቅ ነው።

ከምርጥ ዘር አቅርቦትና ፍላጎት ጋር በተያያዘ በሚጠቀሱ ብዙ ችግሮች የተነሳም አርሶ አደሩ የተሻሻሉ የሰብል ዝርያዎችን አሟልቶ እየተጠቀመ እንዳልሆነ ጥናቶች አረጋግጠዋል። ለዚህም በዩኒቨርሲቲ ቆይታችን የክፍል ጓደኛዬ የነበረው ክብሮም አርአያ (ዶ/ር) ከባልደረቦቹ ጋር በመሆን እ.ኤ.አ በ2016 “Understanding farmers’ technology adoption decisions: input complementarities and heterogeneity” በሚል ርዕስ በአገሪቱ በከፍተኛ አምራችነት ከሚታወቁት ወረዳዎች ውስጥ ከ7,500 አርሶ አደሮች ናሙና ተወስዶ በተሰበሰበ መረጃ ባካሄዱት ጥናት፣ የምርጥ ዘር ተጠቃሚው አርሶ አደር ድርሻ ከኻያ በመቶ በታች እንደሆነ ደምድመዋል።

ይህንን ለምርታማነት ማነስ ዋና ማነቆ በማስተካከል የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ከማገዝ ይልቅ ግብርናውን ለማዘመን ትኩረት እየሰጠሁ ነው የሚለን መንግሥት አስፈላጊው ቴክኖሎጂዎችን ስላለማቅረቡ፣ አንድም የማዳበሪያ ማምረቻ አገር ውስጥ ያልገነባ መሆኑንና የአርሶ አደሩ የማዳበሪያ ፍላጎት የሚሸፈነው ከውጭ በሚገባ እንደሆነ መጥቀስ አግባብ ነው። በእኛ አገር ነባራዊ ሁኔታ የዘመነ ግብርና ማለት በትራክተር ማረስ እንዳልሆነ በሚገባ ያልተረዱ የመንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በየሚድያው ስለዚሁ ገለፃ ይሰጣሉ።

ለአብነትም ከቀናት በፊት የፋይናንስ ሚኒስትር ድኤታው ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ ‹ለግብርና ሜካናይዜሽን የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች ያለቀረጥ እንዲገቡ ተደርጓል። በዚህም መሰረት በገበሬዎች እጅ የትራክተር እንቅስቃሴ እየታየ ነው። ይህም የግብርናውን ክፍለ-ኢኮኖሚ ለማሳደግ ወሳኝ ነው›› አሉ።

በመጀመሪያ እዚህ ጋር ለማለት የምፈልገው ግብርና ሳይንስ መሆኑን ነው። ስለዚህ የግብርናው ዘርፍ የግብርና ሳይንስ በሚያውቁ ባለሙያዎች ብቻ እንዲመራ ሁኔታዎች ሊመቻቹ ይገባል። ከዘጠና አምስት በመቶ የሚሆኑት አርሶ አደሮች አነስተኛ ማሳ በማረስ የሚተዳደሩ በሆነበት አገር ውስጥ አይደለም በትራክተር ለማረስ ለትራክተሩ ማቆሚያ እንኳን በማይበቃበት ሁኔታ በእንዲህ ያለ አግባብ የሚነገር ሐሳብ ከፕሮፓጋንዳነቱ ባለፈ ውጤቱ ዜሮ ነው።

እንግዲህ በተደጋጋሚ ከባለሥልጣናቶቻችን እንደሚሰማው ግብርና ማዘመን የሚለው እሳቤ በተሳሳተ የተተረጎመ ይመስላል። በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ግብርናው ለማዘመን በዋናነት የሚያስፈልገው ከአፈሩ ጋር የተስማማ ማዳበሪያና ጥራቱን የጠበቀ በገበሬዎች የተወደደ ምርጥ ዘር ያገኙ እንደሆነ ብቻ ነው። በእኛ ነባራዊ ሁኔታ የትራክተር መተራመስ ግብርናው ያዘምናል ማለት ትልቅ ስህተት ነው። እንደተባለው በትራክተሩ ማረስ ቢጀምር በገጠር ከግብርና ውጭ ሌላ ሥራ ያልተመቻቸለት የተትረፈረፈ ጉልበት የት መሄጃ አለው? ለዚህ ነው እያንዳንዱ ዘርፎች በዘርፉ የትምህርት ዝግጅት ባላቸው ባለሙያዎች ቢመሩ ለአገር እጅጉኑ መልካም እንደሆነ የጠቀስኩት።

ግብርናችን እንደሚወራለት ባለመሆኑ በምግብ እንኳን ራሳችንን መቻል አቅቶን በየዓመቱ እጃችን ለምፅዋት ከመዘርጋት አልፈን ዜጎቻችን ለሥራና ለተሻለ ኑሮ ፍለጋ ባህርና በረሃ አቆራርጠው በእንግልት ወደሌሎች አገራት ይነጉዳሉ። በበለፀገች ኢትዮጵያ ይሄ ሁሉ ባልሆነ ነበር። ይህንን ለመቀየር ከተለመደው ውጪ አዲስ ነገር መሞከር አለብን።

አሁን የተጀመረው በማጠናከር በሁሉም ዘርፎች ሳይንሱን የተማሩ ወጣቶች ኃላፊነት መስጠት ያስፈልጋል። በታማኝ ካድሬዎች ብቻ የመተማመን ጉዞ አገራችንን የት እንዳደረሳት ከእኛ በላይ መስካሪም የለም። ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በዘላቂነት ምን አይነት ፖሊሲ መከተል አለብን የሚለውን መዳሰስ ተገቢም አስፈላጊም ቢሆንም፣ አሁን ትኩረት መደረግ ያለበት ከፊታችን የተደቀነው አደጋ መወጣት ላይ ብቻ መሆን አለበት።

የአንበጣው…አያምጣው
በዓለም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ርዕስ በሆነበት የምሥራቅ አፍሪካ አገራት በ70 ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ አስደንጋጭ የአንበጣ ወረርሽኝ ተጠቅተዋል። አሁንም ለኹለተኛ ዙር ከመጀመሪያው ጋር ሲነፃፀር ከኻያ እጥፍ በጨመረ የአንበጣ መንጋ እንደሚወረሩ ስጋት ማየሉንና በዚህም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ለምግብ እጦት ተጋላጭ ይሆናሉ ተብሏል።

አንድ ዩጋንዳዊ ገበሬ ‹‹አንዴ አትክልት ውስጥ ከገቡ አጠቃላይ ውድመት ነው። በዚህም አንበጣዎች ከኮሮና ቫይረስ በበለጠ አጥፊ መሆናቸውና ቫይረሱ ይህን ያክል ጥፋት ያደርስብናል ብዬ አላምንም›› ብለዋል። የአንበጣው ወረርሽኝ ወሬው መሰማት ከጀመረ የቆየ ቢሆንም እ.ኤ.አ በመጋቢት አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት የምግብ እና እርሻ ድርጅት (FAO) ባወጣው ሪፖርት እንዳስጠነቀቀው ‹ታይቶ የማይታወቅ› የአንበጣ መንጋ በተለይም በመካከለኛው ኬንያ፣ በደቡብ ኢትዮጵያና በሶማሊያ አስደንጋጭ እንደሚሆን ተጠቅሷል። የቫይረሱን ወረርሽኝ ለመግታት በተወሰደው የእንቅስቃሴ እገዳም የአንበጣውን መስፋፋት ለመቆጣጠር ከባድ ፈተና እንደሚደቅን ተሰግቷል።

በኢትዮጵያ በመጀመሪያው ዙር በነበረው መንጋ ብዙ ውድመት የደረሰ ሲሆን፣ በኹለተኛ ዙር እየመጣ ባለው የተጠናከረ ቁጥጥር ካልተደረገበት ‹መጠኑ ከፍ ያለ ሰብል፣ የግጦሽና የደን ሽፋን ላይ ኪሳራ ያደርሳል፣ የምግብ እጥረት እንዲከሰት ያደርጋል› ይላል ማስጠንቀቂያው። ‹በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ› እንዲሉ፣ በኮቪድ-19 ወረርሺኝ ተጨንቀን በሐሳብ ተወጥረን ባለንበት በዚህ ጊዜ፣ ጦም ሊያሳድረን የሚችል ሌላ የአንበጣ መንጋ በደቡብ በኩል በመገስገስ ላይ ነው ማለት ነው።
እናም መንግሥት የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጠጠር ትኩረት እንደሰጠው ሁሉ፣ ለዚህም ፈተና ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር መላ ያበጅለት እላለሁ። ፈጣሪ አገራችንና ሕዝቧን ከዚህ ሁሉ መዓት ይጠብቅልን!

ሽመልስ አርአያ በአሁኑ ወቅት በጀርመን አገር ከሚገኘው ጊሰን ዩኒቨርሲቲ የዶክትሬት ዲግሪ እጩ ሲሆኑ ቀደሞ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል በመምህርነት አገልግለዋል። በ araya.gedam@gmail.com አድራሻቸውም ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 2 ቁጥር 77 ሚያዝያ 17 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com