መነሻ ገጽማረፊያሰሞነኛ‹የሃይማኖተኞች› ዝቅጠት

‹የሃይማኖተኞች› ዝቅጠት

ሠሞኑን ብዙዎችን ያስደነገጠ ሃይማኖታዊ ይዘት ያለው የመጠፋፋት አዙሪት ውስጥ ተገብቷል። በቀላሉ ሊበርድ ይችል በነበረ አለመግባባት ሳቢያ በተፈፀመ ድርጊት እስከ አሁን ብዙዎች መሞታቸው በርካታ ንብረትም መውደሙ እየተነገረ ይገኛል።

ሃይማኖታዊ ጥቃቶችም ሆኑ የእርስ በርስ መጠፋፋቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ካለፉት 4 ዓመታት ወዲህ ተጠናክረው ቢታዩም፣ እንደሰሞኑ ግን የተጋጋሉ አይመስልም። የሁኔታው አሳሳቢነት የታያቸው ከመነሻው ጀምሮ ሲያወግዙና ሕጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ሲጠይቁ የነበረ ቢሆንም፣ በተቃራኒው ፅንፍ የያዙ ደግሞ ተደፈርን በሚል እሳቤ ሌሎችን ለበቀል ሲያነሳሱ ውድመትም ሲፈፀም ነበር።

ሰው ሲከፋው እንደማፅናናት የሚያባብስ ድርጊትን የሚፈፅሙም እየተበራከቱ መሆናቸውን ማስተዋል ይቻላል። ‹‹ሆድ ለባሰው ማጭድ አታውሰው›› እንደሚባለው በቋፍ ላይ ያለውን የኢትዮጵያን ሠላም ገደል ውስጥ ከትቶ የሚያስቀር ተግባር በማን አለብኝነት ሲፈጸምም እየታየ መሆኑን የሚናገሩ አሉ።

ጉዳዩ በቀላሉ ሊበርድ የማይችል ለሁሉም መዘዝ ሊያስከትል የሚችል ቢሆንም ጥፋት ያጠፉን ለይቶ ከመቅጣትና ከማስቀጣት ይልቅ፣ ድርጊቱ እንዲባዛ የሚያደርግ ቅስቀሳ ተደርጎ የበቀል እርምጃ እንዲፈፀሙ ተደርጓል። ‹እኛም ቤት እሳት አለ!› በሚል የዘመኑ እሳቤ አገሪቷን አቃጥሎ የሚጨርስ አዙሪት ውስጥ እንደተገባ የሚናገሩ አሉ።

የቀድሞ እንግሊዘኛ መማሪያ መጽሐፍ ላይ ያለ የአንድ ግለሰብ ታሪክ የወቅቱን ሁኔታ ይገልፀዋል። ግለሰቡ ኹለት ሚስቶች ነበሩት። አንዷ በእድሜ የገፋች እኩያው የምትሆን እና ሌላዋ ዘግይቶ ያገባት ወጣት የሆነች ሴት ጋር የሚኖር ነው። ወጣቷ ባሏ ሽማግሌ እንዳይመስልባት ነጭ ነጩን ፀጉር እየመረጠች ትነቅላለች። እኩያው ደግሞ ባሏ ወጣት ሆኖ ቶሎ አረጀች እንዳያስብላት ጥቁር ጥቁሩን መርጣ ባገኘችው አጋጣሚ ትነቅላለች። የኹለቱ ሚስት የየግል ፍላጎት እየቀጠለ ሄዶ ባላቻውን መላጣ እንዳደረጉት የሚናገር ታሪክ ነው።

የአሁኑ የአገራችን አካሄድም በዚህ ከቀጠለ ምንም አይነት የእምነት ተቋማት የሌሉባት አገር ማድረግ ብቻ ሳይሆን ‹እንደሃይማኖተኛነታችን› አንድም አማኝ ነኝ የሚል ኢትዮጵያዊ ምድሯ ላይ ላይቀርባት እንደሚችል የቀናት ድርጊታችን አመላካች ነው።

የሰሞኑ መነጋገሪያ የነበረው ይህ ሃይማኖታዊ ሽፋን ያለው ጥፋት፣ እንደ ከዚህ ቀደሞቹ ዝም ተብሎ የሚታለፍ አይደለም በማለት፣ ‹ያበጠው ይፈንዳ› እያሉ የተወሰኑት የአፀፋ እርምጃ እንዲወሰድ ሲወተውቱ፣ ሌሎች ደግሞ ራሳችሁን ጠብቁ እያሉ ከሌላ ውድመት እንዲከላከሉ ጥሪ ሲያቀርቡ ተሰምቷል። ብዙዎች የኮነኑትን ድርጊት አንዳንዶች ይበልጥ እንዲስተጋባና ዓለም ዐቀፍ ይዘት እንዲኖረውም እያደረጉት ይገኛሉ።

በመንግሥት አካላት፣ በሰብዓዊ መብት ተቋማት እንዲሁም በሃይማኖት መሪዎች እንዲቆምና ኅብረተሰቡ እንዲረጋጋ የሚያደርግ ጥሪና መግለጫ በፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር ቢሰራጭም፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ የነበረ ቁርሾም ሆነ ጥላቻ ስር ሰዶ ስለነበር ውጤቱ አስከፊ እንደሆነ የተመለከትነው ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 182 ሚያዝያ 22 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች