ሕግ እና ዱላ

Views: 466

የሰው ልጅ በልቦና ሕግ ከመመራት ጀምሮ የተጻፈ ሕግ በማሰናዳት እርስ በእርስ ተስማምቶ፣ ተፈጥሮ ያደለችውንም ሀብት በጋራ የሚጠቀምበትን ስርዓት ሠርቷል። ሕግንም ጽፎ ለተግባራዊነቱና ለጥበቃው የተለያዩ አካላትን አኑሯል። እነዚህ አካላትም ሰው ለተጻፈ ሕግ በልቦናው ላይገዛ ይችላል ብለው፣ ሕጉን ለማስከበር ዱላን ሳይቀር ይጠቀማሉ። ይህም ‹ልጄ ስርዓት ይዞ ማደግ አለበት› እንደሚልና ለዛም በትንሽ ትልቁ ዱላን እንደሚያበዛ ወላጅ፣ ሕግን ያስከብራሉ የተባሉትም ከልክ ያለፈ ‹ለሕግ ተቆርቋሪነት› በማሳየት ዱላቸውን ሲያበረቱ ይታያል።

የዱላቸው ብርታት ሕግን ከማከበር ያሻግራቸዋል። ይልቁንም ራሳቸውን ወደማስከበር ይደርሳሉ። ከሕግ በላይ እነርሱና የእነርሱ ዱላ ተፈሪ ነው። ይህ ዱላ እና ይህ ቅጣት ነው አንድም ሰዎችም ከሕግ በላይ ሕግ አስከባሪን እንዲያከብሩ፣ ሕጉን ማክበራቸው የሚሰጣቸውን ጥቅም ከማመዛዘን ይልቅ የሚጣልባቸውን ቅጣት እንዲፈሩ ያደረገው።

ይህ ሐሳብ በሠለጠነና መረጃን ከዳር እዳር በብርሃን ፍጥነት መቀባበል በቻለ የ21ኛው መቶ ክፈለ ዘመን ሰው ኋላቀር ሊባል የሚገባ አመለካከት ቢሆንም፣ ሰዎች ከአንዳንድ ልምዳቸው በቶሎ የሚላቀቁ አይመስሉም። በተለይም በአዳጊ አገራት ይህ በጉልህ ይስተዋላል፤ በኢትዮጵያችንም እንደዛው።

ከሰሞኑ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ብዙ ከተቀባበሉ ክስተቶች አንዱ በፖሊስ ድብደባ የተፈጸመባት ሴት ጉዳይ አንዱ ነው። ተደብዳቢዋ በመንገድ ላይ እየተራመደች ሳለች አብረዋት ከነበሩ የቤተሰብ አባላት ጋር ርቀቷን እንድትጠብቅ በማዘዝ ነው የ‹ሕግ አስከባሪው› ዱላ ያሳረፈባት/ያሳረፈባቸው። ይህ በእጅጉ ሊወገዝ የሚገባው ድርጊት ነው።

መወገዝ ብቻ አይደለም፣ ከዛም በላይ በሕግ እርምጃ ሊወሰድ ያስፈልጋል። ይህም በጓዳ ሳይሆን በአደባባይ ሊታይ የሚገባ ነው። በሕግ ሥም ራሳቸውን ተፈሪና ተከባሪ ያደረጉ ሰዎች የአምባገነን መንግሥታት ምልክት ናቸው። እነርሱን የሚገዛ ሕግ እንደ ሌለ አድርገው መኖራቸውም፣ የሚያስተባብራቸው መንግሥት ምን ያህል በቸልታ እና በልቅነት እንደያዛቸው ነው የሚያሳብቅበት።

እርግጥ ነው፤ ስርዓት አስከባሪ የተባለን ፖሊስ ሁሉ የግል ጸባይ ማረም አስቸጋሪ ነው። ግን ቢያንስ ያጠፋውን ቀጥቶ ማሳያ አለማድረግ የባሰ ጥፋት ነው። በተለይ በሴቶች ላይ እንዲህ ያለ ጥቃት ለመፈጸም አጋጣሚውን የሚጠብቁ ከሙያም፣ ከሥነ ምግባርም፣ ከሰብአዊነትም የጎደለባቸውንና ያጎደሉትን ማረም የግድ ይላል። ስለሕግ የበላይነትና ስለሰዎች መብት አልገለጥለት ያለን ሰው፣ ሕግን በራሱ ላይ ተግባራዊ አድርጎ ማስተማርና ማሳየት ስህተት አይደለም።

ለነገሩ ደንብ አስከባሪዎችን እንመልከት። በሕግ የተሰጣቸው መብት ከሚመስለው ነገር መካከል አንዱ በዱላ መምታት ነው። ሕገ ወጥ የተባሉ በመንገድ ላይ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመሸጥ የሚተዳደሩ ነጋዴዎችን እያባረሩ ይመታሉ። እንዲያም ሆኖ ቢሆን ሕጉንም በዱላ ያስከበሩት አይመስልም። እንደውም ከእነርሱ ዱላና ማስፈራሪያ በተሻለ ዝናብና ካፊያ አቅም አላቸው።

እናም አቤቱታውን የሰሙ የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ዝም ማለት አይገባቸውም፣ ምላሻቸው ይጠበቃል። ደንብና ስርዓት አስከባሪዎች ከዚህ ቀደምም እንዲያገለግሉት የቆሙለትን ሕዝብ በዱላ እንደሚደበድቡ፣ በቻሉት ሁሉ ዱላን እንደሚያሳርፉ ግልጽ ነው። አሁንም በምክንያት እንኳ ለማድረግ አሳማኝ ያልሆነን ድብደባ ያለ ምክንያት በእነዛ ሴቶች ላይ መፈጸማቸው፣ ምንአልባት እንደ ማንቂያ ደወል ሊወሰድ ይችላል። የጥቂት ሳንቲም የዳቦ ዋጋ ጭማሪ አብዮት እንዳስነሳችና እንዳቀጣጠለች የሌሎችን አገር ተሞክሮ አይተናል። የሞላ ባልዲን አንዲት ጠብታ ታፈሰዋለችና፣ ይህም ለውጥ እንዲፈጠር መንገድ ቀያሪ ክስተት ሊሆን ቢችልስ! ማን ያውቃል!
ሊድያ ተስፋዬ

ቅጽ 2 ቁጥር 77 ሚያዝያ 17 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com