ባለፉት ዘጠኝ ወራት 43 ሚሊዮን ዜጎች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ሆነዋል
የጤና መድኅን አገልግሎት በአርብቶ አደሩ አካባቢ ያለው አፈፃጸም አነስተኛ መሆኑን የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
የጤና መድኅን አገልግሎቱ ዋና ዓላማ በርካታ የኅብረተሰብ ክፍሎች ንብረታቸውን በመሸጥ እና የብድር አገልግሎቶችን በመጠቀም የሕክምና አገልግሎቶችን ያገኙ የነበረበትን ልማድ ማስቀረትና አስቀድሞ በሚከፈል አነስተኛ መዋጮ የሕክምና ሽፋን እንዲያገኙ ማድረግ ነው። ይህን ዓላማ ለማሳካት እንቅስቃሴ ከተጀመረ ቢቆይም፣ በአርብቶ አደሩ አካባቢ ያለውን ዝቅተኛ አፈጻጸም ለማሻሻል ቀጣይነት ያለው ሥራ ይከናወናል ሲል ነው ተቋሙ የገለጸው።
ሰዎችን ወደ ችግር እና ድህነት እየከተተ ያለው የሕክምና እጦት ጉዳይ ምክንያቱ ከመንግሥት ግምጃ ቤት (ትሬዤሪ) የሚመደበው በጀት ምንም እንኳን ቢያድግም ለአጠቃላይ ማኅበረሰብ መዳረስ ስላልቻለ፣ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች የሚደረገው እገዛ በቂ ስላልሆነ እንዲሁም ለጤና ዘርፍ ከውጪ ለጋሾች የሚመጣው እርዳታ ስለቀነሰ ነውም ተብሏል።
ችግሮቹን ለመቅረፍ እና የጤና አገልግሎትን ከፍ ለማድረግ፣ ፍትሐዊ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖር፣ የማኅበረሰብ ተሳትፎን ለማሳደግ፣ የነፍስ ወከፍ የጤና ወጪ ለመቀነስ፣ ከዓመት ዓመት እየናረ የመጣውን የሕክምና አገልግሎት ክፍያ ለመቋቋም፣ የመድኃኒት ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ ስለሔደ የመግዛት አቅምን ከፍ ለማድረግ እና የጤና ተቋማት አገልግሎታቸውን እንዲያሻሽሉ ለማድረግ የጤና መድኅን አገልግሎትን ሥርዓት ተዘርግቶ ኃላፊነቱን እየተወጣ ይገኛል ተብሏል።
የጤና አገልግሎቱን ለማሻሻል እና የሕክምና መሣሪያ ግብዓት አቅርቦትን ለማሳደግ የመድን አገልግሎት ተቋሙ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም የተገለፀ ሲሆን፣ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አማካኝነት እንደ ካንሰር፣ የልብና ኩላሊት ያሉ ሕክምናዎችን ለኅብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየተሠራም ይገኛል ነው የተባለው።
በሌላ በኩል፣ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ለ43 ሚሊዮን ዜጎች የጤና መድኅን አገልግሎትን ተደራሽ ማድረጉንም ተቋሙ አስታውቋል።
ከሐምሌ 1/2013 እስከ መጋቢት 30/2014 ባሉት ዘጠኝ ወራት 43 ሚሊዮን ዜጎች ወይም 9.5 ሚሊዮን አባወራ እና እማወራ የጤና መድኅን የሕክምና አገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት የኮምዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ዘመድኩን አበበ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።
በ2014 ዘጠኝ ወራት 8.2 ሚሊዮን አባወራ እና እማወራዎችን የሕክምና አገልግሎቱ ተጠቃሚ ማድረግ ተችሎ የነበረ ሲሆን፣ ይህም ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር የ1.3 ሚሊዮን ሰዎች ብልጫ እንዳለው ነው የተናገሩት።
የመድኅን ሽፋኑ በአንድ ቤተሰብ ውስጥ የአገልግሎቱ ተጠቃሚ የሆኑ የኅብረተሰብ ክፍሎች ሕመም በሚገጥማቸው ወቅት ተገቢውን አገልግሎት እንዲያገኙ ታሳቢ ያደረገ ነውም ተብሏል።
ተቋሙ በ2013 በ850 ወረዳ የጤና አገልግሎቱን እየሰጠ እንደነበር እና በተያዘው በጀት ዓመት አገልግሎቱን የሚሰጡ የወረዳዎች ብዛት ወደ 879 ማሳደግ መቻሉ ተገልጿል።
የኢትዮጵያ ጤና መድኅን አገልግሎት የማኅበረሰብ ጤና መድኅን ተግባራዊ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ 3 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ለማወቅ ተችሏል።
በኢትዮጵያ ከሚገኙ ወረዳዎች መካከል 78 በመቶ በሚሆኑት ላይ አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ መቻሉም የተገለጸ ሲሆን፣ ተቋሙ ይፋ ያደረገው ሪፖርት እንደሚያስረዳው በኦሮሚያ፣ በአማራ፣ በሲዳማና በደቡብ ክልሎች የተሻለ አፈጻጸም ያለው ሲሆን ትግራይ ክልልን እንደማያካትት ተጠቅሷል።
ቅጽ 4 ቁጥር 182 ሚያዝያ 22 2014



