ፍርድ ቤቶች ለዋስትና የሚይዙት ገንዘብ አብዛኛው ተመላሽ አይሆንም ተባለ

0
1073

በሕግ ቁጥጥር ውስጥ ሆነው በፖሊስ ምርመራ እየተደረገባቸው ወይም በዐቃቤ ሕግ ክስ ተመስርቶባቸው በገንዘብ ዋስትና የሚለቀቁ ሰዎች፣ ጉዳያቸው ውሳኔ ሳይሰጥበት ተንጠልጥሎ ስለሚቀር የዋስትና ገንዘባቸው እንደማይመለስ ቅሬታቸውን ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
በዚህም ፍርድ ቤቶች የዋስትና ገንዘቡን ከሕግ አግባብ ውጭ ለገቢ ምንጭነት እየተጠቀሙበት ነው በማለት የዋስትና ገንዘብ ያስያዙ ሰዎች ቅሬታዎችን ያቀርባሉ።

የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ ጠበቃ ሄኖክ አክሊሉ፣ ሕጉ ክሱ ከተዘጋ ገንዘቡ መመለስ አለበት ይላል። አሁን ባለው ሁኔታ ግን የሕግ ጉዳይ ያለባቸው አባሎቻችን የክስ ጉዳያቸው ተንጠልጥሎ ነው የሚቀረው፤ የዋስትና ገንዘቡም አይመለስም ብለዋል።
አክለውም በርካታ ገንዘቦች በዋስትና ተይዘው ነው የሚቀሩት ካሉ በኋላ፣ መዝገቦች ለዐቃቤ ሕግ ቀርበው ካልተዘጉ ገንዘቡ ሊመለስ አይችልም። ይህም ከሕግ አንጻር ተገቢ አይደለም ሲሉ ተናግረዋል።

‹‹እኛ እንደ ፓርቲ ከመቶ ሺሕዎች በላይ የሚቆጠር ገንዘብ በዋስትና ተይዞብናል። በየጊዜው ወደ ፍርድ ቤት የሚቀርበውን ባለጉዳይ ስናስብ ደግሞ በመቶ ሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በፍርድ ቤቶች ተይዟል›› ነው ያሉት።
‹‹ፍርድ ቤት በአንድ ጉዳይ እስከ 60 ሺሕ ብር ዋስትና መጠየቁ የተለመደ ሆኗል፣ እስካለኝ መረጃም እነዚህ ገንዘቦች ኦዲተር በአግባቡ የሚከታተላቸው አይደሉም።›› ብለዋል።

ገንዘቦች ለሙስናና ለሕገወጥ ድርጊት የተጋለጡ ናቸው የሚሉት ጠበቃው፣ ገንዘብ የተያዘባቸው ሰዎችም ፖሊስ ጣቢያ ሄደው ጉዳዬ የት ደረሰ የማለት ልምድ ስለሌላቸውና ቢሄዱም አንዴ ዐቃቤ ሕግ እያየው ነው፣ ሌላ ጊዜ ፖሊስ ጋር ነው ስለሚባሉ አድካሚ ሂደቶችን ተከታትለው ላያስመልሱ ይችላሉ ነው ያሉት።

እስከ አሁንም ግለሰቦች የተያዙባቸው እንደ ስልክና ፓስፖርት ያሉ ንብረቶቻቸውን ሲያስመልሱ እንጂ፣ ካሉት ጉዳዮች 99 በመቶ የሚሆኑት ክሳቸው ተዘግቶ የዋስትና ገንዝብ ሲመለስ ዐይቼ አላውቅም ሲሉ አክለዋል።

ለዚህም በርካታ ጊዜ ነው የምንመላለሰው፣ ሆኖም እንኳን የዋስትና ገንዘብ ማስመለስ፣ የፓርቲው ፕሬዝዳንት (የእነ እስክንድር ነጋ) የባንክ አካውንት ከ2012 ጀምሮ የታገደ በመሆኑ በተደጋጋሚ ጠይቀው እስከ አሁን አልተከፈተላቸውም ነው ያሉት።
የዋስትና ገንዘብ የተያዘባቸው ሰዎች ማለቂያ በሌለው ቢሮክራሲ ነገሩ ሰልችቷቸው እንዲተውት ነው እየተደረገ ያለው የሚል ሐሳባቸውንም ሰንዝረዋል።

ባለጉዳዮች የዋስትና ገንዘባቸው የሚመለሰው ዐቃቤ ሕግ ክሱ እንዲዘጋ ካደረገ ነው በመባሉም አዲስ ማለዳ የፍትህ ሚኒስቴርን የጠየቀች ሲሆን፣ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ አወል ሱልጣን፣ የዋስትና ገንዘብ ዋነኛ ዓላማ ተከሳሽ በቀጣይ ቀጠሮውን አክብሮ እንዲገኝ ነው ካሉ በኋላ፣ ገንዘቡ ተመላሽ ሊሆን የሚችለው መዝገቡ ፍጻሜ ሲያገኝ ነው ብለዋል።

ጉዳዩ ውሳኔ ሳያገኝ በአየር ላይ እስካለ ድረስ ግን ሂደቱ 10 ዓመት ቢቆይ እንኳን ገንዘቡ ተመላሽ አይሆንም ሲሉ ገልጸዋል። የገንዘቡ ተመላሽነት የሚወሰነውም በምርመራ መዝገቡ ዕድሜ ገደብ ይሆናል ነው ያሉት።

አቃቤ ሕግ በዋስትና ገንዘብ ጉዳይ አይመለከተውም ካሉ በኋላም፣ ተከሳሽ በሚጠፋበት ጊዜ፣ ምስክር ሳይመጣ ሲቀር እንዲሁም ፖሊስ ተከሳሹን ለማቅረብ የሚወስደው ጊዜ ሂደቱን ስለሚያጓትተው ዐቃቤ ሕግ የምርመራ መዝገብ በእጁ ላይ እስካላቆየ ድረስ በዚህ ተጠያቂ ሊሆን እንደማይችል አንስተዋል።

ፍርድ ቤት ተገቢ ባልሆነ መንገድ ቀጠሮ የሚሰጥ ከሆነ፣ አቃቤ ሕግ ምስክሮችን ሳያሟላ ሲቀር፣ ፖሊስ አስረህ አቅርብ የተባለውን ካላቀረበ ሂደቱ ይጓተታል። በዚህ ሂደት ሦስቱም አካላት ችግር አለባቸው ሲሉ ገልጸዋል።
አዲስ ማለዳ ሥማቸውን ለመናገር ፈቃደኛ ያልሆኑ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሠራተኛ ያነጋገረች ሲሆን፣ እርሳቸውም ዐቃቤ ሕግ የከፈተውን ክስ እስካልዘጋ ድረስ የዋስትና ገንዘብ ፍርድ ቤቶችን አይመለከትም ነው ያሉት።

‹‹አቃቤ ሕግ የከፈተውን ለምን አይዘጋም፣ እርሱ በከፈተው ክስ አይደል ፍርድ ቤት ተከሳሾችን ዋስትና አስይዛችሁ ውጡ የሚለው?›› ያሉት ሠራተኛው፣ ዐቃቤ ሕግ ላልዘጋው ክስ ፍርድ ቤት እንዴት የዋስትና ገንዘብ ይለቃል ብለዋል።

የዋስትና ገንዘብ ምንን መሰረት አድርጎ እንደሚተመን ተጠይቀውም፣ ይህ የሚወሰነው በዳኞች ነው። ሆኖም ገንዘቡ የጥፋቱ ምትክ አይደለም፣ አንዳንዴ ከጥፋቱ በጣም ያነሰ ገንዘብ ለዋስትና ይጠየቃል፤ ይህም ተከሳሹ በሕግ ጥላ ስር ሆኖ ጉዳዩን እንዲከታተል ነው በማለት ተናግረዋል።

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ቀጠሮ ዕለት ዐቃቤ ሕግና ተከሳሽ ሳይገኙ ሲቀሩም፣ ፍርድ ቤቱ ጉዳዩን ተዳፍኖ (Inactive) እንዲቆይ ያደርጋል። በዚህም መዝገቡ ውሳኔ እስካልተሰጠበት ድረስ የዋስትና ገንዘቡን ፍርድ ቤቱ አይመልስም ነው ያሉት።
የሚሰበሰበው የዋስትና ገንዘብ ለምንም አገልግሎት እንደማይውልና መንግሥት ልጠቀምበት ሲል፣ ፍርድ ቤት የሕዝብ ገንዘብ ነው በማለት እንደሚከለክል ጠቁመዋል።

አዲስ ማለዳ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ቃል አቀባይ ከሆኑት ተስፋዬ ነዋይ ተጨማሪ ማብራሪያ ፍልጋ ብትደውልም፣ በወቅቱ ሥራ ላይ ነኝ በማለታቸው ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም።


ቅጽ 4 ቁጥር 182 ሚያዝያ 22 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here