ለዓመታት ካገለገሉበት ትምህርት ቤት ወደ ሌላ የትምህርት ተቋማት ዝውውር ያደረጉ መምህራን ከስድስት ወር አገልግሎት በኋላ የሥራ ልምድ ይያዝላችኋል የሚል ቃል ቢገባላቸውም የቀጠሮው ቀን ሲደርስ ልምዱ አልተያዘልንም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ቅሬታ አቀረቡ።
ቅሬታ ካቀረቡት መምህራን መካከል አስናቀ ቤኩማ፣ በአንድ የክፍለ አገር ወረዳ ትምህርት ቤት ተቀጥረው እየሠሩ እንደቆዩ አውስተዋል። ለ15 ዓመታትም በዚሁ በክፍለ አገር በሚገኝ የትምህርት ተቋም በማስተማር ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ከቆዩ በኋላ፤ በአዲስ አባባ ከተማ በወጣው የመምህራን ቅጥር ማስታወቂያ መሠረት ተወዳድረው ማለፍ እንደቻሉ ነው የገለጹት።
ቅሬታ አቅራቢው እንደሚሉት ከሆነ፤ ተወዳድረው ሲያልፉና ወደ ሥራ ገበታ ሲገቡ የ15 ዓመት የሥራ ልምዳቸው ከስድስት ወራት የሙከራ ጊዜ በኋላ እንደሚያዝላቸው ተነግሯቸዋል። ሆኖም ጊዜው ሲደርስ ቃል በተገባላቸው መሠረት የ‹ልምድ ይያዝልን› ጥያቄ ቢያቀርቡም ‹‹አይ አይያዝም፤ እኛ አናውቅም። ሂድና ክፍለ ከተማውን ጠይቅ።›› የሚል ምላሽ እንደተሰጣቸው ነው የተናገሩት።
መምህሩ ወደሚመለከተው ክፍለ ከተማ ትምህርት ቢሮ ሄደው ጥያቄያቸውን ያቀረቡ ሲሆን፤ ‹‹የአዲስ አበባ ከተማን ትምህርት ቢሮ ጠይቅ እንጂ እኛ በጀማሪ እንድንቀጥርህ ነው የተላከልን።›› የሚል ምላሽ ነው የተሰጠኝ ይላሉ።
የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ በበኩሉ ለተነሳው ጥያቄ፣ ‹‹እኛ ይሄ አይመለከትንም፤ ፌዴራል ትምህርት ቢሮ ነው የሚፈታው። ብዙ ሰው እንደ አንተ ዓይነት ጥያቄ ይዞ እየመጣ ተቸግረናል።›› እንዳላቸውም አክለዋል።
ከዚህም በተጨማሪ ‹‹የፌዴራል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎቹ ይባስ ብለው ቅሬታዬን ሳቀርብ ስቀውብኛል።›› ያሉት ቤኩማ፤ ‹‹15 ዓመት ልምድ እያለኝ ለምን በጀማሪ መምህርነት እቀጥላለሁ፤ ልምዴ ይያዝልኝ።›› ብዬ ሕጋዊ ጥያቄ ስለጠየቅሁ እንዴት ይሳቅብኛል?›› ሲሉ ጠይቀዋል።
ሌላኛዋ ሀና ያሬድ የተባሉ መምህርት የስድስት ዓመት የመምህርነት የሥራ ልምዳቸው አለመያዙ ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ሀና በበኩላቸው ጉዳዩን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ በቀጥታ አቅርበው ጉዳዩ በሳምንታት ውስጥ ምላሽ እንደሚሰጥበት የተነገራቸው ሲሆን፤ በተባለው የጊዜ ገደብ ግን መፍትሄ አልተሰጠም ብለዋል።
ቅሬታ አቅራቢዋ አክለውም በሌሎች ሰዎች በኩል በቀጣይ እንጂ በዚህ ዓመት መፍትሄ ሊሰጥ አይችልም የሚል ጭምጭምታ እንደሰሙና የሥራ ልምድ መመዝገብ ለምን ይህን ያህል ቀጠሮ እንዳስፈለገው ጥያቄ እንደሆነባቸው አብራርተዋል።
ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለአዲስ ማለዳ የገለጹት፤ የተሻለ ደመወዝ ማግኘት የሚቻለው የተሻለ የሥራ ልምድ ሲኖር መሆኑ እየታወቀ፣ በዚህ የኑሮ ውድነት እንዴት ሕይወታችንን እንምራ በማለት ነው። በተያያዘም የሥራ ልምድ እያላቸው በጀማሪ መምህርነት ማገልገል አግባብነት የሌለው ተግባር እንደሆነ አንስተው፤ የሚመለከተው አካል በአፋጣኝ መፍትሄ ይስጠን ሲሉ አሳስበዋል።
ከአዲስ ማለዳ ጋር በጉዳዩ ዙሪያ ቆይታ ያደረጉት የመምህራን ማኅበር ፕሬዝዳንት ዮሐንስ በንቲ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ለተነሳው ቅሬታ በሚከተለው መልኩ ምላሽ ሰጥተዋል።
የማኅበሩ ፕሬዝዳንት እንደገለጹት ከሆነ፤ ምናልባት በቅሬታ አቅራቢዎቹና ቃል በገቡት ባለሥልጣናት መካከል ቅድሚያ ልምድ የመያዝ ስምምነት መኖሩንና አለመኖሩን የሚያረጋግጥ መረጃ መኖሩንና አለመኖሩን ለማወቅ እንደሚከብድ ገልጸዋል። በተያያዘም፤ እንዲህ ዓይነት ቅሬታ የሚያነሳ መምህር ወደ ማኅበሩ ያቀረበው ቅሬታ እንደሌለ ዮሐንስ አንስተዋል።
አዲስ ማለዳ ለተነሳው ቅሬታ ምላሽ ለማግኘት ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱን ለማነጋገር ያደረገችው ሙከራ ስልክ ለማንሳት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሊሳካ አልቻለም።
ቅጽ 4 ቁጥር 182 ሚያዝያ 22 2014



