በዘጠኝ ወር ውስጥ ወደ ውጭ ከተላከ እንጀራ 36 ሚሊዮን ዶላር ተሰበሰበ

0
1193

በ2014 በጀት ዓመት የመጀመሪያዎቹ ዘጠኝ ወራት ወደ ውጭ አገር ከተላከ እንጀራ 36 ሚሊዮን ዶላር እንደተገኘ የምግብ፤ መጠጥና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በዘጠኝ ወራት ውስጥ እንጀራ ከመላክ የተገኘው ገቢ ታቅዶ ከነበረው 29 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ ያሳየ መሆኑ ተነግሯል።

በአሁኑ ወቅት እንጀራ ተፈላጊነቱ ጨምሯል የተባለ ሲሆን፣ እንጀራን በተመለከተ በ2014 የዘጠኝ ወር ሥራ አፈጻጸም 71 በመቶ የሚሆነው እቅድ ተግባራዊ ሊሆን ችሏል ሲሉ የኢንስቲትዩቱ ዕቅድ ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አስራት አያሌው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የምግብ መጠጥና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት በዘጠኝ ወር ውስጥ ወደ ውጭ አገር ከተላኩ ምርቶች 81 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱንም አሳውቋል። ተቋሙ በዘጠኝ ወራት ውስጥ 81 ቢሊዮን ዶላር ማግኘቱን የገለፁት አስራት፣ የተገኘው የዶላር ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ41 በመቶ ብልጫ እንዳለውም አያይዘው ጠቅሰዋል።

ወደ ውጭ የተላኩ የምርት አይነቶችም ዱቄትና የዱቄት ውጤቶች፤ የቅባት እህሎች፤ መጠጦች፤ የተቆላ ቡና፤ ሻይ ቅጠል፤ ቅመማ ቅመሞች፤ የአትክልትና ፍራፍሬ ውጤቶች፤ አኩሪ አተር ኮስሞቲክስና የመሳሰሉት መሆናቸውን አስራት በዝርዝር አስቀምጠዋል።
ምንም እንኳ ከ2013 ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በዘንድሮው ዓመት የተሻለ ገቢ ማግኘት ቢቻልም፣ ከዚህ የተሻለ ገቢ ለማግኘት እንደ መሰናክል የሆኑ የምርት ግብዓት ዕጥረት እንዳጋጠመ አስራት አልደበቁም።

እንደ አስራት ገለጻ፤ የኑግ ምርት ግብዓት ከሁሉም የምርት አይነቶች በከፋ ሁኔታ በመጥፋት ላይ መሆኑን ነው ማወቅ የተቻለው። አስራት አያይዘውም፤ የአኩሪ አተር፤ የሰሊጥ፤ በሻይ ቅጠል፤ በአትክልትና ፍራፍሬ (በተወሰነ መልኩ) የግብዓት ዕጥረት ስለተስተዋለባቸው በዘጠኝ ወራት ውስጥ በእነዚህ ምርቶች ዝቅተኛ አፈጻጸም እንደተመዘገበም ለአዲስ ማለዳ ተናገረዋል።

ዕጥረቱ ያጋጠመውም ድርቅ ባለባቸው አካቢዎች ማምረት ስላልተቻለና ጦርነቱን ተከትሎ የተከሰቱት መስተጓጎሎች ተጠቃሽ መንስኤ ናቸው ሲሉ አስራት ምክንያቱን አብራርተዋል።

በሌላ በኩል በዘጠኝ ወር ውስጥ ከውጭ አገር 704 ሺሕ ቶን የምግብ ዘይት ማስገባት የተቻለ ሲሆን፤ 101 ሺሕ ቶን የሚሆነው ደግሞ አነስተኛና ጥቃቅን አምራቾችን ሳይጨምር በአገር ውስጥ እንደተመረተ ተመላክቷል።
በአገር ውስጥ የተመረተው የምግብ ዘይት ከውጭ አገር መግባት የነበረበትን ግብዓት 14 በመቶ መሸፈን እንዳስቻለም አስራት ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

እንዲሁም፤ ከ80 ሺሕ ቶን በላይ በአገር ውስጥ በማምረት፤ ከአንድ ሺሕ 800 ቶን በላይ ከውጭ አገር በማስገባት በአጠቃላይ 82 ሺሕ ገደማ በላይ ቶን ብቅል ማቅረብ የተቻለ ሲሆን፤ 97 በመቶ የሚሆነውን መሸፈን የቻለው በአገር ውስጥ የተመረተው ነው ተብሏል።

የምግብ መጠጥና ፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከበቆሎና ከስንዴ ዱቄት በአዲስ መልክ ተቀላቅሎ እንዲመረት የተደረገው ዳቦ በሙከራ ተረጋግጦ እንደተጠናቀቀና ዳቦው ለሥርጭት ሊውል መሆኑን አዲስ ማለዳ ከወራት በፊት መዘገቧ የሚታወስ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 182 ሚያዝያ 22 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here