“በትግራይ የትጥቅ ትግል ዝግጅት መኖሩ የአደባባይ ሚስጢር ነው”

0
638

አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) የትግራይ ዴሞክራሲያዊ ትብብር (ትዴት) ሊቀ መንበር ናቸው። የተወለዱት በትግራይ አድዋ ሲሆን፣ አንደኛና ኹለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እዛው አድዋ ተከታትለው ከጨረሱ በኋላ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት ማጥናት ጀምረው ነበር።
ኋላቀርነት እና መጥፎ ስርዓት ያመጣው የብሔረሰቦች እኩል አለመሆን አረጋዊን የከፍተኛ ትምህርታቸውን አቋርጠው ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት)‘ን በ1967 ከጥቂት ጓዶቻቸው ጋር ለመመስረትና ትግል ለመጀመር ገፊ ምክንያቶች እንደሆናቸው ይናገራሉ። “ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ እንድትኖር ብለን ነው ትግል የጀመርነው” የሚሉት አረጋዊ

ሕወሓት ውስጥ ተጽዕኖ ፈጣሪ ጽንፈኛና እስከ መገንጠል የሚደርስ አቋም የያዙት ቡድኖች ጠንክረው በመውጣታቸው እሳቸውን ጨምሮ መካከለኛ አቋም የያዙትን ከድርጅቱ ተገፍተው እንዲወጡ እንዳደረጓቸው ይናገራሉ።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሕዝብ ትግል በኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጠረው ለውጥ ከስደት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው ትግላቸውን ቀጥለውበታል።
ባለትዳርና የኹለት ልጆች አባት የሆኑት አረጋዊ በስደት ቆይታቸው የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በፖለቲካ ሳይንስ የሠሩ ሲሆን ፣ጥናታቸውንም ሕወሓት የአገር መሪነቱን እስከጨበጠ ድረስ የነበረውን ታሪክ የሚተነትን ነው። የአዲስ ማለዳው ታምራት አስታጥቄ ከአረጋዊ በርሔ ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል።

አዲስ ማለዳ፡ ዛሬ የአድዋ በዐል ነው። የአድዋ ድል ለእርሶ ምንድን ነው?
አረጋዊ በርሔ(ዶ/ር)፡ የአድዋ ድል በዐል ትልቅ እንድምታ ያለው ነው። በዓለም ደረጃ የሚታወቅ ድል ነው። አውሮፓውያን አፍሪካን ለመከፋፈል ያቀዱለት፤ ዕቅዱን በግንባር ቀደምትነት የተቃወመና ውድቅ ያደረገ ትግል ነው።

[አውሮፓውያን] በርሊን ላይ በ1884 (እ.አ.አ) አፍሪካን ለመቀራመት በተስማሙት መሠረት አገራችንን፣ መሬታችንን ለራሳቸው ጥቅም ለማዋል ነበር የመጡት። ነገር ግን ኢትዮጵያውያን ከጥንት ጀምሮ ስርዓተ መንግሥት መሥርተው የነበሩና አገር ማለት የገባቸው ሰዎች እንደሆኑ አላወቁም ነበር፤ ተበታትኖ በኋላቀርነት የሚኖር ሕዝብ አድርገው ነበር የሚቆጥሩት። የኢትዮጵያ ሕዝብ አገራዊ ስሜቱ፣ እምነቱና ወኔው ቀስቅሶት ተደራጅቶ በአፄ ምኒሊክ መሪነት ትግሉን አካሒዶ ለአገሩ ሲል መስዋዕትነት የከፈለበት ወቅት ነው።

ስለዚህ አድዋ ለእኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በቅኝ ግዛት ይማቅቁ ለነበሩ አፍሪካውያን ትልቅ ትርጉም ያለው አብነታዊ ድል ነው። ከአፍሪካም አልፎ በመላው ዓለም ጭቆና ላስመረራቸው ሕዝቦች የአድዋ ድል ሞራላቸው እንዲነሳ አድርጓል።

አሁን ባለንበት ወቅት የአድዋ ድልን የራስ ብቻ አድርጎ የመቁጠር አዝማሚያ በትግራይ አካባቢ እየተስተዋለ እንደሆነ ይነገራል። እዚህ ላይ ምን ይላሉ?
እንደምታውቀው አድዋ ትግራይ ውስጥ ነው ያለው; [ስለዚህ] የትግራይ አርበኞች እንደሌሎቹ ለምሳሌ እንደ ጎጃም፣ ሸዋ፣ ወሎ፣ በጌምድር፣ ሲዳማ፣ ኦሮሚያ አርበኞች የታገሉ ሰዎች ናቸው። አርበኝነቱ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን የሚሰጥ ነው።

ከዛም በላይ ምናልባት ጦርነቱ ትግራይ ውስጥ በመካሔዱ አርበኞች ብቻ ሳይሆኑ መሬቱ፣ ዕፅዋቱ፣ አራዊቱ፣ እንስሳቱ ሁሉ ታግለዋል። መጫን፣ መቁረጥ፣ ማቃጣል፣ ወዘተ. ተደርጓል። ይሔ ታዲያ ተጨማሪ ስሜት፣ ተጨማሪ አስተዋጽኦ ሊፈጥር ይችላል። ኩራት የሚሰማቸው ሰዎች ፈጥሮም ሊሆን ይችላል። ይሁንና ሁሉም ኢትዮጵያዊ ተሰውቷል።

በአፄ ምኒሊክ መሪነት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የታገለበት ድል ነው። የታሪክ ሽሚያ አንዳንድ ጊዜ ይፈጠራል፤ ሀቁ ግን አይለወጥም። ስለዚህ ሀቁ ሁሉም ኢትዮጵያዊ አገሩን ለባዕዳን አሳልፌ አልሰጥም በሚል የታገለበት የፀረ ቅኝ ግዛት ድል ነው።

በአሁኑ ወቅት የትግራይ ብሔርተኝነት ጣሪያ ነክቷል ይባላል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ተቃውሞን የመሸከም ወይም ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን መስማት የማይቻልበት ደረጃ ደርሷል የሚል ትችት ይሰማል። ፓርቲያችሁ መሬት ላይ ወርዶ ከሚያደርገው እንቅስቃሴ አንጻር ይህንን ትችት እንዴት ያዩታል?
ትክክል ነው! ወደ [ብሔርተኝነቱ] ጣሪያ ሊያስነኩት የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። በመሰረቱ የብሔርተኝነት ዋና ተዋናይ ልኂቁ ነው። ሌላው ያልፍልኛል፤ ኑሮዬ ይሻሻላል ብሎ የሚከተል ነው። ስለዚህ አሁን ያሉት ልኂቃን በብሔርተኝነት ዙሪያ ፅንፈኛ አመለካከቶች የሚያራምዱ አሉ፤ ድሮም ነበሩ።

አሁን ያሉትን ፅንፈኛ [ብሔርተኝነት] አቀንቃኞች ሕዋሓት/ኢሕአዴግ የበላይነት ይዞ በሚመራበት ጊዜ የተፈጠሩ ናቸው። እነዚህ ኃይሎች በኢትዮጵያ ትግል ተገፍተው ጥግ እየያዙ ነው፤ ጥግ ይዘው ያንን ፅንፈኛ ብሔርተኝነት ስሜት መቀስቀስ ወደ ሥልጣን ለመመለስ ወይም ሥልጣንን ተንተርሶ የተገኘውን ጥቅም ለማስቀጠል እየተጠቀሙበት ነው። ይሔ ነው ዋናው ምስጢር እንጂ በእውነት ለትግራይ ሕዝብ አስበው አይደለም።

[የትግራይ ሕዝብ] አለፈለት ብለው የሚያወሩ አሉ፤ ተጨባጭ ሀቁን መሬት ላይ ወርደው ቢያዩ እንዳላለፈለት ይረዳሉ። 27 በመቶ የትግራይ ሕዝብ ከድኅነት ወለል በታች እንደሚኖር፣ አብዛኛው የገጠር ሕዝብ ደግሞ በምግብ ለሥራ ታቅፎ ነው ያለው። በመሆኑም የትግራይ ሕዝብ በጣም ችግር ውስጥ ነው ያለው። ከዚህ ችግሩ እንዳይወጣ ደግሞ እነዚህን ሰዎች ገፍትሮ፣ እሱ የሚፈልገውን ስርዓት እንዳይመሰርት አፍነው ይዘውታል። መዋቅሩን ለማፈኛነት እየተጠቀሙበት ነው።

ወደ ዋናው ነጥብ ስመለስ ፅንፈኛው አመለካከታቸው በሰሜን ሻአቢያ መጣብህ፣ በምዕራብ አማራ መጣብህ፣ በምሥራቅ አፋር ተነሳብህ እያሉ እያስፈራሩ ሰውን የጦርነት ሥነ ልቦና እንዲያድርበት፣ ለጦርነት እንዲዘጋጅ እያደረጉት ነው። ይህንን ሁላችንም ልናውቅ ይገባል።

በትግራይ ክልል ለትጥቅ ትግል ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ እንደሆነ በሰፊው እየተነገረ ይገኛል፤ አንዳንድ መገናኛ ብዙኀንም ዘግበውታል። በዚህ ጉዳይ ዙሪያ እርሶ የሚያውቁትን ቢነግሩን?
ትክክል ነው! በአማራ ቴሌቪዥን ፉከራዎች አይተናል። ትግራይን በአንድ ጊዜ እንይዛታለን ብለው ታጥቀው ታይተዋል። በትግራይ ክልል ደግሞ በተመሳሳይ ማንም ይምጣ ማንም፥ እኛ ምንም መሬት አሳልፈን አንሰጥም እንዋጋለን የሚል ድምፅም ሰምተናል።

በትግራይ የትጥቅ ትግል ዝግጅት መኖሩ የአደባባይ ሚስጢር ነው። ምስጢሩ ግን ሰዉን እነዚህ ገዢ መደቦች በዚህ ሥነ ልቦና ሰልበው ሌላ ጥያቄ እንዳያነሳ፣ ወሬው፣ ሐሳቡ፣ ጥያቄው፣ ዕለታዊው ጉዳዩ ስለ ጦርነት እንዲሆን አድርገውታል። እነሱ ስለሚያደርሱበት ጭቆና እንዲያነሳ የሚያደርግ ስልት ነው።

በትግራይ ብቻ ያለው ሳይሆን በሁሉም አቅጣጫ ያሉት ችግሮች እኛ ብቻ ሳንሆን ጋዜጣኞችም የማጋለጥ ኃላፊነት አለባችሁ።

በተደጋጋሚ የትግራይ ሕዝብ በሕወሓት አገዛዝ ውስጥ ነው ያለው ይባላል። በርግጥ በአገዛዝ ሥር ከሆነ ይሔ ነው የሚባል ሕዝባዊ የተቃውሞ እንቅስቃሴ ሲያደርግ ለምን አይታይም ወይም አይሰማም?
እናንተ ስላላያችሁት ነው እንጂ፣ ትግራይ ውስጥ ብዙ ቦታዎች የመነሳሳት ሙከራዎች ተደርገዋል። በአንድ በተሰባሰበ ሁኔታ ሳይሆን በተናጠል ብዙ ትግሎች በየወቅቱ ተደርገዋል። ለምሳሌ በነበለት፣ በአፅቢ፣ በአቢይአዲ፣ በእግሬ ሓሪባ፣ በመቀሌ አካባቢ ወዘተ. እነዚህ በተናጠል የተነሱት ተቃውሞዎች ክፉኛ ተመተዋል። አሁን ፀጥ፣ ረጭ እንዲሉ ተደርገዋል። አንቀሳቃሾቹ ታፍነው እየተወሰዱ ተገድለዋል፤ እንዲሰደዱ ተደርጓል። እንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ለረጅም ጊዜ ተደርጓል።

የሕወሓት የመጨረሻ የመጨቆኛ መሣሪያ የተጠናከረበት ቢኖር ትግራይ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥም ምን ዓይነት ሁኔታ እንደነበር ታውቃላችሁ፤ ከዛ የባሰ ሁኔታ ያለው ትግራይ ውስጥ ነው። በትግራይ ውስጥ የጭቆና አፈናው በጣም የባሰ ስለሆነ በዛው ምክንያት ሕዝባዊ ተቃውሞ ጎልቶ ሊወጣ አልቻለም።

የትግራይ ክልልና የፌደራል መንግሥቱን ግንኙነት እንዴት ይገልጹታል?
ያለው ጥሩ ግንኙነት አይደለም። ለውጡ በመላው ኢትዮጵያ እየተካሔደ ነው። በመላው ኢትዮጵያ ድሮ የነበሩ አመራር ተለውጠው አዲስ ከለውጡ ጋር የሚሔድ አመራር ነው ያለው፤ ትግራይ ውስጥ ግን የድሮ አመራር ነው ያለው፤ አልተለወጠም።

እነዶ/ር ደብረፂዮን የተሻለ አመላካከት አላቸው፤ ሆኖም ግን እነሱም ቢሆን በድሮው አመራር ክብ ውስጥ ነው ያሉት። ስለዚህ በአጠቃላይ ካየነው ለኢትዮጵያ የመጣው ለውጥ ትግራይ ውስጥ ገና አልገባም፣ አልመጣም።

የዘንድሮው 44ኛ ዓመት የሕወሓት ምስረታ ሲከበር ከድርጅቱ የተባረሩ ሰዎች ተጠርተው የበዐሉ ተካፋይ ሆነዋል። እርሶዎ ለምን አልተሳተፉም? የእናንተስ አከባበር በትግራይ ከተከበረው ጋር በምን ይለያል?
እኛ አልተጋበዝንም፤ ለምን እንዳልተጋበዝን ግን ገና እያጣራን ነው። በዐሉን ስለማክበር በተመለከተ በተለያዩ ቦታዎች ዝግጅ|ቶች ነበሩ። እኛም በሚመስለን መልኩ አዘጋጅተን አክብረናል።

ምንም እንኳን ሕዝቡ ታግሎ ደርግን ለመጣል ትልቅ አስተዋጽኦ ቢያደርግም፥ መጀመሪያ የታገለለት ዓላማ የራስን ዕድል በራስ የመወሰን፣ ሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መከበርን ግን አላገኘም። [ሕዝቡ] እንዲሁ ታገለ እንጂ ድል አልተጎናጸፈም። ስለዚህ ለእኛ ትግሉ ቀጣይ ነው።

እኛ በዚህ ዓመት ዕለቱን አስበን ስንውል፥ ትግል ላይ መሆናችንን እንዲሁም ትግሉን በአዲስ መልክ መቀጠል እንዳለበት ለማስታወስ ነው። እነሱ [ሕወሓት] ግን ትግሉ በድል አጠናቀናል፤ ሥልጣን ይዘናል ብለው ተኩራርተዋል። ነገር ግን ምንም ያመጡት ለውጥ የለም።

በደርግ የነበረው የጭቆና አገዛዝ በሕወሓት/ኢሕአዴግ ተመሳሳይ ነው። የተወሰነ ሰው ከላይ ቁጭ ብሎ መላው ኢትዮጵያን በጨቆና የያዘበትና የድኅነት አረንቋ ውስጥ የከተተበት ነው ያለው። ስለዚህ እነሱ የግላቸው ድል አድርገው ሊወስዱት ይችላሉ። ነገር ግን ከሕዝቡ ጋር እያገናኙ የሕዝቡ ድል ነው እያሉ ይዋሻሉ። ይህንን ውሸታቸውን ደግሞ እኛ አጋልጠነዋል፤ ወደፊትም በተጠናከረ መንገድ እናጋልጠዋልን።

ሌላው በእኛ በኩል የመጣውን ለውጥ ለማጠናከር እንፈልጋለን። ይሔ ለውጥ የትግራይ ሕዝብ የታገለለትን የመናገር፣ የመጻፍ፣ የመደራጀት መብቶች የሚያከብር ለውጥ ነው። ይሔ እንዲጠናከር ሕዝቡ ስለታገለ አሁንም ከለውጡ ጋር ትግሉን አዛምዶ እንዲቀጥል ለማሳሰብ ነው።

ከትግራይ ሕዝብ ምን ያክል ትኩረት አግኝተናል ትላላችሁ?
ገና ግልፅ አልወጣም እንጂ ውስጥ ውስጡን ትልቅ ድጋፍ አለን። ጎልቶ፣ ገፍቶ እንዲወጣ ግን ትልቅ ሥራ ያስፈልጋል።

በአሁኑ ወቅት በትግራይ ውስጥ በምን ሁኔታ እየተንቀሳቀሳችሁ ነው?
ከአራት ወራት በፊት ትግራይን ገጠር ድረስ ሔደናል። የገጠሩ ሁኔታ በጣም አሳዛኝ ሁኔታ ላይ ነው ያለው። አሁንም በትግራይ በገጠር ውስጥ የሚኖረው አብዛኛው ሕዝብ የሚኖረው በምግብ ለሥራ ነው። 27 ዓመት በሥልጣን ላይ ቁጭ ብለው የገጠሩን ሁኔታ ከነጭራሹ ረስተውታል። ሕዝቡ በችግር ላይ ነው ያለው፤ ምንም የተለወጠ ነገር የለም። ልማት እናደርጋለን እያሉ ድርጅት ያቋቁማሉ ነገር ግን ገንዘብ ለማሰባሰብ ቀጣይነት የሌለው ትንሽ ነገር ያሳያሉ። ትኩረታቸው ኪሳቸውን ለመሙላት ስለሆነ የተጀመሩትንም ፈራርሰው ነው ያገኘናቸው።

ከውጪ አገር እንደመጣችሁ ትግራይ መሔዳችሁ ይታወቃል። በአሁኑ ወቅት ትግራይ ላይ ምን እያደረጋችሁ ነው?
አሁንም ተጠናክረን ለመሔድ ዝግጅት ላይ ነን።

በነፃነት የመንቀሳቀስ ሁኔታ ይኖራል ብላችሁ ታስባላችሁ?
በርግጥ ሁኔታው እዛ [ትግራይ] አፋኝ [ሕወሓት] እንደሆነ በደንብ አድርገን እናውቃለን። እንቅፋትም ሊኖር እንደሚችል በደንብ አድርገን እናውቃለን፤ እንቅፋት ፈርተን ግን ወደኋላ የምንልበት ምክንያት የለም። የተከፈለው መስዕዋትነት ይከፈል፥ ሔደን መንቀሳቀስና ሕዝባችንን ማደራጀት፣ ሕዝባችንን የራሱ ዕድል በራሱ ወሳኝ የማድረጉ ቁርጠኝነት ስላለን ምንም የሚያደርገን ነገር የለም።

እርሶዎ የሚመሩት ትዴት በመሠረታዊነት ከሕወሓት የሚለየው በምንድን ነው?
ትልቅ ልዩነት አለን። አንዱ ልዩነት እነሱ የሚያራምዱት አብዮታዊ ዴሞክራሲ የሚባል ፍልስፍና ነው። አብዮታዊ ዴሞክራሲ ስንተነትነው አብዮታዊም ዴሞክራሲያዊም አይደለም። ፍልስፍናውን የሚጠቀምበት [ሕወሓት] ለማዕከላዊ ዴሞክራሲያዊነት ነው። ይህም ሁሉንም ነገር ማለትም ፖለቲካውን፣ ኢኮኖሚውን ሌላውንም እንቅስቃሴ አመራሩ በማዕከል ተቆጣጥሮ ሕዝቡን ችግር ውስጥ የሚከትበት አሠራር ነው የሚከተሉት፤ ትግራይን አንዱ ወደኋላ ያስቀረው ይሔ ፖሊሲ ነው።

እኛ ሶሻል ዴሞክራሲያዊ የሆነ አመለካከት አለን። መንግሥትም ከሆንን የግል ባለሀብቱ ሊገባበት የሚከብደው ሴክተር/ክፍል እንጂ መንግሥት ሁሉንም እንዲቆጣጠር አናደርግም።

የግል ኢንቨስተሮች ሊንቀሳቀሱ አልቻሉም። የትግራይ ባለሀብቶች ወደመሃል አገርና ደቡብ እየመጡ ነው መዋዕለ ነዋያቸውን የሚያፈሱት፤ ይህንን እንቃወማለን።
ከአንድ ማዕከል የሚወጣ ዴሞክራሲ እንደማይሠራ እንገነዘባለን። ዴሞክራሲ ከታች ነው እየተገነባ መውጣት ያለበት፤ ሰዎች በነፃነት መፃፍ፣ መናገር መደራጀት አለባቸው። እነሱ ይህንን አያደርጉም። ይሔ ትልቁ ልዩነታችን ነው።

ሕዝባዊ መሠረቶቻችሁ ወይም አባሎቻችሁ እነማን ናቸው?
በዋናነት ትግራይ ውስጥ ያሉ አባሎች አሉን። ይሁንና እስካሁን ድረስ በይፉ ወጥተው መንቀሳቀስ ስላልቻሉ በሚስጥር ነው እየተንቀሳቀሱ ያሉት። በተጨማሪም ውጪ አገራት፣ መሃል አገርና ደቡብም ውስጥ ደጋፊዎችን አሉ። ጊዜ የወሰደብን እነሱን እያደራጀንና እያጠናከርን በመሆኑ ነው።

ከምትከተሉት ፍልስፍና ጋር ተመሳሳይ ከሆኑትና ዜግነት ከሚያራምዱ የፖለቲካ ድርጅቶች ጋር አብሮ የመሥራት ሐሳብ አላችሁ?
ሐሳቡ ብቻ ሳይሆን፥ አብሮ የመሥራት እንቅስቃሴው ድሮም ነበር፤ አሁንም አለ። ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለማምጣት ብዙ ትግል ተደርጓል። ብዙ ኅብረቶች ተደርገዋል፥ በእነዚህ ኅብረቶች ውስጥ ተሳትፈናል።

በመሠረቱ ዓላማችን ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን ፈጥሮ፤ የብሔሮች እኩልነት እንዲኖር፣ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አንድነት እንደ ስልት ይዘን እስካሁን እየታገልን ነው። በመሆኑም ከሁሉም ፓርቲዎች ጋር አብረን በመሥራት በሶሻል ዴሞክራሲ የምትመራ ኢትዮጵያን ለመገንባት እየታገልን ነው።

የፓርቲዎችን ውይይት በተመለከተ ሒደቱ አዝጋሚ ከመሆኑም በላይ የተሳታፊዎች ብዛትና ጥራትም ይተቻል። አሁን የተጀመረውን ለውጥ ወደ ላቀ ደረጃ ከመውሰድ ይልቅ ወደ ኋላ እንዳይመልሰው አንዳንዶች ስጋታቸውን ይገልፃሉ። እርስዎ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
በርግጥ የሒደቱ አዝጋሚነት ግልጽ ነው፤ ፈጣን አይደለም። ፈጣን ያልሆነበት አንደኛው ምክንያት የድርጅቶች መብዛት ነው። ሁሉም መሳተፍ፣ መናገር፣ አጀንዳ እንዲያዝለት ይፈልጋል። እንደብዛቱ ልዩነቱም እንዲሁ እየበዛ ሔዷል። ይህንን ለመቅረፍ ጥረት እየተደረገ ነው።

በተጨባጭ ምን ተደርጓል?
በተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚመራ የሥነ ስርዓትና ግንኙነት ቃልኪዳን ሰነድ ተዘጋጅቷል። በቅርቡም የመፈራረም ሥነ ስርዓት ይደረጋል።
ከዚህ በላቀ ግን የድርጅቶቹ ብዛት ምክንያት አለው። የነበሩበት የአፈና ስርዓቶች ሰዎች እንዳይጠያየቁ፣ እንዳይወያዩ፣ እንዳይተማመኑ አድርጎት አልፎዋል። ሕዝቡም በዛው ልክ ተበታትኖ ነው ያለው፤ ተሰብስበው ሐሳባቸውን መግለፅ አይችሉም ነበር።

ስለዚህ በነፃነት የሐሳብ ማንሸራሸር በመጀመሩ፥ ጠንካራ ሐሳቦች ጎልተው እየወጡ፣ ሕዝቡም በዚህ ዙሪያ እየተሰበሰበ ይመራበታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
በውይይቱ የሚነሱ የሐሳብ ጥራት ጉድለቶችንስ በተመለከተስ?
አሁን ሰው ሐሳቡን በነፃነት ለመግለፅ የጀመረበት ጊዜ ላይ ነን። ስለዚህ ሁሉም ድርጅቶች ዋና ጉዳዬ ነው የሚሉትን ሐሳብ መድረክ ላይ ሲያወጡና ውይይት ከተደረገባቸው፣ ትችት ከተደረገባቸው ትልቁንና ትንሹን ሐሳብ ለመለየት ዕድል ይፈጥራሉ። በዚህ ሒደት ስንሔድ ትላልቆቹ ወይም ወሳኝ የሚባሉት ጉዳዮች ነጥረው እንደሚወጡ እርግጠኛ ነኝ።

የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባል ሆነው መሾሞት ይታወቃል። ኮሚሽኑ ምን ምን ሥራ እየሰራ ነው? እርሶዎ በግልዎት ምን አበርክቶ ይኖሮታል?
እኔ እንኳን ይህንን ሹመት አልለውም። ይሔ ‘ሲሾም ያልበላ፥ ሲሻር ይቆጨዋል’ ዓይነት ሹመት አይደለም። ስትሾምም የሚቆጭህ ነገር አለበት ለማለት ነው፥ ምክንያቱም የገባንበት ችግር ውስብስብ ነው።

በኢትዮጵያ ውስጥ ቢያንስ ባለፉት 27 ዓመት ውስጥ የተለያዩ የድንበር ግጭቶች ነበሩ፤ አሉም። ምክንያቶቹም በግጦሽ፣ በውሃ፣ በበጀት ወዘተ. ናቸው። ይሔ የድንበር ጥያቄ ውስብስብ ጉዳይ ነው።

አሁን የኮሚሽኑ መዋቅር ሥራ እየተሠራ ነው። በቅርቡ ሥራውን ይጀምራል። ይሔ ለዓመታት ተደራርቦ የመጣ ችግር እንዴት አድርገን ነው የምንፈታው በሚል የክልል ወሰኖች በመጀመሪያ በሕግ ዙሪያ፣ በአካሔድ፣ በወሰኖች አከላለልና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ጥቅል ውይይት የሚካሔድ ይመስለኛል፤ ኃላፊነቱም ከባድ ነው።
ከክልል ወሰን ወይም ድንበር ጋር ተያያዥ የሚነሳው ዋናው የችግሩ መነሻ የፌደራል ሥርዓቱ የተዋቀረበት ቋንቋንና ብሔርን መሠረት ያደረገ አወቃቀር ነው ይባላል።

በእዚህ ላይ የእርሶዎ አቋም ምንድን ነው?
ቋንቋን መሠረት ያደረገ ፌደራላዊ ስርዓት አልቀበልም፤ ከዛ ውጪ መሆን አለበት። ቋንቋን መሠረት ያደረገ ፌደራሊዝም በደፈናው አይሠራም ማለት ግን አይደለም። ለምሳሌ ቤልጂየምን ብትወስድ የፈረንሳይና የደች ቋንቋ ተናጋሪዎች ፌደራሊዝም መስርተው በዴሞክራሲያዊ መንገድ እየተመሩ ይኖራሉ።

ታሪክን መለስ ብለን ካየን፥ የኢትዮጵያ ግን ውስብስብ ነው። ኤድዋርድ ሲድ የሚባለው ጸሐፊ እንዳስቀመጠው ‘pure ethnicity is delusion’ ይኼ ምን ለማለት ነው ንጹሕ ብሔረሰብ አለ የሚል ካለ ወደ እብደት የቀረበ ነው እንደማለት ነው።

ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ካየህ እኔ ንጹህ አማራ ነኝ፣ ንፁህ ትግሬ ነኝ፣ ንፁህ ኦሮሞ ነኝ የሚል የለም። ሁሉም የተሳሰረ ስለሆነ ሌሎች ጉዳዮችን ከግምት በማስገባት የምታዋቅረው ፌደራሊዝም ነው ሊሠራ የሚችለው፣ የሚል እምነት አለኝ። መድረኩም ላይ በዚህ መልክ ነው የምከራከረው።

ከሕወሓት ምሥረታ ከጀመርን የእርሶዎ የፖለተካ ተሳትፎ 44 ዓመታትን አስቆጥሯል። መቼ ነው ጡረታ የሚወጡት? ወጣቶችስ ወደፊት ማምጣት ላይስ ምን እያደረጉ ነው ያለው?
እኔን በሐሳብ ጎልብተው የሚበልጡኝ ሰዎች ከመጡ እነሱ ገፍትረው ጡረታ ያስወጡኛል። ስለዚህ ጡረታ የምወጣው በሐሳብ ስገፈተር እንጂ ዕድሜ ቆጥሬ ጡረታ አልወጣም። ወጣት ይሁን አዛውንት የነጠረ አቅም ይዞ ከመጣ ቦታውን ለመልቀቅ ዝግጁ ነኝ።

በእኛና በወጣቱ ትውልድ መካከል ጥሩ መናበብ አለ። አሁን ያለ ወጣት ትጉህ ነው፤ ለውጥ ይፈልጋል። ለማንበብም፣ ለማወቅም፣ ዝግጁ ነው። ከእኛ በብዙ መልክ ይበልጠናል። አንዱ አዎንታዊ የዚህ ትውልድ ገጽታው ዓለም ዐቀፋዊ አመለካከቱ ነው። ዕይታው ጠባብ አይደለም፤ ሰፋ ያለ ግንዛቤ ያለው ወጣት ነው ያለው። ያንን መልክ አሲዞ፣ ጥናት አድርጎ ከገፋበት የእኛም እገዛ አካሔዱ ጥሩ እንዲሆን፣ እንዲፋጠን ለማድረግ አስተዋጽኦ ማድረግ ይጠበቅበታል።

ማኅበረሰባችን ለሕዝብ ነፃ ሐሳብ ዝውውር የሚፈቅድ አልነበረም። እኛ አስተዋጽኦ ካለን ተመክሮ አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን፣ ተመክሮዎቻችንን ማስተላለፍ፤ እንጂ እኔ ራሴ ለመቀጠል ፍላጎቱም፣ ጉልበቱም የለኝም። ከዛ በተረፈ ዕድሉ አሁን የወጣቱ ነው። ብዙ ርቆ ሔዷል፤ የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር አዛምዶና ካለው አመለካከት ጋር አዋህዶ (‘ሲንተሳይዝ’) አድርጎ ጥሩ ሥራ ሊሠራ ይችላል ብዬ አምናለሁ።

ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here