ውጥንቅጡ የወጣው የግብር አሰባሰብ ስርዓት

0
535

ማስረሻ ከተማ ይባላል ለዓመታት የወንዶች ፀጉር ቤት ከፍቶ በሥሩም ኹለት ሠራተኞችን ቀጥሮ ያስተዳደር እና ኑሮውን ይመራ ነበር ። ለብቻው ቤት ተከራይቶ ለሚኖረው ማስረሻ ታዲያ ከፀጉር ቤቱ የሚገኘው ገቢ የዕለት ጉርሱን ሽፍኖ ነገን የሚያቅድበት አልነበረም።

ከአነስተኛ እና ጥቃቅን 5 ሽሕ ብር ብድር ወስዶ፣ ከወዳጅ ዘመድ በተደረገለት ድጋፍ የከፈተው ፀጉር ቤት ታዲያ ለማስረሻ እንዳሰበው ድኅነትን ማምለጫ መንገድ ካለመሆኑም በላይ 2009 መገባደጃው ላይ ማስረሻ ትልቅ ችግር ጋር ይጋፈጥ ዘንድ ግድ ሆነበት።

በጊዜው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የግብር አሰባሰቡን ለማሳደግና ሕጋዊ መንገድን ያልተከተሉ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለመቆጣጠር በሚል በጀመረው የቀን ገቢ ግብር ግምት አሠራር ምክንያት ማስረሻን በቀን 4 መቶ ብር ገቢ አለህ ሲል ይገምትበታል። ይህ ማለት በወር 12 ሽሕ ብር ገቢ ይኖረዋ ተብሎ በመንግሥት ደረጃ እንደሚታሰብና ይህም ታሳቢ ተደርጎ ግብር እንደሚከፍል ይነገረዋል።

በዚህ ጊዜ ማስረሻ ሥራውን ትቶ በየቀኑ አቤቱታውን ሊሰማኝ ይችላል ብሎ ወደ አሰበበት ቦታ ሁሉ ተመላለሰ ነገር ግን ፍሬ ማፍራት አልቻለም። “በኃይል መቆራረጥ ምክንያት በሳምንት ውስጥ የማልሰራባቸው ቀናት ይበዛሉ፤ ይሄን እንኳን ለገቢዎች እና ጉምሩክ ባለሥልጣን ኃላፊዎች ብነግራቸውም ሊረዱኝ ፈቃደኛ አልነበሩም “ ይላል ያሳለፈውን የጭንቅ ጊዜ ልብ በሚሰብር ትካዜ እያስታወሰ።

ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የተላለፈበት ውሳኔም እንደማይለወጥ ሲገባው ፀጉር ቤቱን ለመዝጋትና ንግድ ፍቃዱን ለመመለስ ያስባል ። በዚህ ጊዜም ነገሮች አልጋ በአልጋ አልሆኑም ንግድ ፍቃድ መመለስ የሚችለው የተተመነበትን ግብር ከፍሎ እንደሆነ ሲነገረው “መጀመሪያ ላይ አእምሮዬንም የሳትኩኝ መስሎኝ ነበር” ይላል ማስረሻ። ከቀናት ቆይታ የፀጉር ቤት ዕቃዎችን በቅናሽ ዋጋ ሸጦ ከአካባቢው መሰወርን መረጠ፤ እንዳሰበውም አደረገ።

ነገር ግን አሁንም ለመኖር መሥራት ስለሚያስፈልገው ሥራ ፍለጋን የሙጥኝ ቢልም ወደ ንግድ መሰማራት የማይታሰብ እና ተስፋ አስቆራጭ ስለሆነበት በፀጉር ቤት ደንበኛው በኩል ሥራ ያገኛል፤ “በደህና ጊዜ ያወጣሁት መንጃ ፍቃድ ስልነበረኝ ይሄው አሁን የግለሰብ ተቀጣሪ ሹፌር ሆንኩኝ ራሴን በራሴ አስተዳድር እንዳልነበር” ይላል በቁጭት። ይህ ሁሉ ሲሆን ማስረሻ መንግሥት የጣለበትን ግብር አልከፈለም አሁንም ድረስ ንግድ ፍቃዱ በእጁ ነው። “አንድ ቀን ፍትህ ይመጣል” የሚል ፅኑ ተስፋ አለው። “ያን ጊዜ እኔም ወደ ነበርኩበት ራሴን በራሴ ወደ ማስተዳድርበት የንግድ ሥራየ እመለሳለሁ” ይላል።

ሌላኛዋ ባለታሪክ ደግሞ ተወዳጅ አማረ ትባላለች የሕፃናት አልባሳትን ትሸጥበት ከነበረው የ22 አካባቢ በሥም እየጠቀሰች ከጠራቻቸው ባለሱቆች በሙሉ ሊባል በሚችል ደረጃ በተጣለባቸው ፍትሐዊ ያልሆነ ግብር ለስደት እንደተዳረጉ ትናገራለች። “መንግሥት የተመነብኝን ከፍያለሁ፤ ነገር ግን ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ የምትባል አገር አላውቅም ብዬ ነው ስደትን የመረጥኩት” ትላለች ። በ2009 መጨረሻ አካባቢ ወደ አረብ አገር እንዳቀናች ምትናገረው ተወዳጅ “በአገሬ ሕግን ተከትየ በሠራሁ ይህን ያህል በደል ከደረሰብኝ የማያውቁኝ አረቦች ቢጨቁኑኝ ምንም አይገርምም ብዬ ነው ራሴን አሳምኘ ወደ ስደት ገባሁ” ትላለች ።

ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ከሚያገኙት ገቢ በአግባቡ ግብራቸውን ቢከፍሉ፥ አሁን ላይ በአገር ዐቀፍ ደረጃ የሚታዩትን የመሰረተ ልማት ችግሮች በቀላሉ እንደሚፈቱ የሚታመኑ የላይኛው መደብ ባለሀብቶች ቢኖሩም፤ ከሚጠበቅባቸው ግብር ሩቡን እንኳን እንደማይከፍሉ መረጃዎች ያመላክታሉ። በተደጋጋሚ ድርጅታቸው ኪሳራ እያሳየ እንደሆነ ለመንግሥት እያስረዱ ከምንም ዓይነት የግብር ግዴታ ነፃ የሚሆኑ በሚሊዮን ብር የሚያንቀሳቅሱ ድርጅቶች አሉ።

ባስ ሲል ደግሞ ሀሰተኛ ደረሰኝ በማቅረብ የከፈሉትን ግብር ከመንግሥት ተመላሽ የሚጠይቁ እና ከግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ሠራተኞች ጋር ከፍተኛ የጥቅም ትስስር በመፍጠር ከደረጃ በታች እንዲከፍሉ የሚደረግበት አግባብ እንዳለ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

ለማስታረቅ በሚከብድ መልኩ የተራራቀው እና ሀብታሞችን የበለጠ ሀብታም የሚያደርገው፣ ዝቅተኛውን ግብር ከፋይ ኅብረተሰብ ደግሞ ከተቻለ ባለበት እንዲረግጥ ከባሰ ደግሞ ወደ ታች እንዲያሽቆለቁል የሚያደርገው የግብር አወሳሰን እንዴት ይታያል?

ገቢዎች ሚኒስቴር
በሰባት ዓመት አንድ ጊዜ ትልቅ እንቅስቃሴ የሚደረግበት የቀን ገቢ ግምት ዋነኛው አላማው ከንግድ መረቡ ውጭ የሆኑ ሕገ ወጥ ንግዶችንና ነጋዴዎችን ለመቆጣጠር የሚተገበር ሲሆን፤ እግረ መንገድ ግን ግብር ሰብሳቢው ከደረጃ በታች ግብር እየከፈሉ ነው የሚላቸው ድርጅቶች ላይ ተመን ለማውጣት እንደሆነ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይገልፃል።

በዚህ ሒደት ላይ ታዲያ የተከሰቱ የአሠራር ሕፀፆች መኖራቸውን ገቢዎች ሚኒስቴር ይገልፃል። በጊዜው በርካታ ቅሬታዎች የተስተናገዱበትና ለቁጥር የሚያዳግቱ እሮሮዎች የተሰሙበት ነበር። ከዚህ በመነሳት በጊዜው የነበረው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን አጣሪ ግበረ ኃይሎችን አቋቁሞ ለበርካታ ቅሬታዎች መፍትሔ ሰጥቻለሁ ያለበት ሁኔታ እንደነበር ይታወሳል። ይሁን እንጂ ከዓመት በላይ መፍትሔ ሳይበጅላቸው ለነበሩት ቅሬታዎች በቅርቡ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ በ2009 በነበረው የገቢ ግምት ሒደት ቅሬታ ለነበረባቸው ነጋዴዎች የዕዳ ስረዛ ማድረጋቸው የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ከፍተኛ ግብር ከፋይ ሆነው በአግባቡ እየከፈሉ ስላልሆኑት ድርጅቶች ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አሁን ላይ ጥብቅ ክትትል እያደረገ ሲሆን ወደ ኋላ አምስት ዓመታት ድረስ ኦዲት እየተደረጉ እንደሆኑና የኦዲት ክፍተት የተገኘባቸው ድርጅቶች እና ግለሰቦች ሕጋዊ እርምጃ እየተዋሰደባቸው እንደሆነ የገቢዎች ሚኒስተሯ አዳነች አቤቤ ይገልፃሉ። ነገር ግን እንደብዛታቸው እና እንደውስብስብ መረባቸው አሁንም እየተወሰደ ያለው እርምጃ በቂ ነው ብለው አያምኑም ሚኒስትሯ። ከዚህም ጋር በተያያዘ ባለፉት ስድስት ወራት 98 ሠራተኞችን ከሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ በሥነ ምግባር ጉድለት መባረራቸውን አዳነች ይገልፃሉ።

 

“መንግሥት የተመነብኝን ከፍያለሁ፤ ነገር ግን ከዚህ በኋላ ኢትዮጵያ የምትባል አገር አላውቅም ብዬ ነው ስደትን የመረጥኩት”

 

በድርጅቶችም በኩል 135 ድርጅቶች ከታክስ ስወራ ጋር በተያያዘ ሕጋዊ እርምጃ ሚኒስቴር በመሥሪያ ቤቱ በኩል የተወሰደ ሲሆን 105 ግለሰቦችም በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።

የችግሩ ጥልቀት በምጣኔ ሀብት ዓይን
የተለያዩ አገር በቀልም ሆነ አለም ዐቀፍ ተቋማት መረጃ እንደሚያሳየው፤ በባለፉት አስር ዓመታት ኢትዮጵያ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ዕድገት አስመዝገባለች። ይህ በአንድ በኩል አገሪቷን ገፅታ በመገንባትም ሆነ የምሥራቅ አፍሪካ ትልቅ ኢኮኖሚ እንዲኖራት ትልቅ ሚና ሲጫወት፤ በሌላ በኩል የመንግሥት የታክስ ገቢ ከዕድገቱ ጋር አብሮ ሊጓዝ አልቻለም። ይህ ግን የታክስ ገቢ ጭማሪ አላሳየም ማለት አይደለም።

በርግጥ፤ የመንግሥት ታክስ ገቢ ባለፉት አምስት ዓመታት በሦስት እጥፍ እድገት በማሳየት 250 ቢሊየን ብር ደርሷል። የተሰበሰበው ገቢ ጭማሪ ቢያሳይም፡- ከዕቅዱ አንፃር ያነሰ ነው። ለአብነትም ያህል፤ በባለፈው በጀት ዓመት የተሰበሰበው ከዕቅዱ አንፃር በ12 በመቶ ያነሰ ነው። እንደ ምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ከዚህ በላይ አሳሳቢ የሆነው ነገር ቢኖር የታክሱ ዕድገት አገሪቷ ባለፈው ዐሥርት ዓመታት ካስመዘገበችው ባለኹለት አኀዝ ዕድገት ጋር አለመጣጣሙ ነው። ለዚህም መንግሥት የሰበሰበው ገቢ ለአጠቃላይ ምርት ያለው ንፅፅር አለማደጉ ነው።

ባለፈው በጀት ዓመት የተመዘገበው ታክስ ለአጠቃላይ ምርት ያለው ንፅፅር ከ11 በመቶ በታች ሲሆን ከሰሃራ በታች ካሉ አገራት ካስመዘገቡት በ4 በመቶ ያነሰ ነው። የአገሪቷን ከ40 በመቶ በላይ የሆነውን አጠቃላይ ምርት የሚሸፍኑት መደበኛ ያልሆኑ ንግዶች ቁጥራቸው መጨመሩ ለንፅፅሩ መቀነስ አንዱ ምክንያት ሆኖ ይጠቀሳል። ቁጥሩን ለመጨመር የግብር መንግሥት የተለያዩ እርምጃዎችን ቢወስድም፤ አንዱም ሊሳካ አልቻለም። ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ነጋዴዎችን ያስቆጣው በባለፈው በጀት ዓመት የተተገበረው የቀን ገቢ ግምት አንዱ ነው። መንግሥት ከግምቱ በኋላ በአዲስ አበባ ብቻ ወደ 8 ሺሕ 651 ነጋዴዎች ወደ ሕጋዊ የታክስ ሥርዓት መግባት እንደቻሉ ቢገልፅም፤ የተወሰደው እርምጃ ያመጣው ለውጥ እምብዛም ነው። ለዚህም እርምጃውን ተከትሎ በባለፉት ኹለት ዓመታት የተመዘገበውን የዋና ከተማውን ሆነ የአገሪቷ ገቢ ማየት ቀላል ነው።

በሌላ በኩል መንግሥት በግብር ስርዓቱ ውስጥ የተካተቱ ነጋዴዎች ላይ ብቻ ትኩረት ማድረጉ እንደ ችግር ይነሳል። የግብር ከፋዮች ቁጥር ለባለፉት አምስት ዓመታት ይህ ነው የሚባል ጭማሪ አለማሳየቱ የችግሩ ማሳያ ነው። የገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው፤ የግብር ከፋዮች ቁጥር በባለፉት አምስት ዓመታት 1 ነጥብ 2 ሚሊየን አካባቢ ሲሆን ቁጥሩም ጭማሪ አላሳየም። ይሁን እንጂ፤ የተሰበሰው የግብር መጠን በነዚህ ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ በአማካይ 22 በመቶ ዕድገት አሳይቷል። ይህም፤ መንግሥት የታክስ መሰረቱን ከማስፋት ይልቅ የግብር ስርዓቱ ውስጥ ያሉትን ላይ ማተኮሩን ያመላክታል ሲሉ የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ያነሳሉ። የግብር ማበረታቻዎችን በተገቢው መልኩ መጠቀምን እንደ መፍትሔ ያነሳሉ።

ሌላው የአገሪቱን ኢኮኖሚ በከፍተኛ ደረጃ እየጎዳ ያለው የኮንትሮባንድ ንግድ ለግብር አሰባሰብ እንቅፋቶች አንዱ ነው፡፡ የኮንትሮባንድ ንግድ ከሕጋዊ የንግድ እንቅስቀሴዎችን መንግሥት ማግኘት የሚገባውን ያህል ገቢ እንዳያገኝ በማድረጉ ረገድም የሚያሳርፈው ተፅዕኖ ቀላል እንዳልሆነ ይገለፃል። በባለፉት ስድስት ወራት ብቻ ግማሽ ቢሊየን ብር የሚያወጡ የኮንትሮባንድ ዕቃዎችን የያዘው የገቢዎች ሚኒስቴር ለገቢ መሰብሰብ ትልቅ እንቅፋት እንደሆነበት በተደጋጋሚ ለፓርላማ አባላት መግለፁ ይታወሳል።

በኮንትሮባንድ ግብይት ውስጥ ቫትና ሌሎች የግብር ክፍያ አለመሰላታቸው፣ እንዲሁም ግብር ከፋዮች ገበያን በማስተጓጎል ሕጋዊ ነጋዴዎች ምርቶቻቸውን ሸጠው ለመንግሥት ያስገቡ የነበረውን ገቢ እንዳይጨምር ማድረጉ ሲታይ የኮንትሮባንድ ጠንቀኝነቱ በግልጽ የሳያል ሲሉ ባለሙያዎች ይገልፃሉ፡፡ የፖሊሲ ለውጥ ማድረግ፣ የመንግሥት ተቋማዊ አቅምን ማሳደግ፣ ትይዩ የውጭ ምንዛሬ ገበያውን ማዳከም፣ የመንግሥት አገልግሎቶችን በተቀላጠፈ መልኩ ማቅረብና ሙስናን መቀነስ የግብር አሰባሰብ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እያሳደረ ያለውን የኮንትሮባንድ ንግድን ለመቀነስ ኹነኛ ናቸው ሲሉ የተለያዩ ባለሙያዎች ያነሳሉ።

የንግድ ሒደቱን ማቅለል
በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ይፋ የሆነውና የአንድ ወር አፈፃፀሙን ከቀናት በፊት የገመገመው ቀላል የንግድ ሒደት ከግብ አሰባሰቡ ጋር በሚኖረው መስተጋብር አዳነች አቤቤ ሲናገሩ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ በመጠቀም ግብር የሚከፈልበት ስርዓት እንደሚዘረጋ ለመረዳት ተችሏል።
በዚህም ረገድ አሁን ላይ 25 በመቶ የሚሆነው የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝጋቢዎች በአዲሱ መንገድ ክፍያ እየፈፀሙ እንደሆነ መረጃዎች ያመላክታሉ። በዚህም ምክንያት ቀጥተኛ የግብር ሰብሳቢ ግለሰቦችን ተሳትፎ ስለሚቀንስ ፍትሐዊ ያልሆነ የግብር አዋሳሰን እንደማይኖር ይጠበቃል።

ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here