የኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን አለባት ወይም መሆን የለባትም በሚል የምጣኔ ሀብት ምሁራን የሐሳብ ሙግት እንደሚያደርጉ ይታወቃል። ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር) አንድ አገር የዓለም ዐቀፍ ድርጅት አባል ከመሆኑ በፊት ማሟላት የሚገባውን መስፈርቶች በመንተራስና የኢትየጵያን የምጣኔ ሀብት የዕድገት ደረጃን በመተንተን፥ ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል ብትሆን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ኢኮኖሚ ልትገነባ በፍጹም አትችልም ሲሉ ይሞግታሉ።
አንድ አገር፣ የዓለም ዐቀፍ ኢኮኖሚያዊ ድርጅት አባል ከመሆኑ በፊት፣
1ኛ) ስርዓተ መንግሥቱ የአገሩን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያ አወቃቀር በሚገባ ማወቅ አለበት፤
2ኛ) በምን ዓይነት ንድፈ ሐሳብ ወይም የአሰራር ስልት የኢኮኖሚውን አወቃቀር እንደሚተነትን ቢያንስ ሊከታተልና ሊገባው ለሚችለው የኅብረተሰብ ክፍል ማቅረብ አለበት። ይህም ማለት አገሪቱ የምትገኝበትን የቴክኖሎጂ፣ የሳይንስና የማኅበረሰብ የዕድገት ደረጃ ማሳየት አስፈላጊ ነው።
3ኛ) ለሰፊው ሕዝብ አስተማማኝ የሆነ ዕድገት ከሌለ ለምን በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ የኢኮኖሚ ዕድገት የለም ብሎ መመርመር አለበት። ስለሆነም ለሁለገብ ዕድገት ማነቆ የሆኑ ነገሮችን ደረጃ በደረጃ እየተነተነ ማሰቀመጥ ይኖርበታል።
4ኛ) ለምን የአንድ ዓለም ዐቀፋዊ ድርጅት አባል መሆን እንደሚያስፈልግ ወደ ውጭ በመውጣት ለሕዝቡ ግልጽ ማድረግ አለበት። በምሁሩ ዘንድም ክርክር እንዲደረግ መጋበዝ አለበት። ይህም ማለት አንድን አገር የሚመለከት ትልቅ ፕሮጀክት በተዘጋ ቤት መጠናቀቅ የለበትም።
5ኛ) የዓለምን ኢኮኖሚያዊ አወቃቀር በሚገባ ማወቅ ያስፈልጋል። በተለይም የግሎባል ካፒታሊዝምን ታሪካዊ አመጣጥና የየአገሮችን ጥሬ ሀብት የመቆጣጠር ስልት በሚገባ ማወቅ አስፈላጊ ነው።
6ኛ) እስከዛሬ ከተደረጉት ስምምነቶች ሌሎች አገሮች የቀሰሙትን ልምድና ያገኙትን ጥቅም ግንዛቤ ውስጥ ማስገባት ያስፈልጋል።
7ኛ) “እንደ ኢትዮጵያ ያለች የተዘበራረቀ ኢኮኖሚ ያላት አገር የዚህ ዓይነቱ ድርጅት አባል ብትሆን ምን ጥቅም ታገኛለች?” ብሎ ሰፋ ያለ የንድፈ ሐሳብ፣ የሳይንስና ተጨባጭ ሁኔታዎችን ማጥናት ያስፈልጋል። በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተደገፈ ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ልትቀዳጅ ትችላለች ወይ? ሰፋፊና የሚያማምሩ ከተማዎችን፣ የባቡር ሃዲዶችን ገንብታ ጠቅላላው ሕዝብ ተጠቃሚ ሊሆን ይችላል ወይ? ብሎ ስርዓተ መንግሥቱ ባሉት ተቋማት አማካይነት መገምገምና ጥቅሙንና ጉዳቱን ማመዛዘን ይኖርበታል። ከዚህም ባሻገር ይህ ዓይነቱ ኢኮኖሚያዊ ግኑኝነትና የድርጅቱ አባል መሆን ለኅብረ-ብሔርና ለጠንካራ ኅብረተሰብ መመስረት ሊያገለግል ይችላል ወይ? ወይስ ኅብረተሰቡን የባሰውኑ ሊያዘበራርቀው ይችላል ወይ? ብሎ ጥናት ማካሔድ አስፈላጊ ይመስለኛል።
8ኛ) ከዚህም በላይ በአንድ ኅብረተሰብ ውስጥ የተለያዩ አመለካከቶች ያላቸውና ጥቅምም የሚያገኙና የሚጎዱ እንደመኖራቸው መጠን ወሳኝ አመለካካት ካላቸው የሚቀርቡትን ማደመጥ ያስፈልጋል። ይህ ከመሆኑ በፊት ዝም ብሎ የሚገባ ስምምነት ብዙ የሦስተኛው ዓለም አገሮች ውስጥ እንደምናየው አስቀያሚ ሁኔታ በአገራችንም ሊከሰት ይችላል። ችግሮች ከተከሰቱና ከተደራረቡ በኋላ እነሱን ለማረም በጣም አስቸጋሪ ስለሚሆን አንዳች ስምምነት ላይ ከመደረሱ በፊት በቂ ጥናት ማድረግ ያስፈልጋል።
በግልጽ እንደሚታወቀው በአገራችን ምድር የ‘ኒዎ-ሊበራል’ አመለካከት ስለተስፋፋ የአገራችንን የኢኮኖሚ ሁኔታ በሌላ ዓይነት የንድፈ ሐሳብ መሳሪያ ትንተና ቢሰጥ በቀላሉ ግንዛቤ ውስጥ ሊገባ አይችልም። የ‘ኒዎ-ሊበራል‘ ርዕዮተ ዓለም ደግሞ ስለምርት ግኑኝነት፣ ስለቴክኖሎጂዎች የዕድገት ደረጃ፣ ስለውስጥ ገበያ መኖርና በምን ዓይነትስ ሕግ እንደሚገዛ፣ ስለገንዘብ ሚናና ገንዘብስ ወደ ካፒታል ሊለወጥ ይችላል ወይ? የሚሉትን መሰረታዊ የኢኮኖሚ ፅንሰ ሐሳቦች ግንዛቤ ውስጥ ስለማያስገባ የአገራችንን የኢኮኖሚ አወቃቀር በሌላ የንድፈ ሐሳብ መሳሪያ በሚገባ ለማስረዳት እጅግ አስቸጋሪ ነው። ምክንያቱም ሁላችንም በአንድ ዓይነት አስተሳሰብ ወይም ርዕዮተ-ዓለም ስለሰለጠን ግራ ልንጋባ እንችላለን። ለማንኛውም አጠቃላዩን የኢኮኖሚ ሁኔታ በሦስት መልክ ከፋፍለን ብንመረምረው የአገራችን ኢኮኖሚ በምን ዓይነት የዕድገት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ በቀላሉ መገንዘብ ይቻላል።
1ኛ. የኢንዱስትሪ መስኩን ስንመለከት
አብዛኛው ኢንዱስትሪ ቀላል ኢንዱስትሪ የሚባለው ነው። በዚህ መስክ ውስጥ በብዛት የሚመረቱት ምርቶች ለተወሰነው የኅብረተሰብ ክፍል የሚሆኑ እንደምግብ ነክ ነገሮች፣ ቀዝቃዛና የአልኮል መጠጦች፣ የጨርቃ ጨርቅ ውጤቶችና ጫማ ናቸው። ቀላል የ‘ሜታለርጂ’ና የሲሚንቶ ፋብሪካዎችም እንዳሉ ግልጽ ነው። ይሁንና ግን አገሪቱ ስትራቴጅክ የሚባሉ ለአንድ አገር የኢኮኖሚ ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ የብረታብረት ኢንዱስትሪና የማኑፋክቱር ወይም የማሽን ኢንዱስትሪዎች የላትም። ከዚህም በላይ ኃይልን ሊያመርቱ የሚችሉና ልዩ ልዩ የኤሌክትሮኒክስ አምራች ኢንዱስትሪዎች የላትም። በዚህም ምክንያት የተነሳ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ብሔራዊ ባህርይ ያለው ሳይሆን የተዝረከረከና ለመባዛት ወይም ሊስፋፋ የሚችል አይደለም። በተለይም አንድ አገር የማሽን ኢንዱስትሪ ከሌላት እንደ ባቡር ሃዲድና ባቡር የመሳሰሉትን ለአንድ አገር ዕድገት እጅግ ጠቃሚ የሆኑ ምርቶችን ልታመርት አትችልም። በዚህም ምክንያት የተነሳ በተለያዩ ኢንዱስትሪዎች መካከል የሥራ ክፍፍልና ውስጣዊ ግንኑኝነት የለም።
ኢትዮጵያ የዓለም ንግድ ድርጅት አባል ብትሆን ይህ ዓይነቱ ውስጣዊ ይዘቱ በጣም ደካማ የሆነ የኢንዱስትሪ መስክ ከውጭ በሚመጡ ተመሳሳይ ምርቶች ሊዳከም ይችላል። የምርት ክንውን ከቀዘቀዘ ደግሞ የኢንዱስትሪ ባለቤቶች የተወሰነውን የሠራተኛ ኃይል ለመቀነስ ይገደዳሉ። ይህ በራሱ ደግሞ ከሥራው በተባረረው ሠራተኛና በቤተሰቡ ላይ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና የሥነ-ልቦና ቀውስ ሊደርስበት ይችላል። የሥራ-አጥ አበል በሌለበት እንደኛ ባለ አገር ከሥራው የተባረረው ሠራተኛ ወደ ድኅነት ዓለም መገፍተሩ የማይቀር ጉዳይ ነው።
2ኛ) የእርሻውን መስክ ስንመለከት
ከሰማንያ በመቶ በላይ የሚሆነው ህዝባችን ከእጅ ወደ አፍ በሚመረት የአስተራረስ ዘዴ ላይ የሚመካ ነው። አብዛኛው ገበሬ የመሬቱን ምርታማናት ለማሳደግ የሚያስችሉት ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን አይጠቀምም። የመግዛት ኃይሉ እጅግ ደካማ ከመሆኑ የተነሳ አዳዲስ የማረሻ መሳሪዎችን በመግዛት ሥራውን በማቃለል ከፍተኛ ምርት ሊያገኝ አይችልም።
ስለሆነም የኢትዮጵያ እርሻ ሳይንሳዊ ባህርይ የሌለው ነው ማለት ይቻላል። ወደ ውጭ የሚላከውን ምርት ስንመለከት ደግሞ የውጭ ምንዛሪ ገቢ በጥቂት የእርሻ ምርቶች ላይ የሚመካ ሲሆን፣ የቡና ምርት ስልሳ በመቶው የሚሆነውን ይይዛል።
የአገሪቱ ገበያ ለውጭ የእርሻ ምርት ውጤት ልቅ ከሆነ በከፍተኛ ደረጃ የሚጎዳው ገበሬው ነው። ቀደም ብዬ ለማሳየት እንደሞከርኩት የአውሮፓና የአሜሪካ ገበሬዎች ከፍተኛ የመንግሥት ድጎማ ይደረግላቸዋል። በዚህም ምክንያት የተነሳ ምግብ በአጠቃላይ በየአገሮች ውስጥም ሆነ ወደ ውጭ ሲላክ በጣም ርካሽ ነው። የአገራችን ገበሬ በድጎማ ከሚመረተው የአውሮፓና የአሜሪካ ምርት ጋር ስለማይወዳደር በ90ዎች መጨረሻ ላይ እንዳየነው ገበሬው ከፍተኛ ጉዳት ይደርስበታል። በሌላው ወገን ደግሞ ምግብ-ነክ ወዳልሆኑ እንደ ጫት በመሳሰሉት የዕፅ ተከላ ላይ ሊሰማራ ይችላል። ገሚሱ ደግሞ ወደ ከተማ በመሰደድ በሥራ እጦት ይሰቃያል።
ከዚህ ባሻገር ከውጭ የሚመጡ የእርሻ ምርት ውጤቶችና የተለያዩ የምግብ ዓይነቶች ለጤንነት ጠንቅ የሆኑ ኬሚካሎችንና ሆርሞኖችን ያዘሉ ናቸው። ይህም ማለት ባለፉት 27 ዓመታት ከነፃ ገበያና ንግድ ጋር ተያይዘው የገቡ የምግብ ዓይነቶች ያደረሱት የጤንነት ቀውስ እየተስፋፋና ሰፊውን ሕዝብ እያዳረሰው ሊመጣ ይችላል። ይህም ካለምክንያት አይደለም በተለይም ባለፉት 20 ዓመታት ጀምሮ በአገራችን ምድር የደም ግፊት በሽታ፣ የስኳርና የኩላሊት፣ እንዲሁም የነቀርሳ በሽታ የተስፋፉትና ወጣቱን ሁሉ ሳይቀር ለሞት የዳረጉት።
3ኛ) የአገልግሎት መስኩን ስንመለከት
በጣም የተዝረከረከና ከኢንዱስትሪዎች ጋር የተያያዘ አይደለም። በገበያ ውስጥ የሚሽከረከሩ ምርቶች አብዛኛዎች ከውጭ የሚመጡ ናቸው። ከዚህ ውጭ የአገሪቱን ገበያ የሚቆጣጠረው ኢንፎርማል መስክ እየተባለ የሚጠራው የተሰበጣጠረና እርስ በእርሱ ያልተያያዘ ሰፋ ያለ የኢኮኖሚ መስክ ነው። ስለሆነም ከውጭ የሚመጣው ዕቃና ገበያውን ያጣበበው በከፍተኛ ደረጃ የአገሪቱን የንግድ ሚዛን ያዛባና፣ የፈጠራ ሥራ እንዳይኖር ያገደ ነው።
በአጠቃላይ ሲታይ የአገራችንን ኢኮኖሚ ሁኔታ ስንመለከት ለጠንካራ ማኅበረሰብና ለኅብረ-ብሔር ምስረታ የሚያገለግል አይደለም። በዚህም ምክንያት የተነሳ በሕዝቡ ዘንድ በምሁር እንቅስቃሴ የሚገለጽ ውስጣዊ ግንኑኝነት (Organic Relationship) የለም። የምርት ኃይሎች በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ሰፋ ያለ በሁሉም መልክ የሚገለጽ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ሊዳብር አልቻለም። ይህም ማለት በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በማኅበረሰብ፣ በባሕልና በኢኮሎጂ የነቃ ወይም የአገራችን ሁኔታ አንገብግቦት ይህንን በሥነ ጽሑፍ፣ በድራማና በትዕይንተ ጥበባት የሚገልጽ ምሁራዊ እንቅስቃሴ ፍጹም የለም ማለት ይቻላል። በዚህም የተነሳ አገራችንና ሕዝባችን ከውጭ በሚመጣ ማንኛውም ነገር እየተጠቁ ነው።
ከዚህ በአጭሩ ከተገለጸው ሁኔታ ስንነሳ ኢትዮጵያ የዓለም የንግድ ድርጅት አባል የመሆን ዕድል ቢያጋጥማት በሳይንስና በቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ኢኮኖሚ ልትገነባ በፍጹም አትችልም። እንደሜክሲኮ፣ አርጀንቲናና ብራዚል፣ እንዲሁም በተቀሩት የማዕከለኛውና የላቲን አሜሪካ አገሮች የሚታዩት የኅብረተሰብ መዝረክረክና ቀውሶች በአገራችንም ምድር ሊከሰቱ ይችላሉ። በተለይም የኒዎ-ሊበራል ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተግባራዊ መሆን ከጀመረ ከዛሬ 26 ዓመት ጀምሮ በአገራችን ምድር የተከሰተውን የማኅበራዊና የሥነ-ልቦና ቀውስ ስንመለክት የዓለም ንግድ ድርጅት አባል መሆን ያለውን ሁኔታ ከማባባስ በስተቀር ጤናማ ኅብረተሰብ እንዲመሰረት በፍጹም አያግዝም። እንደምናየው ባለፉት ስድስት ወራት ወደ ውጭ ሊሸሽ ሲል በአጋጣሚዎች የሚያዘው የውጭ አገራት ገንዘቦችና በብዛት ሽጉጦች መያዛቸው የሚያረጋግጠው ልቅ የሆነ ስርዓት የመጨረሻ መጨረሻ የአገርን እሴት የሚበጣጠስና ሰላማዊ ዜጋን ለአደጋ እንደሚያጋልጥ ነው። ስለሆነም ‘ኦሊጋሪኪ’ የሆኑ ኃይሎች በመነሳትና የራሳቸውን የታጠቀ ኃይል በማሰልጠን በሰፊው ሕዝብ ላይ ጦርነት ያውጃሉ። በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ሰርገው በመግባትና አገዛዙን በቁጥጥር ስር በማድረግ ከረጅም ጊዜ አንፃር ፋሺሽታዊ ስርዓትን ሊመሰርቱ ይችላሉ። ይህ ዓይነቱ አገላለጽ ፈጠራ ሳይሆን ዛሬ በብዙ አገሮች የሚታይና ሕዝቦችን ለስደት የዳረገና፣ የነቃውን ምሁር ደግሞ የማያነቃንቅ ነው።
ስለሆነም ቅድሚያ መስጠት የሚኖርብን የአገር ውስጥ ገበያ ሊዳብር የሚችልበትን ሁኔታ ማመቻቸትና ሰፋ ያለ ምሁራዊ ኃይል ብቅ እንዲል አስፈላጊውን የባሕል ለውጥ ማድረግ ነው። በአገራችን ምድር ዛሬ የተጀመረው የፖለቲካ እንቅስቃሴና መጠነኛ ነፃነት ስር ሊሰዱና የሰፊው ሕዝብም ንቃተ-ህሊና ሊዳብር የሚችለው ወደ ውስጥ ያተኮረና ሰፊውን ሕዝብ በዕድገት እንቅስቃሴ ውስጥ ተካፋይ የሚያደርግ ስልት የተከተልን እንደሆን ብቻ ነው።
ፈቃዱ በቀለ (ዶ/ር) የምጣኔ ሀብት ባለሙያ ናቸው። በኢሜል አድራሻቸው fekadubekele@gmx.de ሊገኙ ይችላሉ።
ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011