በአዲስ አበባ 8 ቢሊዮን ብር በሚደርስ ወጪ ስድስት ትላልቅ የጤና ማዕከላት የግንባታ ፕሮጀክቶች ሊካሄዱ ነው

0
464

በአዲስ አበባ 8 ቢሊዮን ብር በሚጠጋ ወጪ ስድስት ትላልቅ የጤና ማዕከላት የግንባታ ፕሮጀክቶች ሊካሄዱ መሆኑን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የጤና አገልግሎት ለማሻሻል የሚያስችሉ በርካታ የሕክምና ማዕከል ግንባታ ፕሮጀክቶች በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች እየተካሄዱ መሆኑን ገልጾ፣ አሁን ላይ ደግሞ በስፋት ሊከሰቱ የሚችሉ የድንገተኛ ወረርሽኞችን ለመቆጣጠር የሚያስችል ባለ 11 ወለል ሕንጻ ያለው ኹሉን ዐቀፍ ሆስፒታል ለመገንባት ዝግጅት ተደርጓል ነው ያለው። ለግንባታውም 2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር መመደቡ ተገልጿል።
ጎን ለጎንም በ550 ሚሊዮን ብር ወጪ ኹሉን ዐቀፍ ሕንጻ የሚገነባ ሲሆን፣ በውስጡ የሕክምና መስጫ ማዕከላት፣ ላብራቶሪዎችና የምርምር ማዕከላት እንደሚገኙበት ተጠቅሷል።
እንዲሁም ደግሞ የደም ናሙና ምርመራና የሲቲ ስካን የመሳሰሉ ውስብስብ ምርመራዎች የሚካሄዱበት ትልቅ የምርመራ ማዕከል በ800 ሚሊዮን ብር ለመገንባት ዝግጅት መጠናቀቁ ተገልጿል።
በአዲስ አበባ በሚገኘው በቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ ለሚገነባው ለዚሁ የጤና ማዕከል ዲዛይን ተዘጋጅቶ፣ የጨረታው ሂደት ተጠናቆ ግንባታ ለመጀመር እየተሠራ መሆኑም ነው የተጠቆመው።
ከእነዚህ ግንባታዎች በተጨማሪ ከዓለም ባንክ ከተገኘ 2 ቢሊዮን ብር ድጋፍ የኹለት ሕክምና ተቋማት ግንባታ ሥራ የተጀመረ ሲሆን፣ ከእነዚህ አንደኛው የጨረታ ሂደቱ በመጠናቀቅ ላይ ሲሆን፣ በአፍሪካ የልህቀት ማዕከል ይሆናል የተባለው የምግብና የመድኃኒት ቁጥጥር ማዕከል መሆኑ ታውቋል።
በበጀት እጥረት ሥራው ቆሞ የሚገኘውን የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የማስፋፊያ ፕሮጀክትም ከባንክ በተገኘ 1 ቢሊዩን ብር ድጋፍ ግንባታውን የማስቀጠል ሥራ እንደሚከናወን ተጠቁሟል።
ኹሉንም ፕሮጀክቶች በሦስት ዓመት ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ መታቀዱም ተመላክቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 183 ሚያዝያ 29 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here