የኮ/ል መንግሥቱ ኃ/ማርያም የመርካቶ ድንገተኛ ጉብኝትና የ‹‹እምቦቲቶ›› ቤተሰቦች

0
1019

ጎዳና ተዳዳሪነት አሳሳቢ ከሆኑ ማኅበራዊ ችግሮች መካከል አንዱ ነው። በአዲስ አበባ ከፍሽስት ጣሊያን ወረራ ጀምሮ ጎዳና ተዳዳሪነት ሕይወት እንደተጀመረ በማስታወስ ብርሃኑ ሰሙ ከርዕሰ ጉዳዩ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮችንና ሕይወት የተጻፉ መጽሐፍትን በማጣቀስ በጣም በጥቂቱ ያቃምሱናል።

 

 

በአዲስ አበባ ከተማ የጎዳና ተዳዳሪነት ሕይወት መቼና እንዴት እንደጀመረ ከሚቀርቡ መረጃዎች ቀዳሚው የፋሽስት ጣሊያን ወረራ ዘመንን መነሻ የሚያደርግ ነው። ወረራው በፈጠረው ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ምስቅልቅል ምክንያት የአእምሮ ታማሚ በሽተኞች ቁጥር ተበራክቶ በየአደባባዩ እንዲገኝ ምክንያት መሆኑን ያዩት ፋሽስቶች፣ በ1929 የአማኑኤል ሆስፒታልን ያቋቋሙት በዚህ የተነሳ ነበር።

ከፋሽስት ጣሊያን ወረራ በኋላ የንጉሠ ነገሥቱ መንግሥት ለአገርና ሕዝብ ጠቃሚ ናቸው ያላቸውን የተለያዩ የልማት ሥራዎችን ተግባራዊ ቢያደርግም፤ በፋሽስቶች ዘመን ቦይ ቀይሶ መፍሰስ የጀመረው ጎዳና ተዳዳሪነት፣ በቀጣዩ ዘመንም ምንጩ የማይደርቅ ሆነ። በ1955 የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን በአዲስ አበባ ከተማ ለመመስርት ሽር ጉድ ሲባል የጎዳና ተዳዳሪዎች አኗኗር የከተማዋን ገጽታ እንደሚያበላሽ ስለታመነበት፤ ለዚህ ችግር መፍትሔ ሆኖ የተገኘው ‹‹ጡረታ ሰፈር››ን መመስረት ነበር።

‹‹ጡረታ ሠፈር›› ከመርካቶ ጭድ ተራ በታች የሚገኝ መንደር ነው። የመንደሩ የቀድሞ መጠሪያ ‹‹እቴጌ መስክ›› ይባል እንደነበር ሞላ ማሩ (በቀኛዝማች) የሕይወትና የሥራ ታሪክ መጽሐፍ (ያልታተመ) ውስጥ ተመልክቷል። አፍሪካ አንድነት ድርጅት በሚመሰረትበት ዋዜማ፤ ከአዲስ አበባ ጎዳናዎች ‹‹የታፈሱ›› የእኔ ቢጤዎች ለከተማዋ ‹‹ጡረታ ሠፈር›› የተባለውን አዲስ መንደር አስገኘ። ይህ ሙከራ የአዲስ አበባን ጎዳና ተዳዳሪዎች ቁጥር አሳንሶ ‹‹ችግሩ የለም›› የሚያስብል ደረጃ ደርሶ እንደነበር የጌታቸው ቢራቱ ምስክርነት አንዱ ማሳያ ነው።

የጂጂ ሮያል ሆቴልና የልብስ ስፌት ማምረቻ ባለቤት የሆኑት ጌታቸው ቢራቱ፣ ‘ኢምፐርቴክ ኢትዮጵያ ቢዝነስ ሶሳይቲ’ ‹‹የብልፅግና ቁልፍ›› በሚል ርዕስ በ2005 ባሳተመው መጽሐፍ ውስጥ ስለሥራና የሕይወት ታሪካቸው በሰጡት ምስክርነት፤ በ1955 መርካቶ ውስጥ የሚገኙ የጎዳና ተዳዳሪዎች በቁጥር ውስንና እርስ በእርስ ይተዋወቁ እንደነበር ሲናገሩ ፡-

‹‹የሕይወት ታሪኬ ከጎዳና አዳሪነት የሚጀምር ነበር ተብሎ ሊገለጽ የሚችል ነው። ከዛሬ 40 ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ በጎዳና የሚያድሩ በጣም ጥቂት ሰዎች ቢኖሩም ጎዳና ተዳዳሪ የሚለው ቃል አልነበረም። ተወልጄ ያደኩት መርካቶ አብነት አካባቢ ነው። ከከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ በአብነት አድርጎ፣ በከፊል አውቶቢስ ተራ፣ ተክለሃይማኖትና በርበሬ ተራ ዙሪያ በጎዳና አዳሪነት የምንታወቅ ልጆች ቁጥራችን 6 ነበር። ከስድስታችን ሁለቱ ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ሁለቱ በአሜሪካን ይገኛሉ። የተቀረነው ሁለታችን በአገር ውስጥ እንገኛለን።››

በ1950ዎቹ አጋማሽ በመርካቶና ዙሪያ መንደሮቿ፣ በጎዳና ተዳዳሪነት ይታወቁ የነበሩት ‹‹ስድስቱ ልጆች›› ብቻ ነበሩ ቢባልም፤ በገበያዋ ውስጥ መነገጃ ቦታ አጥተው ጎዳናዎቿን ያጥለቀለቁ ‹‹የጎዳና ነጋዴዎች›› ብዛት ችግርን መቅረፍ ያስችላል በሚል የአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ያስገነባቸው ሁለቱ የመሀል ገበያ (አዳራሽ) መደብርና ሱቆች በነፃ የታደለው በ1955 ነበር።

ጌታቸው ቢራቱ፣ ከጎዳና ተነስቶም ስኬታማ ሰው መሆን እንደሚቻል የራሳቸውን ልምድና ተመክሮ በማቅረብ የስድስቱን ‹‹ልጆች›› የሕይወት ዕጣ ፈንታ ላይ ተወስነው ምስክርነታቸውን ቢሰጡም፤ እርሳቸውን ወደ ጎዳና የመራው ባህላዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር (ኢምፐርቴክ ኢትዮጵያ ቢዝነስ ሶሳይቲ በተመሳሳይ ርዕስ በ1999 ባሳተመው ቁጥር አንድ መጽሐፍ ውስጥ ቀርቧል) ሌሎችንም ወደ ጎዳና ማባረሩ ስለቀጠለ ቀውሱ ዘመን ተሸጋሪነቱ ቀጥሏል።

የጎዳና ተዳዳሪዎች ሕይወት የአዲስ አበባ ከተማ አንዱ ገጽታ ሆኖ በጀመረው ቦይ እየፈሰሰ ከንጉሠ ነገሥቱ ወደ ደርግ ዘመን ተሸጋገረ። ደርግም ችግሩን ከምንጩ አደርቃለሁ ብሎ ብዙ ለፍቶለታል። ጎዳናዎችን ያጥለቀለቁ ሴተኛ አዳሪዎች በ‹‹አፈሳ››ም ጭምር እየሰበሰበ፣ በተለያየ ሙያ አሰልጥኖ በየፋብሪካው እንዲቀጠሩ ያድርግ ነበር። ደርግ ተጠምዶበት ለነበረው ዘመቻና ጦርነት፤ ዘማችና ወታደር መመልመያ አንዱና ዋነኛው ምንጩ የጎዳና ተዳዳሪዎች ነበሩ ማለትም ይቻላል።
መርካቶ ውስጥ አማኑኤል ሆስፒታል እንዲቋቋም፣ የ‹‹ጡረታ ሠፈር›› እንዲመሰረት፣ ሁለቱ የመሐል ገበያ መደብርና ሱቆች ለችግረኞች በነፃ እንዲሰጡ ምክንያት የሆነው የጎዳና ተዳዳሪነት ችግርን ለመቅረፍ በሚል፤ በደርግ ዘመነ መንግሥት የተከናወኑት ተግባራት በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ጭምር የሚመራበት ጊዜ ነበር። አንዱ እና በወቅቱ የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ጭምር ስቦ የነበረው እንቅስቃሴ በ1970ዎቹ መጀመሪያ የተፈጸመ ነበር።

በዚያ ዘመን ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በድንገት መርካቶ ውስጥ ተገኝተው፣ ጎዳና ተዳዳሪዎችን ሰብሰበው፣ ቀጣይ ሕይወትና ኑሯቸውን መንግሥት ሊለውጥላቸው ማቀዱን አበሰሩ። ከዚያ ታሪካዊ ሌሊት ጋር በተያያዘ ‹‹እምቦቲቶ›› የሚባል ሕፃን የወቅቱ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። በኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ታቅፎ በጋዜጦች ጭምር ፎቶግራፍ የወጣው ሕፃን ጥቁር፣ የደስ ደስ ያለውና ድምቡሽቡሽ ያለ ልጅ ስለሆነ ነበር ‹‹እምቦቲቶ›› የሚል ቅጽል ሥም የወጣለት። በዘመኑ የመርካቶ ጎዳና ተዳዳሪ ልጆች፣ ዳቦ መሐል የተቀቀለ ዳቦ ወይም እንቁላል የተሰነገበትና በተለይ በሲኒማ አዲስ ከተማ ደጃፍ በቅናሽ የሚያገኙትን ምግብ ‹‹እምቦቲቶ›› በሚል ነበር የሚጠሩት። የሕፃኑ ቅጽል ሥም ያንን መነሻ ያደረገ ነበር። በዚያ አጋጣሚ ከወላጆቹ ጋር ከጎዳና የመነሳት ዕድል ያገኘው ‹‹እምቦቲቶ›› ዝዋይ የሕፃናት ማሳደጊያ ገብቷል፤ የለም ወደ ኩባ ነበር የተላከው የሚሉ የተለያዩ ወገኖች አሉ።

በ1970 ዎቹ የመርካቶ ጎዳና ተዳዳሪዎች ታሪክ ምን ይመስል እንደነበር፣ የደራሲ ጃርሶ ሞትባይኖር ኪሩቤል ቀልብና ትኩረት ስቦ ‹‹የአዲስ አበባ ልጆች››ን ታሪክ ጽፈውበታል። 7 ታሪኮችን ይዞ ‹‹አስኮ ጌታሁንና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች›› በሚል ርዕስ በ1992 በሜጋ አሳታሚ ድርጅት የታተመው መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘው ‹‹የአዲስ አበባ ልጆች›› አጭር ልቦለድ ታሪክ፣ ‹‹አገራቸው ገና ሳታሳድጋቸው ያስረጀቻቸውና ስቀው ሳይጠግቡ እንዲያለቅሱ የተገደዱት›› የ4 ጨቅላ የመርካቶ ልጆች ውሎና አዳር ምን እንደሚመስል ተርከውታል።

በደራሲ ጃርሶ ሞትባይኖር ኪሩቤል አጭር ታሪክ የቀረቡት ልጆች ከፊሎቹ ወላጆቻቸውን አያውቁም፤ ወላጆቻቸው ስለሞቱባቸው ወደጎዳና የወጡም አሉ። የአገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ምስቅልቅል ሰለባ ሆነው ለጎዳና የተዳረጉ ቤተሰቦች ሕይወት በመርካቶ ምን እንደሚመስል ሌላኛውን ታሪክ በልቦለድ ያቀረቡት ደራሲ አንቀፀ ደስታ ናቸው። በ2007 ታትሞ ለአንባቢያን በቀረበው ‹‹የከሀዲዎች ወግ›› የአጭር ልቦለድ ስብስብ መጽሐፍ 14 ታሪኮችና 1 ግጥም ይዟል። በ‹‹ወርቃማው የይባላል ዘመን›› ነው ስለመርካቶ የጎዳና ተዳዳሪዎች የሚተረከው።

ነዋሪነቱ በጡረታ ሠፈር የሆነ ታከለ የሚባል ገጸ ባሕሪይ ብሩክታዊት ለምትባል ፍቅረኛው በሚጽፍላት ደብዳቤ ውስጥ ነው ስለመርካቶ ጎዳና አዳሪ ቤተሰቦች የሚነገረው። ዋናው ባለታሪኮች 4 ሲሆኑ ከእነዚህ አንዱ እምቦቲቶ የሚባል ልጅ ነው። ኩርንችት የእምቦቲቶ አባት፣ ታዱ እናቱ ስትሆን ሎንጎ የቤተሰቡ ወዳጅና የሥራ አጋር ነው።

‹‹ምናለሽ ተራን›› ለመጎብኘት የሚመጡ የወጭ አገር ዜጎች በእንግሊዝኛ ቋንቋ የማስተርገም አገልግሎት የሚሰጠው ኩርንችት፤ የሀብታም ልጅ እንደሆነ፣ ቀንደኛ የኢህአፓ አባልም እንደነበር፣ ትልቅ የመንግሥት ባለሥልጣን የነበረ ሳይሆን አይቀርም … የሚሉ የተለያዩ መላምቶች ቢቀርብም እሱ ስለማንነቱ አንድም ቃል ትንፍሽ አይልም።

ታዱ ከተወለደችበት ገጠር ሸሽታ ወደ አዲስ አበባ የመጣችው፣ ትምህርትሽን አቁመሽ ባል አግቢ ብለው ቤተሰቦቿ ሲያስገድዷት በእምቢታ ነበር። መርካቶ ገብታ ሴተኛ አዳሪ ሆነች። ውበቷ ተሟጦ ሲያልቅ ከመርካቶ ጠጅ ቤቶች ከማይጠፉ የየዕለት ቋሚ ደምበኞች አንዷ ሆነች። ‹‹ታዱና ኩርንችት ጠጅ ቤት አምሽተው ሰክረው ሲወጡ ተንገዳግደው አብረው ወደቁ›› በዚያው ባልና ሚስት ሆኑ።

የሉንጎ ማንነትና አገሩን አውቃለሁ የሚል የለም። ‹‹ከአገሩ የወጣው ሚስቱንና ልጁን የገደሉበትን ባላባት አንገታቸውን በመጥረቢያ ቀንጥሶ በመጣሉ ነው›› ቢባልም እሱ ማረጋገጫ አይሰጥም። ከመርካቶ ጎዳና አዳሪዎች አንዱ ቢሆንም ከሴቶች ጋር ለመተኛት ፈቃደኛ አይደለም። ‹‹ድንግልናውን›› የመጠበቁ ምክንያት ‹‹እኔ ሉንጎ! የብርቅዬ ባል! የማንም አንቡላ ጨላጭ መቀለጃ አይደለሁም !›› የሚል ነው።

ቤተሰቡ ከመርካቶ ሆቴሎች የሚሰበስቡትን ትርፍራፊ ምግብ (በዘመኑ ኡፋ ይባል ነበር) በመሸጥ ነው የሚተዳደሩት። እምቦቲቶ ሌብነትን ተጨማሪ ሥራው አድርጎ ይዟል። ደንበኞቻቸው ጎዳና ተዳዳሪዎች፣ ኩሊዎች መንታፊዎ ናቸው። ‹‹ቡሌ›› በ1970ዎቹ መጀመሪያ መርካቶ ውስጥ የ5፣ የ10፣ የ20 እና የ25 ሣንቲም ይሸጥ እንደነበር እግረ መንገዱን ታሪካዊ መረጃ የሚሰጠው የደራሲ አንቀፀ ደስታ ልቦለድ፣ ብዙ ያልተነገረለትን የመርካቶ የድህነት ኑሮና አኗኗርን በጥልቀት አሳይተውበታል።
‹‹የፖለቲካ ፍትጊያ አሽቶ›› ያሰለላቸው›፣ ‹‹መማርና ማወቅ የኑሮ ሀዲዳቸውን›› የፈነቃቀለባቸው፣ ‹‹የቤተሰብ የንዋይ ንትርክ የአእምሮ ወለምታ›› የፈጠረባቸው፣ ‹‹የሕብረተሰቡን ጎጂ ባህልና ልማድ›› የጠሉ፣ ‹‹ስልጣንና ሀብታቸውን ተመክተው›› ላደረሱባቸው በደል በግላቸው የወሰኑት የበቀል እርምጃ ከማህበረሰቡ ያሸሻቸው … ገጸ ባህሪያትን በማሳያነት በማቅረብ፤ የጎዳና ነዋሪዎች የጀርባ ታሪክ ፈርጀ ብዙ መሆኑን ደራሲ አንቀፀ ደስታ አመልክተዋል። የጎዳና ኑሮ በተለይ ለህፃናት አስከፊነቱ ምን እንደሚመስል እንቦቲቶ ጥሩ ማሳያ ሆኖ ቀርቧል፤ ‹‹እንቦቲቶ ጠጅ መጠጣት የጀመረው ገና የ6 ወር ህፃን እያለ ነው። ታዱ በጡጦ ውስጥ አድርጋ ነው ያለማመደችው።››

በ1970ዎቹ ኮ/ል መንግስቱ ኃይለማርያም በመርካቶ ያደረጉት ጉብኝት፣ ደራሲው አጭር ልቦለድ ታሪኩን እንዲጽፉ መነሻ የሆናቸው ይመስላል። ፋሽስት ጣሊያን አማኑኤል ሆስፒታልን እንዲያቋቁም፣ ንጉሥ ኃይለሥላሴ ጡረታ ሠፈርን እንዲመሠርቱ፣ ደርግና ኢሕአዲግም ለመፍትሔው ተመሳሳይ ጥረት እያደረጉለት ያለው አገራዊ ችግር፣ ምንጩን ማድረቅ ይቻል ይሆን ? ለሚለው ጥያቄ በደራሲ አንቀፀ ደስታ ‹‹ወርቃማው የይባላል ዘመን›› አጭር ልቦለድ የምናገኘው መልስ በቀላሉ ይሳካል የሚያስብል አይደለም።

ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here