እህተ ማርያም በሚል ስም የምትታወቀው ወ/ሮ ትዕግስት ፍትህአወቅ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ድንጋጌ በመተላለፍ ወንጀል በቁጥጥር ስር ውላ ምርመራ እየተጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

Views: 314

ራሷን ንግስተ ነገስት ዘኢትዮጲያ ብላ የምትጠራውና እህተ ማርያም በሚል ስም የምትታወቀው ወ/ሮ ትዕግስት ፍትህአወቅ የኮሮና ቫይረስ (ኮቪድ 19) ስርጭትን ለመከላከል፣ለመቆጣጠር እና የሚስከትለውን ጉዳት ለመቀነስ በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማንኛውንም ተግባር ለመፈፀም፣ለመነጋገር፣ለመወያየት ወይም መሰል ተግባራትን ለማከናወን የአንድ ቤተሰብ አባላት ከሆኑ ዉጪ አራት እና ከዚያ በላይ ሆኖ በአንድ ቦታ በአካል መገኘትን የሚከለክለውን ድንጋጌ በመጣስ በአዲስ ከተማ ክ/ከተማ ወረዳ 4 ሉባር ሆቴል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ መኖሪያ ቤቷ ውስጥ በርካታ ሰዎችን በመሰብሰቧ በደረሰ ጥቆማ በቁጥጥር ስር ውላ ምርመራ እየተጣራ መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም ‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ በሽታ የለም ተቃቀፉ ተሳሳሙ›› ወዘተ የሚል መልዕክት በማህበራዊ ትስስር ገፅ በመልቀቅ በርካታ የማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮች የተሳሳተ ግንዛቤ ይዘው የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ከሚወስዱት የጥንቃቄ እርምጃ እንዲዘናጉ የማድረግ ተግባር መፈፀሟን ነው ፖሊስ ኮሚሽኑ የገለፀው፡፡

ወ/ሮ ትዕግስት ፍትህ አወቅ እንግሊዛዊት እንደሆነችና የኢትዮጵያ ዜግነት እንደሌላት በ1986 ዓ/ም ከኢትዮጵያ እንደወጣችና በ2007 ዓ/ም ከ21 ዓመታት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሰች በ2008 ዓ/ም የኢትዮጵያ ሠንደቅ አላማ ላይ የሚገኘውን አርማ በመቅደድና በማቃጠል እንዲሁም በ2009 ዓ/ም ወደ ቃሊቲ ማረሚያ ቤት በመሄድ “ታራሚዎችን ላስፈታ እመቤቴ ማርያም ልካኝ ነው የመጣሁት” በማለት ታራሚዎችን በማነሳሳት በፈፀመችው ህገ-ወጥ ተግባር በቁጥጥር ስር ውላ እንደነበር ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ምንጭ፡- የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com