አጋቹ ማን ነው?

ካለፈው ሳምንት ቀደም ብሎ የአንድ የመገናኛ ብዙኅን ባለሞያ የሆነ ጋዜጠኛ <መታሰር> ጉዳይ በማኅበራዊ ሚድያው መነጋገሪያ ሆኖ ነበር። የጋዜጠኛ መታሰር እንግዳ ነገር አይደለም፤ ግን በስውር <ታግቶ> ነው የተወሰደው መባሉ የብዙውን ትኩረት ስቧል። ጋዜጠኛውን ማን እንደወሰደው፣ የት እንደተወሰደና ማን እንደመለሰው ሳይታወቅም ነው የተገኘበት ቦታ ተመልሷል የሚል ዜና ከአንድ ሳምንት ቆይታ በኋላ የተሰማው።

ብዙዎች በጉዳዩ ላይ ሐሳባቸውን ሲያጋሩ የቆዩ ሲሆን፤ <ይፈታ> የሚል መልዕክት በብዛት ተስተውሏል። በኋላ ላይ ይፈታ የምትሉት መጀመሪያ ታስሮ ነው ወይ፣ ማን አሰረው፣ የትስ ነው የታሰረው የሚለው መች ታውቆ ነው ያሉ ነበሩ። ይህን ያሉትም የት ወሰዳችሁት እንጂ ጥፋት የተገኘበት ሰው አይታሰር አንልም ዓይነት ሐሳብን ይዘው ነው።

በእርግጥም የተባሉት ጥያቄዎች ሁሉ መልሳቸው አይታወቅም ነበር። ያም ብቻ ሳይሆን ጥያቄው ለማን እንደሚቀርብም አይታወቅም። ድሮ የነበረው <ያልታወቀ አካል> ዳግም ነፍስ ሳይዘራ አይቀርም ያሉት ሰዎችም በዚህ ምክንያት ነው።

እና ከዛ በኋላ ታድያ ጥያቄው ጋዜጠኛውን የት አደረሳችሁት የሚል ሆነ። ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም! ባለሞያው ሥራውን ስለሠራ እንዲህ ያለ <እርምጃ> ሊወሰድበት አይገባም፣ በምስጢር እንዲህ ማድረግ አግባብ አይደለም፣ የት እንዳለ አሳውቁ የሚሉ መግለጫዎች ከዛ በኋላ ይፋ ሆኑ።

ከሳምንት በኋላ፣ መግለጫዎቹ ተሰምተው ይሆን ወይም መልዕክቶቹ <ለማይታወቁ አካላት> ደርሶ፤ አይታወቅም። ግን ጋዜጠኛው <ደኅና ነኝ፤ አካላዊ ጉዳት የለኝም። የት እንዳቆዩኝና በየት በኩል ወደቤቴ እንደተመለስኩኝ እንዳላውቅ ዐይኔን የሸፈኑት ቢሆንም፤ መጀመሪያ አግኝተው ከወሰዱኝ ቦታ ማለትም ከቤቴ መልሰውኛል> ሲል ይፋ አደረገ።

ቅድሚያ አብዛኛው ተመስገን ያለ ሲሆን፣ የተከተለው ቀልድ ነው። <እነማን መቼ እንደሚያግቷችሁ ስለማይታወቅ፤ ሁሌም ቤታችሁ ተገኙ፤ ቤታችሁ እንዲመልሷችሁ> የሚለውን ብዘዎች ተጋርተውታል። ይህም በተዘዋዋሪ <በዚህ ዓይነት እኛም እንሰጋለን> የሚል መልዕክት ያዘለ ነው።

ያም ሆነ ይህ ጋዜጠኛው ክስ እንዳቀረበ ጠቅሶ የተጨነቁለትን ሁሉ አመስግኗል። <ጋዜጠኛሬ የት አለ?> ብሎ ሲጠይቅ የነበረ ሁሉም፤ ዋናው ጋዜጠኛው በደኅና መመለሱ ነው ያለ ይመስላል። ምን ተፈጠረ ብሎ ለመጠየቅ ጊዜ አልተወሰደም። ምን እንደተፈጠረ የሚያውቀው ጋዜጠኛው እና <ያልታወቁ አካላት> ብቻ ናቸው። አጋቹ ማነው ጥያቄም ጥያቄ ሆኖ ይቆያል። በቀረው ግን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ባለሀይማኖት እንዳላት አገር፤ ሁሉም ነገር ለበጎ ነው የሚለውን መዘመር የቀለለ ይመስላል።


ቅጽ 4 ቁጥር 184 ግንቦት 6 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች