ዓለም አቀፋዊ የኮሮና መረጃዎች

Views: 346

ቬትናም በኮቪድ 19 ምክንያት ሞት ያልተመዘገበባት እና ስርጭቱ በአጭር የተቀጨባት አገር
በዓለም አቀፍ ደረጃ ከኹለት መቶ ሽ በላይ ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው ኮቪድ 19 ወረርሽኝ በአገረ ቬትናም ቢከሰትም ምንም አይነት ሞት አልተዘገበም። ቬትናም ከቻይና ውጭ ያሉ አገራት ቫይረሱ በተዛመተ ወቅት ቀዳሚ ከሚባሉት አገራት ተርታ ምትሰለፍ ቢሆንም ይህ ጽሑፍ እስከ ተሰናዳበት ጊዜ ድረስ በኮቪድ 19 ምክንያት ምንም አይነት ሞት ያልተመዘገበባት አገር ሆናለች።

በቬትናም ወረርሽኙ በመከሰቱ ሦስት መቶ የሚሆኑ ዜጎች በቫይረሱ የተጠቁ መሆኑ ቢዘገብም 270 የሚሆኑት ግን አገግመው ወደ ሕብረተሰቡ እንዲቀላቀሉ እንደተደረገ ታውቋል። ማዘርሽፕ የተሰኘው ድረ ገጽ እንዳስነበበው 97 ሚሊዮን የሕዝብ ብዛት ያላት ደቡብ ምስራቅ እስያዋ አገር ቬትናም እንዴት አድርጋ ወረርሽኙን እንደተቆጣጠረችው የሚያስደንቅ ተግባር ሲሆን ነገር ግን ሞት ተመዝግቦባቸው እምብዛም ሳይስፋፋ በጊዜ ስለተጠቆጣጠሩት የቀጠናው አገራት ስለሆኑት ደቡብ ኮሪያ እና ታይዋን ሲዘገብ ቬትናም አትጠቀስም ሲል አስነብቧል።

ቬትናም በፈረንጆች አዲስ አመት 2020 መባቻ ላይ ነበር ቫይረሱ ወደ አገሯ መግባቱን ያስታወቀችው፤ ይህንም ተከትሎ የተለያዩ ክልከላዎችን እና የጉዞ ዕገዳዎችን ያስተላለፈች ሲሆን ከሚያዚያ 16/2012 ጀምሮ ክልከላዎችን እና ታግደው የነበሩ እንቅስቃሴዎችን ቀስ በቀስ በማስጀመር ላይ እንደሆነች ተሰምቷል። ቬትናም ከኮቪድ 19 መነሻ ከሆነችው ቻይና ጉርብትና እና ሰፊ ድንበሮችን እንደመጋራቷ መጠን እንዴት ልትቋቋመው ቻለች በሚል ጥያቄዎች ይነሳሉ። በዚህም በቬትናም የዓለም ጤና ድርጅት ተወካይ ኪዶንግ ፓርክ ምላሽ ሲሰጡ፤ ቬትናም ወረርሽኙ በቻይና ከተከሰተ እና ወደ አገሯ ከገባ ጀምሮ አፋጣኝ እና ጠንካራ እርምጃ በሚገባ በመውሰዷ አመርቂ ውጤት ልታስመዘግብ መቻሏን አስታውቀዋል።

በቀናት ልዩነት ሕይወታቸው ያለፈው መንትዮች
ከወደ እንግሊዝ ዓለምን በማሸበር ላይ የሚገኘው በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ኹለት መንታ እህታማቾችን በሦስት ቀናት ልዩነት ሕይወታቸውን ነጥቋል። ኬቲ እና ኤማ ዴቪስ የተባሉ 37 ዓመት ዕድሜ ያላቸው መንታ አህትማማቾች ቫይረሱ ከተገኘባቸው በኋላ በሳውዝ ሀምፕተን ሆስፒታል በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በሦስት ቀናት ልዩነት ሕይወታቸው ማለፉን ቢቢሲ አስነብቧል። የሕጻናት ነርስ የሆነችው ኬቲ ዴቪስ አስቀድማ ማክሰኞ ሚያዚያ 13/2012 ህይወቷ ያለፈ ሲሆን ከሦስት ቀናት በኋላ ደግሞ መንታ እህቷ ኤማ ዴቪስ አርብ ሚያዚያ 16/2012 አሸልባለች።

የመንትዮችን እህት ዞይ ዋቢ አድርጎ ቢቢሲ እንደዘገበው ኤማ እና ካትሪን ‹‹አብረን ወደዚህ ምድር እንደመጣን በአንድ ላይ ከዚህ ምድር እንሔዳለን›› የሚል ጽኑ እምነት እንዳላቸው እና ይህንም ዘወትር በአንደበታቸው ይናገሩት እንደነበር ገልጿል። ህይወቷ ባለፈበት ሳውዝ ሀምፕተን ሆስፒታል በሕጻናት ነርስነት ታገለግል የነበረችው ኬቲ በስራ ባልደረቦቿ አንደበት ሙያዋ ከሙያነትም ያለፈ ልዩ ትርጉም የነበረው እና ሰዎችን ለመርዳት ረጅም ርቀቶችን የምትጓዝ ትጉህ ሰራተኛ እንደነበርችም ይነገርላታል። እህታቸው ጨምራም ከልጅነታው ጀምሮ ኹለቱም ለሚጫወቱባቸው አሻንጉሉቶቻቸው የሕክምና ባለሙያ በመሆን ይተውኑ እና ሰውን መርዳት ክልጅነታቸው ጀምረው ይተገብሩት የነበረ የህይወት ዘመን ህልም እንደነበር ታስታውሳለች።

በኮቪድ 19 ቫይረስ ከመጠቃታቸው አስቀድሞ ኹለቱም መንታዎች ተመሳሳይ የሆነ የጤና ዕክል እንደነበረባቸው የተነገረ ሲሆን በአንጀታቸው ክፍል ከፍተኛ የሆነ ሕመም እንደነበረባቸውም ታውቋል። በአገረ እንግሊዝ አዲስ ማለዳ ወደ ማተመሚያ ቤት እስከ ገባችበት ጊዜ ድረስ 50 የሚሆኑ ነርሶች ከኮቪድ 19 ጋር በተያያዘ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

አሜሪካ በቬትናም ጦርነት ከሞተው ይልቅ በኮቪድ 19 የሞቱት ዜጎቿ ይበልጣሉ
አሜሪካ ከ65 አመታት በፊት በተደረገውና ለ20 አመታት በቆየው በመጨረሻም ለተሸነፈችበት ከቬትናም ጋር ባደረገችው ጦርነት 58,220 ወታደሮችን የጣች ሲሆን ኹለት ወር ባስቆጠረው በኮቪዲ19 ግን 60 ሽሕ ዜጎች (ይህ ጽሑፍ በተዘጋጀበት ወቅት) ሞተውባታል ሲል ሲ ኤን ቢሲ ዘግቧል። አሜሪካ በታሪኳ ረጅም ጦርነት ያደረገችው ከቬትናም ጋር መሆኑን እና በርካታ ዜጎቿን በተለይም ደግሞ ወታደሮቿን የገበረችበት አስከፊ ጦርነት እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ።

በ1947 ጀምሮ እስከ 1967 የዘለቀው የኹለቱ አገራት ጦርነት በተለምዶ ኹለተኛው የኢንዶንቺ ጦርነት በመባል ይታወቃል። ይህም በመጀመሪያው ኢንዶንቺ ጦርነት ፈረንሳይ ቬትናምን እንደ ቅኝ ግዛት በመቁጠሯ የተደረገ ጦርነት ሲሆን ዘጠኝ ዓመታትን ፈጅቷል። ከ1938 እስከ 1947 የተካሔደው የመጀመሪው ጦርነት ቅጣይ እንደሆንም ይነገርለታል የአሜሪካ እና ቬትናም ጦርነት።

በአሁኑ ሰዓት የኮቪድ 19 በአገረ አሜሪካ መከሰቱን ተከትሎ በርካቶች ለሕክምና ስፍራ እንኳን ሳይበቁ እንደሚያልፉ እና ችግሩም እየተባባሰ እንደመጣ የዓለም መገናኛ ብዙኃን ሰፊ ሽፋን ሰጥተው እየዘገቡት ይገኛሉ። በአሜሪካ አዲስ ማለዳ ለህትመት እስከበቃችበት ጊዜ ድረስ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ዜጎች በወረርሽኙ የተጠቁ ሲሆን 60 ሽህ የሚሆኑት ደግሞ ህይወታቸው አልፏል። በአሜሪካ በዋናነት ዘጠኝ በሚሆኑ ግዛቶቿ ቁጥሩ ከፍ ያለ ሞት አስመዝግበዋል። ከእነዚህም ውስጥ የንግድ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ የሌሎች ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ማደሪያ የሆነችው እና ቅንጡ ከተማ በመባል የምትታወቀው ኒው ዮርክ 295 ሽሕ ነዋሪዎች በወረርሽኙ የተጠቁ ሲሆን ከእነዚህም 17 ሽሕ የሚሆኑት ለህልፈት ተዳርገዋል። ከኒው ዮርክ በማስቀጠልም አጎራባች ግዛት ኒውጀርዚ እና ማሳቹሴትስ በ114 ሽሕ እና በ58 ሽሕ የተጠቂዎች ቁጥር ኹለተኛ እና ሦስተኛ ደረጃ ላይ ሲቀመጡ የሟቾች ቁጥርም ከ6 ሽህ 4 መቶ በላይ እና ከ3 ሽ በላይ በቅደም ተከተል ተቀምጧል።

ራስን ከኮሮና መጠበቂያ መሳሪያዎች ለወንዶች ብቻ ታስቦ ነው የሚመረተው የሚል ቅሬታ
ከወደ እንግሊዝ ሴት የጤና ባለሙያዎች የአፍ እና የአፍንቻ፣ የፊት መሸፈኛ እና የእጅ ጓንት ልኬታቸው ትላልቅ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለተገቢው አገልግሎት ለመጠቀም እንዳልቻሉ ቅሬታቸውን እያሰሙ ነው። ሴት የሕክምና ባለሙያዎችን ቅሬታ ቢቢሲ እንደዘገበው በመጠን ያነሱትን እንኳን ለመጠቀም እንደማይቻልና ከሚፈለገው በላይ ሰፋፊ በመሆናቸው ከወረርሽኙ ሸፋኝነታቸው አጠራጣሪ እንደሆነ ገልጸዋል።

ከሴት የሕክምና ባለሙያዎች የቀረበውን ቅሬታ በሚመለከት የአገሪቱ የጤና ክፍል ባወጣው መግለጫ እነዚህ መገልገያዎች ሴቶችም ወንዶችም እንዲጠቀሙባቸው ታስበው ስለተዘጋጁ በተለያየ መጠን ይገኛሉ ሲል አስታውቋል።

የህክምና ባለሙያዎች ባጠቃላይ መገልገያ ለማግኘት በተቸገሩበት በዚህ ወቅት ሴት ሀኪሞች ደግሞ ተጨማሪ ፈተና ገጥሟቸዋል። የሴቶች እኩልነት ፓርቲ ነገሩ “እጅግ አሳፋሪ ነው” ሲል በትዊተር ገጹ አስፍሯል።

ከሦስት ዓመት በፊት የተሠራ ጥናት አብዛኞቹ በአውሮፓና በአሜሪካ ጥቅም ላይ የሚውሉ የሀኪሞች መገልገያዎች ወንድን ታሳቢ አድርገው እንደሚመረቱ ያሳያል። በእንግሊዝ 77 በመቶ የሕክምና ባለሙያዎች ሴቶች ናቸው።

የጊኒ ቢሳዉ ጠቅላይ ሚንስትር ኑኖ ናቢያም በኮሮና ቫይረስ ተያዙ
ምእራብ አፍሪካዊቷ አገር ጊኒ ቢሳው ጠቅላይ ሚኒስትር ኑኖ ናቢያም በኮቪድ 19 ወረርሽኝ መጠቃታቸው ታወቀ። ከጠቅላይ ሚንስትሩ በተጨማሪም ሦስት የካቢኔ አባላታቸው በቫይረሱ መጠቃታቸው ተገልጿል፡፡በጊኒ ቢሳዋ ዋና ከተማ ቢሳዋ በሚገኝ ሆቴል ራሳቸዉን አግልለዉ የቆዩ ሲሆን በተደረገላቸዉ ምርመራ በቫይረሱ ስለመጠቃታቸዉ የአገሪቱ የጤና ሚንስቴር አስታዉቋል፡፡

በምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ጊኒ ቢሳዉ ከ70 በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸዉ ሲረጋገጥ የአንድ ሰዉ ህይወት ማለፉም ተዘግቧል፡፡ በወረርሽኙ ተጠቅተዋል ተብለው ከተመዘገቡት ውስጥም 18 የሚሆኑት አገግመው ወደ ኅብረተሰቡ ተቀላቅለዋል።

በፈረንሳይ የባቡር እንቅስቃሴ 70 በመቶ ሊጀምር ነው
በተከሰተው ዓለም አቀፋዊ ወረርሽኝ ምክንያት እንቅስቃሴዎችን እና በጎዳናዎች ላይ መታየትን በከፍተኛ ትዕዛዝ ከከለከሉ የአውሮፓ አገራት መካከል ግንባር ቀደም በሆነችው ፈረንሳይ ከመጪው ግንቦት 3 /2012 ጀምሮ 70 በመቶ የሚሆነው የምድር ውስጥ ባቡር እነቅስቃሴዋ ሊጀምር መሆኑ ተነግሯል። ጀርመን ድምጽ እንደዘገበው ጠቅላይ ሚንሥትር ኤድዋርድ ፊሊፔ ምክር ቤት ውስጥ ባሰሙት ንግግር ፈረንሣይ ውስጥ አካላዊ ርቀትን መተግበር የማይቻል ከኾነ በሥራ ቦታ የፊት እና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ ግዴታ ይኾናል ያሉ ሲሆን የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እንደሚከፈቱም መናገራቸው ተዘግቧል።

በሳምንቱ ደግሞ የኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እንደሚከፈት ዐስታውቀዋል። ትምህርት መስጠት የሚቻለው ግን በአንድ መማሪያ ክፍል ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ከ15 ካልበለጡ ብቻ ነው ሲሉም አስጠንቅቀዋል።

አፍና አፍንጫን አለመሸፈን ከ50 እስከ 5000 ዩሮ ያስቀጣል
ጀርመን በሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርቶችና በማኅበራዊ ቦታዎች ላይ የሕክምና አፍና አፍንጫ መሸፈኛ አልያም በአንገት ልብስ፣ በሻሽ ወይም በስካርፍ አፍን እና አፍንጫን የመሸፈን የወጣውን ደንብ ተከትሎ ተግባራዊ በማያደርጉ ሰዎች ላይ ከ50 እስከ 5000 ዩሮ ቅጣት እንደሚጣል ተደንግጓል። ጀርመን ወረርሽኙን በቁጥጥር ስር ሰውላ የተቀዛቀዘውን እንቅስቃሴ በመክፈት ከአውሮፓ ቀደማት አገር የለም። ይህንም ተከትሎ ተዘግተው የነበሩ ትምህርት ቤቶች እና የገበያ ስፍራዎች እየተከፈቱ እና ወደ ስራ መግባት ጀምረዋል።

ቅጽ 2 ቁጥር 78 ሚያዝያ 24 2012

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com