ኢትዮጵያ በ10 ወራት ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት 153 ሚሊዮን ዶላር አገኘች

0
1033

ኢትዮጵያ በ2014 በጀት ዓመት ባለፉት 10 ወራት 153 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር ማግኘቷን የኢትዮጵያ የጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ኢንዱስትሪ ምርምር ልማት ማዕከል አስታወቀ።

ገቢው የተሰበሰበው በበጀት ዓመቱ ይገኛል ተብሎ ታቅዶ ከነበረው 178 ሚሊዮን ዶላር ሲሆን፤ በዚህም የእቅዱን 85 በመቶ አሳክቷል ተብሏል። 2014 በ10 ወራት የተገኘው ገቢ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ28 ሚሊዮን ዶላር ብልጫ አሳይቷል።

በ2013 ከክር፤ ጨርቅ፤ ልብስና ባህላዊ አልባሳት የተገኘው ዶላር 125 ሚሊዮን ነበር። በ2014 በጀት ዓመት በሚያዝያ ወር ብቻ ከጨርቃ ጨርቅና አልባሳት ዘርፍ 13 ሚሊዮን ዶላር ገቢ መገኘቱም ከተቋሙ ከተገኘው መረጃ ማወቅ ተችሏል። በዚህም 21 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የነበረ ሲሆን፤ በተገኘው የዶላር ገቢም የእቅዱን 62 በመቶ ማከናወን ተችሏል ተብሏል።

በሌላ በኩል በመለዋወጫ (ስፔር ፓርት) አለመገኘት ምክንያት ቆመው የነበሩ የጥጥ ዕንዝርቶች (ጥጥን ወደ ክር መቀየሪያ መሣሪያዎች) ከ675 ወደ 430 መቀነስ መቻሉን ከተቋሙ በተገኘው መረጃ ማወቅ ተችሏል። መለዋወጫው ከአገር ውጪ የሚገኝ እንደሆነና ዝርዝር ዋጋውን ለመግለጽ የሌሎች ድርጅቶች ቅንጅት ምላሽ እንደሚያስፈልገው ነው የተገለጸው።

ከጦርነቱ ጋር ተያይዞ በቆላማ ቦታዎች እንደተለመደው ጥጥ ማምረት ፈታኝ እንደሆነም ተብራርቷል። በተመረጡ ሦስት ጥጥ የሚለማባቸው ክልሎች (በአማራ 40፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች 26 እና በአፋር 3) አነስተኛ የአርሶ አደር ማሳዎች ላይ የጥጥ ልማት ሠርቶ ማሳያ ሥራ ተከናውኗልም ተብሏል።

በሌላ በኩል የአጎዋ ገበያ መቋረጥ እያመጣ ያለው ተጽዕኖ ብዙ በመሆኑ የኤክስፖርት ገበያ ትዕዛዝ እንዲቋረጥ እና ገዢዎች የገበያ ትዕዛዝ መጠን እንዲቀንሱ ምክንያት በመፍጠሩ ድርጅቶች ስጋት ውስጥ መግባታቸው ተመላክቷል።

በፓርኩ የሚገኙ የውጪ መሠረት ያላቸው አምራቾች በአብዛኛው የአጎዋ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ የኢንቨስትመንት ዓላማ ይዘው የመጡ መሆኑ፣ ‹‹መንግሥት መቋቋሚያ መፍትሄ ካልፈጠረልን ጥለን እንሄዳለን›› የሚሉ ድርጅቶች መብዛት ዋና ዋና ችግሮች መሆናቸውም ተጠቅሷል።

የአገር ዐቀፍ የግብዓት ምርት ጥምረት እስኪጸድቅ ድረስ የሚጠይቀው ረጅም ጊዜ እና የምክክር ሂደት በወቅቱ የሚሠራበት ሁኔታ በእቅድ የተመሠረተ አለመሆን፤ እንዲሁም ፋብሪካዎች በጉዳዩ ላይ ያላቸው ዝግጁነት ዝቅተኛ መሆንና አስፈላጊ መረጃዎችን በሚፈለገው መልኩ ማቅረብ አለመቻላቸው ሌላኛው ተግዳሮት ነው።

ፋብሪካዎች የተከራዩበትን የሼዶችን ስፔስ በሚገባ አለመጠቀም (Poor shed utilization) እና ለካፍቴሪያ፣ ለስቶር እንዲሁም ባዶ የተተዉ ቦታዎች መብዛት ፓርኩ ይሸከማል ተብሎ የታቀደውን ያህል የሰው ኃይል መቅጠር እንዳይቻል አድርጎታል ተብሏል።
በፓርኩ የሰው ኃይል ፍልሰት መብዛት እና በፋብሪካዎች በኩልም ሠራተኞች ከሥራ እንዲሰናበቱ ማድረግ፤ ‹ከፍተኛ ሌብነት› የተስተዋለ ሲሆን፤ ለዚህም የሚጠበቀው እርምጃ እና ቅንጅታዊ ክትትል አለመኖር ተጨማሪ ክስተት ነው ተብሎ ተገልጿል።


ቅጽ 4 ቁጥር 184 ግንቦት 6 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here