የሽንኩርት ዋጋ በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች ከፍተኛ ጭማሪ እያሳየ ነው

0
1439

በአንድ ሳምንት በኪሎ ከ10 ብር በላይ ጨምሯል

በአዲስ አበባና በክልል ከተሞች የቀይ ሽንኩርት ዋጋ በአንድ ሳምንት ውስጥ ከፍተኛ ጭማሪ ማሳየቱን ሸማቾች ለአዲስ ማለዳ ገለጹ።
የአስፔዛ ዋጋ በየወቅቱ ጭማሬ እየተስተዋለበት ነው የሚሉት አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሸማቾች፣ በተለይም ቀይ ሽንኩርትና ቲማቲም ከፋሲካ በዓል መዳረሻ ወዲህ በየሳምንቱ የዋጋ ጭማሪ እያሳዩ ነው ብለዋል።

አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው ሸማቾች በአሮሚያ ክልል የሱልልታ ከተማ ነዋሪ ገነት ዓለሙ በሱልለታ ከተማ ከአንድ ሳምንት በፊት 45 ብር ሲሸጥ የነበረው አንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት ሰሞኑን 70 ብር እየተሸጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዋ ሰዓዳ መሐመድ በበኩላቸው፣ ከኹለት ሳምንት በፊት አንድ ኪሎ ሽንኩርት 40 ብር ይገዙ እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ግን ኪሎ ቀይ ሽንኩርት 50 ብር እንደገባ ነው በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን ጭማሪ የገለጹት። የዋጋ ጭማሪው በየሳምንቱ ነው የሚቀያየረው ያሉት ሰዓዳ፤ ከፋሲካ በዓል በፊት አንድ ኪሎ ሽንኩርት 40 ብር ሲሸጥ ቆይቶ በኋላ ግን ወደ 45 ብር ከፍ እንዳለና ከዚህም አልፎ ሰሞኑን 50 እንደደረሰ ተናግረዋል።

ይህን ተከትሎም በተለይም ቤተሰብ ለሚያስተዳድሩ ሰዎች፣ አስፔዛ የሚጠይቀው ዋጋ መቀያየር ብቻ የኑሮ ውድነቱን አባብሶታል ሲሉ ያለውን ችግር አንስተዋል።
የአዲስ አበባ ነዋሪ የሆኑት እቴነሽ አራጋው የአምስት ልጆች እናት እንደሆኑ ገልጸው፤ ‹‹ሦስት ራስ ሽንኩርት በ50 ብር ገዝቼ ልጆቼን እንዴት ማስተዳደር እችላለሁ?›› ሲሉ ይጠይቃሉ።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ሸማቾች እንደገለጹት የዋጋ መናር እየተስተዋለ ያለው በሽንኩርት ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አስፔዛዎች ጭምር ከጊዜ ወደ ጊዜ የዋጋ መናር እየተባባሰ ቀጥሏል።

አዲስ ማለዳ በካራ የአትክልት መሸጫ ተገኝታ የተመለከተች ሲሆን፤ ከሦስት ቀን በፊት አንድ ኪሎ ቲማቲም ከ12 ወደ 24 ብር ከፍ ብሎ እንደነበርና ከግንቦት 3/2014 ጀምሮ ደግሞ ዋጋው 18 ብር መሆኑን አረጋግጣለች። ነጋዴቹም የጭማሪው መንስኤ ምን እንደሆነ እንዳላወቁና የመረከቢያ ዋጋ እንደጨመረባቸው አመላክተዋል።

ነጋዴዎች በበኩላቸው ከሚረከቡበት ጨምሯል እንደሚሏቸው ጠቅሰው፤ እስከ አሁን ሲሸጡበት በነበረው ዋጋ ቢሸጡ እንደማያዋጣቸው አስረድተዋል።

ከቸርቻሪዎች መካካል አህመድ መሐመድ የተባሉት የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪ፤ ከአሁን በፊት አንድ ኪሎ ሽንኩርት ከ23 እስከ 26 ብር ሲረከቡ እንደነበር ጠቅሰው፤ ሰሞኑን ግን ወደ 43 ብር ከፍ ማለቱን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል። ይህን ተከትሎም በኮምቦልቻ ከተማ 43 ብር ሲሸጥ የነበረው አንድ ኪሎ ቀይ ሽንኩርት ሰሞኑን ከ55 እስከ 60 ብር እየተሸጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የዋጋ ጭማሪውን ተከትሎ አንዳንድ ቁርስ ቤቶች ሥራ ማቆማቸውንም ለማወቅ ተችሏል። ብዙአየሁ አክሊሉ የተባሉት እናት ‹‹የሚሸጥን ምግብ ያለ ሽንኩርት አጣፍጦ መሥራት አይቻልም። ስለዚህ ቁርስ ሥራዬን ትቼ ሌላውን እየሠራሁ ነው።›› ብለዋል።
ሽንኩርትን በሱቅ ለተጠቃሚው ሲያቀርቡ የነበሩ ተረካቢዎች ሰሞኑን ያለው የዋጋ ጭማሪ ከትራንስፖርት ጋር ተዳምሮ ወጪ እንጂ ትርፍ ሊያስገኛቸው ስለማይችል ማቅረብ እንዳቆሙ ገልጸዋል።

አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የንግድ እቃዎች ዋጋ ጥናት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር መስከረም ባህሩን ለማግኘት ተደጋጋሚ ሙከራ ብታደርግም ሳይሳካ ቀርቷል።


ቅጽ 4 ቁጥር 184 ግንቦት 6 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here