መነሻ ገጽዜናአቦል ዜናየነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ተከትሎ አሽከርካሪዎች በራሳቸው ፈቃድ ከግማሽ በላይ ዋጋ ጨምረዋል

የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ተከትሎ አሽከርካሪዎች በራሳቸው ፈቃድ ከግማሽ በላይ ዋጋ ጨምረዋል

ሰሞኑን የተደረገውን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ተከትሎ ከአዲስ አበባ ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የሚደረጉ ጉዞዎች ላይ አሽከርካሪዎች በራሳቸው ፈቃድ ከፍተኛ የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸውን አዲስ ማለዳ ተመልክታለች።
የተደረገው ጭማሪ በመንግሥት የተደረገ ሳይሆን አሽከርካሪዎች በራሳቸው ያደረጉት ሲሆን፣ ትራንስፖርት ተጠቃሚዎችን በሙሉ ለከፍተኛና አላስፈላጊ ወጪ እንዲሁም እንግልት የሚዳርግ ስለመሆኑ አዲስ ማለዳ ከተጓዦች ሰምታለች።

ለአብነትም አዲስ ማለዳ ከአዲስ አበባ እስከ ላሊበላ ከተማ ድረስ ያለውን መስመር የትራንስፖርት ዋጋ ለማጣራት ባደረገችው መኩራ፣ ከአዲስ አበባ ደብረ ብርሃን ቀድሞ 90 ብር የነበረው የአንድ ሰው የትራንስፖርት ዋጋ የነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ከተደረገ ጀምሮ 150 ብር ሆኗል።

በተመሳሳይ ከደብረ ብርሃን ከሚሴ ድረስ ቀድሞ ከነበረው የትራንስፖርት ዋጋ በትንሹ 50 ብር ጭማሪ የተደረገበት ሲሆን፣ ከኮምቦልቻ ደሴ 20 ብር የነበረው 30 ብር እንዲሆን ተደርጓል። ከደሴ ላሊበላ ከተማ ድረስ መደበኛ የትራንስፖርት ዋጋው 192 ብር መሆኑ የታወቀ ሲሆን፣ ከሚያዚያ 30/2014 ጀምሮ ተሳፋሪዎች 300 ብር እየከፈሉ መሆኑን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።

ከወልዲያ ላሊበላም እንዲሁ ቀድሞ የነበረው መደበኛ የጉዞ ዋጋ 120 ብር ቢሆንም በነዳጅ ዋጋ ጭማሬው ቀን ጀምሮ ከ80 ብር እስከ 150 ብር ጭማሬ ተደርጎበታል። ከላሊበላ ከተማ ባህር ዳር ድረስም እንዲሁ ከ250 ብር ወደ 300 ብር ከፍ እንዲል ተደርጎ የትራንስፖርት አገልግሎት እንደሚሰጥ ለማወቅ ተችሏል።

አዲስ ማለዳ የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሬ ከተደረገበት ከሚያዚያ 30/2014 ጀምሮ ያለውን የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ አስመልክቶ በሌሎች ከአዲስ አበባ-ባቱ(ዝዋይ)-ሻሼመኔ-ሐዋሳ፣ ከአዲስ አበባ ጅማ፣ ከአዲስ አበባ-ባህር ዳር- ጎንደር፣ እንዲሁም በሌሎች የኢትዮጵያ ከተሞችም ባደረገችው የማጣራት ሙከራ፣ እስከ ሚያዚያ 30 ድረስ በነበረው የትራንስፖርት መደበኛ ዋጋ እየጫኑ አይደለም። በትንሹ ከግማሽ በላይ የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ ተደርጓል።

ከትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪው በተጨማሪ በብዙ ቦታዎች በተለይም ከአዲስ አበባ ወደ ክፍለ አገር እና ከአንድ ቦታ ወደሌላ ቦታ በሚደረጉ ጉዞዎች፣ ጥብቅ የትራፊክ ቁጥጥር የማይደረግባቸው መሆኑን ተከትሎ፣ ከልክ በላይ በመጫን ተሽከርካሪዎች ለከፍተኛ አደጋ የተጋለጡ መሆናቸውን አዲስ ማለዳ ታዝባለች። እስከ አሁንም በትራንፖርት ዘርፉ ላይ ተደጋጋሚ ቅሬታ የሚነሳ ቢሆንም፣ ችግሩ ሲባባስ እንጂ ሲቃለል እንደማይታይ ተሳፋሪዎች ቅሬታቸውን ይገልጻሉ።

በትራንስፖርት ሚኒስቴር የመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ይርጋ ታደሰ፣ ተደርጓል ስለተባለው የትራንስፖርት ዋጋ ጭማሪ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ ገልጸዋል። ሆኖም ግን የነዳጅ ዋጋ ጭማሪውን ተከትሎ የትራንስፖርት ዋጋ ማስተካከያም እንደሚደረግ ለአዲስ ማለዳ ጠቁመዋል።

በዚህም ‹‹ንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር የዋጋ ማስተካከያ ደብዳቤ ሲደርሰን እሱን መሰረት በማደረግ በሁሉም የትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ ላይ የዋጋ ማስተካከያ ይደረጋል።›› ሲሉ ተናግረዋል።

ከሚያዚያ 30/2014 ጀምሮ በተደረገ የነዳጅ ዋጋ ክለሳ መሠረት ቤንዚን በሊትር 36 ብር ከ87 ሳንቲም፣ ነጭ ናፍጣ በሊትር 35 ብር ከ43 ሳንቲም፣ ኬሮሲን በሊትር 35 ብር ከ43 ሳንቲም እንዲሁም የአውሮፕላን ነዳጅ በሊትር 78 ብር ከ87 ሳንቲም እንዲሆን መወሰኑን የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ማስታወቁ ይታወሳል።


ቅጽ 4 ቁጥር 184 ግንቦት 6 2014

- ይከተሉን -Social Media
ተዛማጅ ጽሑፎች

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here

- Advertisment -
Ads

የቅርብ ጊዜ ጽሑፎች