የክረምቱን ዘመን መሻገሪያ ተስፋን እንሰንቅ!

0
1302

ካህሳይ ገብረእግዚአብሔር ኅብረ ብዕር ከተሰኘ ተከታታይ መጽሐፋቸው በኹለተኛው ክፍል ስለ ግንቦት ወር ሲጽፉ፣ ባህልንና ልምድን መሠረት ያደረጉ ነጥቦችን ያነሳሉ። ይልቁንም ‹በግንቦት የተቆረጠ እንጨት (ዛፍ) ይነቅዛል፣ ካልሆነም ለምስጥ ይዳረጋል› የሚለውን ብሂል መግቢያቸው አድርገው እንዲህ ይቀጥላሉ፡-

‹በግንቦት የተቆረጠ እንጨት (ዛፍ) ይነቅዛል፣ ካልሆነም ለምስጥ ይዳረጋል። ከኹለቱ ግን አያመልጥም። ሌላው ቀርቶ ጉቶው ደርቆ ይቀራል እንጂ ዝናብ ዘነበም አልዘነበ፣ በግንቦት ወር የተቆረጠ ዛፍ አያቆጠቁጥም ነው የሚባለው። ስለዚህ ‹ወርሃ ጽንጽን› ይባላል።› ይላሉ።
ግንቦት ወር ለኢትዮጵያ ልክ እንደዚህ ማኅበረሰብ እንዳለው ዕይታ ሆኖባት ያለፈባቸው ዓመታት ጥቂት አይደሉም። እንደሚታወቀው ግንቦት ወር በኢትዮጵያ ታሪክ በርካታ የሚባሉ ፖለቲካዊ ክዋኔዎች የተስተናገደበት ወር ነው። በታሪክ ውስጥ በዚህ ወር ብዙ ተስፋ የተጣለባቸው እድሎች ከሽፈዋል፤ ብዙ አዳዲስ መንገዶች ተጀምረው ቀርተዋል። ደግሞም ዛሬም ድረስ የቀጠሉ የቀደሙ ዘመናት የግንቦት ወር ውጤቶች አሉ።

በአንዳቸውም ግን ለኢትዮጵያ የዘለቀ ለውጥ አልመጣላትም። ይልቁንም ተጀምሮ የቆመ፣ የነበረውን ያስጣለ ወይም አዲስ ጅምርን የጠለፈው ብዙ ነው። ባይሆን የዘለቀውና የከረመው፣ ዛሬም ድረስ የቆየው ትዝታና የ‹ኖሮ› ተረክ ብቻ ተርፏታል። እንዲህ ሆኖ ቢሆን ኖሮ፣ እንዲህ ተደርጎ በነበረ ኖሮ!

በግንቦት ወር ኢትዮጵያን በተለያየ መልክና አሠራር የመሯት መሪዎች ተወልደዋል፣ በግንቦት ወር የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተደርጓል፣ የውጫሌ ውል የተፈረመው በግንቦት ወር ነው፣ የአንዱ መንግሥት መውደቅ ሲጻፍ፣ ሌላው በዚሁ ወር የድል ቀኔ እያለ ወደ አገር አስተዳዳሪነት የተሻገረበትን እለት ያከብራል። በግንቦት ወር እንደ ጸሎት መጽሐፍ ቃል ዛሬ ድረስ የሚደጋገመው ምርጫ 97 ተካሂዷል። በዚሁ ወር በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተሳትፈዋል የተባሉ ተገድለዋል። ሌላም ብዙ ብዙ።

ግንቦት የሹመት የሽረት፣ የልደትና የሞት፣ የነውጥና የለውጥ፣ የደስታና የሀዘን…ማዶ ለማዶ አንጻር ላይ ያሉ ክስተቶች በብዛት የተስተናገዱበት ወር ነው። ዛሬስ? በዚህኛው ዘመን የግንቦት ወርስ ኢትዮጵያ የት ናት? አዲስ ማለዳ ትጠይቃለች።
የዛሬዋ ኢትዮጵያ በግንቦት ወር እንደ ወትሮው ሁሉ በቆየ አገራዊ ፈተና ውስጥ ናት። በታሪክ ጎልተው እንደሚታዩት የግንቦት ወራት ጉዳዮች ሁሉ፣ ዛሬም እድሎችና ፈተናዎች አሏት።

ሲፈራለትና እንደ እንቁላል በስስት ሲታይ በነበረው ከአራት ዓመት ገደማ በፊት በመጣው ‹ለውጥ› ሰሞንም ‹ይህ እድል እንዳያመልጠን› የሚሉ ማሳሰቢያዎች በተደጋጋሚ ሲሰሙ ነበር። በኋላ እድሉ ማን ጋር እንደተቀመጠና ምን ሁኔታ ውስጥ እንዳለ እንኳ መለየት አስቸግሮ ነበር። አሁን ላይ ደግሞ በእርግጥ እድሉን ያለመጠቀም ነው ወይስ በአመራር በኩል የተፈጠረ ክፈተት የሚለው የተለየ ባይሆንም፣ እድሉ ተወደደም ተጠላ ከበርካታ ፈተናዎች ጋር አብሮ ቀርቦ እድል እንደነበር ራሱ የተረሳበት ደረጃ ላይ ደርሷል።

አሁን ኢትዮጵያ በሁኔታዋም በወቅቷም በሰኔ ወር ዋዜማ ላይ ናት። በአንድ ወገን ምርጫና እድል አላት፣ በሌላ በኩል ከባድ ፈተና ይጠብቃታል። ሰኔ የደመና፣ የዝናብ ወቅት ነው። ይህ አንድም በመከራ ይመሰላል። ዝናብ ምድርን የሚያረሰርስ ቢሆንም ደመናው ፀሐይና ብርሃንን የሚጋርድ፣ ሰማዩም መብረቅ የማያጣው አስጨናቂ ስለሆነ ነው ሰኔ ጽናትን በሚፈልግ ፈተና የሚመሰለው።

የኑሮ ውድነት፣ ነጋሪቱ እየተመታ ያለውና እንደ አዲስ ሊጀምር እንደሚችል የሚያሰጋው የሰሜኑ ጦርነት፣ የተፈናቃዮች በዛም በዚህም ማረፊያ አጥቶ መሰቃየት፣ የሕዝቡን ማኅበራዊ ሕይወትና ትስስር ለመፈተን እንደተሞላ የስልክ ደወል እየቆዩ የሚከሰቱ፣ አንዴ ሀይማኖትን ደግሞ ብሔርን መሠረት እያደረጉ የሚነሱ ግጭቶችና አለመግባባቶች፤ ሁሉም የፊታችን የሰኔ አካል ክፍሎች እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

አሁን ሁሉም በየድርሻው እንደየድርሻው ሊሠራ የሚጠበቅበት ሰዓት ነው። መንግሥት እንደ መንግሥትነቱ፣ ሕዝብም እንደ ሕዝብ፣ የሃይማኖት ተቋማት እንደ አስተምህሮአቸው…ሁሉም እንደየድርሻው ትክክለኛውን ሚና ሊወጣ ይገባል። ነገሮች የሚስተካከሉትና መጪውን ሰኔ፣ ከዛም እየበረቱ የሚመጡትን ሐምሌና ነሐሴን መሻገር የሚቻለው በዛ መልክ ብቻ ነው።

ሰከን ብሎ ማሰብ ከሁሉም እንደሚጠበቅ አዲስ ማለዳ በጽኑ ታምናለች። ሰከን ማለት ሲባል፣ በመንግሥት በኩል አንደኛ ‹ግመሎቹ ይሄዳሉ፣ ውሾች ይጮኻሉ› የሚለውን ብሂል መቼ መጠቀም እንዳለበት በሚገባ ሊያውቅ ይገባል። ዝምታ መልስ የሚሆንባቸው ጉዳዮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ይታሰባል። ነገር ግን መንግሥት ኃላፊነት በተረከበበት የሕዝብ ደኅንነት ጉዳይ ላይ ዝምታ ከቸልተኝነትና ከግዴለሽነት የሚቆጠር ነው። እናም በዚህ ከቀጠለ ሰኔን አያሻግርም።

ሕዝብም እንደ ሕዝብ ማስተዋል፣ በስሜት አለመነዳትና በመንጋ አለማሰብ ይጠበቅበታል። ‹ሕዝብ አይሳሳትም› የሚለው አባባል ትክክል ነው ከተባለ፣ ስህተቱን ሁሉ ትክክል ነው እያለ የመሄድ ሥልጣን አለው እንደማለት ነው። ይህ ደግሞ አይሆንም። ስለዚህ ሕዝብ ያለውን ኃይልና አቅም በማወቅ፣ ያም ለጥፋት ሳይሆን አገር ለመታደግ ይውል ዘንድ በማስተዋል ሊራመድ ይገባል። ሕዝብ እንዲስተካከል ደግሞ የሁሉም የእያንዳንዱ ሰው ማስተዋል ማስፈለጉ አያጠራጥርም፤ ያ ነው ኢትዮጵያ ሰኔን እንድትሻገር የሚያስችለው ኃይል።

የሃይማኖት ተቋማትም በዚህ ልክ ኃይላቸውን ተቀምተው ‹አቅመ ቢስ› ሆነው መታየት የለባቸውም። ባደላቸው አገራት የሀይማኖት ተቋማት በፓርላማ ውስጥ ወንበር አላቸው። በእነርሱ ላይም ሆነ እነርሱን በሚመለከት የሚወሰን ውሳኔ ይመለከታቸዋል። ‹ገናን በአገር ቤት፣ ከዒድ እስከ ዒድ› ወዘተ የሚሉ ‹መርሃ ግብሮችን› ጭራሽ በመንግሥት አቅጣጫ ተቀብለው አሜን የሚሉ ሊሆኑ አይገባም።

እነዚህ ተቋማት ትልቅ አቅም ያላቸው እንደመሆኑ፣ መንግሥት እንካችሁ የሚላቸውን ሁሉ መቀበል የለባቸውም። በምትኩ ምን እንጠየቃለን ብለው ማሰብ ይጠበቅባቸዋል። በየአንዳንዳቸው ላይ እየደረሰባቸው ያለውን ጥፋት ተመልክተው ኅብረት ሊፈጥሩ ይገባል። ግባቸውንም ማወቅና መለየት አለባቸው።

መንግሥትን በሀይማኖት ተቋማት ጉዳይ ጣልቃ አትግባ ከማለት ይልቅ፣ የሀይማኖት ተቋማት መንግሥት ጣልቃ እንዳይገባ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ማሳሰብ ይቀላል። ምክንያቱም መንግሥት የሀይማኖት ተቋማት ያላቸውን አቅም የማያውቅ አይደለምና ክፈቱልኝ ልግባ ማለቱ እንደማይቀር እሙን ነው።

ከዚህ በተጓዳኝ የሃይማኖት ተቋማት የውስጥ ችግራቸውን ጠራርገው ለምዕመኑም ለአገርም የሚጠቅሙ መሆንና መንግሥትም በስውር እጁን ሊያስገባ ቢሞክር በግልጽ የሚታይበትን ስርዓት ማበጀት ያስፈልጋቸዋል። ይሄኔ የሁሉም ምዕመን እምነት እና ተስፋን ሰንቆ፣ ሁሉም እለት እለት የሚጸልዩላት ኢትዮጵያ ሰኔን እንድትሻገር ትሆናለች።

ከዛ ባለፈ በ‹መንግሥት ነን› ሥ የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦችም ሃይ ባይ ያስፈልጋቸዋል። መንግሥት የቀጠራቸውን ሠራተኞች፣ የሾማቸውን ሹማምንት መከታተል አለበት። በየወረዳውና በየክፍለ አገሩ እጃቸው ቆሽሾና ‹አሸባሪ› ከተባለ ቡድን ባልተናነሰ እያጠፉ የሚገኙት ‹እኔን አይወክሉኝም› የሚልበት እድል የለውም። ይልቁንም ከታች እስከ እላይ መዋቅሩን ማጽዳት ይጠበቅበታል። ይህም ሊሆን ካልቻለ ኢትዮጵያዊያን ሰኔን የሚሻገሩበት ስንቅ አያገኙም።

አዲስ ማለዳ የሚሰማ የለም ብሎ ዝም ማለት ተገቢ አይደለም ትላለች። ለዚህም ነው ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትንና የሚጠብቃትን ክረምት የሆነ ፈተና የምትሻገርበትን ስንቅ ተስፋ ሁሉም እንዲያከማችና ውጤቱን ለማግኘት በተግባር ወደየእርሻው እንዲሰማራ የምትጠይቀው። እርሻው ሁሉም የተሰማራበት የየራሱ መስክና የተረከበው ድርሻ ነው።


ቅጽ 4 ቁጥር 184 ግንቦት 6 2014

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here