ማክሰኞ ግንቦት 9 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) የማዕከላዊ ዕዝ በአገራችን ሉዓላዊነት ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩ አሸባሪዎችን መደምሰስ በሚያስችል ወታደራዊ ቁመና ላይ እንደሚገኝ በዕዙ የአመራር ሥልጠና ላይ ተገለፀ።
ማዕከላዊ ዕዝ “ስልጠና ለተሻለ የግዳጅ አፈፃፀም” በሚል መርህ በተሠጠው የአመራር ሥልጠና በምንም የማይበገር አዋጊና ተዋጊ አባላት ማፍራት እንደተቻለ የዕዙ ዋና አዛዥ ሌ/ጀኔራል ዘውዱ በላይ አረጋግጠዋል።
“በሳል አመራር ብቁ ተዋጊ የሠራዊት አባላትን ለማፍራት አይቸገርም።” ያሉት ጀኔራል መኮንኑ የማዕከላዊ ዕዝ አመራሮች የሠራዊቱን ሞራላዊና ሥነ ልቦናዊ ዝግጁነት በመገንባት ለማንኛውም ግዳጅ ዝግጁ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል።
“ዕዙ በአሁኑ ሰዓት የታጠቀው መሣሪያ ብቻ ሳይሆን የአሸናፊነት ሥነ ልቦና ጭምር ነው” ያሉት ደግሞ በዕዙ የኮር ዋና አዛዥ ብ/ጀኔራል ተስፋዬ ረጋሳ በሥልጠና የተገኘውን የተሟላ ዝግጁነት አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባ ገልፀዋል።
የማዕከላዊ ዕዝ በተሰጠው የግዳጅ ቀጣና በአገራችን ላይ ጥቃት የሚሰነዝሩ አሸባሪዎችን መደምሰስ በሚያስችለው አስተማማኝ የዝግጁነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝም መገለፁን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።
____
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n






