በዩኔስኮ የተመዘገበው የማጃንግ ጥብቅ ደን በህገ ወጥ ግለሰቦች ጭፍጨፋ እየተካሄደበት መሆኑ ተገለፀ

0
984

ማክሰኞ ግንቦት 9 ቀን 2014 (አዲስ ማለዳ) በጋምቤላ ክልል ማጃንግ ብሄረሰብ ዞን የሚገኘው የማጃንግ ጥብቅ ደን በህገ ወጥ ግለሰቦች ጭፍጨፋ እየተካሄደበት መሆኑ ተገለፀ።

ከአራት ዓመታት በፊት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የተመዘገበው ጥብቅ ደኑ በአሁኑ ሰዓት ህልውናው አደጋ ላይ መውደቁ ነው የተነገረው።

የጎደሬ ወረዳ የካቢኔ አባላት እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በህገ ወጥ ግለሰቦች የተጨፈጨፈውን የማጃንግ ደን ባዮስፌር ሪዘርቭ በቦታው በመገኘት ተመልክተዋል።

የጎደሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ይሳቅ አብርሃም እንደተናገሩት፤ አንዳንድ ጊዜያዊ ጥቅም ፈላጊ ህገ ወጦች እያደረሱ ባሉት የደን ጭፍጨፋ ተፈጥሮአዊ ደኖች በመመናመን ላይ ናቸው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በህገወጥ ደን ጨፍጫፊዎች ምክንያት ከ300 እስከ 400 ዓመት የሆናቸውን እድሜ ጠገብ የተፈጥሮ ዛፎችን ጨምሮ በከፍተኛ ሁኔታ ጭፍጨፋ በማካሄድ የደኑ ህልውና አሳሳቢ ሁኔታ ላይ እንዳለ በጉብኝታው ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል።

በመሆኑም በፍጥነት እየተካሄደ የሚገኘውን ወረራና የደን ጭፍጨፋ ለመከላከል ወራሪዎቹን የመለየት ፣ ከጥብቅ ደኑ ይዞታ የማስወጣትና በህግ ተጠያቂ የማድረግ ሥራ እንደሚሰራም ገልፀዋል።

የጎደሬ ወረዳ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት ሀላፊ ካድሬ አበበ በበኩላቸው፤ በዩኒስኮ የተመዘገበውን የማጃንግ ደን ባዮስፌር ሪዘርቭ በደላሎች አማካኝነትና በጥቂት ግለሰቦች ስግብግብነት በድብቅና ጨለማን ተገን በማድረግ ደኑን በመጨፍጨፍ ህልውናውን አሳሳቢ ደረጃ ላይ አድርሰውታል።

ስለሆነም አግባብነት በሌለው መንገድ የሚፈፀሙ ህገ ወጥ የደን ጭፍጨፍዎች ለአንድ ሴክተር እና ለተወሰነ አካል ብቻ የሚሰጥ ሳይሆን ማህበረሰቡ እና ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ልንከላከላቸው እና ልንታገላቸው ይገባል ሲሉም ማሳሰባቸውን ከጋምቤላ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

በህገ ወጥ ደን ጨፍጫፊዎች በጎደሬ ወረዳ ውስጥ ጉዳት ከደረሰባቸው ቀበሌዎች መካከል ነሪ፣ ሰንቲ ንዑስ፣ ገንገበቲ፣ ዱንቻይ፣ ጎንች ጌለሻ ይገኙበታል።

በማጃንግ ባዮስፌር ሪዘርቭ ውስጥ 550 የሚደረሱ የእፅዋት ፣ከ180 በላይ የአእዋፍ ፣ 33 የአጥቢ እንሰሳትና 20 ተሳቢ እንሰሳት ዝርያዎች እንደሚገኙ መረጃዎች ያመለክታሉ።
______________________________
ትክክለኛውን የአዲስ ማለዳ ሶሻል ሚዲያ በመቀላቀል ቤተሰብ ይሁኑ
Telegram ➲ t.ly/SOXU
Facebook ➲ t.ly/flx8
YouTube ➲ t.ly/vSgS
Twitter ➲ t.ly/mxA4n

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here