የመጀመሪያው የዐቢይ ቃለ ምልልስ ሲፈተሽ፤አምባገነን እየፈጠርን ይሆን?

0
1032

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመጀመሪያ አንደ ለአንድ ቃለ ምልልሳቸውን በየካቲት ወር 2011 ‘ፋይናንሻል ታይምስ’ ከተባለ ጋዜጣ ጋር አድርገው ነበር። በኃይሉ ሽፈራው ቃለ ምልልሱን በጥሞና ከተመለከቱት በኋላ ‘አምባገነን እየፈጠርን ይሆን?’ በማለት በምሣሌ ይሞግታሉ።

‘ፋይናንሺያል ታይምስ’ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር ያደረገውን ቃለ ምልልስ በድረገጹ እንዳተመ አንድ ጎበዝ ታዛቢ “አንድ ለአንድ የሚደረጉ ቃለ ምልልሶች ብዙ ነገር ይገልጣሉ” የሚል ለትርጉም ክፍት የሆነ ትዝብቱን በትዊተር አካውንቱ ጻፈ። ቃለ ምልልሱ ምንን ገለጠ? ስልታዊስ ነበር ወይ? በዚህ ጽሑፍ ልመልሳቸው የምሞክራቸው ጥያቄዎች ናቸው።

ቃለ ምልልሱ የገለጠው የመጀመሪያው ነገር ዐቢይ እስካሁን የተከተሉት ማኅበራዊ ድረገጾቹን በዋናነት በመጠቀም (በተለይ ከውጭ መገናኛ ብዙኃን ጋር የሚደረግ) አንድ ለአንድ ቃለ ምልልስን የመሸሽ ስልት ትክክለኛ እንደ ነበር ነው። ኹለተኛ የመጀመሪያ ቃለ ምልልሳቸው እንደመሆኑ መጠን የመገናኛ ብዙኃን ምርጫውም ሆነ ቃለ ምልልሱን ያስተናገደበት መልክ ትክክል እንዳልነበር ነው። ሦስተኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ከልክ በላይ እያንቆለጳጰስን አዲስ አምባገነን እየፈጠርን ሊሆን እንደሚችል አመላካች ምልክቶችን ነው። አንድ በአንድ እንያቸው።

የአንድ ለአንድ ቃለ ምልልሶችን መሸሽ
ሰውየው መስህብ አላቸው። አንደኛ እጅግ የሚበረታቱ ቀዳሚ እርምጃዎችን ወስደዋል። ኹለተኛ እነዚያ የመጀመሪያ እርምጃዎች በዋናነት የሕዝብ አመለካከት ቀራጮች የሆኑትን የፖለቲካ፣ የመገናኛ ብዙኃንና የሲቪክ ማኅበረሰብ ልኂቃን ተቀዳሚ ተጠቃሚ ያደረጉ ስለነበሩ፥ እኛም በቻልነው መጠን፣ በሔድንበት ሁሉ ስለ እርሳቸው መልካም መልካሙን በማውራት ጥሩ ሥም ገንብተንላቸዋል። ገና መንፈቅ ሳይሞላቸው ለኖቤል ሽልማት ያጨናቸው ሁሉ ነበርን። ስለዚህም የዓለም መገናኛ ብዙኃን እኚህን ሰው ሊያገኙና ሊያናግሩ ቢጥሩ የሚገርም አይደለም። ቃለ ምልልስ ማድረጉም የጊዜ ጉዳይ ነበር። ‘ፋይናንሺያል ታይምስ’ ግን ስልታዊ ምርጫ ነበር ወይ? ዐቢይስ ፈተናውን ተወጥተው ከዚህ በፊት ከገነቡት ማንነታቸው ጋር የማይጋጭ ቋሚ ስብዕና አንፀባርቀውበታል ወይ? የሚሉት መመለስ አለባቸው።

የመገናኛ ብዙኃን ምርጫው
‘ፋይናንሺያል ታይምስ’ን እንደ የመጀመሪያ የቃለ ምልልስ መድረክ መምረጣቸው ትክክል ነበር ወይ? የሚለውን ለመመለስ ኹለት ነገሮች ማየት ይጠይቃል። የመጀመሪያው የቀረቡላቸውን አማራጮች በሙሉ ማየትና ማመዛዘን ነው። እንደዚያ ዓይነት መረጃን ማግኘት ስለማንችል ሌላ ሚዛን ለመጠቀም እንገደዳለን። በዚህ በኹለተኛው ሚዛን የመገናኛ ብዙኃን ምርጫቸውን ትክክለኛነት ለመተቸት የጋዜጣውን የትኩረት አቅጣጫ እና የዐቢይን ጥንካሬዎች ማነፃፀር ያስፈልጋል። ‘ፋይናንሺያል ታይምስ’ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የሚታወቀው እንደ ሥሙ በፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ነክ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ዘገባዎችን በማቅረብና ዓለም ዐቀፍ የፋይናንስ ፖሊሲ አውጭዎች እና ውሳኔ ሰጭዎች ላይ ሙያዊ ተፅዕኖ በመፍጠር ነው። በዓለም ትላልቅ የፋይናንስ ዘርፍ ውሳኔ ሰጭዎች ዘንድ ሕትመቶች ያላቸውን ተነባቢነት የሚለካው ‘Global Capital Markets Survey’ እንደሚያሳየው ‘ፋይናንሺያል ታይምስ’ ከ‘ዎል ስትሪት ጆርናል’ ጋዜጣና እና ‘ዘ ኢኮኖሚስት’ መጽሔትም ይልቅ በብዙ የፋይናንስ ውሳኔ ሰጭዎች የሚነበብ ዕለታዊ ጋዜጣ ነው። የጋዜጣው የትኩረት አቅጣጫ ከታወቀ ቀጣዩ ጥያቄ ፋይናንስ እና ኢኮኖሚ ከዐቢይ የሥራና የትምህርት ዝግጅት አንፃር ጠንካራ ጎኖቹ ናቸው ወይ? የሚለው ነው። አይደሉም።

ይህን ለማየት ብዙ ማሰላሰል አያስፈልግም። ጋዜጠኞቹ መርጠው ጽሑፉ ውስጥ ካካተቷቸው ከዐሥራ ስድስቶቹ የዐቢይ ምላሾች (በትዕምርተ ጥቅስ ውስጥ የገቡና ከሌላው በአራት ነጥብ የተለዩት እንደ አንድ ተቆጥረው) ውስጥ አንዳቸውም የአገሪቱን ፋይናንስ፣ ኢኮኖሚ ወይም የዕድገት ሁናቴ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ ማስረዳት አልቻሉም። እንደ ኢኮኖሚ ዕድገት እና የውጭ ዕዳ ያሉ ሙያ ነክና ተቆጣሪ (quantifiable) እውነታዎችን እንኳን “ቢግ ቢግ ቼንጅ”፣ “የዕዳው ክምር ሊገድለን ነው” እና “ዕዳው እዚህ ጋር ደርሷል (አንገታቸውን እየጠቆሙ)” በሚሉ ጥቅል ቋንቋዎች ሲገልጽ ተስተውሏል። ስለቤተ መንግሥቱ እድሳት እያወሩ “ይህን ግቢ (ቤተ መንግሥቱን መሆኑ ነው) መቀየር ከቻልክ አዲስ አበባን ትቀይራለህ። አዲስ አበባን መቀየር ከቻልክ ደግሞ ኢትዮጵያን ትቀይራለህ” የሚል ‘ትንታኔ’ ሲያቀርቡ እናገኛቸዋለን። ወደ መጨረሻም “60 እና 70 ሚሊዮን ሕዝብ ከድህነት አረንቋ ካወጣሁ ወደድኩም ጠላሁም ሥሜን ታገኑታላችሁ” ብሏቸዋል። በማዕከላዊ የስታቲስቲክስ ባለሥልጣን መረጃ መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ ከድህነት ወለል በታች ያሉት ሰዎች ጠቅላላ ቁጥር ዐቢይ ከጠሩት አሐዝ ግማሽ አካባቢ (30-35 ሚሊዮን) የሚገመት ነው። ጋዜጠኞቹ ያንን የተጨባጭ ዕውቀት ቀዳዳ ለመሙላት መጀመሪያ ወደ ትውልደ ኢትዮጵያዊው ዘመዴነህ ንጋቱ (ዶ/ር) ከዚያም ደግሞ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ፖሊሲና የዕድገት አቅጣጫ ከእስያውያን ተምሣሌቶቻችን ጋር አስተያይቶ የተሻለ የሚያስረዳ ምሁር ፍለጋ ወደ ኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ ለመሔድ ተገደዋል።

 

የዱር እንስሳትን ዝርያ ከምድረ ገጽ ከመጥፋት ለመታደግ ካልሆነ በስተቀር ነጻነታቸውን ነጥቆና በብረት አጥሮ ለመዝናኛነት መጠቀም በአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ተግባር እየሆነ እንደመጣ የተረዱ የማይመስሉት ዐቢይ፥ እስከ 250 ድረስ የዱር እንስሳት የሚኖሩበት አነስተኛ ፓርክ በማደራጀት ቤተ መንግሥቱን ዘመናዊ የቱሪስት መስህብ ሊያደርጉት እንዳቀዱም ለጋዜጠኞቹ ነግረዋቸዋል

 

ሞያዊ ምክሬ ሥልጣን ከተያዘ በኋላ መጀመሪያ የሚደረጉ ቃለ ምልልሶች መሪዎች በተቻለ መጠን ራሳቸውንና ርዕያቸውን ከዓለም ጋር የሚያስተዋውቁበት፣ ገጽታቸውንም የሚገነቡበት ዕድል ስለሆነ በከፍተኛ ጥንቃቄ መመረጥ አለባቸው የሚል ነው። የመጀመሪያ ቃለ ምልልሶች መሪዎቹ ዘና ብለው በሙሉ ራስ መተማመን በሚናገሩባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ቢደረጉ የበለጠ ስልታዊ ይሆናል። ይህ ብቸኛው ቀመር ነው ማለት ግን አይደለም።

ፕሬዚደንት ኦባማ ለምሳሌ ትላልቆቹ አሜሪካውያን ቴሌቪዥን ኔትዎርኮች እየጠበቋቸው ተቀዳሚ የዓለም ዐቀፍ ግንኙነት ፖሊሲው መካከለኛው ምሥራቅ እንደሆነ ለማሳየት የመጀመሪያዎቹን አራት ኦፊሴላዊ ስልኮች የደወሉት ወደ መካከለኛው ምሥራቅ መሪዎች እንደሆነው ሁሉ፥ የመጀመሪያ ቃለ ምልልሳቸውን የሰጡትም ለዱባዩ ‘አል አረቢያ’ ቴሌቪዥን ኔትወርክ ነበር። ለ‘አል አረቢያ’ ቃለ ምልልስ በሰጡ ማግስትም የመጀመሪያ ልዑካቸውን ጆርጅ ሚሸልን ወደ ካይሮ ልከው፣ የዓለም ዐቀፍ ግንኙነታቸው ቀዳሚ አጀንዳ ምን ሊሆን እንደሚችል የጠቆመበት አካሔድ በወቅቱ በጋዜጠኝነት ውስጥ ወይም ጋዜጠኝነትን በመማርና ማስተማር ውስጥ የነበርን ሰዎች የምናስታውሰው ነው።

ጋዜጠኞቹ ምን ተሰማቸው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአዲስ መልክ የተዋበውንና ጋዜጠኞቹ በማሽሟጠጥ ‘white, of course’ ያሉትን የዳግማዊ ምኒሊክ ቤተ መንግሥት ራሳቸው እያዞሩ በማስጎብኘትና አሁንም ጋዜጠኞቹ “በአብዛኛው በምዕራቡ ዓለም የተማሩ ወጣት ሠራተኞች” ያሏቸውን፥ ዐቢይን የከበቡ አዳዲስ ልኂቃን እንደ ኤግዚቢት በማቅረብ በጋዜጠኞቹ ዘንድ ለራሳቸውና ለአስተዳደሩ መልካም ምስል ለመፍጠር ሞክረዋል። የዱር እንስሳትን ዝርያ ከምድረ ገጽ ከመጥፋት ለመታደግ ካልሆነ በስተቀር ነጻነታቸውን ነጥቆና በብረት አጥሮ ለመዝናኛነት መጠቀም በአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾች ዘንድ ተቀባይነት የሌለው ተግባር እየሆነ እንደመጣ የተረዱ የማይመስሉት ዐቢይ፥ እስከ 250 ድረስ የዱር እንስሳት የሚኖሩበት አነስተኛ ፓርክ በማደራጀት ቤተ መንግሥቱን ዘመናዊ የቱሪስት መስህብ ሊያደርጉት እንዳቀዱም ለጋዜጠኞቹ ነግረዋቸዋል። ነገር ግን ዳግማዊ ምኒሊክ ሥልጣን ላይ ከመውጣታቸው በፊት የተመሠረተው አንጋፋ ጋዜጣ፣ አንጋፋ ጋዜጠኞች እንዲህ በቀላሉ የሚማልሉ አይደሉም። በወቅቱ ምን ዓይነት ምላሽ እንደነበራቸው መገመት አንችልም። ትዝብታቸው በጽሑፋቸው ውስጥ በምን መልኩ ተንፀባርቋል የሚለውን ግን የሚከተሉት ማስረጃዎች በማቅረብ ማሳየት ይቻላል።

ምሣሌ አንድ፣ ‘In an act of political theatre, he leads the FT on a tour of the prime ministerial grounds…’ (የፖለቲካ ቲአትር በሚመሰል መልኩ ጋዜጠኞቹን ራሳቸው እየመሩ ቤተ መንግሥቱን ‘ፋይናንሻል ታይምስን’…)
ምሣሌ ኹለት፣ ‘…since he was catapulted to the premiership last April…’ (ባለፈው ሚያዚያ ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ተወንጭፈው ከወጡ ጀምሮ…)
ምሣሌ ሦስት፣ ‘…he alternates between homespun prophet, hard man and visionary leader’ ([በባሕሪያቸው] ቀለል ያለ ነቢይነት፣ ብርቱ ሰውነት እና ባለ ራዕይ መሪነት መካከል ይመላለሳሉ)
ምሣሌ አራት፣ ‘Such bravado aside,’ (‘ብራቫዶ’ ማለት ለማስፈራት ወይም ለማማለል የሚደረግ ሙከራ ነው (ጉራ ላለማለት ነው)… ጋዜጠኞቹ ያንን ሙከራቸውን እንተወውና ማለታቸው ነው።)

የዐቢይ ማንነት ተውነታዊ ወይስ እውነተኛ?
ከላይ ከተጠቀሱት አራት ምሣሌዎች ውስጥ ሦስቱ አገላለጾች (ፖለቲካዊ ቴአትር/ተውኔት፣ በሦስት ሰብዕና ውስጥ መመላለስ እና ‘ብራቫዶ’ የሚሉት ባሕርያት በውስጣቸው አልፎ የሚያገናኛቸው አንድ ክር አለ፤ ትወና የሚል። እውነት ዐቢይ የተተወነ ገጸ ባሕርይ ናቸው? ከሰሞኑ ካለ ጽሑፍ ሲናገሩ የሚሰጧቸው መልሶች በቃለ ምልልሱ ውስጥ ከተናገሯቸው ጋር ሲደመሩ ጥያቄ ማንሳቱ ተገቢ ነው። ለምሳሌ በዚህ ቃለ ምልልስ ቢሮዬ ድረስ የመጡትን ወታደሮች፥ “እኔም ወታደር እንደሆንኩ አሳየኋቸው። ነገሮች ከተበላሹም አምስት፣ ስድስታችሁን ሳልገድል አልሞትም” አልኳቸው ያሉት ዐቢይ ትናንት “መግደል መሸነፍ፣ መግደል ፈሪነት ነው” ያሉን ዐቢይ ናቸውን? ብለን እንድንጠይቅ እንገደዳለን። በመጀመሪያዎቹ ንግግሮቻቸው ውስጥ አንስተው የማይጠግቧቸው ‘ኢትዮጵያ’፣ ‘ኢትዮጵያዊነት’ እና በተለይም ‘ኢትዮጵያዊያን/ት’ የሚሉ ቃላት በቃለ ምልልሱ ውስጥ ‘እኔ’ እና ‘የእኔ’ በሚሉ ቃላቶች ተተክተዋል። ለምሣሌ በጽሑፉ ውስጥ በቀጥታ በትዕምርተ ጥቅስ የተለዩትን ብቻ ስንቆጥር 16 የዐቢይ ምላሾች ሰፍረዋል። በእነዚህ ምላሾች ውስጥ 24 ጊዜ ‘እኔ’ (22 “I”s and 2 “me”s)፣ ኹለት ጊዜ ‘የእኔ’ (2 “my”s) የሚሉትን ቃላት የተጠቀሙ ሲሆን፥ ‘ኢትዮጵያ’ የሚለውን ቃል ኹለት ጊዜ፣ ‘ኢትዮጵያዊያን’ የሚለውን ደግሞ አንድ ጊዜ ብቻ አንስተዋል። ይህ አንዴ የተጠቀሰውም “ብዙ ኢትዮጵያዊያን ትናንትናን ያያሉ፤ እኔ ነገን እመለከታለሁ” በሚል ሁሉንም በአንድ ጨፍላቂ ዐውድ የጠቀሱበት ነው።

አምባገነን እየፈጠርን ይሆን?
“His words may sound boastful, not to say arrogant, the sorts of qualities that have led many a leader in the past to cultivate a cult of personality.” ሲተረጎም “ቃላቶቹ መታበይን ሊያሳብቁ ይችላሉ። እንደዚህ ዓይነት ባሕርያት ናቸው ብዙ ያለፉ መሪዎችን ወደ አይነኬ ሰብዕና ግንባታ የቀየሯቸው” ብለዋል ጋዜጠኞቹ በሌላው ትዝብታቸው።

ምን ጊዜም ለውጥ የሚመጣው በብዙኃኑ ትግል ነው። ሽግግርን የሚመራው ግን ልኂቃኑ ነው። እጅግ ብዙ ትንታኔዎችና እርምቶች በመስጠት ሽግግሩን ሊያግዙ፣ ለውጡን አቅጣጫ ሊያስይዙ ይችሉ የነበሩ ወጣት ልኂቃን ወደ አዳዲስ የቤተ መንግሥት አካባቢ ገድል ጸሐፊነት ተቀይረው ድምፃቸውን አጥተዋል። ይህም አገራችንን ዋጋ ያስከፍላታል የሚል ስጋት አለኝ። የሴቶችን ተሳትፎና እኩልነት ለማረጋገጥ በመታገል የምናውቃቸው ሰዎች በተገኙበት፥ በእርቅ ኮሚቴ ውይይት መድረክ ላይ በኮሚቴው ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ አንሷል ተብሎ በባልደረባቸው የተነገራቸው ዐቢይ ሲመልሱ፥ “…ሴቶች እስካሁን ኢትዮጵያ ላይ የነበሩት ዐሥር ናቸው፤ ዐሥሩም ሚኒስትር ሆኑ። የተቀሩ ዐሥር ተገኙ፤ ዐሥሩን እዚህ አስገባን።…” ብለው ሲናገሩ በይፋ ወጥቶ “ተዉ!” የሚላቸው ሰው የጠፋው፥ ሒስ ሊያቀርቡ ይችሉ የነበሩ ልኂቃኖችን የአስተዳደራቸው ሠራተኞች ወይንም ተጠባባቂ ወንበር ላይ ያሉ ተስፈኞች አድርገው ስላስቀመጧቸው ነው። ፕሬስ ሴክሬተሪዋ ቢልለኔ ሥዩም ዐቢይ ሥልጣን በያዙ በመጀመሪያዎቹ ኹለት ወራት ውስጥ የሴቶች እኩልነት ማረጋገጥን የተመለከተ ግልጽ ደብዳቤ ለራሳቸው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እስከ መጻፍ የደረሱ የማከብራቸው ‘ፌሚኒስት’ ናቸው።

ዐቢይ ወደ ቢሮው ጠቀለላቸው እና ድምፃቸውን ነጠቃቸው እንጂ፥ በኢትዮጵያ አቅም ያላቸውን ሴቶች ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጣታቸው ሊቆጥሯቸው ሲዳዳቸው ውጭ ሆነው ቢሆን ኖሮ አቅም ባለው ብዕራቸው ይመልሱለት ነበር። አንዴ ሥራው ውስጥ ስለገቡ አልፈርድባቸውም። ምናልባትም አሁን ባሉበት ቦታ ያስፈልጉናል። ነገር ግን ይህ የአብዛኞቹ ልኂቃኖቻችን ዕጣ ፈንታ ከሆነ ለሐሳብ ብዝኃነት እንደትልቅ ስጋት እቆጥረዋለሁና ቢታሰብበት!

ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here