ክብረ ዓደዋ የካቲት ፳፫ – ፲፰፻፹፰

0
722

በቅኝ ግዛት ዘመን ‹‹አፍሪካን መቀራመት›› የሚል አጀንዳን ያነገቡ የአውሮፓ ኃያላን አገራት ባህር አቋርጠው ፣ ጦራቸውን ሰብቀው ፣ ህያዋንን እየፈጁ አፍሪካ ላይ ከተሙ። ይሁን እንጂ ወደ ምሥራቅ አፍሪካዊቷ የአናብስት ምድር ዓይኑን የጣለው የዱቼ ሞሶሎኒ ጦር ግን እንዳሰበው የልቡን ሊሞላ አልቻለም። ኋላቀርነታቸው እና ድኅነታቸው ብቻ ቀድሞ የደረሰው ወራሪው ኃይል በመጣበት ፍጥነት ድንበርን ማለፍ ቀርቶ ከነጭራሹ የቋመጠላትን ምድር በሩቁ እያየ እግራቸውን ለጠጠር፤ ደረታቸውን ለጦር በሰጡ ጀግኖች የኢትዮጵያ ልጆች ድባቅ ተመታ። የአድዋ ድልም በወራሪው ጣልያን ሽንፈትና በጀግኖች አርበኞች የአልደፈር ባይነት ተጋድሎ ተበሰረ።

የ123 ዓመት ዕድሜ ባለፀጋው እና ዛሬም ድረስ ትናንት የተከወነ እስኪመስል ድረስ ሥሙ በተጠራ ቁጥር ከኢትዮጵያውያን አልፎ አፍሪካውያንን ብሎም መላው የጥቁር ሕዝብን ልብ በኩራት የሚሞላው የአድዋ ድል ዛሬም በዚህኛው ትውልድ ልብ ውስጥ ጎልቶ ከመፃፍ ባለፈ በድምቀት ይዘከራል።

ባሳለፍነው ሳምንት በብሔራዊ ቤተ መፃሕፍትና ቤተ መዛግብት የተካሔደው ‹‹ዝክረ አድዋ››፤ የተለያዩ ጥበባዊ ክዋኔዎች፣ የስዕል ኤግዚቢሽንን ያካተተ ሲሆን፤ አዲሱ ትውልድ ‹‹ጀግኖቼ›› የሚላቸውን ግለሰቦች ያወደሰበት ነበር። በመጠይቅ መልኩ የተዘጋጀው ‹‹ጀግናዎትን ይሹሙ›› በተለያዩ የዕድሜ፣ የትምህርት እና የሥራ ደረጃ ላይ ያሉ ግለሰቦች ተሳትፈውበታል። አብዛኛው በመጠይቅ ከተሳተፉት የአንደኛና ኹለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በብዛት ወላጆቻቸውን፣ የኢትዮጵያ ኩራት የሆኑ ጀግኖች አባቶቻችንንና አትሌቶቻችንን ጀግና ብለዋል።

ከተሳታፊዎች መካከል የስምንት ዓመት ዕድሜ ያላት ታዳጊ ‹‹ጀግናዬ ጥሩነሽ ዲባባ ናት ምክንያቱም ኢትዮጵያን ስላኮራች›› ስትል ጀግናዋን ታወድሳለች። የሥነ ሕንፃ ባለሙያ የሆነው ሌላኛው ተሳታፊ ደግሞ ‹‹የኔ ጀግና፤ በተስፋ ሚያቅዱ፣ በእምነት ሚሠሩ እና በፍቅር የሚኖሩ ሁሉ ናቸው›› ይላል። ምክንያቱ ደግሞ ‹‹ሁሉን ችለዋልና›› ብሏል። እነዚህና ሌሎች ለቀልብ ሳቢ ዝግጅቶች እንዲሁም የታዋቂ ሰዎች ምስልና ሥራዎቻቸው ለዕይታ ቀርቧል።

በሌላ በኩል ደግሞ የዘንድሮውን 123ኛው የአድዋ ድል በዓልን ምክንያት በማድረግ ከተካሔዱና በመካሔድ ላይ ከሚገኙ ዝግጅቶች መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ሳምንቱን ሙሉ ያዘጋጀው መርሃ ግብር ይገኝበታል።

በዝክረ አድዋ የሳምንት ቆይታ ከነበራቸው ዝጅቶች ውስጥ፣ የዋዜማ ቴአትር፣ ባዶ እግር፣ ግብር ማብላት ፣ መስትያት ፊልም ፌስቲቫል፣ ዐውደ ርዕይ፣ የክብረ ዓደዋ የሊቃውንት ጉባዔ እና ጀግና ማነው?፣ የደራሼ ባሕላዊ ቡድን የፕሮግራሙ ድምቀቶች የነበሩ ሲሆን በዋዜማውም አንጋፋ ገጣሚያን እና የቴአትር ባለሙያዎች በጣይቱ ሆቴል ዝግጅቶቻቸውን እንዳቀረቡ ለማወቅ ተችሏል።

በዘንድሮ የአድዋ በዓል ላይ የተለያዩ ሥራዎች የተሰሩ ሲሆን፣ በተለያዩ ጊዜ ለየብቻቸው በዐሉን አስመልክቶ ከታሪኩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ሥራዎች ይሠሩ የነበሩ ድርጅቶች ጉዞ አድዋ፣ ክብረ አድዋ እና ባዶ እግር ጉዞ በአንድ ላይ እንዲሠሩ የተደረገ ሲሆን ፤ በዓሉን አስመልክቶ ምሁራን ከወጣቶች ጋር የመወያያ መድረክ ተዘጋጅቷል። ለዚህም የተለያዩ ድርጅቶች እገዛ እንዳደረጉና እያደረጉም እንደሆነ የከተማ አስተዳድሩ የኪነ ጥበብ ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ የሆኑት ነብዩ ባዬ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ፣ በመልዕክታቸው ‹‹በአንድነትና በፍቅር አንድ ላይ ሆነን የምንዘምርበት፣ የምንጫወትበት እና እየተዝናናን ሐሳብ የምንለዋዋጥበት የጋራ መድረክ ነው›› ብላዋል። እንዲህ ዓይነቱ የበዐል አከባበር በሐሳብ የረቀቀ፣ በዕውቀት የበሰለ እና በክውን ጥበባት ትውልድን ከትላንት ጋር በማነጋገር ማንነቱን እንዲፈትሸ እና ለነገ የምትተርፍን አገር ለመሥራት ከራስ ጋር ለመመካከር እድልእንደሚሰጥ የምክትል ከንቲባው መልዕክት ያትታል።
በዓሉ ኢትዮጵያውያን ፈተናዎችን በጋራ ትግል በማለፍ እዚህ ለመድረሳቸው አንዱ ማሳያ መሆኑን የሚናገሩት ታከለ ኡማ ‹‹አባቶቻችን ከወራሪ ቅኝ ገዢዎች ጋር ተፋልመው ደምና አጥንት ገብረው በነፃነቷ የምትኮራ አገር ባለቤት አድርገውናል›› ብለዋል።

ምክትል ከንቲባው በዚህ አያበቁም፤ ኢትዮጵያ ይህን ድል የተቀዳጀቸው በመሳሪያ ብልጫ ሳይሆን፣ በሞራልና በሐሳብ ልዕል እንደሆነና ፍቅርና ኅብረት ትልቅ ብርታት እንደሆናቸው አስገንዝበዋል። በዚህም የአድዋ ታሪክ የኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን፣ የመላው አፍሪዊያን ወንድሞቻችን ጭምር እንደሆነ ለዓለም መድረክ በተገኙ አጋጣሚዎች ሁሉ አዲስ አበባ የማስተዋወቅ ኃላፊነቷን እንደምትወጣም አረጋግጠዋል።

‹‹ዓደዋ ከሰው በላይ ሰው ነኝ ብሎ ያሰበ፣ የሰውነት ልኩን የተረዳበት የፍትሕ አደባባይ፤ ከሰው በታች ሰው ነኝ ብሎ እንዲያምን የተደረገ የሰውነት ክብሩ የተገለጠበት የነጻነት ሃውልት፤ ለዘመናት የተዛባን ትርክት ያቀና የሰውነት ማኅተም ነው።›› ድግሱ ይሄንን እውነት የሰው ልጅ ይደማመጥ ይዋደድ እና በሰውነቱ ብቻ ይከበር ዘንድ ከዓደዋ ያገኘነውን ቱሩፋት የሚያንፀበርቁ፣ በተለይም በኪነ ጥበብ ማር የተላሱ ሐሳቦች የሚመላለሱበት እንዲሆን ተደርጎ የተዘጋጀ ፕሮግራም ነው›› የሚሉት ደግሞ የሰውኛ ፕሮዳክሽንና ኢንተርቴይንመንት ሥራ አስኪያጅ ሚካኤል ሚሊዮን ናቸው።

በሐሳብ የረቀቀ፣ በእውቀት የበሰለና በክውን ጥበባት ትውልድን ከትናንት ጋር በማነጋገር የማንነት ስብዕናውን እንዲፈትሽ፣ ለነገ የምትተርፍን አገር ለመሥራት ከራስ ጋር ለመመካከር እድል የሚፈጥር ፕሮግራም እንደነበረ የዝግጅት ኮሚቴው መረጃ ያመለክታል።

ዛሬ የካቲት 23 በአዲስ አባባ ከጊዮርጊስ እስከ አድዋ ድልድይ የባዶ እግር ጉዞ፣ እንጦጦ ማርያም ቤተክርስቲያን ግብር ማብላት ሥነ ስርዓት የሚተገበሩ ሲሆን፣ ከሰዓት ከ8፡00 ጀምሮ በመስቀል አደባባይ በተዘጋጀ የሙዚቃ ድግስ በርካታ ድምፃዊያን የሚሳተፉበት ሲሆን በዚህም ዝግጅት ላይ ድምፃዊ መሐሙድ አሕመድ፣ ቤቲ ጂ፣ አስጌ ዴንዴሾ፣ ሐጫሉ ሁንዴሳ፣ መስፍን በቀለ፣ ብርሃኑ ተዘራ፣ እሱባለው ይታየው (የሺ)፣ ኤፍሬም አማረ፣ ታደለ ሮባና ዘቢባ ግርማ ዝግጅቶቻቸውን እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here