የአድዋ ድል ምንነት

0
1266

ዛሬ የሚከበረውን የአድዋ ድል አስመልክተው የጻፉት ሙሉጌታ ገዛኸኝ፣ የድሉ አንፀባራቂነት የድሉ ባለቤት ለሆኑ ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን በፀረ-ቅኝ ግዛት ትግል ውስጥ ለነበሩ ሌሎች አፍሪካውያን ሁሉ አንፀባራቂ ነው ይላሉ።

 

 

ጦርነት መንሥኤውና ዓይነቱ የተለያየ ቢሆንም ከሰው ልጅ ሁለንተናዊ ዑደት ተቆራኝቶ በሕይወት፣ በንብረት እና በተፈጥሮ ሥነ ምኅዳር ላይ ከባድ ጉዳት ሲያስከትል ኖሯል፤ ይኖራልም።

ይሁን እንጂ እብሪተኛው በከንቱ ጀብደኝነት ተነሳሳቶ አንዱ በሌላው ላይ ወረራ ሲቃጣ ደካማው ራስን ለማዳን መከላከሉ አይቀሬ ነው። በአንፃሩ ደግሞ አገርን ከውጭ የግፍ ወረራ መከላከልና ሉዓላዊነትን ማስጠበቅ ፍትሐዊ መሆኑን ጸሐፍት የሚሥማሙበት ጉዳይ ነው።

ኢትዮጵያ በስልታዊ መልክዓ ምድር፣ በተፈጥሮ ፀጋዎቿ፣ እንዲሁም ምቹ የአየር ፀባይ፣ ለም መሬትና ወንዞቿ ምክንያት ተደጋጋሚ የውጭ ወረራዎች ከጥንት እስከ ዛሬ ሲፈታተኗት ኖረዋል። በተለይም ከ19ኛው ምዕተ ዓመት አጋማሽ ወዲህ የኦቶማን ቱርኮች ወኪል የነበረችው ግብፅ የመሐዲስት-ድርቡሽ ሱዳን፣ የእንግሊዝ እና የጣሊያን ቅኝ ገዥዎች ዓይናቸውን የጣሉባት ስትሆን ወረራቸውን እውን ለማድረግ ደፋ ቀና ብለዋል። አገራችን የተቃጣባትን ወረራ ምንጊዜም በነጻነት ወዳድና በአይበገሬ ወኔ ዳር ድንበሯን ለማስከበር የአርበኝነት ተጋድሎ ፅናት የአንድነት ትሥሥር ቃል ኪዳን መንፈስ ሉዓላዊቷ ተጠብቆ ለመዝለቅ ችሏል።

ቀደምት አበው ወ እመው ጀግኖች ኢትዮጵያውያን በአርበኝነት ከወራሪ ጠላት ጋር ተፋልመው ለአገራዊ ክብር ሲሉ ውድ ሕይወታቸውን ከከፈሉባቸው ዋና ዋና ታሪካዊ የውጊያ አውድማዎች አንዱ የአድዋ ሰንሰለታማ ተራሮች ምን ጊዜም ይታወሳል።

በየካቲት 23 ቀን 1888 አድዋ ላይ በዐፄ ምኒልክ መሪነት ድል የተመታው ወራሪው የኢጣልያ ሠራዊት የቅኝ ገዥነት ሕልሙን ለማሳካት ያካሔደው ጦርነት በአፍሪካዊቷ የጥቁሮች ተምሣሌት አገር ኢትዮጵያ ከሽፎበታል። ድሉ የተፈፀመበት ታሪካዊ ሥፍራ አድዋ አርዓያነቱ ለእኛ ኢትዮጵያውያን ሰንደቅ ዓላማችን ከፍ ብሎ መውለብለብ ብቻም ሳይሆን በፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ውስጥ ለነበሩ መላው ጥቁር ሕዝቦች ጭምር አንፀባራቂ ነው።

የአድዋ ድል ወራሪዎችን የውርደት ካባ አከናንቦ በታሪክ መዘክርነቱ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተሸጋገረ ለዛሬው አፍሪካዊ አኩሪ የነጻነት አሻራ ሆኖ ለነጻነትና አንድነት በተከፈለ ብሔራዊ መስዋዕትነት ተረክበናል። በመሆኑም የአድዋ ድል ከፖለቲካዊ ጠቀሜታ ባሻገር ልንኮራበት የሚገባ የታሪክ አሻራ ቅርሳችን ነው።

የድሉ በዓል ሲዘከር ጦርነቱ የተካሔደበት ሥፍራ ለታሪካዊ ቅርስነትና ለቱሪስት መዳረሻነት ጉልሕ ጠቀሜታ እንዲኖረው የመላው ጥቁር ሕዝቦች (ፓን-አፍሪካኒዝም) የፀረ ቅኝ ግዛት ትግል ችቦ የተቀጣጠለበት ተምሣሌትነቱ በሚገባው ልክ መዘከር ይኖርበታል።

የአሁኑ ትውልድ ያለአንዳች ነቀፌታ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን ላበረከቱለት አስተዋፅዖ ክብርና ምስጋና ንፉግ መሆን የለበትም።

ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here