ለእራት 5 ሚሊዮን ብር!?

0
500

የብዙዎችን ትኩረት ሲስቡ ከሰነበቱት ርዕሰ ጉዳዮች መካከል ከጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ጋር እራት ለመብላት የፈለገ 5 ሚሊዮን ብር ይክፈል የሚለው የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት መገለጫ ተጠቃሽ ነው።

5 ሚሊዮን ብር እንዴት ለአንድ ሳህን እራት ይከፈላል? ካሉም ጉዳዩ ከእራት ጀርባ ያለው የአዲስ አበባ ወንዞች ልማት ነው ተብሏል። ባለፈው ሳምንት በ29 ቢሊዮን ብር ወንዞቹን ለማልማት በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ‹‹ሐሳብ አመንጭነት›› የሦስት ዓመታት ፕሮጀክት ይፋ ሆነ መባሉ ከጅምሩ የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች መከራከሪያ ሆኖ ሰንብቷል።

በአንድ በኩል የጠቅላይ ሚንስትሩን አዲስ አበባ የማልማት ሐሳብ የሚያደንቁ በሌላ በኩል ደግሞ ሐሳቡ ቢደነቅም ‹‹በዐቢይ አይደለም የመነጨው፣ ይልቁንም ከተማዋ በታኅሣሥ 2008 ወንዞቿን የሚለማላትን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አቋቁማለች፣ ከሰሞኑ እንደአዲስ የታየው የተንቀሳቃሽ ምስል ንድፍም ቀድሞ የተሰራ ነው›› በሚል ሐሳብ ሲናዘሩበት ሰንብተዋል።

አሁን ደግሞ የወንዞች ልማቱን በገንዘብ ለመርዳት ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር እራት እንዲበሉና ለዚህም በአንድ ሰው 5 ሚሊዮን ብር እንደሚያስከፍል መነገሩ የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። የፌስቡክ ደንበኞች ጉዳዩን ከሃማኖታዊ ተረክ ጋር በማነፃፀር የፈገግታ ምንጭ ሲያደርጉት፣ በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ ዓይነቱ ዘመናዊና ተመካሪ የልማት ማነሳሻ ስልት በጎ ቢሆንም ገንዘቡ ተወደደ የሚለው ዋነኛ መነጋገሪያ ሆኗል። እነ አሜሪካም ይህ ዓይነቱ ልምድ አላቸው የሚሉ ሰዎች የኢትዮጵያው እራት ተወዷል እያሉ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 16 የካቲት 23 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here