የሴቶች የሥልጣን ደረጃ በኢትዮዽያ ሥርዓተ መንግሥታት

0
1109

በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ታስቦ የሚውለውንና ትላንትና ታስቦ የዋለውን በተለምዶ ‘ማርች ኤይት’ በሚባል የሚታወቀውን የሴቶች ቀን ተንተርሰው ሙሉጌታ ገዛኸኝ በኢትዮጵያ ሥርዓተ መንግሥታት ታሪክ ውስጥ ሴቶች የነበራቸውን ሥልጣን እስከ አሁኗ የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ድረስ ያለውን ታሪክ አጣቅሰው እንዲህ አቅርበውልናል።

 

በዓለማችን ሰፊ ዘመናትን በሚሸፍነው ጥንታዊ የጋርዮሽ ሥርዓተ ማኀበር አንዱ መገለጫ የሴቶች የበላይነት እንደነበር መዛግብት ያትታሉ። ከቤት ውስጥ ሥራም ሆነ ማስተዳደር እስከ አደባባይ መሪነት ሴታዊ ተምሳሌት (matriarchal) ባሕርይ ጎልቶ ይንፀባረቅበታል። ሕፃናት ከአባታቸው ይልቅ በእናት ሥም መጠራት ተቀባይነት ነበረው። ሔዋን የሚል ሥያሜ መጠሪያነት መዋሉም ይጠቀሳል። እንዲያው ሴቶች ደፋር መሆናቸውን ባሎቻቸውንም ለማጀገን ወደኋላ እንደማይሉ በእነርሱ ዘንድ ጀግና ሆነው እንዲታዩላቸው ምንጊዜም ይፈልጋሉ።

ይህ ሲባል የእንስቶቻችን ጀግንነት እምብዛም የማይወሳበት አገር ስለሆን ሳይሆን የትርክት አቀራረባችን የፈጠረው ክፍተት ነው። ለአብነት ሴት የላከው ሞት አይፈራም፣ የሴት ልብ ጭብጥ አይሞላም፣ ሴት ምን ብታውቅ በወንድ ያልቅ፣ ወዘተ. እየሰማ ለሚያድግ ትውልድ ለአቅመ አዳም ዕድሜው ሲደርስ ሴቶችን ዝቅ ራሱን ላቅ በማድረግ የሕይወት ውጣ ውረድን ይለማመዳል።

ሥልጣኔ ብቅ ማለት ከጀመረበት የኒዎሌቲክ (Neolithic) ዘመን ወዲህ የወንድ የበላይነት አስጠባቂ (male dominant) ማስፈኑንና የሴቶች ሚና እያሽቆለቆለ በጓዳ ብቻ እንዲወሰኑ ማድረጉ አልቀረም። የሕጻናት መጠሪያ ከእናት ወደ አባት ተዛውሮ እየተለመደ መምጣቱን ለመገንዘብ ይቻላል።

በጥንቱ የአገራችን ወግ ልማድ ረገድ የእንስቶቻችን የፖሊቲካ ተሳትፎና የኀላፊነት ሚና ከታሪክ ማኅደራት ስንፈትሽ ያው የወንዶች የበላይነትን በተመሳሳይ ሁኔታ እውቅና ይሰጣል። ይህ ከባሕል አኳያ እንጅ ሌላ ሳይንሳዊ ማረጋገጫ ለማስደገፍ ለትንታኔ ያስቸግራል። ዛሬም ድረስ በሥርዓተ ጾታ እኩልነት የማያምኑ በርካቶች መሆናቸው የማይካድ ነው። የሴቶች እኩልነት ተቀባይነት እየቀነሰ በተለይም አስተዳደር ነክ ጉዳዮች ለወንዶች ብቻ የተተወ አስመስሎታል። ይሁን እንጅ ሴቶች ጥንት የነበራቸውን ዓይነተኛ ሚና ለማስጠበቅ በዘመናዊው እሳቤ ሴታዊ እኩልነት(feminism) ንቅናቄ አስፈልጓል። የወንድ የበላይነት ሰፍኖ በኖረበት አገራችን ይህ ምን ያህል የአስተሳሰብ ለውጥ አምጥቷል ቁርጥ ያለ ምላሽ የሰጠ ጥናት ማግኘት ያዳግታል።

ክብረ ነገሥት እንደደነገገው ሴት ንግሥት ወይም መሪ ሆና ዙፋን ላይ እንድትሰየም አያበረታታም። ይህ ልማድ ፀንቶ የቆዬ መሆኑ ቢነገርም በአክሱም ገናና ከነገረችው ከንግሥት ሳባ ወዲህ ልጇ ቀዳማዊ ምኒልክ እና ተከታይ ወራሴ የሰሎሞናውያን ሥርወ መንግሥት በወንዶች የዘር ሀረግ በኩል እንዲቀጥል በመደረጉ ነው የሚል አፈታሪክ ይጠቀሳል። ከቀዳማዊ ምኒልክ አንስቶ እስከ ዐሥረኛው መቶ ክፍለ ዘመን ድረስ በዚሁ ሥርዓት ቀጥሎ ለወራሴነት የሚታጩት ከአፄው ወንድ ልጆች መካከል የበኩር ልጅ ብቻ ነበር። የሌሎቹ ዕጣ ፋንታ ደግሞ አንድ በተቀናቃኝነት እንዳይነሳሱ በጥብቅ የንጉሣውያን ቤተሰቦች የቁም እስረኝነት ኹለትም በዐይነ ቁራኛ መጠበቅ ብቻ።

ከፈላሻ አመፅ አስተባባሪዋ ዮዲት ‘ጉዲት’ አነሳስ ጋር ተያያዞ የተፋለሰው የሰሎሞናውን ተባዕታይ አገዛዝ በዚህች ሴት ጥቃት ሥር ለኻያ አምስት ዓመታት ያኽል ለመቆየት ተገዷል። አክሱም ላይ ሆና ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ በገዥነት አሳልፋለች። ታዲያ በብዙ መከራ ያለፈውና በዮዲት በተለምዶ አጠራር ‘እሳቷ’ ለመሰደድ የተገደደው የአክሱም ንጉሥ ሸዋ ውስጥ በመንዝ አካባቢ እንደኖረ ይጠቀሳል። ይህ የሰሎሞናው ሥርዓት እንደገና በተከታዮቹ ተጠናክሮ ወደ አክሱም ለመመለስ የቻለ ሲሆን በቆየው ልማድ የወንድ የዘር ሀረግ ንግስናን አስቀጥሏል።

በሌላ በኩል በ12ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሥልጣን ከአክሱማውያኑ የነጠቀው የዛግዌ ገዥ በሥርወ መንግሥቱ አንስት በዙፋን እንድትቀመጥ የሚፈቅድ አግባብ አያመላክትም። ከዛግዌ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ በኋላ በይኩኖ አምላክ መራሄ መንግሥትነቱ እንደገና ያንሰራራው «አዲሱ ሰሎሞናዊ» ሥርወ መንግሥት ወራሾቹ ክብረ ነገሥት ላይ በተደነገገው አሰራር እንዲተገበር አስገድዷል።

በዘመነ መሣፍነት ወቅት ጎንደር በዋና መቀመጫነት ከ17ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እስከ 19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ድረስ ይገዙ የነበሩት ወንድ ወራሾች ብቻ ናቸው። ሆኖም የአፄ በካፋ ሚስት የነበረችውና በልጇ ሥልጣን ሞግዚትነት ሰበብ አድራጊ ፈጣሪ ሆና ብቅ ያለችው ገናናዋ እቴጌ ምንትዋብ ቋረኛ ስትሆን ለአስተዳደር አቅም ያልደረሰው ብላቴና ከባድ ፈተና ተጋርጠውበት እንደነበር ሳይጠቀስ አይታለፍም። በአመራር ብቃት እየተወጣች በልጇ አቤቶ ኢዮስያስ ስም ‘ቀጥ ለጥ’ አድርጋ ያስተዳደረችው መለኛ ሴት በርካታ የሥልጣን ተቀናቃኞች ከውስጥም ከውጭም ተጋፍጣለች፡ ይህ ብቻ አይደለም እቴጌ ምንትዋብ ሊያስደነግጣት የመጣውን ነብር ሳይቀር በግብር ውሃ ጣሳ ግንባሩን ተርትራ የፈጠፈጠችው ነገር ሳይቀር በቀልድ መልክ የሚነገርላት ዝነኛ ሴት ነበረች።

ከኢማም አሕመድ ጋር በተካሔደ እልህ አስጨራሽ ጦርነት ስፍር ቁጥር የሌለው ሰው ከኹለቱም ወገን አልቆ በስተመጨረሻ ግራኝ በጎንደር ወይና ደጋ (አርባያ በለሳ) በጦርነቱ ተገደለ። በዚያን ጊዜ ሚስቱ ባቲ ድል ወንበራ የተበታተነ ሠራዊቱን አስተባብራ በአዋጊነት ከፊት መርታለች። ምንም እንኳ እንደ ስሟ ድል ባይቀናትም በስተመጨረሻ ወደ ዘይላ ለማፈግፈግ ተገዳለች።

ወሎ ውስጥ ታዋቂ ሴት ባላባቶች የነበሩ ወርቂት እና መስታወት ለአፄ ቴዎድሮስ ከፍተኛ ተገዳዳሪ ኀይል የነበሩ መሆናቸው አይካድም። በሴትነት ብቻም ሳይሆን የንጉሡ ጭካኔ በትር ሳይበግራቸው ሠራዊት አሰልፈው ተፋልመዋል።

በእኝሁ ገናና ንጉሠ ነገሥ ቴወድሮስ የዘመናዊ ኢትዮዽያ አስተዳደር ሲበሰርም ከወንዶች በስተቀር ሴቶችን ወደ ሥልጣን የሚጋብዝ ምቹ አሰራር አልተፈጠረም። ከእሳቸው በኋላ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ ከባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ እየተማከሩ አገሪቱን በማዘመን ረገድ በርካታ አስደማሚ ለውጥ ማስመዝገብ ችለዋል። ይሁን እንጅ ለወራሴ ዙፋን የታጨው የልጅ ልጃቸው አቤቶ ኢያሱ በጥቂት ዓመታት ውስጥ በተቀነባበረ የውስጥ ሽኩቻ ሥልጣኑን የመነጠቅ ዕጣ ፋንታ ሰለባ ሆኗል።

ዙፋናቸውን የሚረከብ ወንድ ልጅ ያልነበራቸው ምኒልክ ክብረ ነገሥቱን ባልጠበቀና ባልተለመደ ሁኔታ ወይዘሮ ዘውዲቱ እንዲነግሱ በመኳንንቶች ይሁንታ ተገኝቷል። ከጥንቱ ዘልማድ ተቃራኒ ተከናውኗል የሚሉና የሚያወግዙ ወግ አጥባቂዎች ተቃውሞ እንዳሰሙ በታሪክ ተመዝግቧል። ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሆነው አስዳደራዊ ሥራው በልዑል አልጋወራሽ ባለሙሉ ሥልጣን እንደራሴው ራስ ተፈሪ መኮንን እንዲሆን በቃለ መሐላ ተሰየሙ። ይህ ያልተለመደ ጥምር ዘውዳዊ አስተዳደር ለዐሥራ አምስት ዓመታት ቆይቷል። የዚህ ባሕላዊ ሥልጣን በዘመናዊው አንድምታ ሲገለፅ አልጋ ወራሹ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ንግስት ደግሞ እንደ ርዕሰ ብሔር ሊወሰድ ይችላል።

ንግሥቲቷ በድንገተኛ ህመም ካረፉ በኋላ አባ ጠቅል ተፈሪ ዙፋኑን ጠቅለው በእጃቸው አስገቡና ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ተሰኝተው ነገሱ። ባለቤታቸው ወይዘሮ መነንም እቴጌ ተብለው ማዕረግ ተጎናፀፉ። እቴጌ መነን እንደ እቴጌ ጣይቱ ጎልተው የሚጠቀሱበት ፖሊቲካዊ ሚና ባይታወቁም ማኀበራዊና መንፈሳዊ በጎ አድራጎት ተቋማትን ገንብተው አስፋፍተዋል። በሌላ በኩል ከትምህርት ቤት ዲሬክተርነት ጋር በተያያዘ ሥማቸው ይጠራል ሊባል የሚችለው ሌላኛዋ ጠንካራ ሴት ስንዱ ገብሩ ሲሆኑ የመጀመሪያዋ አንስት የፓርላማ አባል ናቸው።

ከዘውዳዊ ሥርዓት መገርሰስ ወዲህ ወደ ሥልጣን ብቅ ያለው ደርግ ፈላጭ ቆራጭ ወታደራዊ መሪ መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ባለቤት ወይዘሮ ውባንች ቢሻው ጉብኝት ላይ አብረው የጓዙ እንደሁ እንጅ ይህ ነው የሚባል የፖሊቲካ አስተዋፀዖ አላሳዩም። ከሶሻሊስቱ ርዕዮተ ዓለም መንኮታኮት ማግስትም ቢሆን የመራሔ መንግስትነትም ሆነ የርዕሰ ብሔርነቱ ቦታ ለወንዶች ብቻ የተተወ ይመስላል የሚል ትችች ይሰነዘራል። በቅርቡ አዲስ ሴት ርዕሰ ብሔር የተሰየሙት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ የአምባሳደርነቱ ረጅም ዘመን የሥራ ልምዳቸው ጋር የሚጣጣምላቸው ባይመስልም ይህንኑ ትችት ይደፍኑ ዘንድ በዶክተር ዐቢይ አማካኝነት የለውጡ አካል ሆነዋል።

እንግዲህ በአንድም በሌላም ሁኔታ ትውልዱ የዘነጋቸውን አንስት ርዕሰ ብሔር የነበሩትን ስናወሳ በአገራችን የቤተ መንግሥት ወግና ልማድ የሣህለ ወርቅ ዘውዴ መሰየም እምብዛም አዲስ ክስተት ላይሆን ይችላል። በጥንቱ ዘመን አስተዳደራዊ ተሳትፎአቸው የይስሙላ ሳይሆን በጦርነት ጊዜም አዝማች ሆነው የሚሰለፉ ያልተገደበ የመሪነት ግዙፍ ሚና የነበራቸው አንስቶችም እንደነበሩ በታሪክ ይወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 17 የካቲት 30 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here