ኢትዮጵያና ያመለጡ የዴሞክራሲ ዕድሎቿ!

0
609

ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመመሥረት የተደረጉ ሙከራዎች በሙሉ በመክሸፋቸው ምክንያት ላለፉት አምስት ዐሥርት ዓመታት ትግሉ ቀጥሏል። ከ2010 ወዲህ በኢትዮጵያ የታየው ለውጥ ዴሞክራሲ ያመጣ ይሆን ወይስ እንደቀድሞዎቹ ሙከራዎች ይከሽፍ ይሆን? ግዛቸው አበበ የኢትዮጵያን የባከኑ የቀድሞ መልካም አጋጣሚዎች በማስታወስ አሁንም የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ወደ አምባገነናዊ ስርዓትነት አፋፍ መድረሱን አመላክተዋል።

 

ኢትዮጵያ መልካም አጋጣሚዎችን በፍፁም መጠቀም ያልቻለችበት መስክ አለ ከተባለ ዴሞክራሲን የማንገሡ መስክ ነው። ከ1950ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ በርካታ ልጆቿ ኢትዮጵያን የዲሞክራሲ፣ የፍትሕና የእኩልነት አገር ለማድረግ ደፋ ቀና ቢሉም፥ ከሙከራ ያለፈ ሥራ ሳይሠሩ ብዙዎች ተሰውተዋል።
ሕገ መንግሥታዊ ዘውድ

እነመንግሥቱ ነዋይ በ1953 መፈንቅለ መንግሥት ያካሔዱት ዘውዳዊው አገዛዝ እንዳለ ሆኖ፥ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ አስተዳደር ለማስፈን መሆኑ ይነገራል። በጃፓን፣ በስፔን፣ በእንግሊዝ፣ በስዊዲን ወዘተ… እንደሚታየው የዘውዳዊው ስርዓት ሕልውና እንደተጠበቀ ሆኖ አገሪቱን በሕዝብ በተመረጡ ወገኖች ለማስተዳር አቅደው እንደነበረና ለዚህ ስኬታማነትም ለዘመናዊ አስተዳደር እምቢተኛ የሆኑትን ንጉሥ ከዙፋናቸው አውርደው በልጃቸው በመተካት ነገሩን ለመጀመር ሙከራ ማድረጋቸው ይነገራል። ነገር ግን ብዙም ሳይራመዱ አላማቸው ከሸፈ። ይህ አጋጣሚ ኢትዮጵያችን በታሪኳ ለመጀመሪ ጊዜ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ አስተዳደር ለመትከል ታስቦላት የከሸፈበት ጊዜ ነበረ ማለት ይቻላል። ይህ ጊዜ ፍትሐዊ አስተዳደር የማንገሥ፣ ሕዝብ መሪዎቹን ራሱ እየመረጠ የሚተዳርበትና የሚዳኝበት ዕድል ያመለጠበት ጊዜ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል።

ድኅረ አብዮት
በዚህ መስክ ሌላው ዕድል የተከሰተው የ1966ቱን አብዮት ተከትሎ ነበረ ማለት ይቻላል። የመጨረሻውን የኢትዮጵያ ዘውዳዊ አገዛዝ መወገድ ተከትሎ በመጡት ወደ ሦስት የሚጠጉ ዓመታት ውስጥ በአገሪቱ ውስጥ የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች በግልጽ ይንቀሳቀሱ እንደነበረ የሚዘነጋ አይደለም። ይህ ጊዜ ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች በይፋ የተንቀሳቀሱበትና ሕዝብ የመረጠው ቡድን ወደ ሥልጣን ሊመጣ የሚችልበት ጭላጭል የታየበት ጊዜ ነበር። ይህ ተስፋ ስለነበርነው አንዳንድ የፖለቲካ ድርጅቶች ከውጭ ወደ አገር ቤት የመጡትና ሌሎችም እዚሁ አገር ቤት ተመሥርተው መንቀሳቀስ ጀምረው የነበረው።

ይህ ተስፋ ወሬ ብቻ አልነበረም። ንጉሡ ከሥልጣናቸው እንደተወገዱ በወቅቱ ሥልጣን የያዘው ወታደራዊ ቡድን ‘ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር-ደርግ’ ነኝ ይል ስለነበረና ወታደራዊው ቡድን ሥልጣኑን ለሕዝብ ወይም ሕዝብ ለመረጠው ቡድን ያስረክባል የሚል ተስፋ ይናፈስ ስነበረ የተሰነቀ ተስፋ ነው። ጊዜው የሽግግር ዘመን መስሎ ይታይ ነበረና ነው ወደ አምስት የሚሆኑ የፖለቲካ ቡድኖች በሕዝብ ተመርጠን አገሪቱን እናስተዳድራለን ብለው የየራሳቸውን ዝግጅት እያደርጉ የነበረው። በወቅቱ ይፋ በሚባል መንገድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩት የፖለቲካ ድርጅቶች አብዮታዊ ሰደድ (አብዮታዊ ነበልባል)፣ ማርክሲስት ሌንኒስት ሪቮሉሽነሪ ድርጅት (ማሌሪድ)፣ የኢትዮጵያ ጭቁኖች አንድነት ትግል (ኢጭአት)፣ የመላ ኢትዮጵያ ሶሻሊሶት ንቅነናቄ (መኢሶን) እና የወዝ አደሮች ሊግ (ወዝ-ሊግ) ሲሆኑ ኢሕአፖ ደግሞ ይፋ በመሆንና ባለመሆን መካከል እየዋለለ ቆይቶ ሕቡዕ የገባ ድርጅት ነው። በፍጥነት ደበዘዘ እንጅ በዚህ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ የብዙ ፓርቲዎች ስርዓት እያቆጠቆጠ ነው የሚል ተስፋ በብዙዎች ልብ አድሮ እንደነበረ የሚካድ አይደለም።

ቀስ በቀስ በደርግ ውስጥ የኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ቡድን የሆነው አብዮታዊ ሰደድ ውስጥ ውስጡን ራሱን የማጠናከርና ሌሎቹን የማዳከም ሥራዎችን ይሠራ እንደነበረው ሁሉ፥ ሌሎቹ ቡድኖችም በተናጠልና አንዱ ከሌላው ጋር በመተባበር ደርግን ወይም ሰደድን ጠልፈው ለመጣል ውስጥ ውስጡን ያደቡ እንደነበረ በነዚህ ቡድኖች ውስጥ የነበሩ ሰዎች ከጻፉት ታሪክ መረዳት ይቻላል። ሽኩቻው ቀጥሎ በመጀመሪያ ሰደድ እንደ ቡድን፣ ቀጥሎም በሰደድ ውስጥ ጥቂቶችን ያቀፈው የመንግሥቱ ኃይለማርም ቡድን እየገነነ መጥቶ የቡድን አምባገነንነት ተወለደ። ይህ የቡድን አምባገነንነት ደግሞ በተራው በኮሎኔል መንግሥቱ የበላይነት ተሸንፎ ግለሰባዊ አምባናገነናዊነት ሰፍኗል።

ቡድናዊውና ግለሰባዊው አምባገነንነት ውስጥ ውስጡን እያቆጠቆጠ በነበረበት ጊዜ ላይላዩን የማስመሠያ ድራማዎች ይሠሩ ነበረ። የማስመሠል ሥራው በወቅቱ የነበሩት ቡድኖች ሁሉ አፍቃሪ ኮምኒዝም ስለሆኑ ተደምረው ኅብረት መፍጠር አለባቸው በሚል ሽፋን ነው የተካሔደው። ቡድኖቹ ኅብረት ፈጠሩ ተብሎ ኢማሌድኅ (የኢትዮጵያ ማርክሲስት ሌኒንስት ድርጅቶች ኅብረት) ተመሠረት ተብሎ የቡድኖቹ የተናጠል ሕልውና በግዴታ ተደፈጠጠ። ይህ ሲሆን የየቡድኖቹ አመራሮችም ሆኑ ቡድኖቹ ያቀፏቸው አባላት በጉዳዩ ላይ በነጻነት ተነጋግረው የመወሰን ዕድል አልተሰጣቸውም።

የካቲት1969ላይ የተመሠረተው ‘…ኢማሌድኅ ወደፊት ሊመሠረት ለታሰበው የሠራተኞች ፓርቲ አስኳል ነው…’ እየተባለ እየተዘመረለት ስለነበረ፥ አገሪቱ ከብዙ ፖርቲዎች ስርዓት እየራቀች መሆኑና አንድ ፈላጭ ቆራጭ ፓርቲ ዕውን ሊሆን መሆኑ ለማንም ግልጽ ሆነ።

በነ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ካምፕ ኢማሌድኅ ሕያው እንደሆነ ተቆጥሮ ‘ከኅብረት ወደ ውሕደት’ በሚልአንድ ትልቅ ፓርቲ ይመሠረታል በተባለበት ጊዜ መኢሶንና ኢጭአት ከኢማሌድኅ ወጡ። የነዚህ ኹለት ቡድኖች አመራሮች ሸሽተውና ተሰውረው፣ ሽሽቱና መሰወሩ ያልተሳካላቸው ታስረው፣ ከታሰሩት ውስጥም ጥቂት የማይባሉት ተገድለው የብዙ ፓርቲ ስርዓት እና የዴሞክራሲ ግንባታው ወደ መቃብር እየወረደ መሆኑ ግልጽ ሆነ። ወዝሊግ ደግሞ ወደ ሰደድ ውስጥ አባላቱን አስርጎ አግብቶ መፈንቅለ ሥልጣን ሊያካሒድ ሲል ተደረሰበት ተብሎ የኢጭአትና የመኢሶን ዕጣ ደርሶበታል።

 

ብዙዎች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቡድን የመለስንና የመንግሥቱን ዓይነት ዓይን ያወጣ አፈና አያካሒድም ብለው ይሞግታሉ

 

የኢማሌዲኅ ተልዕኮ መክሸፉ ሊደበቅ ከማይችልበት ደረጃ ላይ ሲደርስ፥ የሠራተኞችን ፓርቲ ለመመሥረት መንገድ የሚጠርግ ሌላ ቡድን መቋቋሙ አለበት ተባለ። ታኅሣሥ 1971 ላይ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፓርቲ አደራጅ ኮሚሽን (ኢሰፓአኮ) መመሥረቱ ይፋ ሆነ። የኢሰፓአኮን መመሥረት ተከትሎ ኢትዮጵያ ውስጥ ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም በአዋጅ ተከለከለ፤ እነ ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርም ወታደራዊ ልብሶቻቸውንና ማዕረጋቸውን ጥለው ራሳቸው በሲቪልነት ተሰልፈው የጊዜያዊው ወታደራዊ መንግሥት ጊዜ (የደርግ ዘመን) አክትሞ ሥልጣን የሲቪሎች ሆነ ተባለ። ኢሰፓአኮ ወደ አምስት ዓመታትን ካስቆጠረ በኋላ መስከረም 1977ላይ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ፖርቲ ነው የተባለውኢሠፓ ተወለደ። ፕሬዘደንት መንግሥቱ ወታደራዊ ጓደኞቻቸውንና ጥቂት ሲቪል ጓዶቻውን አሰባስበው የሠራተኛው መደብ ወኪል ነው የሚባለው የኢሠፓና የአገሪቱ አመራሮች ሆኑ።የመድብለ ፓርቲዎች ስርዓት የማይታሰብ ሆነ።

ድኅረ ግንቦት 83
ግንቦት 1983 ላይ ሌላ የመድብለ ፓርቲዎች ስርዓት እውን የሚሆንበት ዕድል ያጋጠመ መሰለ።ብዙም ሳይቆይ ግን ሥልጣን ብቻ ሳይሆን ዝርፊያ የጠማው የዘረኛነት ስርዓት መስፈኑና የመድብለ ፓርቲዎች ስርዓት አለ መባሉ የይስሙላ መሆኑ ታወቀ። የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ አገዛዝ ሕዝብ በሰፊው የሚያሰባስብና ጠንካራ የመሆን አዝማሚያ የሚታይበት ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅት ሲያይ፥ ሰበብ ፈልጎ እየኮረኮመ፣ አንገቱን እስደፋና እየበታተነ እስከ 1990ዎቹ አጋማሽ ላይ አደረሰው። የጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲ ፀር የሆኑት መለስ ዜናዊ፥ “ጠንካራ ፓርቲ አጣን” እያሉ በመቀለድም ይታወቃሉ።

በምርጫ-97 (ግንቦት 1997) ወቅት ሕዝብ ከጎናቸው በሰፊው ማሰለፍ የቻሉ ቡድኖች ብቅ ሲሉ ግን፥ መለስ የጠመንጃ ጨዋታ ጀመሩ።በምርጫ 97 ማግስት ከጠመንጃው ጨዋታ ጎን ለጎን ሌላ በብዙ ፓርቲ ስርዓት ላይ የመቀለድ ሥራ ጀመሩ። ተለጣፊ ፓርቲዎችን ማራባትና በጠንካራ ፓርቲዎች ሥምና አምሳያ የሚንቀሳሱ ሌላ ፓርቲዎች እንዲፈጠሩ በማድረግ ጠንካራ ፓርቲዎችን መከፋፈልና ማውደም የእነ አቶ መለስ ቋሚ ሥራ ሆነ። ለምሳሌ በቅንጅት እና በኦብኮ ላይ የተሠራውን ደባ ማስታወስ ይቻላል። የእነ መለስ ዜናዊ ስርዓት የብዙ ፓርቲዎችን ስርዓት መቀለጃ አድርጎ በ2010 ቦታውን ለቀቀ።

ድኅረ 2011 ምን ያሳየን ይሆን?
ብዙዎች የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቡድን የመለስንና የመንግሥቱን ዓይነት ዓይን ያወጣ አፈና አያካሒድም ብለው ይሞግታሉ። እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው መለስ ዜናዊ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን ያከሸፉበት መንገድ ከኮሎኔል መንግሥቱ አካሔድ ለየት ያለ ነው፤ ነገር ግን ኹለቱም የአንድ ፈላጭ ቆራጭ ፓርቲ የበላይነትን በማስፈን ተመሣሣይ ሥራ ሠርተዋል። ስለዚህ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድም መለስ ዜናዊ የመድብለ ፓርቲ ስርዓትን ባከሸፉበት በዚያው መንገድ ይሔዳሉ ተብሎ ባይጠበቅም፥ እንደ መለስ ዜናዊ የአንድ ፈላጭ ቆራጭ ፓርቲ የበላይነትን በማስፈን ተመሣሣይ ሥራ ሊሰሩ ይችላሉ። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የመድብለ ፓርቲዎች ስርዓት ሊያሽመደምዱ ይችላሉ ሲባል አንድም የኢሕአዴግ አባል እና አጋር የሚባሉ ዘጠኝ ድርጅቶችን በአምባገነናዊ ዘዴ ሊጨፈልቁና የዚያ ስብስብ አውራ ሊሆኑ ይችላሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ተቃዋሚና ተፎካካሪ የሚባሉትን ቡድኖች በመደመርና በመዋሐድ ሥም ግራ አጋቢ ስብስቦች በማድረግና በማሽመድመድ ዋጋ ቢስ ይሆኑ ዘንድ ያደርጋሉ።

ለምሳሌ ሰማያዊ ፓርቲ እንደ ጨው ራሱን ያሟሟው ሕጋዊ ሆኖ ላልተመዘገበው፣ አርበኞች ግንባር ከሚባለው ቡድን አብሮ ለመሆን ሲል መሆኑ ጤነኛ ያልሆነ አካሄድ ነው። መኢአድ፣ ኢሕአፓ፣ ኢዲኅ እና ሌሎች የኦሮሚያና የአፋር ፓርቲዎች ውሕድ ሊመሠረት ነው የሚባለው ቡድንም ሕጋዊና ሕጋዊ ያልሆኑ ቡድኖችን ያቀፈ ስብስብ ከመሆኑም በላይ በምን መሠረት ላይ አንድ ሆነው ለመቆም እንደቻሉ የሚታወቅ ነገር የለም። የዚህ ዓይነቱ የተውሸለሸለ መሰባሰብ ፈጥሮ አብረን ቆመናል ማለቱ የይስሙላ ከመሆኑም በላይ፥ ምርጫ ሲመጣ ምን እንደሚሆኑ መገመት አዳጋች ነው። የዚህ ዓይነቱ ግርግር ኢትዮጵያ ይህን ወቅት ሳትጠቀመበት ታልፍ ይሆን ብሎ ለመጠየቅ ያስገድዳል።

ከ‘ለማ ቡድን’ ወደ ‘ዐቢይ ቡድን’
ከ‘ዐቢይ ቡድን’ ወደ ‘ዐቢይ ብቻ’
በ2010 የተከሰተው ልውጥ በመላ የኢትዮጵያ ሕዝቦች መስዋዕትነት የመጣ ለውጥ ነው። ነገር ግን ለውጡ የመጠለፍ አዝማሚያ እየታየበት ነው። በውጭ ሆነው በፖለቲከኛነትና በአክቲቪስትነት ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ግለሰቦችና ቡድኖች በብልጠት ራሳቸውን የለውጥ አውራዎች አድርገው ለውጡን መጠቀሚ ለማድረግ በርትተው እየሠሩ ነው። ሌላው ትልቁ አደገኛ ነገር ሕዝብ ተስፋ የጣለበት የለውጡ አመራር ‘ለማ ቡድን’ ወደ ‘ዐቢይ ቡድን’ ከዚያም ወደ ‘ዐብይ ብቻ’ሲወርድ የታየው ለውጡ ተከስቶ ብዙም ሳይራመድ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተደጋጋሚ መገናኛ ብዙኀንን መወረፋቸውን ተከትሎ እነ ኢቲቪ፣ አዲስ ቲቪ፣ አማራ ቲቪ፣ ኦሮሞ ብሮድካሲቲንግ ሰርቪስ ወዘተ… ወደ ቀድሞው ባሕሪያቸው ተመልሰው በአገሪቱ ዙሪያ ገባ የሚከሰቱ አሳሳቢና አጠያያቂ ነገሮችን ያላዩና ያልሰሙ መስለው እያለፉ፥ በየዕለቱ ሊባል በሚችል ደረጃ ከጠቅላይ ሚኒስትርዐቢይ አሕመድ እና ከቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው ጋር የተያያዙ ደግ ደግ ዜናዎችን በማስኮምኮምሥራ ላይ ተጠምደዋል። ይህም ሌላው ጠለፋ ነው። ይህ ከጠቅላዩ አልፎ የባለቤታቸውን ገጽታ ለመገንባት ሲባል የሚካሔደው ዘመቻ አመጣጡ በውል የማይገለጥና ምንጩ ይፋ በማይደረግ ከፍተኛ ገንዘብ አማካኝነት እየተደገፈ‘በወይዘሮ ዝናሽ ገንዘብ የሚገነባ’፣ ‘ወይዘሮ ዝናሽ ባሰባሰቡት ገንዘብ የሚገነባ’ ወዘተ… እየተባለ እዚህና እዚያ የመሠረት ድንጋይ እየተጣለ በጥድፊያ ሲከናወን ይታያል። ይህ ርብርብ አዲስ ‘ዐፄ’ እና ‘እቴጌ’ አከል ሰብእና ለመፍጠር ታስቦበት የሚደረግ አካሔድ ይመስላል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤት ስብሰባዎች፣ የአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በታደሙበትአንድና ብቸኛ አጋጣሚ፣ የመከላከያ ባለሥልጣናትን በሰበሰቡበትና በሌሎችም ጊዜያት የቀረቡላቸውን ጥያቄዎች በቁጣና ለምን የዚህ ዓይነት ጥያቄ ይነሳል በሚል ቃና ሲመልሱ በተደጋጋሚ ተሰምተዋል፤ ታይተዋል። በአጭር ጊዜ ውስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ማድረግና መደመጥን እንጅ መጠ፡የቅን የሚሹ አለመሆናቸውን የሚያሳብቁ በርካታ አጋጣሚዎች ተፈራርቀዋል። የካቲት 10 ቀን 2011 ከአምስቱ ታዳጊ ክልሎች የተጠሩ ወደ 3 ሺሕገደማ ሰዎችን ያነጋገሩበት ስብሰባ ደግሞ፥ ሰዎች አስተያየተ ስለዘነዘሩ፣ ማሳሰቢያ ስለሰጡ፣ ጥቆማዎችን ስለሰነዘሩና ጥያቄዎችን ስላቀረቡ ብቻ ዘለፋ የታከለበት ምላሽ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መሰንሰዘሩ ነገሮች ወደ የት እየሔዱ ነው የሚስብል ነው። ‘አለቀሳችሁብኝ’ ብለው ሲማርሩና ‘በሚቀጥለው ስብሰባ መሐረም ይዘን መገኘት ይገባናል’ ብለው ሲያላግጡም ተሰምተዋል።

በሌሎች የሚሰነዘረውን ሐሳብ ‘ከተበላሸ ጭንቅላት የፈለቀ’ አድርገው ሲያቃልሉትም ተደምጠዋል። በዚህ ስብሰባ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምን ማለታቸው ብሎ በሥጋት መጠየቅን የግድ የሚል የባልና የሚስት ‘ታሪክም’ ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንድ ወዳጄ ያካፈለኝ ብለው ለ50ኛ ዓመት ክብረ በዓላቸው የደረሱ ባልና ሚስት ለዚህ ክብር እንዴት እንደበቁ ሲጠየቁ ባል ሆዬ በጋብቻው የመጀመሪያ ቀን የሚስትን በቅሎ በመግደልና ሚስታቸው ከረበሸችም የበቅሎዋ ዕጣ እንደሚደርስባት በማስፈራራት ሚስት ፀጥ ለጥ ብላ እየተገዛችላቸው እነዚያ 50 ዓመታት መቆጠራቸውን ተናግረዋል።ይህ ደግሞ የኢትዮጵያን ሕዝብ የጠመንጃ አገዛዝ ነው የሚስፈልገው የሚል አንደምታ ያለው ማስጠንቀቂያ መሠል ንግግር ነውና በእርግጥ ‘ዐቢይነታቸው በእርግጥ የኢትዮጵያ ሕዝብ የተመኘውን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመትከል ይፈልጋሉን?’ ‘በኢትዮጵያ ውስጥ ነጻ፣ ግልጽና ተአማኒነት ያለው ምርጫ ተካሒዶ፣ ሕዝብ የመረጣቸው ፓርቲዎችና ግለሰቦች ብቻሥልጣን የሚይዙበት ዘመን ቀርቧልን?’ ብሎ መጠየቅን የግድ ይላል።

ግዛቸው አበበ መምህር ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው gizachewabe@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 17 የካቲት 30 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here