መንግሥት የሕዝብን ድጋፍ እያጣ ነው ሲሉ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ገለፁ

0
684

መንግሥት ከወራት በፊት የነበረውን የሕዝብ ድጋፍ እያጣ ነው ሲሉ፣ የአገር ውስጥና በውጪ አገር የሚገኙ የፖለቲካ ማኅበራት የመሰረቱት ብሔራዊ መግባባትና ዕርቀ ሠላም ዓለም ዐቀፍ አስተባባሪ ኮሚቴ ገለጸ።

በሕዝብ ሁለንተናዊ ትግል ከኢሕአዴግ ማሕጸን የወጣው የለውጥ ኃይል፣ በጅምሩ በሕዝብ ያገኘውን ስሜታዊና ወቅታዊ ድጋፍ ተከትሎ፣ ለብሔራዊ መግባባትና ዕርቀ ሰላምም ሆነ ሁሉን አካታች የሽግግር ወቅት ጥያቄ የለውጡ መሪዎች ʻእኔ አሻግራችኋለሁʼ በሚል ጥያቄውን ሲያጣጥሉ ነበር፤ ያለው የኮሚቴው መግለጫ፣ ይሁንና ከሕገ መንግሥት ጋር ተያይዘው የሚነሱ ጥያቄዎችና ዛሬ የሚታዩት የሰብኣዊና ዴሞክራሲያዊ መብት ረገጣዎች፣ በየቦታው የሚታዩ ግጭቶችና መፈናቅሎች፣ ሰብኣዊ ቀውሶች፣..ወዘተ ʻበእኔ አሻግራችኋለሁʼ ፕሮፓጋንዳ በቀላሉ የማይታለፉ መሆናቸው የተረጋገጠ ጉዳይ መሆኑን አስምሮበታል። የትላንቱ ድጋፍ ከለውጡ ኃይል ጋር ያለመኖሩን ለማረጋገጥ የተለየ የፖለቲካ ዕውቀት የማይጠበቅበት ደረጃ ላይ እንገኛለን ሲልም ያክላል።

በሌላ በኩል የለውጡ መቀልበስ አደጋ ግልጽ ነው ያለው ጽሑፉ፣ በመሆኑም ሁላችንም የበኩላችንን አስተዋጽኦ በማበርከት ጅምር ለውጡን የማስቀጠል የጋራ ኃላፊነት ያለብን ስለመሆኑ ብዙዎች እየመከሩ ነው ሲል ተንትኗል።

ሕገ መንግሥት፣ የአንድ አገር ሕዝብ ከመንግሥት ጋር የሚኖረውን ግንኙነት በሚመለከት በተወካዮቹ አማካኝነት በጉባዔ ተሰብስቦ የሚያዘጋጀው የጋራ ውል ሲሆን፣ ይህ የጋራ ውል እንደ ማኅበረሰቡ እድገትና እንደዘመኑ የሕዝብ ጥያቄና ፍላጎት በየጊዜው የሚሻሻል ነው፤ በተለያዩ አገሮች ሕገ መንግሥት ለበርካታ ጊዜያት ታድሶ ያውቃል ያሉት የፕሮግራሙ አስተባባሪና የሲያትሉ ተወካይ ስለሺ ጥላሁን፣ በእኛ አገር ከመነሻው፣ ሕዝብ በተወካዮቹ ያጸደቀው ሕገ መንግሥት ልንቀርጽ አልታደልንም፣ መንግሥታት ራሳቸው የጻፉትን ሕገ መንግሥት ሊያከብሩ ሳይሆን የመጨቆኛ መሳሪያ አድርገው ሲጠቀሙት ኖረው፣ ሲወድቁ ሕገ መንግስቱን አሻሽሎ ለማስቀጠል አልታደልንም፣ በየመንግሥት ለውጡ ቀደን ስንጥለውና አዲስ ግን፣ በተመሳሳይ መንገድ ስንጽፍ ኖረናል። ዛሬም ያለው ሕገ መንግሥት ከዝግጅቱ እስከ ትግበራው ተመሳሳይ ነው፤ እንዲያውም ሕዝቡ አለመሳተፉን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ ያረቀቁትና ያጸደቁት እየመሰከሩ ነው፤ ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በሕገ መንግስት ሥም በሕዝብ ላይ መንግሥት የሚፈጽመው ጭቆናና አፈና እየጸና መጣ እንጂ ሕዝብ የሕገ መንግሥቱ ተጠቃሚ አልሆነም የሚል የሕገ መንግስታዊነት ጥያቄ እየሰፋ መጥቷል ማለት ይቻላል ብለዋል።

ስለዚህ፣ ይህ አጀንዳ በህገ መንግስቱ አሳታፊ ያለመሆንና በውስን ድርጅቶች ፍለጎት ማስፈጸሚያ ሆኖ የተዘጋጀ በመሆኑ ያደረሰው ጥፋት ከባድ ቢሆንም፣ ያለውን ህገ መንግስት እንደለመድነው ቀደን ከመጣል ልናሻሽለውና ልናስቀጥለው አይቻለንምን? የሚቻለን ከሆነስ የትኞቹ አንቀጾች ሊሻሻሉ ይገባል? ይህን በመፈጸም አገራችን ከገባችበት ቀውስ ለማውጣት አይቻለንም? አምባገነኖች እንዲህ ላለው ጥያቄ በጄ አይሉምና እንደምን በአንድነት ልናስገድዳቸው ይቻለናል?…..ወዘተ በሚሉ አጀንዳዎች ላይም ውይይቶች በቅርቡ እንደሚካሄዱ የመኢአድ ም/ሊ በዛብህ ደምሴ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

ከላይ በተገለጸው የሕገ መንግስት ችግር የተዛባ የመንግሥትና የሕዝብ ግንኙነት ብቻም ሳይሆን ከታሪክ ትርክትና አረዳድ ልዩነታችን እንዲሁም፣ በተለይ ባለፉት 27 ዓመታት የተገዛንበት የሕወሓት/ኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት በከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ የታጀበ በመሆኑ በሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነታችን ላይ ያሳደረው የጥርጣሬ ሲያልፍም የጥላቻ ስሜት እንደብቀው ብንል ከማንደብቀው ደረጃ ደርሷል ሲል ጽሑፉ ያብራራል።

በሕዝብና መንግሥት፣ በፖለቲካ ድርጅቶችና መንግሥት፣ በፖለቲካ ድርጅቶች መካከል (አሁንማ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶን ጨምሮ) ልዩነትና ያለመተማመን እየሰፋ መምጣቱ አሌ አይባልም ያሉት የዕለቱ አወያይና የሲያትሉ ተወካይ ስለሺ ጥላሁን፣ እንዲሁም በቡድኖች ፊት አውራሪነትና ፕሮፖጋንዳ በሕዝብ መካከል የሚከሰቱ ግጭቶችና በክልሎች መካከል ያለው ጤናማ ያልሆነ ግንኙነት…ወዘተ የብሔራዊ መግባባትና ዕርቀ ሠላም ጥያቄ እንደ ትናንቱ ʻማን ከማን ተጣላʼ በሚል የሚሸፈን፣ ወይም እንደዛሬው ለመንግሥት ሐሳብ፣ መዋቅርና ጥረት ብቻ የሚተው ሳይሆን፣ የአገሪቱ ጉዳይ የሚመለከታቸው ሁሉ በባለቤትነት የሚሳተፉበት ሁሉን ዐቀፍ መድረክ የማይታለፍ መሆኑንና በተለይም፣ ጅምሩ ለውጥ ይዞ ከመጣው ተስፋና ሥጋት የተስፋው ክበብ እየጠበበ፣ የሥጋቱ አድማስ እየሰፋ በመጣበት በአሁኑ ወቅት የዚህ ጥያቄ ወቅታዊነትና አስፈላጊነት ለውይይት የሚቀርብ ሳይሆን የግድ ከሚባልበት ደረጃ ደርሷል ማለት ይቻላል ነው የሚሉት። ስለዚህ በዚህ ዙሪያ አጀንዳ ከፍቶ ተወያይቶ አንድ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ፣ የተዘራውንና በፍጥነት የተሰራጨውን የጥርጣሬና ጥላቻ አረም መንቀል እንዴት ይቻላል? ብሎ መምከር ጊዜ የሚሰጠው አይደለም ባይ ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን እንደመጡ፣ ከፕሬዝዳንቱ ጋር መገናኘታቸውንና ከሲያትሉ ጉባዔ ውሳኔዎች ከታየው የለውጥ ጅማሮ አንጻር በተለይ በሁሉን ዐቀፍ ብሔራዊ መግባባትና ዕርቀ ሰላም ላይ ትኩረት በመስጠት የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልጸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለዓላማው ድጋፍ እንዲሰጡ በደብዳቤ ከአገር ቤት ኮሚቴውና ከዓለም ዐቀፍ አስተባባሪ ኮሚቴው ሦስት ደብዳቤዎች ቢቀርብም ምላሽ አላገኘንም ያሉት በዛብህ ደምሴ (ዶ/ር)፣ ይሁን እንጂ፣ ኮሚቴው በዚህ ተስፋ ቆርጦ ከእንቅስቃሴው አልተገታም ብለዋል።

ከፖለቲካ ድርጅቶች ጋር ለመመካከር ነሐሴ 20/2010 በተደረገው ጥሪ ከዚህ በፊት በዚሁ ራስ ሆቴል በተዘጋጀው መድረክ ከ50 በላይ የፖለቲካ ድርጅቶች ከአገር ቤትና ከውጪ የገቡ፣ ከኢሕአዴግ የወቅቱ ብአዴን/የአሁኑን አዴፓ/ ጨምሮ ተሳትፈው የኮሚቴውን ዓላማ በማጽናት ስምምነታቸውን ገልጸው፣ ለጉባኤው ጠቃሚ ግብዓት ከማቅረባቸው በተጨማሪ፣ ማንኛውንም ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል ያሉት ስለሺ፣ በጳጉሜ 03/2010 ከ100 በላይ ባለድርሻ አካላት ጋር የተደረገው ምክክር ውጤቱ ተመሳሳይ እንደነበርና በቀጣይ የአገር ቤት ኮሚቴው ፕሬዝዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር) ሥልጣናቸውን በመልቀቃቸውና የሰላም ሚኒስቴር በመቋቋሙ ደብዳቤ ለኹለቱም ጽፈው ከፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ መልስ ባያገኝም ከሰላም ሚኒስትሯ ሙፌሪያት ካሚል ጋር ቀጠሮ ተይዞ በኅዳር 29/11 በብሔረሰቦች ቀን በዓል ምክንያት በቀጠሯቸው ሳይገኙ ቀርተው፣ ክብርት ሚኒስትሯ ይቅርታ ጠይቀው በቅርብ ቀን እንደሚያገኙን ቃል ቢገቡም እስከዛሬም አልተገናኘንም ሲሉ የተሰማቸውን ሐዘን ገልጸዋል።

ከዚህ በኋላ ለስድስት ወራት በየሳምንቱ በቴሌኮንፍረን ሲገናኝና በሒደቱ ላይ ሲወያይ የቆየው ዓለም ዐቀፍ አስተባባሪ ኮሚቴ አብዛኛው የሲያትል ተሳታፊዎች ወደ አገር ቤት በመግባታቸው አስተባባሪ ኮሚቴው አንድ ከውጪ አንድ ከአገር ቤት የወቅት አስተባባሪዎች በመመደብ ዓለም ዐቀፍ እንቅስቃሴው ሙሉ በሙሉ አገር ቤት መግባቱን ጠቁመዋል።
የወቅቱ አስተባባሪዎች ከአገር ቤት ኮሚቴው ጋር በመሆን ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ኹለት ውይይቶች አድርገው ባስቀመጡት አቅጣጫ መሰረት የሐሙሱ የቅድመ ጉባዔ የምክክር መድረክ ተዘጋጅቷል።

የምክክሩ ዋና ዓላማም የአስተባባሪ ኮሚቴው ለጉባኤው ባቀረባቸው አጀንዳዎችና በአጀንዳዎቹ ጠቋሚ ሐሳቦች ላይ የቀረበውን ጠቋሚ ሐሳብና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ ማብራሪያ ለማቅረብና ምክር ለመቀበል ነው። በቀጣይም በሚዘጋጀው ሰፊ የውይይት መድረክ ላይ የሕገ መንግሥት መሻሻል፣ ሁሉን ዐቀፍ ብሔራዊ መግባባትና ዕርቀ ሠላም፤ የለውጡ ሒደት እንዴትና በማን ይመራል? የሚሉት ናቸው።

ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንደሚያራምዱት ርዕዮተ ዓለም ተመሳሳይነት፣ አንድነት በመፍጠር ራሳቸውን እንዲያጠናክሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‘የዴሞክራሲ ባህል በኢትዮጵያ’ በሚል ርዕስ ባቀረቡት የውይይት ጽሑፍ ላይ፤ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ጠንካራና ለአገር ግንባታ የሚበጅ አጀንዳ ይዘው የሚንቀሳቀስ ፓርቲዎች ያስፈልጓታል። በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ቁጥራቸው የበዙ ፓርቲዎች መኖራቸውን አስታውሰው፤ እነዚህ ፓርቲዎች “እኔ ብቻ በቂ ነኝ” ከሚል እሳቤ ወጥተው ለጋራ ዓላማ ቅድሚያ መስጠት አለባቸው ብለውም ነበር። ይህ እውን እንዲሆን በፖለቲካ ሜዳው የሚጫወቱ ሰዎች ራሳቸውን መግዛትና በመደመር አገር ለመገንባት መሥራት እንዳለባቸው ጠቁመውም ነበር።

የኢሕአዴግ በራሱ አንድ ድርጅት ሳይሆን ግንባር መሆኑን አስታውሰው፤ ፓርቲዎቹ ሰብሰብ ለማለት ይህን አማራጭ መከተል እንደሚችሉ ጠቁመው፣ ፓርቲዎቹ ወደ ሦስት ወይም አራት ቢመጡ ከመንግሥት ጋር በቀላሉ በመሟገት የተሻለ ሐሳብ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ እንዲሰርጽ ማድረግ እንደሚችሉም አክለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው ኅዳር በኢትዮጵያ ከሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተወያዩበት ወቅትም፣ መንግሥት ቀጣይነት ያለው የፓርቲዎች መድረክ እንዲፈጠር ፍላጎት አለው ማለታቸው ይታወሳል።

 

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here