ዐቢይ ላይ የተንጠለጠለው የአፍሪካ ቀንድ ጉዞ

0
868

የአፍሪካ ቀንድ መልክ
የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በዓለም የተወሳሰቡና የግጭት አካባቢዎች ከሚባሉት አንዱ ስለመሆኑ የሚያስታውሰው እና ኤስኤስአርሲ በተሰኘ የበይነ መረብ ገጽ ላይ የወጣው ʻCrisis in the Horn of Africaʼ የተሰኘ ጽሑፍ የአፍሪካ ቀንድ አገራት የሚባሉት ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ሶማሊያ፣ ጅቡቲ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን ለረጅም ዘመናት በፖለቲካ ኹከት ውስጥ የኖሩና ያሉ፣ በአካባቢያዊና አገራዊ ተቃውሞዎች የሚፈተኑ፣ በማንነት ፖለቲካና በቀጣናዊ የእርስ በእርስ አመፃና ፉክከር የመጡ መሆናቸውን ያክላል።

ቀጣናው ለ150 ዓመታት በስትራቴጂካዊ የኃይል ሽሚያ የቴአትር መድረክ ሆኖ መኖሩንም ይኸው ጽሑፍ ያትታል። በምሳሌ ሲያስረዳም የእንግሊዝ በቀይ ባሕር እና የግብጽ በአባይ ውኃ የበላይ ለመሆን ግብግብ መግጠም፣ የአፍሪካ ቀንድ ለዓለም ኃያላን የቀዝቃዛው ጦርነት መጋጠሚያ ቦታ ሆኖ ማገልገል፣ እንዲሁም የአሜሪካ አስተዳደር በሽብርተኝነት ላይ ዓለም ዐቀፋዊ ጦርነት የመክፈቻ አንድ ቀጣና መሆን ለአፍሪካ ቀንድ ፈተና ሆነው መዝለቃቸውን ይዘረዝራል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ ጠንክረው የመጡት የተለያዩ አገራት በአፍሪካ ቀንድ የጦር ሰፈር መገንባት ሌላው የቀጣናውን የመልክዓ ምድራዊ ፖለቲካ መቋመሪያ መሆንን የሚሳዩ ጽሐፍትም የበረከቱ ናቸው። ለዚህ ደግሞ የቀጣናው አገራት ከወዲሁ ሊነቁ ካልቻሉ የኋላ ኋላ በብሔራዊ ጥቅምና ደኅንነታቸው ላይ የከፋ ስጋት ይደቀንባቸዋል የሚሉም አሉ።

በፖለቲካ ሳይንስ ኹለተኛ ድግሪያቸውን ከአንካራ ይልድሪም ቤያዚት ዩኒቨርሲቲ ያገኙት ሞሐመድ ሳሌህ አሕመድ ከጥቂት ወራት በፊት በጻፉት ሐቲት የአፍሪካ ቀንድ አገራት በውስብስብ ችግር ውስጥ ስለማለፋቸው በመግለጽ በኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ አመራር መምጣቱን ተከትሎ የነበሩባቸውን ቁርሾዎች ለማሻርና አዲስ የትብብር መንፈስ ለመፍጠር እየሠሩ መሆናቸውን ያነሳሉ። በተለይም አዲስ እየተፈጠረ ላለው ግንኙነት የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚንስትር (ዶ/ር) ጉልሁን ድርሻ እንደሚወስዱ የእሳቸውም ፍላጎት በአፍሪካ ቀንድ አዲስ ዓይነት ትብብር ፈጥሮ የአዲስ ታሪክ ባለቤት መሆን እንደሆነ ይጠቅሳሉ። ጠቅላይ ሚንስትሩ በተለይም ከሶማሊያና ኤርትራ ጋር የጀመሩት ግንኙነት ለዓመታት የዘለቀና ያልተፈታ የድንበር ጥያቄ ላላቸው አገራት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውም በእጅጉ የሚፈተንበት እንደሚሆን ያስረዳሉ። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በተደጋጋሚ ሲያነሱ ከተደመጡት ጉዳይ አንዱ በምሥራቅ አፍሪካ በተለይም የአፍሪካ ቀንድ አገራት መካከል ድንበር የሚባል ነገር እንደሌለና የቅኝ ገዥዎች እሳቤና የሐሳብ ወሰን እንደሆነ የሚገልጽ ነው። ጸሐፍት ግን የአገራት የድንበር ጥያቄ እንዲህ በቀላሉ የቅኝ ገዥዎች እሳቤ ነው በሚል ድንበር አያስፈልገንም በሚለው ይስማማሉ ወይ ሲሉ በተደጋጋሚ በመጠየቅ ባሉት የተለያዩ ፍላጎቶች ጉዞው ቀላል እንደማይሆን ያሰምሩበታል። ከፈታኞቹ ነገሮች መካከልም የሀብት (ጥቅም) ግጭት አንዱ አንደሚሆን ያነሳሉ።

አዲሱ ትብብር
ሞሐመድ በጽሑፋቸው ዐቢይ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሶማሊያ አቅንተው የነበረው የተባበሩት አረብ ኢሚሬቶች ለኢትዮጵያ የሦስት ሚሊዮን ዶላር የኢንቨስትመንት ድጋፍ ባደረገች በጥቂት ቀን ውስጥ መሆኑን በማስታወስ በዚህም ሶማሊያዊያን የጠቅላይ ሚንስትሩን ጉብኝት በጥርጣሬና በተቃውሞ እንዲያዩት ማድረጉንም ያክላል። የጥርጣሬው መንስኤ ደግሞ አረብ ኢሚሬቶችና ሶማሊያ በበርበራ ወደብ ጉዳይ ተቃርኖ ውስጥ ገብተው መገኘታቸው ነው።

ኢትዮጵያም ብትሆን ከሱማሌ ላንድ የበርበራ ወደብ በገዛችው 19 በመቶ ድርሻ ባለፈው ዓመት ከሶማሊያ ታዕታይ ምክር ቤት ተቃውሞ ገጥመሟት እንደነበር አይዘነጋም። በወቅቱ በኢትዮጵያ መንግሥት አቋም ላይ ማብራሪያ ተጠይቀው ነበሩት የውጭ ጉዳዳ ቃል አቀባዩ መለስ ዓለም ጉዳዩ የሶማሊያዊያን የውስጥ ጉዳይ እንደሆነ በመግለጽ፣ ኢትዮጵያ ወደቡን የገዛችው ለምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ብቻም እንደሆነ አስረድተው ነበር።

በዚሁ ተያይዞም በርበራ ወደብ የሚገኝባት ሶማሊ ላንድ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሌሎቹ አገራት ዘንድ ያላት እውቅና (የሉዓላዊ አገርነት ወይስ አንዷ የሶማሊያ ግዛት) ሌላው ቀጣናውን አንድ በማድረግ ሒደት የሚፈትን ጉዳይ እንደሚሆን ይነሳል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ሞሐመድ አዲሱ የፖለቲካ ግንኙነት በዐቢይ ላይ የተንጠለጠለና ስኬቱም ወይም ዕጣ ፈንታው እሳቸው በሚያመጡት ውጤት ሊወሰን የሚችል እንደሆነ ያሰምሩበታል። በሶማሊያ ክልላዊ አስተዳደሮችና በፌደራል መንግሥቱ መካከል ያለውን የፖለቲካ ውጥረት መፍታት ለብቻው በቀጣናው አዲሱ የፖለቲካ ትርክትና ተስፋ ላይ የጎላ ድርሻ እንደሚኖረው በማስገንዘብም እሱ የሚፈታበት አግባብ ሌላው ፈታኝ መሆኑን ጽሑፉ ያሳስባል።

ሌላው ጉዳይ አዲሱ የትብብር ስሜት በአፍሪካ ቀንድ የበላይነትን (በምጣኔ ሀብት፣ ንግድና ገበያ) ለመያዝ ከሚፋተጉት የባሕረ ሰላጤው አገራት ጣልቃ ገብነትና እጅ ነፃ መሆኑን ማረጋገጡ እንደሆነም የሞሐመድ ሐቲት ያነሳዋል።

የኃያላኑ ፍትጊያና የአፍሪከ ቀንድ የትብብር ዐውድ
መሃሪ ታደለ (ዶ/ር) በሰላምና ፀጥታ እንዲሁም በሕግና አስተዳደር ተመራማሪ ናቸው። እሳቸው ባለፈው መስከረም 29 አልጀዚራ ላይ ያሰፈሩት ጽሑፍ እንደሚለው፣ ከአፍሪካ ቀንድ ትብብር ጀርባ የሌሎች አገራት እጅ አለበት። የቀጣናውን አዲስ የትብብር መንፈስ በገንዘብ በማገዝ በኩል ሳዑዲ አረቢያና አረብ ኢሚሬት ከፊት መስመር እንደሚገኙ ያነሳሉ። ለእነሱ የኋላ ደጀን በመሆን በኩል ደግሞ እጀ ረጅሟ አሜሪካ እንዳለችበትም በጽሑፋቸው ያመለክታሉ።

አሜሪካ በቻናና ሩሲያ እየተወሰደባት የመጣውን የልዕለ ኃያልነት ሥልጣን እስከወዲያኛው ላለመነጠቅ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት ቅድያሚ የሚሰጠውን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ትኩረት ከቀየረች ሰነባብታለች። በተለይም የቻይና በአፍሪካ ምድር የገዘፈ ኢንቨስትመንት ባለቤት እየሆኑ መምጣት ስጋት አሜሪካ የምጣኔ ሀብት ጦርነቱን በአፍሪካ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ ላይ አነጣጥራለች። በቀይ ባሕር ላይ የበላይነቱን ለመውሰድ በሚደረግ ግብግብም ጅቡቲ ላይ በቻይና የተቀደመችው ፈርጣማዋ አሜሪካ ጅቡቲን ያገለለና ኤርትራ ላይ ትኩረት ያደረገን አካሔድ ስለመምረጧም ይነሳል።

ምሥራቅ አፍሪካ የኃያላኑ መፋተጊያ መሆናቸውን በተለያዩ ማስረጃዎች የሚያብራሩት መሃሪ የአፍሪካ ቀንድ አገራት ከዚህ በኋላ ከኃያላኑ የሚያገኙት ድጋፍ ቅድመ ሁኔታን መሰረት ያደረገ እየሆነ እንደሚመጣ ግምታቸውን በማስቀመጥ አገራቱ ዋስትና ከሌለው የውስጥ ጉዳያቸው ጣልቃ ገብነት ራሳቸውን ሊከላከሉና ሊመክቱ እንደሚገባም ይመክራሉ። በፖሊሲያቸውና በሉዓላዊ ጉዳያቸው ላይ ጥንቃቄ የተሞላበት አካሔድ መምረጥንም ለድርድር ማቅረብ እንደሌለባቸው ያስጠነቅቃሉ። አፍሪካዊያን ይህን ማድረግ ከቻሉ እያደገ በመጣው የኃያላኑ የምጣኔ ሀብት ፉክክር አትራፊ መሆን እንደሚችሉም ይመክራሉ።

የአፍሪካዊያኑ የሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም ጉዳይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የብዙዎች ጥያቄና ስጋት እየሆነ መጥቷል። ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ የአገራቱን አዲስ ትብብርና የኃያላኑን ጉዳይ በተመለከተ ኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሟን አሳልፋ እንደማትሰጥና በዚህም ላይ ድርድር እንደማይኖር መናገራቸው ይታወሳል።

በአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ተመራማሪነታቸው የሚታወቁት ማርቲን ፕላውት ለአዲስ ማለዳ አስተያየት ሲሰጡ የአፍሪካ ቀንድ አገራት አንድ ላይ መሆናቸውና መተባበራቸው እጅግ ጠቃሚ ነው ይላሉ። በቀጣናው የቻይናና አሜሪካ ፍላጎት እያደገ መምጣቱ መረሳት የለበትም የሚሉት ማርቲን የቱርክ፣ የአረብ አገራት እና ቅኝ ገዥ የነበሩት እንግሊዝና ፈረንሳይ ፍላጎትም መዘንጋት እንደሌለበት ያነሳሉ። ስለሆነም ከወዲሁ ትብብራቸውን ማላቅ እንደሚጠበቅባቸው ይመክራሉ።

ስጋት ተስፋ
ማርቲን እንደሚሉት በአፍሪካ ቀንድ በታሪክ፣ ዘርና ምጣኔ ሀብትዊ ፍላጎቶች የተነሳ እስከዛሬም ያልተፈቱ የእውነተኛ ችግሮች አሉ። እንዲህ ዓይነት ችግሮች ግን በአውሮፓዊያንም መካከል ያለ መሆኑን በመጥቀስ አውሮፓዊያን ከኹለቱ የዓለም ጦርነቶች ተምረው እንዴት በጋራ መሥራት እና መተባበር እንዳለባቸው አውቀው ዛሬ ላይ ተጠቅመዋል፤ የአፍሪካ ቀንድ አገራትም ለምን ችግራቸውን መፍታት አይችሉም ሲሉ ይጠይቃሉ። የአገራቱ መሪዎች ውይይት መልካም መሆኑን የሚያነሱት ማርቲን እጥረቶች እንዳሉም ይገልፃሉ። የኬንያው ፕሬዘዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ከአዲስ አበባ መልስ ከዐብይ ጋር ወደ ኤርትራ መጓዛቸውንና ኋላም ኢሳያስና ዐቢይ ወደ ደቡብ ሱዳን ሲያቀኑ ኡሁሩ መቅረታቸውን ያስታውሳሉ።

በተጨማሪም ስለምን ከውይይታቸው በኋላ መግለጫ እንዳልሰጡ፣ የደቡበ ሱዳኑ ውይይት መግለጫስ ለምን ጎዶሎ ወይም ባዶ ሆነ፣ ሲሉ የሚጠይቁት ማርቲን መሪዎቹ ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ቃለ ምልልስ ማድረግን እንደሸሹ በመጥቀስም ተገቢ አይደለም ይላሉ። ምክንያታቸው ደግሞ ሕዝቡ መሪዎቻቸው ስለሚያደርጉት ውይይትና ስለሚደርሱበት ውሳኔ የማወቅ መብት፣ መሪዎቹም የማሳወቅ ግዴታ አለባቸው የሚል ነው። የመሪዎቹ ውይይት በአገራቱና ዜጎቹ መፃዒ ላይ እስከሆነ ድረስ ከሕዝብ መደበቅ እንደሌለበትም ያሰምሩበታል።

በሰሞኑ ጉዞ ዐቢይ ከደቡብ ሱዳን በኋላ ወደ ሱዳን መሔድ እቅድ የነበራቸው ቢሆንም መሰረዙን ሱዳን ትሪቡን አስነብቧል። ምክንያት በሚል ካስቀመጣቸው ትንበያዎች መካከል አንዱ አብረዋቸው የነበሩት ኢሳያስ አፈወርቂ ከሱዳን ጋር ገብተውበት በነበረው እሰጥ አገባ ካርቱም መሔዱን ስላልፈለጉት ነው የሚል ነው።

ሌላው የሶማሊያና የኬንያ ሕንድ ውቅኖስ ላይ ያለው የግዛት ይገባኛል ጥያቄ ውዝግብ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከሰሞነኛ የአፍሪካ ቀንድ ጉዞና የመሪዎች ውይይታቸው መልስ የሶማሊያውን ፕሬዚዳንት መሐመድ አብዱላሂ መሐመድ አዲስ አበባ አግኝተዋቸው ነበር። የጠቅላይ ሚንስተር ጽሕፈት ቤት እንዳሳወቀው ውይይታቸው በአራት ጉዳዮች ላይ የተካሄደ ነው። ይህም የቀጣናውን ሰላም ማጠናከር፣ የኬንያና ሶማሊያ ግንኙነትን ማደስ፣ ለጋራ የወደብ ልማትና ለአካባቢው ሰላም ከሶማሊላንድ አስተዳደር ጋር የሚኖረውን ግንኙነት ስለማጠናከር መሆኑ ተሰምቷል። ከኬንያ ጋር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እስከማቋረጥ የደረሰችው ሶማሊያ መሪ መሐመድ አብዱላሂ ከአዲስ አበባው ውይይት በኋላ ከኬንያ አቻቸው ጋር ፊት ለፊት ተገናኝቶ ለመምከር ፍቃደኛ በመሆናቸው ከዐቢይ ጋር ወደ ናይሮቢ መጓዛቸውን የገለጹት የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት ፕረስ ሴክሪታሪ ኃላፊ ንጉሡ ጥላሁን የሶማሊያና ኬንያ ውጥረት እየባሰ ከሔደ ከእነሱ አልፎ ለቀጣናውም የሚተርፍ ስለሆነ በውይይት ለመፍታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን ጠቅሰዋል። በሰሞኑ ውይይት ሶማሊያና ኬንያ ተቃርኗቸውን በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ብቻ ለመፍታት መስማማታቸውም ተሰምቷል።

በአፍሪካ ቀንድ ያሉትን ችግሮች ሁሉ የማስማማቱ ሥራ በብዛት ዐቢይ ወይም ኢትዮጵያ ላይ ወድቋል የሚሉ ተንታኖች የአፍሪካ ቀንድን የማስተባበሩና አንድ የማድረጉ ሥራ ከባድ መሆኑን ያስገነዝባሉ።

ኢትዮጵያ ቀጠናውን ለማስተባበር የመሪነት ድርሻ ስለወሰደችበት ምክንያት ንጉሡ ለመገናኛ ብዙኃን ሲያስረዱ በኢትዮጵያ የተጀመረው የለውጥ ጉዞ እንዲሳካ ጎረቤት አገራት ሰላም መሆን አለባቸው፣ ከጎረቤቶች ጋር ተባብሮ መሥራትም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ነው ብለዋል። ቀጠናው ሰላም ከራቀው ለኢትዮጵያም ጥሩ አይሆንም ያሉት ንጉሡ የሰሞነኛው ውይይቶች መግባባት ላይ የተደረሰባቸውና ስኬታማም ነበሩም ሲሉ አክለዋል።

ማርቲን ደግሞ በአገራት የባለቤትነት ጥያቄ የሚነሳባቸው ስፍራዎች መኖራቸውን በመጥቀስ እነሱ መፈታት አለባቸው ይላሉ። ለምሳሌም በቱርካና ሃይቅ ዙሪያ ያለው የኬንያ፣ ኢትዮጵያና ደቡብ ሱዳን ጥያቄ እስካሁን ግልፅ እልባት እንዳላገኘ በመጥቀስ ድንገት የነዳጅ ዘይት ክምችት ቢገኝበት የባለቤትነት ጥያቄው እንዴት ሊፈታ ነው ሲሉ የጥቅምና ይገባኛል ጥያቄዎች ያሉባቸው ስፍራዎች ቀድመው እልባት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ይመክራሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 17 የካቲት 30 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here