የሕዝብና ቤት ቆጠራ ተስፋና ሥጋት

0
683

ከዓመት ዓመት የጊዜ ሰሌዳው ሲገፋ የሰነበተው የሕዝብና ቤት ቆጠራ በመጋቢት ወር ይካሔዳል። ሆኖም አገሪቱ ባልተረጋጋችበት ወቅት መካሔዱ ሌላ አለመረጋጋት ይፈጥራል የሚል ሥጋት እና ከዚህ በኋላ ሊራዘም አይችልም የሚሉት አጣብቂኞች እንቆቅልሽ ፈጥረዋል። ታምራት አስታጥቄ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕሰ ጉዳይ በማድረግ ባለሙያዎችን እና የሚመለከታቸውን ወገኖች እንዲሁም ሰነዶች በማገላበጥ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባውን ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ እና ሌሎችም ትኩረት ይሰጣቸው የሚል ጥቆማ አቅርቧል።

በዓለም የሕዝብ ቆጠራ መካሔድ የጀመረው ከብዙ ሺሕ ዓመታት በፊት ጀምሮ መሆኑን በተለያዩ ድርሳናት ተመዝግቧል። የመጀመሪያ የሕዝብ ቆጠራ ተብሎ የሚታመነው በጥንት ባቢሎናዉያን ከስድሰት ሺሕ ዓመታት በፊት የተካሔደው እንደሆነ በታሪክ መጽሐፍት ላይ ሰፍሯል። ሌላው ቀደምት የሕዝብ ቆጠራ አካሒደዋል ከሚባሉት ውስጥ ጥንታዊቷ ሮማ አንዷ ስትሆን በዋነኛነት የሕዝብ ቆጠራው ለወታደራዊ ግዳጅ ብቁ የሆኑ ጎልማሳ ወንዶችን ለመመዝገብ ዓላማ እንደሆነ የተለያዩ የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ።

ቆጠራዎች በዓይነታቸው ብዙ ሲሆኑ ከሕዝብና ቤት ቆጠራ በተጨማሪ የግብርና፣ የንግድና የትራፊክ ሊኖሩ እንደሚችሉ በጉዳዩ ዙሪያ የተጻፉ ድርሳናት ያወሳሉ። ዘመናዊ የሕዝብና ቤት ቆጠራን በተመለከተ የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን ʻየአራተኛው ዙር ሕዝብና ቤት ቆጠራ ትምህርትና ቅስቀሳ መሪ ሰነድʼ በሚል ርዕስ በጥር 2011 ባሳተመው ምጥን መጽሐፍ መሠረት የሕዝብና ቤት ቆጠራ በተወሰነ ወቅትና በአገር ዐቀፍ ደረጃ ወይም በአገር ውስጥ በተወሰነ የአስተዳደር ክልል ስለሚገኝ ሕዝብ ብዛትና ስለ ሕዝቡ የሥነ ሕዝብ ባሕሪያት፣ የማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ እንዲሁም በአገር ዐቀፍ ወይም በተወሰነ የአስተዳደር ክልል ስለሚገኙ ቤቶች ብዛት፣ ስለቤቶች ሁኔታ የሚገልጹ ስታትስቲካዊ መረጃዎችን የመሰብሰብ፣ የማጠናቀር፣ የመተንትንና ትክክለኛነቱንም በመገምገም ሪፖርት የማዘጋጀትና የተገኘውን ውጤት ለተጠቃሚዎች የማሰራጫት ተግባራትን ያጠቃልላል። የሕዝብና ቤት ቆጠራ ውጤት ሪፖርት በከተማ እና በገጠር፣ በአገር ዐቀፍ፣ በዞን፣ በወረዳ እና በቀበሌ ደረጃ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ የሚያመለክት መረጃ ለማዘጋት መሠረት ነው።

የተባበሩት መንግሥታት በበኩሉ የሕዝብና ቤት ቆጠራን በአጭሩ ‘‘በተወሰነ ግዛት ውስጥ፣ በተመሳሳይ ጊዜና በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ የሚካሔድ የግለሰብ ቆጠራ’’ በማለት ብያኔ ሰጥቶታል። አገራት ቢያንስ በየዐሥር ዓመቱ ቆጠራ እንዲያካሒዱም ድርጅቱ ይመክራል። ይህም ዓለም ዐቀፍ ስታትስቲካዊ ንፅፅር ለማካሔድ እንደሚጠቅም አመላክቷል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝብ ቆጠራ መካሔድ የጀመረው ዘግይቶ ነው። የሕዝብ ቆጠራ ኮሚሽን ከላይ በተጠቀሰው መጽሐፍ ኢትዮጵያ በጥቂት አካባቢዎች ማለትም በአዲስ አበባና በሌሎች ትላልቅ ከተሞች የሕዝብ ቆጠራዎች የተካሔዱ ሲሆን፥ በተለይ በአዲስ አበባ በ1953 እና 1961 ቆጠራዎች መካሔዳቸውን የአገሪቱን የቆጠራ ታሪክ ጠቅሶ አስፍሯል።

በኢትዮጵያ ዘመናዊ የሕዝብ ቆጠራ መሥፈርትን ያሟላ ቆጠራ እንዲሔድ ቀድም ካሉት ዓመታት ጀምሮ ሙከራዎች የተደረጉ ሲሆን በተለይ ቀደም ብሎ ጠቅላይ ስታትስቲክስ ጽ/ቤት ተብሎ ይጠራ በነበረውና በአሁኑ ማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ አማካኝነት አዋጅ ቁጥር 303/1964 በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በ1968 ቆጠራ ለማካሔድ ከፍተኛ ጥረት ቢደረግም በወቅቱ የነበረው የመንግሥት ለውጥና ሌሎችም ሁኔታዎች ባለመፍቀዳቸው ቆጠራው ሊካሔድ አለመቻሉን ከላይ የተጠቀሰው መሪ ሰነድ አገሪቱን የቆጠራ ታሪክ አጣቅሶ ጽፏል። በመሆኑም በኢትዮጵያ ሳይንሳዊ የቆጠራ መሥፈርቶችን ያሟላው የመጀመሪያው አገር ዐቀፍ የሕዝብና ቤት ቆጠራ በግንቦት 1976 ተካሒዷል።

የሕዝብና ቤት ቆጠራ በየተወሰነ ወቅት መካሔድ የሚያስፈልግ በመሆኑ ኹለተኛው የሕዝብና ቤት ቆጠራ በጥቅምት 1987፣ ሦስተኛው በግንቦት 1999 የተካሔዱ ሲሆን አራተኛው የሕዝብና ቤት ቆጠራ ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዝያ 20/2011 ለማካሔድ የቆጠራ ኮሚሽን ጽሕፈት ቤት (የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ) አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጀት በማከናወን ላይ እንደሚገኝ በሰፊው በመገናኛ ብዙኀን እየገለጸ ይገኛል።

የቆጠራው ፋይዳ
የሕዝብና ቤት ቆጠራ ሕዝብን በተመለከተ መረጃዎች የሚሰበሰቡበት ነው። ቆጠራው ምን ያክል ሕዝብ አለ የሚለው ጥያቄ ብቻ ሳይሆን በርካታ መረጃዎችን የሚያጠናክሩበትም በመሆኑ አገራዊ ፋይዳው ዘርፈ ብዙ ነው።

በሕዝብና ቤት ቆጠራ የሚሰበሰቡ መረጃዎች ለአገር ዕድገት ማለትም በትምህርት፣ በጤና፣ በሥራ ሁኔታ፣ በስርዓተ ፆታና በተለያዩ ማኅበራዊና የምጣኔ ሀብታዊ ዕቅድና ፖሊሲ ዝግጅት የሚያበረክተው አስተዋፅዖ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን የሥነ ሕዝብ ባለሙያዎችም ይናገራሉ።

ሁሉንም የአገሪቱን አካባቢዎች ፍትሐዊ በሆነ መልክ ሀብት እንዲከፋፈሉ፣ በአካባቢዎች መካከል የተመጣጠነ ዕድገት እንዲኖር፣ የአገሪቱን በጀት ለምን ተግባር ማዋል እንደሚገባ ፍንጭ የሚሰጥና እንዲሁም አገሪቱ ከሌሎች አገሮች ጋር ስትነፃፀር በምን ዕድገት ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ለማወቅ የሕዝብና ቤት ቆጠራ በእጅጉ ይጠቅማል ሲሉ በሕዝብ ቆጠራ ላይ የተጻፉ ጽሑፎች ያትታሉ።

በምርጫ ወቅትም የሕዝብ ወኪሎችን ለመለየት ቆጠራውን ማካሔድ አስፈላጊ እንዲሆን ያደርገዋል። ʻየአራተኛው ዙር ሕዝብና ቤት ቆጠራ ትምህርትና ቅስቀሳ መሪ ሰነድʼ ላይ እንደተጠቀሰው ምርጫ ዴሞከራሲያዊ በሆነ መንገድ እንዲካሔድ፣ የማንነት ጥያቄዎች ሊመለሱ የሚችሉት፣ የሕዝብ ውክልናዎች የሚታወቁት በሕዝብና ቤት ቆጠራ መረጃ ላይ ተመሥርቶ መሆኑን አመልክቷል።

የቆጠራው ውጤት ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 10 ዓመታት የምታከናውናቸውን ተግባራትንም ለማቀድ ይጠቅማል። ለክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በጀት የሚመደበው በሕዝብ ብዛት ላይ ተመሥርቶ እንደመሆኑ የሕዝብ ብዛት ስንት እንደደረሰ ማወቅ ተገቢ ነው። ውስን የሆነውን የአገሪቱ ሀብት በግምት ላይ ወይም ወቅታዊ ባልሆነ ነገር ላይ ተመሥርቶ መከፋፈል ሰለሌለበት በመርሕ ደረጃ ቢያንስ የቆጠራውን አስፈላጊነት ያጎላዋል።

በ2025 (እ.አ.አ.) ኢትዮጵያ ዝቅተኛ መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ተርታ ለመሰለፍ ራዕይ ሰንቃ እየሠራች ለምትገኝበትም ወቅታዊ መረጃ ያስፈልጋል። ለማንና እንዴት መሥራት እንዳለበት ለማወቅ የቆጠራ መረጃዎች ወሳኝ መሆኑን የመስኩ ምሁራን ይዘረዝራሉ።

የአራተኛው ዙር ቆጠራ ተስፋና ሥጋት
ቅድመ ዝግጅትና ተስፋ
በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 103 ንዑስ አንቀጽ 5 የሕዝብና የቤት ቆጠራ በየዐሥር ዓመቱ እንደሚካሔድ ደንግጓል። በዚሁ መሠረት ኅዳር 2010 ይካሔዳል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ቆጠራ አገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠረው አለመረጋጋት ሳቢያ ከአንዴም ኹለቴ መራዘሙ ይታወሳል።

አሁንም አንዳንድ ወገኖች ሰላምና መረጋጋት በሌለበት ሁኔታ ቆጠራ ማካሔዱ አደጋ እንዳለው ቢገለጽም፥ መንግሥት አሁን አንጻራዊ ሰላምና ደኅንነት መኖሩን በመግለጽ ቆጠራው በተቀመጠው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ለማከናወን ዝግጅቱን ማጠናቀቁን ቆጠራውን የሚመራው የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ በተደጋጋሚ አስታውቋል።

የሕዝብና ቤት ቆጠራ ኮሚሽን በይፋ ለመገናኛ ብዙኀን እንዳስታወቀው የአራተኛው ዙር ቆጠራ ከዚህ ቀደም እንደተካሔዱት ቆጠራዎች ሳይሆን በሁሉም ክልሎችና በአዲስ አባባና በድሬዳዋ የከተማ አስተዳደሮች በአንድ ጊዜ የሚካሔድ ይሆናል።

ስለ ቆጠራው ይፋ የተደረጉ አኀዞች እንደሚያመለክቱት በአጠቃላይ ለቆጠራው 3.5 ቢሊዮን ብር የተበጀተ ሲሆን በተጠባባቂነት ደግሞ 946 ሚሊዮን ተይዟል። 200 ሺሕ የቆጠራ ጣቢያዎች፣ 152 ሺሕ የቆጠራ ማዕከላት የተዘጋጁ ሲሆን ከ190 ሺሕ በላይ ባለሙያዎችና ተቆጣጣሪዎች እንደሚሠማሩም ታውቋል። በተጨማሪም 180 ሺሕ ታብሌት ኮምፒውተሮች እንዲሁም 126 ሺሕ ኤሌክትሪክ ቢጠፋ በሚል ተንቀሳቃሽ ቻርጀሮች መዘጋጀታቸውን ኮሚሽኑ አስታውቋል።

የማዕከላዊ ስታትስተክስ ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነትና መረጃ አሰባሰብ ዳይሬክተር ሳፊ ገመዲ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ኢትዮጵያ 4ኛውን የሕዝብና ቤቶች ቆጠራ የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም ከዚህ ቀደም ከተካሔዱት ቆጠራዎች በተሻለ ጥራት ታካሒዳለች፤ ቴክኖሎጂውን በመጠቀም ቆጠራ ባካሔዱት አገሮች ተመክሮ ላይ ተመሥርቶም እንደሚካሔድም ገልጸዋል።

የዘንድሮውን ቆጠራ በተመለከተ ከዚህ ቀደም ከተካሔዱት ሁሉ ለየት የሚያደርጉትን አንኳር ነገሮችን ሳፊ ዘርዝረዋል። በበፊቱ ቆጠራ አርብቶ አደርና አርሶ አደሮች ቆጠራው በሁሉም አካባቢዎች በተለየ ጊዜ ይካሔዱ የነበረው፥ በአራተኛው ቆጠራ ግን አንድ ላይ እንደሚካሔድ አስታውቀዋል። የማዕከላዊ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክትር ቢራቱ ይገዙ ለፋና ቴሌቪዥን በሰጡት ቃለ ምልልስ ˝ውሱን ቦታዎች ከነበሩ የድንብር አለመግባባቶች ውጪ፣ ሁሉም ቦታዎች በካርታ ተሸፍነዋል። ያልተሸፈነ ቦታ የለም˝ በማለት በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች ቆጠራው እንደሚካሔድ በመግለጽ ከሳፊ ሐሳብ ጋር የሚመሳሰል ምላሽ ሰጥተዋል።

ሌላው ቃለ ምልልሶችና መመሪያዎች በአምስት ቋንቋዎች ማለትም በአማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ትግሪኛ፣ ሶማሊኛ እና አፋርኛ መዘጋጀታቸው እና ቆጠራው ዲጅታል ቴክኖሎጂን በሥራ ላይ የሚያውል በመሆኑ የሳይበር ጥቃቶች እንዳይደርስ የመከላከል ሥራ በቂ ዝግጅት መደረጉን የዘንድሮውን ቆጠራ ለየት የሚያደርጉት መሆኑን ሳፊ አስታውቀዋል።
የዚህ ዓመቱ ቆጠራ በዘመናዊ መንገድ የሚካሔድ በመሆኑ ከዚህ ቀደም ሲታዩ የነበሩ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚያስችል ቆጠራውን የሚያካሒደው ተቋም ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሚሰጡት መግለጫዎች ተስፋ ማድረጋቸውን በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

ሥጋት
እነዚህ ሁሉ ጠቀሜታዎች እውን የሚሆኑት ግን ቆጠራው በጥንቃቄ ከተካሔደ ብቻ ነው። ከዚህ በተቃራኒው ከተፈፀመ ግን የሚመጣው አደጋ የከፋ እንደሚሆን ብዙዎች ግምታቸውን አስቀምጠዋል። በተለያዩ አካባቢዎች የሥልጣን ውክልናና የምጣኔ ሀብት ዕድገት ልዩነት ስለሚፈጥር ተቃውሞና አለመረጋጋት ሊያጋጥም እንደሚችል አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሥራ አስፈፃሚ አባልና የፓርቲው የሕግ ክፍል ኃላፊ የሆኑት ጥበበ ሰይፈ ቆጠራውን በተመለከተ ፓርቲያቸውን ያለው አቋም በተመለከተ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት እንደባለፉት ዓመታት የአማራን ሕዝብ የማሳነስ አካሔድ ሊኖር አይገባም ሲሉ ተናግረዋል።

የቀድሞ የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲዊ ፓርቲ(ኢዴፓ)ከፍተኛ አመራር የነበሩትና በአሁኑ ወቅት ሙሉ በሙሉ ከቀጥተኛ የፖለቲካ ፓርቲ ተሳትፎ ራሳቸውን ያገለሉት፣ ነገር ግን ወቅታዊውን የኢትዮጵያን ማኅበረ ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ጉዳዮች በሰፊው በመተንትን የሚታወቁት ሙሼ ሰሙ የጥበበን አስተያየት ይጋራሉ። ከዚህ ቀደም የተካሔዱት በተለይ የመጨረሻዎቹ ኹለት ቆጠራዎች በብዙዎች ተቀባይነት እንዳላገኙ የገለጹት ሙሼ በአማራ ክልል፣ በአዲስ አባባ እንዲሁም አንዳንድ ክልሎች የትግራይን የሕዝብ ቁጥር ጨምሮ ጥያቄ ያነሱበት ሁኔታ እንደነበረ በምሳሌ በማስደገፍ አብራርተዋል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀ መንበርና የኅብረት ከፍተኛ አመራር የሆኑት መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) እና የአብኑ ጥበበ ከዚህ በፊት ከተካሔደው ቆጠራ ጋር በማያያዝ ቆጠራውን የሚያካሒደው ኮሚሽንም ሆነ የማዕከላዊ ስተታትስቲክስ እንዲሁም የቆጣሪዎችና የተቆጣጣሪዎችን ተቋማዊ ተአማኒነታቸውና ግለሰባዊ ገለልተኝነታቸው ላይ ጥያቄ አንስተዋል። ሙሼም የኹለቱን አስተየየት በመደገፍ የተቋማቱ ገለልተኝነትን፣ የሕዝብ አመኔታ ላይ በቂ የሕዝብ ግንኙነት ሥራ አለመሠራቱ ሥጋት ላይ እንደጣላቸው አልሸሸጉም።

አስቻለው ጽምፀ በአርበኞች ግንቦት 7 ሥር በመመሥረት ላይ ያለው አዲስ ፓርቲ የአዲስ አበባ ከተማ ጊዜያዊ አደራጅ ኮሚቴ አባል ናቸው። አስቻለው ከዚህ በፊት የተካሔዱ ቆጠራዎችንና እንደ አገር ያለብንን ደካማነት ከግምት በማስገባት ተአማኒነት መጠበቅ አስቸጋሪ ቢሆንም፥ አሁን ካለው አገራዊ ለውጥ አንፃር ተቋማዊ ብቃትንና ተአማኒነትን በተመለከተ ትክክለኛው ሳይንሳዊ መረጃ እንደሚገኝ ይጠብቃሉ። ይሁንና ግለሰባዊ አለመታመኖች በቆጣሪዎችም ሆነ በተቆጣጣሪዎች እዚህም እዛም ሊከሰት እንደሚችል ግን መጠነኛ ሥጋታቸውን ብቻ ገልጸዋል።

በዚህ ቆጠራ ዋነኛ ፈተና ሆኖ የሚወጣው ብሔርን ከማስመዝገብ ጋር የተያያዘው እንደሚሆን የጠየቅናቸው አስተያየት ሰጪዎች አመልክተዋል። ይሁንና የብሔር ማንነትን በተመለከተ በምዝገባ ቅፁ ላይ የተካተቱትን ነገሮች በዝርዝርና በግልጽ በሚመለከተው አካል መገለጫ ባልተሰጠበት ሁኔታ በጉዳዩ ላይ ብዙዎች አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል።

ይሁንና በማንነት ዙሪያ የአማራ ክልል የኮሚውኒኬሽን ዋና ዳይሬክትር አሰማኸኝ አስረስ ከአማራ መገናኛ ብዙኀን ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ ፍንጭ ሰጥተዋል። ˝ኢትዮጵያዊነት ዜግነት እንጂ ብሔር አይደለም። ስለዚህ ኢትዮጵያዊ የሚል መሥፈርቱ ላይ የለም። በፌዴሬሽን ምክር ቤት የፀደቁ 76 ብሔረሰቦች ተዘርዝረዋል፤ ከተለያዩ ብሔረሰቦች የተወለዱ ሰዎች፥ የተወለዱ መሆኑን እንዲገልጹ ዕድል ሰጥቷቸዋል ̋ ሲሉ በማንነት ዙሪያ መጠነኛ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕገ መንግሥት መምህር የሆኑት ደረጀ ዘለቀ (ዶ/ር) በቆጠራ በመመዝገቢያ ቅፁ ላይ ምን ዓይነት መረጃ በዝርዝር እንደተቀመጠ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ በመግለጽ ˝አንድ ሰው በብሔር ማንነቴ አልመዘገብም፤ መገለጫዬ ኢትዮጵያዊነት ነው˝ ማለት መብቱ መሆኑን ጠቁመው ˝ኢትዮጵያዊነትን እንደ ማንነትን አንቀበልም ማለት፣ ለአንተ እኔ አውቅልሃለው እንደማለት ነው˝ ብለዋል። ይህን ማለት ደግሞ ትልቅ የመብት ጥሰትን የሚያስከትል አካሔድ ነው በማለት ማንኛውም ሰው ማንነቱን በፈለገው መንገድ እንዲገልጽ መብቱ ሊረጋገጥለት ይገባል ሲሉ በአፅንዖት ተናግረዋል።
አሰማኸኝ በአማራ መገናኛ ብዙኀን ቴሌቪዥን፣ ጥበበ ደግሞ ለአዲስ ማለዳ በሰጡት አስተያየት ˝ማንነት ኩራት ነው። በክልላችንም ውስጥ ይሁን ከክልላችን ውጪ የሚኖረው አማራ፥ በአማራነቱ ኮርቶ አማራ ነኝ ብሎ ማስመዝገብ አለበት˝ በማለት ፍፁም አንድ ዓይነት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

በቆጠራው ላይ ተፅዕኖ ሊፈጥሩ የሚችሉ የተለያዩ ኃይሎች ይኖራሉ ያሉት መረራ ˝እነዚህ ኃይሎች እጃቸውን ሊሰበስቡ ይገባቸዋል˝ ሲሉ አሳስበዋል። ሙሼ ሰሙ በመረራ አስተያየት ላይ ተመሳሳይ አቋም ያንፀባረቁ ሲሆን ተፅዕኖ አድራሽ ኃይሎችንም ዘርዝረዋል። የመጀመሪያው ኃይል የፌደራልና የክልል መሪዎች ናቸው ያሉት ሙሼ እንደ ኢትዮጵያ ሥልጣንና በጀት በብሔር ተሸንሽኖ በሚሰጥበት አገር ፌደራልም ሆነ የክልል ባለሥልጣናት በክልላቸው የሚገኙ ዜጎች ቁጥር ከፍ ለማድረግና ውጤቱ ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር አይከጅሉም ለማለት አይቻልም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ያላቸውን ሥጋት ገልጸዋል።
ሌላው የሙሼ አስተያየት በኅብረተሰቡ ላይ በተለይም በገጠር የሚኖረው ሕዝብ ላይ በቂ ቅስቀሳ ወይም የሕዝብ ንቅናቄ አለመሠራቱ ኅብረተሰቡ ስለቆጠራ በቂ መረጃ እንዳይኖረውና የሚጠበቀውን ያክል ውጤት እንዳያገኝ ሌላው የሥጋት ምንጭ መሆኑን ጠቅሰዋል። በሌላ አነጋገር በቆጠራው ውጤት ላይ ተፅዕኖ የሚያደርስ ሌላው ኃይል ራሱ ተቆጣጣሪው ሕዝብ ነው። በኢትዮጵያ የተካሔዱ ቆጠራዎች እንደሚያሳዩት ቀላል የማይባለው የገጠሩ ኅብረተሰብ በባሕላችን እና መንግሥትን ከመጠራጠር ጋር ተያይዞ የቤተሰቡን ቁጥር ብዛት የማስመዝገብ ፍላጎት አልነበረውም። ይህ ባሕል ዛሬ ስለመቀየሩ አሳማኝ መረጃ ባይኖርም በብዙ ቤተሰብ የልጅን ብዛት መናገር በፈጣሪ ዘንድ የሚወገዝ ተደርጎ ስለሚወሰድ በውጤቱ ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ መፍጠሩ አይቀርም ሲሉ ሙሼ አብራርተዋል።

የመገናኛ ብዙኀን በብዛት በማይደርስባቸው ገጠራማ አካባቢዎች በቂ ትኩረት ካልተሰጠ ባሕሉ እንኳን ተቀይሯል ቢባል ሥራውን ትቶ ቤተሰቡን ለማስመዝገብ ጊዜውን ያጠፋል ብሎ መናገር ይከብዳል ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ተናግረዋል።
በሌላው ለአራተኛው ዙር ቆጠራ እንደ ሥጋት አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ፖለቲከኞች፣ የሕግና የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት ምሁራን በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ የፀጥታና ደኅንነት ጉዳዮች መሆናቸውን በአንድ ድምፅ አስተጋብተዋል።

መፍትሔ
“የአብኑ ጥበበ ቆጠራው ከመካሔዱ በፊት መሟላት የሚኖርባቸው ጉዳዮችን አሉ” ሲሉ ከመፍትሔ ሐሳብ ጋር አስተያየታቸውን ሰጥተዋል። ተአማኒነትን በተመለከተ አንደኛው የሚመደቡ ቆጣሪዎች አደረጃጀት፣ ገለልተኝነት አፋጣኝ ምላሽ ሊያገኙ ይገባል ይላሉ።

የቆጠራ አስፈፃሚው አካል እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ለመከላከል ምን ዓይነት ቅድመ ዝግጅት እንደተደረገ የሚያውቁት ነገር እንደሌለ አስተያየት ሰጪ ፖለቲከኞችና ምሁራን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ይሁንና የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ቢራቱ ለእንደዚህ ዓይነት ሥጋቶች በፋና ቴሌቪዥን ˝ውጤቱ እኛ ጋር ካለው መረጃ ጋር የሚጣረስ ሆኖ ከተገኘ ግብረ መልስ እንሰጣለን፤ ነገሮች እንዲፈተሹም እናደርጋለን። በተለየ ሁኔታ የሚታዩ አዝማሚያዎች ካሉም እኛ ባቋቋምናቸው ገለልተኛ ታዛቢ ቡድን በድጋሜ ቆጠራው እንዲሔድ እናደርጋል ̋ በማለት ምላሽ ሰጥተዋል።

ሙሼ ሰሙ በበኩላቸው ሥጋቶቹ እንዳሉ ሆኖ ቆጠራውን የሚያካሒደው ኮሚሽንም ተአማኒ፣ ነጻና ገለልተኛ ለመሆኑ ኅብረተሰቡን ለማሳመን በሰፊው የሕዝብ ግንኙነት ሥራ መሥራት እንደሚገባ ምከረ ሐሳብ አቅርበዋል። ሳፊ እስካሁን ድረስ ከቅድመ ዝግጅት ጋር በተያያዘ ስንሠራ ነበር፤ ለኹሉም ዓይነት መገናኛ ብዙኀን የሚሆኑ መረጃዎች አዘጋጅተናል በማለት ሕዝቡን ተደራሽ ለማድረግ ሁሉም መገናኛ ብዙኀን ሊያግዙ ይገባል በማለት ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

ሙሼ ቆጠራን በተመለከተ ኅብረተሰቡ ላይ ከፍተኛ የተጋጋለ ዘመቻ መካሔድ አለበት፤ አንድም የኅብረተሰብ ግንዛቤ ከፍ ለማድረግ ኹለትም ተአማኒነታቸውን፣ ነጻና ገለልተኛ መሆናቸውን መተማመን እንዲፈጥር። ˝አሁንም ጊዜው አልረፈደም፤ የሕዝብ ንቅናቄ መዘጋጀት አለበት˝ ብለዋል። መረራ በበኩላቸው ሌላ አማራጭ ሊኖረን ስለማይችል ቆጠራው መካሔድ ይኖርበታል። ይሁንና በሐቅ መሠራት እንዳለበት ግን አሳስበዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 17 የካቲት 30 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here