ዴሞግራፊ እና ዴሞክራሲ

0
721

የሕዝብ ስብጥር (ዴሞግራፊ) ለዴሞክራሲ ወሳኝ ነው። ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ከሌሎች ስርዓቶች የሚለየው ሁሉንም የማኅበረሰብ ክፍሎች የመወከል ዕድል የሚሰጥ በመሆኑ ነው። የሕዝብ ስብጥር በዘውግ፣ በፆታ፣ በሃይማኖት፣ በአሰፋፈር እና ሌሎችም ከጊዜ ወደ ጊዜ ይቀያየራል። ይህ በአንድ ወቅት፣ በአንድ ቦታ ብዙ የነበሩ የማኅበረሰብ ክፍሎች፣ በሌላ ወቅት ትንሽ ሊሆኑ ወይም ከነአካቴው ላይኖሩ ይችላሉ፤ አዳዲሶችም ሊከሰቱ ይችላሉ። የዴሞግራፊ ለውጦችን መከታተል መጪው ጊዜ ምን እንደሚመስል ተረድቶ ለማቀድ እና ለመዘጋጀትም ይበጃል።

የዴሞግራፊ ለውጦችን ለመረዳት ወቅታዊ ሕዝባዊ ቆጠራዎች አስፈላጊዎች ናቸው። የሕዝብ ቆጠራዎች በተለይ በማኅበረሰቡ ውስጥ ተጋላጭ የሆኑ ክፍሎች በአግባቡ ተቆጥረው ውክልና እንዲያገኙ ለማድረግም ወሳኝ ነው። ለዚህም ነው ልክ ወቅቱን ጠብቆ በየጊዜው እንደሚደረግ ምርጫ ሁሉ ወቅቱን የጠበቀ ቆጠራ የሚያስፈልገው።

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 61 ንዑስ አንቀፅ 2 ላይ እንደተመለከተው “እያንዳንዱ ብሔር፣ ብሔረሰብ፣ ሕዝብ ቢያንስ አንድ ተወካይ ይኖረዋል፤” ይልና “በተጨማሪም የብሔር ወይም ብሔረሰቡ አንድ ሚሊዮን ሕዝብ አንድ ተጨማሪ ወኪል ይኖረዋል” ይላል። ስለሆነም የሕዝብ ቆጠራ ሲካሔድ በተለይም በብሔር ዴሞግራፊ ላይ ተመሥርቶ የወኪሎች ቁጥር በፌዴሬሽን ምክር ቤት እንዲቀይር ያደርጋል ማለት ነው።

በኢትዮጵያ በ2000 በተደረገው አገር ዐቀፍ ምርጫ ወቅት እንደ ምሳሌ የአማራ ሕዝብ ቁጥር በስታትስቲክስ ኤጀንሲ ተገምቶ ከነበረው በሚሊዮኖች ቀንሶ መገኘቱ የውዝግብ መነሻ ሆኖ ነበር። ይህ የዴሞግራፊ ለውጥ የፖለቲካ ጥርጣሬ በመፍጠር “የአማራን ሕዝብ ቁጥር ለመቀነስ ሴራ ተሸርቧል” የሚል አስተሳሰብ በመፈጠሩ በዚሁ ጥርጣሬ ነፍስ የነጠቀ ግጭት መንሥኤ እስከመሆን ደርሷል። በሌላ በኩል በ1988ቱ ቆጠራ የቅማንት ሕዝብ በኢትዮጵያ እንደ አንድ ብሔረሰብ ታይቶ በቆጠራው የተካተተ ሲሆን፣ በ2000 በተደረገው ቆጠራ ግን ሳይቆጠር ቀርቷል። ይህም እስካሁን እያወዛገበ ነው። በሌላ በኩል በመጋቢት ወር በሚደረገው ቆጠራ መልሶ እንደ አንድ ብሔረሰብ የሚቆጠር መሆኑ ተነግሯል። ይህ የዴሞግራፊ ለውጡን በቅጡ ለመረዳት የተዘበራረቀ ያደርገዋል።

በኢትዮጵያ፣ በተለይም የብሔር ዴሞግራፊ መቀየር የሥልጣን እና የሀብት ማግኛ ወይም ማጪያ መንሥኤ ስለሚሆን የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታውን በከፍተኛ ደረጃ ተፅዕኖ ያሳድርበታል። ለዚህም ይመስላል የኦሮሚያ ፕሬዚደንት ለማ መገርሣ የከተማ የፖለቲካ ስበትን በተወዳዳሪነት ለመወጣት ዴሞግራፊን መቀየር ቁጥር አንድ ጉዳይ መሆኑን አውቀን እየሠራንበት ነው እስከማለት የደረሱት።

በጥቅሉ የዴሞግራፊ ለውጥ በዴሞክራሲ ውስጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ትልቅ ተፅዕኖ አለው። ለዚህም ነው የሕዝብ ቆጠራ ሲደረግ በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊደረግ የሚገባው።

ቅጽ 1 ቁጥር 17 የካቲት 30 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here