የፖለቲከኞቹ ውይይት ትርፍ ምን ይሆን?

0
766

በኢትዮጵያ ነገ በለስ ከቀናቸው ሥልጣን ለመጨበጥ በሚል የተደራጁት የፖለቲካ ማኅበራት ብዛት ከ100 ዘሏል። ቁጥራቸው የበረከተው እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች አካሔዳቸውን መስመር ለማስያዝና የጋራ ግንዛቤ ለመጨበጥ መምከር ከጀመሩ ሰነባብተዋል።

ባሳለፍነው ሐሙስ፣ ብሐራዊ መግባባትና ዕርቀ ሰላም የፖለቲካ ፓርቲዎች ቅድመ ጉባኤ ኹለተኛው የምክክር መድረክ ውይይት መነሻ ጽሁፋቸውን ባቀረቡበት ወቅት፣ በአገሪቱ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስከዛሬ በነበራቸው ጉዞ ኅብረት የሌላቸውና ጥንካሬም የጎደላቸው ስለነበሩ፣ መንግሥትን መታገል የሚችሉበት ቁመና ላይ የደረሱ ስላልነበሩ፣ አምባገነናዊ ስርዓትን ለመጣል ተፈትነው እንደነበር አምነዋል፡፡ በቀጣይም ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን እንዲቻልና መንግሥት ላይም ጫና ፈጥሮ በአገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲሰፍን ለማድረግ እንደዚህ በጋራ መሥራታችን ግድ ነው ብለዋል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ጠቅላይ ሚንስትርና የኢሕአዴግ ሊቀ መንበሩን ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጨምሮ፣ በፖለቲካው ዓለም የረጅም ዓመታት ልምድ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ጽሑፍ እያቀረቡና ልምድ እያካፈሉ ለሦስተኛ ጊዜ የካቲት 17 ተገናኝተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ጥር 25/2011 ከተለያዩ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎች ጋር፣ በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ውይይት ማካሔዳቸው የሚታወስ ነው። የውይይት መድረኩም ከጥቂት ወራት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋባዥነት ከተደረገው መድረክ የቀጠለ ነበር።

ከውይይቱ አስተባባሪዎች መካከል የሺዋስ አሰፋ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ የመድረኩ ዋና ዓላማ የሽግግር ወቅቱን የፖለቲካ አመለካከት በሰላማዊ መንገድ የመለዋወጥ ልምድን ለማሳደግ ነው። በዚህም የፖለቲካ ፓርቲዎቹ ጠቃሚ ልምዶችን ይቀስማሉ የሚል ተስፋ አለ ብለዋል።

አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና የሚወክሏቸው ሰዎች የሰከነ ዕውቀት ይኖረን ዘንድና ለአገር ማሰብ እንድንችል ይህ የውይይት መድረክ አስፈልጓል›› ይላሉ። አክለውም ‹‹በእውቀት የተደገፈ እንቅስቃሴ ከሁላችንም የሚጠበቅ በመሆኑ፣ የልምድ ልውውጥ ማድረጋችን ከራሳችንም አልፎ ለሚከተለን ሕዝብ ጠቃሚ ነው›› ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባሕል ላይ ባቀረቡት ገለጻ፣ ˝ዋናው የፖለቲካ ባሕል ስርዓታችን ከራሳችን ወገን ክልል አልፎ ሌሎችን ወደ ማሳመንና ገንቢ ክርክር ወደ ማድረግ ከፍ አላለም። ትርጉም ያለው ዴሞክራሲን ለመገንባት ትክክለኛው አካሔድ በተለያዩ የፖለቲካ መስመሮችና እሳቤዎች ውስጥ በተቀናጀ መልኩ መሥራት ነው˝ ሲሉ የፖለቲካ ባሕሉን ተችተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅቱ ባቀረቡት ጽሑፍ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ባሕል መልካም ገፅታዎች በሚል የአገር ለፍትሕና ሕግ የሚቆረቆር፣ ብዝኃነት የሞላበት፣ ረጅም የመንግሥት ታሪክ ባለቤትና እና ለነፃነት ቀናኢ መሆንን ዘርዝረዋል። አዲሱ ትውልድም በእነዚህ አዎንታዊ ጎኖች ላይ ማትኮርና በጎዎቹን ማጎልበት እንደሚያስፈልገው ተናግረዋል። በመቀጠልም ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባሕልን በኢትዮጵያ ለመገንባት የፖለቲካ ምኅዳሩ አካታች መሆኑን ማረጋገጥ፣ ሁሉም ተዋናዮች የመንግሥትን አቅም ለማጠናከር መንቀሳቀስ እና መተማመንን ለማጠናከር መሥራት እንደሚያስፈልግ ጠቅሰዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ˝በጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት አዘጋጅነት እየተባለ ከሚካሔደው የፖለቲካ ፓርቲዎች ውይይት ተገልለናል˝ ሲሉ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲን (ኢራፓ) ጨምሮ ለመዋሐድ እየሰራን ነው ያሉ ስምንት የፖለቲካ ድርጅቶች ሐሙስ፣ የካቲት 21 በጋራ በሰጡት የጋራ መግለጫ ውይይቱ በጥቂት ፖለቲከኖችና ግለሰቦች አድራጊ ፈጣሪነት እየተካሔደ ነው ያሉት መግለጫ ሰጭዎች መንግሥት አንዱን ፓርቲ እያወደሰ አንዱን ማግለል የለበትም ሲሉም አቋማቸውን አሳውቀዋል። መግለጫውን ከሰጡት መካከል የኢራፓው ሊቀ መንበር ተሻለ ሰብሮ ቀድሞ በውጭ አገርና በረሃ እያሉ ˝ምናልባትም አንዳንዶቻችን እነሱ በሌሉበት አገር ቤት ገብተው አራት ኪሎ ላይ አብረን እንድንሠራ ታግለናል በወቅቱ ታሪክ ምስክር ነው˝ ያሏቸውን የፖለቲካ ኃይሎች በማንሳት ወደ አገር ውስጥ ከገቡ በኋላ እንሱን የመገፋፋት ተግባር እንደፈፀሙባቸው አንስተው ወቅሰዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ደረጀ ዘለቀ (ዶ/ር) ˝የፖለቲካ ፓርቲዎቻችን በሕዝብ ዘንድ ያላቸው ተጽዕኖ ፈጣሪነት በጣም ዝቅተኛ ነው። ምክንያቱ ደግሞ፣ ማኒፌስቶ ኖሯቸው፣ ያንን ማኒፌስቶ ለሕዝቡ አቅርበውና ለሚነሳላቸው ጥያቄ በቂ ምላሽ መስጠት የሚችሉ ባለመሆናቸው ነው˝ ሲሉ ያስረዳሉ።

˝ሲጀመር ማኒፌስቶ ያላቸው የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ያህሉ ናቸው?˝ ሲሉ የሚጠይቁት መምህሩ ደረጀ ˝እስከዛሬ በነበረው አካሔድ ሁሉም ቢሮ ይዞ ከመጮኸ ባለፈ፣ ዓላማውንና እቅዱን ለሕዝብ ሲያስተላልፍ የነበረ ፓርቲ አላየሁም፤ አሁን ግን መልካም የሚባሉ እንቅስቃሴዎችን እያየን በመሆኑ በዚሁ መቀጠል ይሻላል˝ ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሌላው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር ታደለ ሌንጮ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች የእስከዛሬ አካሔድ እርስ በርስ መነቃቀፍና መተቻቸት የበዛበት መሆኑን አንስተው፣ በዚህ መንገድ መራመድ የትም እንደማያደርስና የሕዝብንም አመኔታ እንደሚያሳጣ ይመክራሉ። ˝የፖለቲካ ፓርቲ ሲቋቋም በሕዝብ ድጋፍ እንደመሆኑ በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያቸው ሕዝብን መሰረት አድርገው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል˝ ሲሉም መክረዋል።

የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ
በጥር 25ቱ ምክክር ከጥናት አቅራቢዎቹ መካከል የሆኑት ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር)፣ ˝የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ሲቪክ ማኅበራትና ሚዲያ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ˝ በሚል ርዕስ ባቀረቡት የመወያያ ጽሑፍ፣ ዴሞክራሲ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድነት የሚያቀነቅኑት ጉዳይ መሆኑን ተናግረው ˝በጠባብ ማንነት ላይ መሰረት ተደርጎ የሚቋቋም ፓርቲ ቁጥር ከማብዛት በዘለለ ፋይዳው እንደማይጎላ˝ ገልጸዋል። ትርጉም ያለው ዴሞክራሲ እንዲመጣ ፓርቲዎቹ ልዩነታቸውን በውይይት ማጥበብ እንዳለባቸው በጽሑፋቸው ሲያነሱም ተደምጠዋል። ፓርቲዎቹ ተመራጭ ለመሆን ከሚከውኑት ተግባር ጎን ለጎን፣ ዜጎች ማኅበራዊ ትስስር እንዲፈጥሩ ሊያስተምሩ እንደሚገባም መክረዋል።

በአንድነት አቀንቃኝ ኃይሎችና ብሔርን መሰረት አድርገው በተዋቀሩት መካከል ያለው ሰፊ የአካሔድ ልዩነት ሊጠብ እንደሚገባ የተናገሩት ደግሞ በመድረኩ የኢትዮጵያን ፌደራሊዝም ስርዓት በሚመለከት መወያያ ጽሑፍ ያቀረቡት ፖለቲከኛው መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር) ናቸው። መረራ ˝የአንድነት ኃይሉ የኢትዮጵያዊነት ሰርተፍኬት ሰጭና ከልካይ ከሚያስመስለው አካሔድ መቆጠብ አለበት˝ ሲሉም ይሞግታሉ። ˝በብሔር ለተደራጀው ደግሞ ዋነኛ ጠላት አምባገነኖች እንጂ ሕዝብ ባለመሆኑ ከታሪክ ሒሳብ ማወራራድን መተው አለባቸው˝ ሲሉም ያክላሉ። ሁሉንም በእኩልነት የምታስተናግድ ኢትዮጵያን ለመፍጠር በጋራ መሥራት እንደሚገባ በመጠቆም።

አረጋዊ በበኩላቸው በኢትዮጵያ ˝ከአምባገነናዊ ስርዓት ወደ ዴሞክራሲ የሚሔድ˝ አዲስ የመንግሥት አካሔድ መፈጠሩን አስታውሰው፣ የተፈጠረውን የሐሳብ ነጻነት ለአገራዊ ችግሮች መፍትሔ ማድረግ እንደሚገባ መክረዋል። ˝ይህች አገር አንድ በመሆኗ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት ቀጣይነት ያለው ምክክር ማድረግ አለባቸው˝ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

በብሔር ላይ የተመሰረቱ የፖለቲካ ኃይሎች በበኩላቸው ዓላማቸው ኢትዮጵያዊነትን ማኮሰስ አለመሆኑን በመጥቀስ የሚደርስባቸውን ወቀሳ እንደማይቀበሉት በተደጋጋሚ ሲናገሩ ይሰማል። ገዥው መንግሥት ኢሕአዴግ ራሱ የተመሰረተው ብሔር ላይ ነው በማለትም የብሔር ማንነትን በማጠንከር ኢትዮጵያዊነትንም መገንት እንደሚቻል ሲከራከሩ ይደመጣሉ።
በፓርቲዎች መካከል ጎራ ተከፍሎ የሚስተዋሉ እንቅስቃሴዎች እልባት ሊበጅላቸው እንደሚገባ ያሳሰቡት የሕግ ምሁሩ ደረጀ ˝የቃላት ጦርነቶች በሒደት ወደ አፈሙዝ ጦርነት ሊወስዱ ስለሚችሉ ጥንቃቄ ያስፈልጋቸዋል˝ ይላሉ። በየመድረኩ የሚደመጡ የፖለቲካ አመራሮች ንግግሮችን ለዚህ ማሳያ እንደሆኑም ያክላሉ።

የሸዋስ በበኩላቸው ችግሮቹ እንዳሉ ሆነው፣ አሁን እየተካሔዱ ያሉ ውይይቶች ቀጣይነት ባለው መልኩ ከተጓዙ መፍትሔ አምጪ ይሆናሉ የሚል ተስፋ አላቸው።

የብሔረ መንግሥት ፈተናዎች
ባለፈው ሳምንት በነበረው የሦስተኛ ውይይት መድረክ በመድብለ ፖለቲካ ሥርዓት ዙሪያ በየነ ጴጥሮስ (ፕሮፌሰር)፣ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር)፣ ብናልፍ አንዱዓለም እና አብርሃ ደስታ ያቀረቧቸው ጽሑፎች የውይይት መነሻ ሆነዋል።

በዕለቱም ተሳታፊዎቹን በብዛት ሲያወያይ የነበረው በኢሕአዴግ ተወካዩ ብናልፍ አንዱዓለም ያቀረበው ‹‹የአገረ መንግሥት እና የብሔረ መንግሥት ግንባታ በኢትዮጵያ›› የሚል ጽሑፍ ነበር።

አገረ መንግሥቱን ከስርዓተ መንግሥቱና ከመንግሥት አስተዳደሩ ነጥሎ ያለማየት ችግር መኖሩን የተናገሩት ብናልፍ፣ በአንድ በኩል በስርዓተ መንግሥቱና አስተዳደሩ ላይ የሚነሱ ችግሮችን በቅንነት ተቀብሎ ያለማየትና ችግሩን በቀጥታ ከአገረ መንግሥቱ ጋር የማያያዝ ችግር፣ በሌላ በኩል በኅብረ ብሔራዊ መንግሥታት የውስጥ አስተዳደራዊ ጥያቄ በተነሳ ቁጥር አገረ መንግሥቱ ላይ ጥያቄ እያነሱ፣ አገረ መንግሥቱ የተረጋጋ እንዳይሆን የማድረጉ ችግር ሰለባ መሆንን ያነሳሉ። ይህንንም ሲያስረዱ አንዱ ብሔር በሆነ ምክንያት የተጎዳ ወይም የተገለለ ሆኖ ከተሰማው በመንግሥት አስተዳደሩ ወይም በሥርዓተ መንግሥቱ ላይ ሳይሆን በአገረ መንግሥቱ ላይ ጥያቄ በማንሳት የመገንጠል አዝማሚያ ያሳያል ይላሉ።

የፖለቲካ ልኂቃኑም፣ ከአንድነት ይልቅ መነጠልን (መገንጠልን) የሚያቀነቅኑ፣ አገረ መንግሥቱን ከኅብረ ብሔራዊ ወደ ብሔረ መንግሥት በኃይልና በአስቸኳይ ካልተገባ የሚሉ እንዲሁም ሥርዓተ መንግሥቱ ካለበት ሁኔታ ከተነቃነቀ ወዮላችሁ የሚሉ መሆናቸውን ብናልፍ በጥናታቸው አሳይተዋል።

በሌላ በኩል ልዩነቶችን በመደፍጠጥ ዜግነታዊ ብሔር መፍጠር በዚህ ዘመን የማያስኬድና ለደም መፋሰስ ምክንያት ሊሆን ስለሚችል፣ የግል የሆኑ ታሪኮችና ማንነቶች ለግል በመተው ወይም ሳይነካኩ አክብሮ በማለፍ የጋራ የሆኑና በአንድነት ሊገኙ ስለሚችሉ እሴቶች ሰፊ የፖሊሲ፣ የሚዲያ፣ የጥበብ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ ነፃ የሰው ዝውውር እና ለዜጎች ነፃነትና ሕይወት የሚሳሱ ተቋማት (መንግሥታዊ) በመፍጠር፤ የጋራ ተጠቃሚነትን በማስፋትና በመሠረተ ልማት በማስተሳሰር፣ አግላይ እና አድሏዊ የሆኑ ምልክቶችን፣ አገላለፆችንና ውሳኔዎችን ነውር በማድረግ የጋራ ዜግነታዊ ማንነት መፍጠርን የብናልፍ ጽሑፍ ይመክራል።

በሐሙሱ የምክክር መድረክ ፓርቲዎቹ በጋራ መሥራት ላይ የተስማሙ ሲሆን፣ በቀጣይም አጀንዳ ቀርጸው እየተገናኙ በአገሪቱ ሰላም፣ መግባባትና ዕርቀ ሰላም ላይ እንደሚመክሩ አስታውቀዋል፡፡ በቅርቡም በሀገሪቱ ያለውን ነባራዊና ተጨባጭ ሁኔታ የሚያሳይ ጥናታዊ ጽሁፍ የሚቀርብበትና ለውይይት ክፍት የሆነ፣ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ያቀፈ መድረክ እንደሚኖርም ተጠቁሟል፡፡

ቅጽ 1 ቁጥር 17 የካቲት 30 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here