ቤተልሔም ነጋሽ ትላንት ታስቦ የዋለውን የሴቶች ቀን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ የሴቶች መብቶች አራማጆች ከሚነሱ በርካታ ጥያቄዎች መካከል አንኳር ናቸው ያሏቸውን ሦስቱን ብቻ በማንሳት መንግሥት ያለውን ቀርጠኝነት ያድስ ሲሉ በጽሑፋቸው ይሞግታሉ።
እንደ ዛሬ የማኅበራዊ ሚዲያው ሴቶችን የሚመለከቱ ጉዳዮችን ጨምሮ ለሌሎች የመብት ጥያቄዎችና ክርክሮች መድረክ ሳይሆን የዛሬ አምስት ዓመት አካባቢ ለመጀመሪያ ጊዜ በአውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር ማርች 8 የሚውለውን ዓለም ዐቀፍ የሴቶች ቀን አስመልከቶ ከማውቃቸው ሴቶች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ለጥቂት ቀናት ዘመቻ ሲደረግ ጥሪ ቀርቦልኝ መሳተፌን አስታውሳለሁ። በዘመቻው ወቅት በተለያዩ ዘርፎች እውቅና ያገኙና አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሴቶችን ታሪክና ፎቶግራፍ ለዚሁ ዓላማ በተከፈተ ገጽ ላይ ስናጋራ ገጹንም በግን ገጾቻችን በኩል አስተዋውቀን ነበር። በበኩሌ በግል የተሳተፉኩበት የመጀመሪው የሴቶችን ጉዳይ የሚመለከት የማኅበራዊ ሚዲያ የተቀናጀ ዘመቻ ይመስለኛል። የአሜሪካ ድምጽ ራዲዮን ጨምሮ በመደበኛ ሚዲያዎች ላይ ስለዘመቻው ዘገባ መቅረቡንም አስታውሳለሁ።
የሴቶች ቀን ሲባል “የሴት ጉዳይ አንድ ቀን ብቻ ነው ወይ መወራት ያለበት” ከሚል “ቀን በማክበር የሚመጣ ለውጥ፣ ለብዙኀኑ የኢትዮጵያ ሴት ጠብ የሚል ነገር የለም” እስከሚል እና “ጨርሶ መከበር የለበትም” እስከሚል አስተያየቶችና ጠንካራ ትችቶች ይቀርባሉ።
ዓመቱን ሙሉ ሲከበሩ እንደምናያቸው እንደሌሎች ቀኖች ሁሉ መከበሩ፣ በቀኑ አካባቢም ሴቶችን ማስታወስ፣ ማክበር፣ ጉዳዮቻቸውንና ጉዳቶቻቸውን መመልከትና ማሳየት ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ። ቀኑ በመከበሩ የሴት መብት ይጠበቃል ወይ ለሚለው ጉዳዩ ተለጥጦ ባይታይ ይልቁንም ምናልባት በመንግሥት ደረጃም የሚከበርና ትኩረት የሚሰጠው ቀን በመሆኑ ቀኑን መንግሥት የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በፈረማቸው ዓለም ዐቀፍ ስምምነቶችም ይሁን ባወጣቸው ሕጎች የደነገገውን መብትና የገባውን ቃል እንዲያከብር ለሴቶች እኩልነት የመቆም ቁርጠኝነቱንም በድጋሚ እንዲያረጋግጥ የምንጠይቅበት ቢሆን በጎ ነው ብዬ አስባለሁ። ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ከሞላ ጎደል በተለያዩ የሴቶች መብቶች አራማጆች ጭምር የሰማሁትና የማምንባቸውን ጥቂት ጥያቄዎች አቀርባለሁ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሴቶች ተወካዮች ጋር ተገናኝተው ጥያቄዎቻቸውን ሊሠሙ ይገባል
ትርጉም ባለው መልኩ ሴቶችን ማካተት
“እኔ ባደግኩበት ባሕል ሴቶች ልጆቻቸውን በጀርባቸው ያዝላሉ። በሔዱበት ሥራም ይሥሩ መንገድ ልጆቹ ጀርባቸው ላይ ይቆያሉ። በሔዱበት ይሔዳሉ። የሴቶች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጉዳይ በዚህ ይመሰላል። ያቺን ሴት ስትጠቅማት ልጇ አብሮ እንደሚጠቀም፣ ሴት ቤተሰቧን፣ በዚያም ውስጥ አገርን ትሸከማለችና አገርንም ትጠቅማለህ።
ትናንት በሥራ አጋጣሚ በተገኘሁበት አህጉር ዐቀፍ ስብሰባ መክፈቻ ላይ የአንድ ዓለም ዐቀፍ ተቋም ተቀዳሚ ምክትል ዳይሬክተር ካደረጉት ንግግር የተወሰደ ነው።
ተደጋግሞ እንደሚነገረው ሴቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ቤተሰባቸው ጭምር ላይ ኢንቨስት ማድረግ ነው። የዓለም ዐቀፉ የገንዘብ ድርጅት ጥናት እንዳረጋገጠው ሴቶች የሥራ መሪ በሆኑባቸው ታላላቅ ኩባንያዎች በወንዶች ከሚመሩት ጋር ሲነፃፀሩ የተሻለ ትርፋማ ነበሩ። ጥሩ የትምህርትና የተሻለ ገቢ ደረጃ ያላቸው እናቶች ያሳደጓቸው ልጆች ካልተማሩትና ገቢ ከሌላቸው ጋር ሲነፃፀር በልጆቻቸው ኹለንተናዊ ዕድገት ላይ የተሻለ አስተዋጽኦ ማድረግ ችለዋል። ከዚህ በላይ እንደ አገር ሲታሰብ 50 በመቶውን ሕዝብ ሳያሳትፉ አድጋለሁ ማለት አይታሰብም።
ማሳተፍ ወይም ማካተት ሲባል ለኮታ ወይም አደረግኩ ለማለት ሳይሆን ትርጉም ባለው መልኩ ሊሆን ይገባል። እንደ ሲዊድን ያሉ በሁሉም መስክ ኹለንተናዊ ዕድገት ያስመዘገቡ አገሮች በአጭር ጊዜ እዚህ ለመድረስ ከሌላው የተለየ ምን አደረጉ ሲባል የሚመጣው መልስ “ሴቶችን ትርጉም ባለው መልኩ አካተቱ” የሚል ነው። አስተዋጽኦ ሊያበረክቱ የሚችሉ ብቁ ሴቶችን መመደብ ክፍተት ያለባቸውንም ሥልጠናና ከሌሎች ሴት መሪዎች የሚማሩበትን ዕድል ማመቻቸት የግድ ይላል።
የ50/50 ክፍፍልን በሁሉም የሥልጣን እርከኖች መድገም
የተሰለቸ ጉዳይ አንስቶ ማድከም አይሁንብኝ እንጂ በዚሁ ዓመት ኢትዮጵያ ሃምሳ ሃምሳ ተዋጽኦን በሚኒስትሮችና በካቢኔዋ ተግባራዊ በማድረግ በዓለም ሥሟ በበጎ እንዲነሳ ሆኗል። ከዚህም ሌላ ሴት ፕሬዚዳንት፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንትና የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር በመሾምም ሴቶችን የማሳተፉ ነገር በመንግሥት ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠው የሚያሳይ ጠንካራ እርምጃው ተደግሟል።
እርምጃውን ከማድነቅ አለፍ ስንል ለውጡ ትርጉም እንዲኖረውና ዘላቂ እንዲሆን ተቋማዊ መሠረት ማስያዝ የግድ ይላል እንላለን። ለምሳሌ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከሚሰየሙ የቦርድ አባላት ቢያንስ 30 በመቶው ሴቶች እንዲሆኑ መወሰኑ አንድ ጥሩ ምሳሌ ነው። በሌሎችም ተቋማት ለምሳሌ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በመንግሥት ሥር ያሉ የልማት ተቋማት፣ ኤጀንሲዎችና ኮርፖሬሽኖች በየደረጃው ያሉ የአመራር አካላት ሴቶችን ያካተቱ ሆነው እንዲዋቀሩ መመሪያ ማውጣት ይህን ለውጥ ተቋማዊ ለማድረግ እንደ አንድ እርምጃ ሊታይ ይችላል።
በዚህ መሠረት ከከፍተኛው እስከ መጨረሻው የመንግሥት መዋቅር ወረዳ/ቀበሌ ድረስ፣ በአንድ ጊዜ ይፈፀም ሳይሆን ደረጃ በደረጃ የማስፈፀሚያ ጊዜ ገደብ ተሰጥቶ ከ 30 እስከ 50 በመቶ ቦታዎች በሴቶች እንዲያዙ ማድረግ ላይ መሥራት ይገባል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠሩ ባንኮችና ቢዝነሶች እንዲሁም በግሉ ሴክተር ያሉ ተቋማት ሁሉ ሴቶችን ወደ አመራር እንዲያመጡ ማበረታታት፣ ይህን አድርገው ሲገኙም በታክስ እፎይታና በሌሎች ድጎማዎች መሸለም፣ አስፈላጊም ሲሆን የድጋፍ እርምጃ መመሪያ ማውጣት ይህን ሴቶችን በሁሉም ዘርፍ ወደ አመራር የማምጣት ሒደት ማፋጠን ይቻላል።
ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በተመለከተ የህግ ክፍተቶችን መፈተሸ
ኢትዮጵያ የሴቶችን መብቶች ከማክበር ጋር ተያይዞ ሥሟ በበጎ ከሚነሳበት ነጥብ አንዱ አስፈላጊ የሕግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀቷ ነው። ከዓለም ዐቀፍ እና አህጉር ዐቀፍ እስከ ብሔራዊ ሕጎችና መመሪያዎች እንዲሁም ፖሊሲዎች ሴቶችን የሚመለከቱ ብዙ ማዕቀፎቸ አሉ። ነገር ግን ያሉት ሕጎች በበቂ ሁኔታ ካለመተግበራቸውም በላይ ያለው እውነታ ሲለወጥ አብረው በቶሎ ባለመለወጣቸው እንዲሁም ወደ አፈፃፀም ሲመጣ የተለየ ሁኔታ በማጋጠሙ ምክንያት ክፍተት ሲያጋጥም ይታያል።
ነገር ግን እዚህ አገር መንግሥት አለ ወይ የሚለው ጥያቄ እስኪነሳ በሕፃናትና ታዳጊ ሴቶች ላይ ሳይቀር ዘግናኝ ጥቃት ሲፈፀም ይታያል።
ማኅበራዊ ሚዲያ የምትከታተሉ ሰዎች ምናልባት ባለፈው ሰሞን በሴቶች እኩልነት ላይ የተለያዩ ሥራዎችን በምትሠራው ተቋም ሴታዊት አነሳሽነት ብዙ ሺሕዎች የፈረሙት “የአሲድ ጥቃት ላይ ሕግ ይውጣ” የ‘ኦንላይን’ ፊርማ ዘመቻ ታስታውሳላችሁ ብዬ ተስፋ ላድርግ። ካልተሳሳትኩ በመደበኛ ሚዲያውም ይኸው ጉዳይ እንደርዕስ ተነስቷል። እየጨመረው የሔደው በሴቶች ላይ የሚደርሰውና አሰቃቂ ጉዳት የሚያደርሰው የአሲድ ጥቃት ትኩረት እንዲሰጠው፣ በሥራ ላይ ያለው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ የሚያስቀምጠው ቅጣት ከአስተማሪነትና ከጉዳቱ አንፃር ተመጣጣኝ ቅጣት እንዲጣል የሚያደርግ አለመሆኑ ከዚህም ጋር የአፈፃፀም ችግር መኖሩ ታይቶ ተጨማሪ ይህንን የሚመለከት ሕግ እንዲወጣ የሚጠይቅ ነበር። ለምሳሌ ይህ ዘመቻ ታሳቢ ያደረገው ጥያቄ አሲድ በችርቻሮ መሸጥ ይከልከል፣ ለምን አገልግሎት እንደተፈለገ ሳይታወቅ ለማንኛውም ሰው የሚገኝ አይሁን ቁጥጥር ይደረግበት የሚል ነው።
በሕግ ክፍተት በኩል መነሳት የሚችለው ሌላ ምሳሌ የሴቶች የቤት ውስጥ ጥቃትን የሚመለከት ሕግ ነው። በተለይ በባልና ሚስት እንዲሁም አብረው በሚኖሩ ተጓዳኞች መካከል በሚፈጠር አለመስማማት ድብደባ የሚፈፀምባቸው ሴቶች ወደ ሕግ ሲሔዱ አስቸጋሪ ሁኔታ ይገጥማቸዋል። ይኸውም በግልጽ የሚታይ የአካል ጉዳት የሚጠበቅ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ከጥቃቱ ሁኔታ ጋር በማይሔድ መልኩ ምስክር እንዲያመጡ መጠየቅ እንዲሁም ተደጋጋሚ ጥቃት የሚደረስባቸው ሳይቀሩ ከለላ የሚያገኙበት ሁኔታ አለመኖር ሴቶች ወንጀሉን ሪፖርት እንዳያደርጉ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል።
እነኝህንና መሰል ሕጎችን ፈትሾ ክፍተቶችን መሙላትና የሴቶች መብቶች በተሻለ መልኩ በሕግ የተጠበቁ እንዲሆኑ ማድረግ ሌላው የሴቶች ቀንን አስመልክቶ መንግሥት ቁርጠኛነቱን እንዲያሳይ የሚፈለግበት ጉዳይ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሴቶች ተወካዮች ጋር ተገናኝተው ጥያቄዎቻቸውን ሊሠሙ ይገባል።
በተረፈ ከላይ የተዘረዘሩት የሴቶች ቀንን አስመልክቶ በእነኝህ ሦስት ጉዳዮች ላይ መንግሥት ያለውን ቁርጠኝነት ያድስ ስንል እንደ ማሳያ ቀረቡ እንጂ ከዚህ ገጽ ውስንነት አንፃር ጥያቄዎቹ እነኝህ ብቻ ናቸው ለማለት አይደለም። ይልቁንም ሴቶች ብዙ ጥያቄዎችና ሥጋቶች አሏቸው። ይህንን ሥጋትና ጥያቄ ለማድመጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጊዜ ሰጥተው ከወጣት ሴቶች ተወካዮች ጋር መምከር አለባቸው። ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ሴቶችም አብረው መወያየታቸው እንዳለ ሆኖ ሴቶችን ብቻ የሚመለከቱ አሳሳቢ ጉዳዮችንና ድምጾችን ለመስማት ግን ቀጠሮ ሊይዙ ግድ ይላል። (እዚህ ላይ ከተለያዩ የሴቶች መብቶች ተሟጋቾችና ድርጅቶች ፊርማ ተሰባስቦ ከወራት በፊት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ለመነጋገር ጥያቄ መቅረቡን በተደጋጋመ “ጠብቁ” የሚል ምላሽ መሰጠቱን መጥቀስ ያሻል)
ለማጠቃለል የዓለም ዐቀፉ የሴቶች ቀን በዛሬው ዕለትና ሰሞኑን በአገራችንና በዓለም ዐቀፍ ደረጃ “እኩል እናስብ፣ በብልሃት እንገንባ ለለውጥ እንላቅ” በአገራችን ደግሞ “የላቀ ትኩረትና ቁርጠኝነት ለሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት” በሚል መሪቃል ሲከበር እንደተለመደው በየዘርፉ ሴቶችን የማካተትና ተጠቃሚ የማድረግ ዘመቻን ዓላማ ይዞ ነው።
በተለይ በውጪው ዓለምና በሴቶች አጀንዳ ላይ በሚሠሩ ተቋማት ዘንድ “የሴቶች ታሪክ ወር” እየተባለ የሚጠራው የፈረንጆቹ መጋቢት ወር በእኛ አቆጣጠር የየካቲት ወር መጨረሻ ሳምንትና የመጋቢት መጀመሪያዎቹ ሦስት ሳምንታት በሙሉ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ ታላላቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ሴቶችና ለመብት የሚታገሉ በማኀበረሰባቸው ለውጥ ለማምጣት የሚሠሩ ወጣት ሴቶች ጭምር የሚታወሱበት ወር ነው።
ቅጽ 1 ቁጥር 17 የካቲት 30 ቀን 2011